98358 contract law/ shipping contract/ non-performance/ period of limitation

የባህር ላይ የእቃ ማጓጓዝ ውልን በተመለከተ የዕቃው ርክክብ ከተፈፀመበት ወይም የማስረከቡ ጉዳይ ሳይፈፀም ቀርቶ እንደሆነ እቃውን ማስረከብ ከሚገባበት ቀን አንስቶ በአንድ አመት ውስጥ ክስካልቀረበ በይርጋ የሚታገድ ስለመሆኑ፡-

 

የባህር ህግ ቁጥር 203፤180፤162

የሰ/መ/ቁ. 98358

 

ጥር 05 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ -ነገረ ፈጅ ኃይሉ ተሰማ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- የኢትዩጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጠበቃ ማረን ወንዴ

- ቀረቡ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

              

 

ጉዳዩ የመድን ውልን መሠረት አድርጎ የቀረበውን የገንዘብ ይተካልኝ ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች በአሁኑ ተጠሪ ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- የአሁኑ አመልካች ለደንበኛው ለነፃ ኃላፊነቱ የተ.የግል ማህበር ከቱርክ ሀገር ለሚያስመጣቸው 246 ጥቅል ብረቶች ከተጫኑበት ሀገር ተጓጉዞ እስኪመጣ ድረስ ለሚያጋጥም ጉዳት በፖሊሲ ውል ቁጥር 01/ኤም አር ኦኤ/00001/07 የባህር ላይ የጉዞ መድን ሽፋን መስጠቱን፣ተጠሪ የመድን ሽፋን የተሰጣቸውን 246 ጥቅል ብረቶችን ተረክቦ ሆውማ ቤሊ ቪ.ኢኤስቲአር53  በሚባለው  መርከብ ከሊአጋ ኢዝሚር ቱርክ አጓጉዞ ጅቡቲ ለማድረስ በባህር እቃ መጫኛ ሰነድ ቁጥር 305/ኤስሲ ግዴታ መግባቱን፣ተጠሪ ጅቡቲ ለማድረስ ግዴታ ከገባባቸው 246 ጥቅል ብረቶች ውስጥ እቃው ጅቡቲ ወደብ ደርሶ ሲራገፍ 11(አስራ አንድ) ጥቅል ብረቶች መጥፋታቸውን፣ ከተጓጓዘው 246 ጥቅል ብረቶች ውስጥ የአመልካች ደንበኛ በ11/04/2004 ዓ/ም 226 ጥቅል አዲስ አበባ ላይ በእቃ መረከቢያ ሰነድ ቁጥር 10431 መረከቡን፣ቀሪው 20 ጥቅል ብረት ውስጥ 9 ጥቅል ደግሞ ዘግይቶ በ05/06/2004 ዓ/ም በእቃ መረከቢያ ሰነድ ቁጥር 10999 መረከቡን፣ይህ የተጫነ እቃ መጥፋትና መጉደሉ በጅቡቲ የሰርቬየር ስራ በሚሰራው ገልፍ ኤጄንሲ አገልግሎት የሚባል ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ/ም ማረጋገጡን ገልጾ አመልካች ለደንበኛው የከፈለውን ካሳ ብር 289,527.23 ተጠሪ እንዲተካለት ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጠው መልስም፡-የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎችን ያስቀደመ ሲሆን በዚህም መሰረት የአመልካች ክስ እቃው በጅቡቲ ወደብ ላይ መራገፉ ከተረጋገጠበት ከጳጉሜ 03 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ በሚታሰብ በአንድ አመት ይርጋ ጊዜ ውስጥ የሚታገድ መሆኑን የባህር ሕግ ቁጥር 203(1) ድንጋጌ እንደሚያሳይ እንዲሁም አመልካች ክስ ለማቅረብ መብት ወይም ጥቅም የሌለው መሆኑን ገልፆ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡


የስር ፍርድ ቤትም በዚህ መልክ የቀረበውን የይርጋ ክርክር በጭብጥነት ይዞ ጉዳዩን በመመርመር እቃው በጅቡቲ ወደብ የተራገፈው ጳጉሜ 03 ቀን 2003 ዓ/ም መሆኑን መነሻ አድርጎ ይርጋውን በመቁጠር የካቲት 05 ቀን 2005 ዓ/ም የቀረበው የአመልካች ክስ በባህር ሕግ ቁጥር 203(1) መሰረት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያልቀረበ በመሆኑ በይርጋ የታገደ ነው በማለት መዝገቡን ዘግቶታል፡፡በዚህ ብይን የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ብይን በመቃወም ለማስቀየር ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የመጨረሻ ርክክብ የተደረገው የካቲት 05 ቀን 2004 ዓ/ም ሁኖ እያለና የደንበኛው እቃ መጉደሉም የተገለጸው ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ/ም ሁኖ እያለ የእቃው ርክክብ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ይርጋው ሊቆጠር ይገባል ተብሎ የአመልካች ክስ ውድቅ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት ሊታይ ይገባዋል ተብሎ ተጠሪ ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ነጥብ የአመልካች ክስ በይርጋ የታገደ ነው ተብሎ ውድቅ መደረጉ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነው፡፡

 

አመልካች በተጠሪ ላይ ክስ ሊመስርት የቻለው ለደንበኛው ለነፃ ኃላፊነቱ የተ.የግል ማህበር ከቱርክ ሀገር ለሚያስመጣቸው 246 ጥቅል ብረቶች ከተጫኑበት ሀገር ተጓጉዞ እስኪመጣ ድረስ ለሚያጋጥም ጉዳት በፖሊሲ ውል ቁጥር 01/ኤም አር ኦኤ/00001/07 የባህር ላይ የጉዞ መድን ሽፋን መስጠቱን መሰረት አድርጎ ሲሆን በዚህ ጉዞ ሂደት ጠፉ ለተባሉት 11 ጥቅል ብረቶች ለደንበኛው ከፈልኩ የሚለውን ገንዘብ እቃዎቹን የማጓጓዝ ግዴታ አለበት የሚለው ተጠሪ እንዲተካለት ነው፡፡ስለሆነም ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ሕግ የባህር ህግ ሲሆን ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለውን የይርጋ ጊዜ የሚያስቀምጠው የህጉ ድንጋጌ ቁጥር 203 ሲሆን ድንጋጌው ሁለት ንዑስ ቁጥሮችን የያዘ ሁኖ የመጀመሪያው ንዑስ ቁጥር ከማመላለሻው ውል ውስጥ የተገኙ መብቶች በይርጋ የሚታገዱት የንግድ እቃውን ከተረከበበት ቀን ጀምሮ ወይም የማስረከቡ ጉዳይ ሳይፈፀም ቀርቶ እንደሆነ እቃውን ማስረከብ ከሚገባበት ቀን አንስቶ የአንድ አመት ጊዜ ካለፈ በኋላ ነው በማለት አስገዳጅነት ባለው ሁኔታ አስቀምጧል፡፡የተጠቃሹ ቁጥር ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ደግሞ ከሂሳብ አከፋፋል ጋር ተያይዞ የሚነሳው ክርክር የሚታገድበትን አግባብ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ የባህር ህግ ቁጥር 203 ድንጋጌ የሚገኘው በጭነት ማስታወቂያ የተረጋገጠ ደረሰኝ የማመላለሻ ውልን የሚመለከቱ ልዩ ድንጋጌዎች በሚገዛው ክፍል ሲሆን የድንጋጌዎችን ወሰን በተመለከተ በቁጥር 180 ስር ሕግ አውጪ  አስቀምጧል፡፡ይህ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር አንድ ስር በክፍሉ ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች የሚፀኑት በተለይ በመርከብ ላይ በተጫኑት የንግድ እቃዎች የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ወይም ይህን በመሰለ ሌላ አይነት ሰነድ በተረጋገጡ የጭነት ማመላለሻ ውሎች ላይ ብቻ መሆኑን ሲያስቀምጥ የድንጋጌው ንዑስ ቁጥር ሁለት እና ሶስት ደንጋጌዎች ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው የመርከብ መከራየት ውል ሰነድ ባለው ጉዳይ ላይ ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉና በዚህ ጊዜም ድንጋጌዎቹ ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ልዩ ሁኔታዎችን የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡


ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ ጅቡቲ ለማድረስ ግዴታ ከገባባቸው 246 ጥቅል ብረቶች ውስጥ እቃው ጅቡቲ ወደብ ደርሶ የተራገፈው ጳጉሜ 03 ቀን 2003 ዓ/ም ሁኖ በዚህ ጊዜ ከተጓጓዘው 246 ጥቅል ብረቶች ውስጥ የአመልካች ደንበኛ በ11/04/2004 ዓ/ም 226 ጥቅል አዲስ አበባ ላይ በእቃ መረከቢያ ሰነድ ቁጥር 10431 መረከቡን፣ቀሪው 20 ጥቅል ብረት  ውስጥ 9 ጥቅል ደግሞ ዘግይቶ በ05/06/2004 ዓ/ም በእቃ መረከቢያ ሰነድ ቁጥር 10999 መረከቡን

፣ይህ የተጫነ እቃ መጥፋትና መጉደሉ በጅቢቲ የሰርቬየር ስራ በሚሰራው ገልፍ ኤጄንሲ አገልግሎት የሚባል ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ/ም ማረጋገጡንና አመልካች ክስ የመሰረተው የካቲት 05 ቀን 2005 መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡አሁን ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው ጉዳይ በባህር ህጉ ቁጥር 203(1) የተመለከተው የአንድ አመት የይርጋው ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ከመቼ ጀምሮ ነው? የሚለው ነው፡፡አመልካች የበታች ፍርድ ቤቶች የይርጋ ጊዜ አቆጣጠር ስህተት ነው በማለት የሚከራከረው የእቃዎቹ ርክክብ ጊዜ በማስጫኛ ውሉ ላይ አልተገለፀም፣በመጀመሪያው ዙር 226፣ቀጥሎ ደግሞ 9 ጥቅል ብረቶች የተላኩ መሆኑንና ለክሱ መነሻ የሆኑት ቀሪዎቹ 11 ጥቅል ብረቶች መጥፋታቸው የተረጋገጠው ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ/ም ነው በሚል ነው፡፡እንግዲህ ከክርክሩ ይዘት በግልጽ መረዳት የሚቻለው እቃው በባህር ላይ ተጉዞ ጅቡቲ የተራገፈበት አግባብ በአንድ የማስጫኛ ሰነድ ያለመሆኑን ነው ፡፡በአንድ የማስጫኛ ሰነድ እቃዎቹን ተጠሪ ባልተረከበበት ሁኔታ የመጀመሪያው የማራገፊያ ቀን ማለትም ጳጉሜ 03 ቀን 2003 ዓ/ም ከይርጋው መቆጠር መነሻ ቀን የሚሆንበት አግባብ የለም፡፡እንዲሁም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመጀመሪያ የርክክብ ቀን የሆነው ታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ/ም ለይርጋው መነሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ማለቱ እቃው በሙሉ አንድ አይነት፣በአንድ የጭነት ሰነድ በአንድ የማጓጓዣ ውል የተጓጓዘ መሆኑን ከክሱ መረዳት ይቻላል በሚል ነው፡፡ይሁን እንጂ ከዚሁ ከመጀመሪያው ርክክብ በኋላ 9 ጥቅል ብረትን የአመልካች ደንበኛ የካቲት 05 ቀን 2004 ዓ/ም መረከቡ ያልተካደ ፍሬ ነገር ነው፡፡ስለሆነም ርክክቡ የቆመው ከዚህ ከየካቲት 05 ቀን 2004 ዓ/ም በኋላ በመሆኑ የአመልካች ደንበኛ እቃዎቹ መጥፋታቸውን እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰበው ከዚህ ቀን በኋላ እንጂ የመጀመሪያው ርክክብ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ አይደለም፡፡ተጠሪ የባህር ህግ ቁጥር 180(2) ድንጋጌን መሰረት አድርጎ የሚያቀርበው ክርክርም እቃዎቹ ከመርከቡ ላይ ከተጫኑበት አንስቶ አስከሚራገፉበት ጊዜ ብቻ የበህር ህግ ቁጥር 203 ድንጋጌ ተፈፃሚ መሆኑን የሚያስቀምጥ ሲሆን ይህም እቃዎቹ ሙሉ በሙሉ ተጭነው ባልተቆራረጠ ሁኔታ ርክክቡ የሚፈፀምበትን አግባብ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተቀመጠ ድንጋጌ ነው ከሚባል በስተቀር በመርከብ ላይ የተጫኑት እቃዎች በተግባር በተለያዩ ጊዜያት እየተራገፉ ርክክቡም በተለያዩ ጊዜያት ሲደረግ የነበረበትን ሁኔታ ለመግዛት ታስቦ የተቀመጠ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡የአመልካች ደንበኛ እቃዎቹን በተለያዩ ጊዜያት ሲረከቡ የነበሩ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጠ እቃዎቹ የተራገፉበትን ቀን ወይም የመጀመሪያ ርክክብ የተደረገበትን ቀን መነሻ አድርጎ ክሳቸው በይርጋ እንዲታገድ ማድረግ ከይርጋ ፅንሰ ሃሳብም ውጪ መሆኑ የሚታመን ነው፡፡

 

የይርጋ ህግ መሰረታዊ አላማ ተገቢውን ጥረት የሚያደርጉ ገንዘብ ጠያቂዎችን ወይም መብት አስከባሪዎችን መቅጣት ሳይሆን መብታቸውን በተገቢው ጊዜ ለመጠየቅ ጥረት የማያደርጉትን ሰዎች መቅጣት መሆኑ ይታመናል፡፡ስለሆነም የአመልካች ደንበኛ መብታቸውን ማስከበር ሲችሉ ያላግባብ የዘገዬበት ሁኔታ መኖሩን የክርክሩ ሂደት አያሳይም፡፡በባህር ህግ ቁጥር 162  ድንጋጌ ስር የይርጋ አቆጣጠር ጊዜ የሚጀምርበትን አግባብ ያስቀመጠ ሲሆን ለተያዘው ጉዳይ ግን ድንጋጌው ሙሉ በሙሉ አግባብነት አለው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም፡፡ምክንያቱም


ድንጋጌው በንኡስ ቁጥር አንድ ስር ለመጫን ወይም ለማራገፍ የተወሰነው ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ካፒቴኑ መርከቡን ሊጫን ወይም ሊራገፍ ተዘጋጅቷል ብሎ ካስታወቀበት  ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ሲያስቀምጥ የድንጋጌው ንዑስ ቁጥር ሁለት ደግሞ ጊዜም የሚታሰበው ካፒቴኑ ማስታወቂያውን ሰጥቶ ስራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መሆኑን ያሳያል፡፡በሌላ አገላለፅ ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነው የመጫኛና የማራገፊያ ጊዜ የሚጀምርበት ጊዜ በግልጽ በታወቀበት ሁኔታ ነው እንጂ እቃዎቹ በተለያዩ ጊዜያት በተጫኑበትና በተራገፉበት ግንኙነት ውስጥ አይደለም፡፡የአመልካች ደንበኛ እቃዎች ሙሉ በሙሉ የተጫኑበት ቀንም ሆነ የሚራገፉበት ቀን ያለመታወቁን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡

 

አመልካች በእርግጥም መብቱን ማስከበር የሚችልበት ጊዜ የካቲት 05 ቀን 2004 ዓ/ም ከተባለ ይኼው ጊዜ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1848(1) ድንጋጌ መሰረት ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ በባህር ህጉ አንቀጽ 203(1) የተቀመጠው የአንድ አመት ጊዜ የሚያበቃው ከየካቲት 06 ቀን 2005 ዓ/ም ጀምሮ ሲሆን አመልካች ግን ይሄው ጊዜ ከማለፉ በፊት የካቲት 05 ቀን 2005 ዓ/ም ክሱን ያቀረበ በመሆኑ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ሁኖ አልተገኘም፡፡ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካች ክስ በአንድ አመት ይርጋ የሚታገድ ነው በማለት የሰጡት ብይን ተገቢውን የይርጋ መቁጠሪያ ጊዜ መነሻ ያላደረገ ከመሆኑም በላይ የባህር ህግ ቁጥር 162 ድንጋጌን ይዘቱንና መንፈሱን ከተያዘው ጉዳይ ልዩ ባህርይ ጋር ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ብይኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳኔ

 

1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 203024 ግንቦት 06 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 137802 ታህሳስ 08 ቀን 2006 ዓ/ም በትእዛዝ የፀናው ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1)መሰረት ተሸሯል፡፡

2.  የአመልካች ክስ በይርጋ የታገደ አይደለም ብለናል፡፡

3. የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክሩን በመ/ቁጥር 203024 ቀጥሎ በሌሎች የግራ ቀኙ የክርክር ነጥቦች ተገቢውን የክርክር አመራር ስርዓት ተከትሎ ተገቢውን ዳኝነት እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይፃፍ፡፡

4.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 


 

ት/ጌ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡