100631 civil procedure legal status of associations legal personality standing

civil procedure

legal status of associations

legal personality

standing

 

በህግና በሚመለከተው መንግስት አካል እውቅና የተቋቋሙ ማህበራት የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት፣የአባላታቸውን መብትና ጥቅም ለማስከበርፍ/ቤት፣ለግልግል ተቋም ወይም ለሌሎች የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጣቸው አካላት የዳኝነት ጥያቄ የማቅረብ መብት ያላቸው ስለመሆኑ፣

 

የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 454(1) የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 35

አዋጅ ቁጥር 62/2001 አንቀፅ 55፣110

 

የሰ/መ/ቁ. 100631

 

ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመስል

 

አመልካች፡- ሮፓክ ነዋሪዎች  ልማት ማህበር   - ጠበቃ አቶ ማርሻል ፍቅረ ማርቆስ ቀረቡ ተጠሪ፡- ሮፓክ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወ.የግል ማህበር  -ጠበቃ አቶ ያለለት ተሾመ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 128626 ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር

98701 ሚያዝያ 22 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 197501 ነው፡፡ በስር ፍርድ ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩ የግልገል ዳኛ እንዲሰየም ትእዛዝ ይስጥልኝ በሚል መንገድ የቀረበ የዳኝነት ጥያቄ ነው፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ አመልካች ለስር ፍርድ ቤት ያቀረበው ማመልከቻ ነው፡፡ ከሳሽ (አመልካች) ተከሳሽ(ተጠሪ) ከአባላቱ ጋር በተለያየ ጊዜ በተዋዋለው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ውል ቤቶቹ ለሚሰሩበት መንደር የመሰረተ ልማት ግንባታና ልማት ስራ ለማከናወን ለነዋሪዎቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግየውል ግዴታ ገብቷል፡፡ ሆኖም ተከሳሽ (ተጠሪ) በውሉ በገባው ግዴታ መሠረት የመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲያከናውን ሲጠየቅ፤የግንባታ ስራውን ለመስራት ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ተከሳሽ ከከሳሽ አባላት ጋር ባደረገው ውል በአፈፃፀም ሂደት የሚፈጠር አለመግባባት ለግልግል ዳኛ የሚቀርብ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ተከሳሽ የግልግል ዳኛ እንድንሰይም ባቀረባቸው ጥያቄ መሰረት የግልግል ዳኛ ለመሰየም ፍቃደኛ ባለመሆኑ ፍርድ ቤት ተከሳሽ የግልግል ዳኛ እንዲሰይምና ስብሳቢ ዳኛ ሊሰየም በሚችልበት ሁኔታ ትእዛዝ እንዲሰጥልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

2. ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ፤ ከከሳሽ (አመልካች) ጋር ያደረኩት የውል ግንኙነት የለም፡፡ ከሳሽ አባላቱን ለመወከል በግልግል ጉባኤ ለመከራከር የሚያስችለው ልዩ ውክልና በአባላቱ አልተሰጠውም፡፡ ከሳሽ በተከሳሽ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው መብትና ጥቅም ወይም የውክልና ስልጣን የለውም፡፡ ስለዚህ ከሳሽ ያቀረበውን ክስ ውድቅ በማድረግ እንዲያሰናብተኝ


በማለት ተከራክሯል፡፡ የስር ፍርድ ቤት የተከሳሽን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግና ከሳሽ የተቋቋመበት አላማ በተከሳሽ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው በመሆኑ ተከሳሽ የግልግል ዳኛ እንዲሰይም በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

3.  ተጠሪ የስር ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ  ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኃላ መልስ ሰጭ(አመልካች) አባላቶችን በመወከል ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው የውክልና ማስረጃ ያላቀረበ በመሆኑ፤ ይግባኝ ባይ (ተጠሪ) የግልግል ዳኛ እንዲሰይም ጥያቄ ለማቅረብ አይችልም በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ አመልካች ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በሰጠው ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ  ሰሚ ችሎት አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካች ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 377 መሰረት ሰርዞታል፡፡

4. አመልካች ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ አመልካች የአባላቱን መብትና ጥቅም ለማስከበር የተቋቋመ ማህበር መሆኑን ተጠሪ አምኖ የተለያዩ ደብዳቤዎችን ሲፃፃፍ ቆይቷል፡፡ ተጠሪ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያቀረበውን ክርክርና መቃወሚያ በመቀበል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት ውሣኔ የሕግ መሠረት የሌለው በመሆኑ በሰበር ታይቶ እንዲሻርልኝ የሚል ይዘት ያለው የሰበር አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ተጠሪ በበኩሉ አመልካች በተጠሪ ላይ የግልግል ዳኛ እንዲሰየምለት ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስችለው ውክልና ወይም ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መብትና ጥቅም የሌለው በመሆኑ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም የሚል ይዘት ያለው መልስ ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ/ም በፅሁፍ አቅርቧል፡፡ አመልካች ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

5. ከስር የክርክሩ አመጣጥና ግራ ቀኙ ለዚህ ችሎት ያቀረቡትን የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካች ለተጠሪ የግልግል ዳኛ እንዲሰይም ክስ ለማቅረብና ለመጠየቅ የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም በማለት የሰጡት ብይን (ውሳኔ) የህግ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

6. ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ አመልካች ህጋዊ  ህልውና  ሲያገኝ ሊያሳካቸው የሚችላቸው መሰረታዊ ዓላማዎችና አመልካች አላማዎቹን ለማሳካት ሊፈፅማቸው ስለሚችላቸው ህጋዊ ተግባራት መመርመር  አስፈላጊ  ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች በኦሮሚያ ክልል በፊንፍኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ሮፓክ ቀበሌ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች የተመሰረተና የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል፤ጎርፍለመከላከል፤ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ የልማት ስራ የመስራትና የመሰረተ ልማትና የማህበሩ የአገልግሎት ተቋማት በፕላን መሰረት መገንባታቸውን በአባላቶቹ ስም ለመከታተልና ይህ ግዴታ ያለበት ሶስተኛ ወገን በሕጉ መሰረት ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ በአባላቱ ስም አስፈላጊውን ለመፈጸም ለማስፈፀምና ሌሎች አላማዎችን ለማሳካት የተቋቋመ ማህበር መሆኑን ከማህበሩ መመስረቻ ፅሑፍ አንቀጽ 5 የተዘረዘረ መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች ከሰጡት ውሳኔና ግራ ቀኙ ካቀረቡት ክርክር ይዘት ለመረዳት ችለናል፡፡

7. ይህም ከተጠሪ ጋር በተናጠል የቤት ግንባታና የማዘዋወር ውል የተዋዋሉ ግለሰቦች፣ተጠሪ በተናጠል በገባላቸው የውል ግዴታ በአንቀጽ 1 በተደነገገው መሠረት የመሠረተ ልማት ተቋማትን የመገንባትና የአገልግሎት ሰጭ ማዕከላትን የመገንባት ግዴታውን ያልተወጣ


በመሆኑ፣ ተጠሪን ከውል ወይም በሕግ ስልጣን ለተሰጠው አካል በማቅረብ የውል ግዴታውን እንዲወጣ ክስ የማቅረብና ተከታትሎ የማስፈፀም ዓላማና ሌሎች አላማዎችን የሚያሳካ ማህበር በመፍጠር፣ የፈጠሩት ማህበር፣ የማህበሩ አባላት በተናጠል ከውል የመነጨ መብታቸውን፣ለማስከበር ቢንቀሳቀሱ፣ የሚያወጡትን ወጭዎችና ጊዜ በሚቆጥብ ሁኔታ በተደራጀ መንገድ ማህበሩ ጥያቄ እንዲያቀርብላቸው ሙሉ ፈቃድና ስምምነታቸውን ሥልጣን ባለው የመንግሰት አካል ፊት በመቅረብና የማህበሩን መመስረቻ  ፅሑፍ በፊርማቸው በማፅደቅ የሰጡ መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች በውሣኔያቸው ካሰፈሩትና ከደረሱበት የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ ለመረዳት ይቻላል፡፡

8. አመልካች የተቋቋመበት አንደኛው መሰረታዊ ጉዳይ የማህበሩ አባላት አመልካችን ከማቋቋማቸው በፊት በተናጠል ከተጠሪ ጋር ባደረጉት የመኖሪያ ቤት ግንባታና የማዘዋወር ስምምነት መሰረት ተጠሪ ግዴታውን እንዲወጣ አባላቱን በመወከል አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን  ክስና ሌሎች  የዳኝነት ጥያቄዎችን በማቅረብ ኃላፊነት  ያለበት ሶስተኛ   ወገን

/ተጠሪ/ ግዴታውን እንዲፈጽም ለማድረግ መሆኑ በአመልካች መመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 11 በግልጽ ተደንግጓል፡፡ አመልካች ይህንንና ሌሎች ዓላማዎችን ለማሳካት እንዲንቀሳቀስ ዕውቅና ፈቃድ ስልጣን ባለው የመንግስት አካል  ተሰጥቶታል፡፡ይህም አመልካች በአላማነት ይዟቸው የተነሱ ተግባሮች ለመፈጸም የሚያስችልን ህጋዊ ተግባራት እንዲፈጽም አባላቱ ማህበሩን ሲመሰርቱ በሰጡት ፍቃድና ስምምነት መሰረት የመንቀሳቀስ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ከአዋጁ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 55 ድንጋጌዎችና ከአዋጅ ድንጋጌ ጋር የሚቃረን ይዘትና ውጤት ያላቸው የሌሎች ህጎች ተፈጻሚነት የሌላቸው መሆኑን ከሚደነግገው የአዋጁ አንቀጽ 110 ድንጋጌዎች መሰረታዊ ይዘት ህጋዊ ውጤት በማገናዘብ ለመረዳት ይችላል፡፡

9. ለዚህም ምክንያቱ የአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 110 ድንጋጌ፣ ከአዋጅ ጋር የማይቃረኑ የፍትሐብሔር ሕጉና የሌሎች ሕጐች ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሚከለክል ይዘትም ሆነ ሕጋዊ ውጤት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ይህም ስለ ማህበራት “ችሎታ” የሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 454 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንድናገናዝብ የሚጠይቅ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ስለማህበራት ችሎታ የሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 454 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማህበሩ ከዓይነቱ ጋር የሚያስማማበትን ብሔራዊ የኑሮ  ተግባሮች ሁሉ ለመፈፀም ይቻላል” የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ከዚል አንፃር ሲታይ፣ አመልካች የተቋቋመበትን መሠረታዊ ዓላማ ለማሳካት የሚያስችለውን የዳኝነት ጥያቄ የአባላቱን መብትና ጥቅም ለማስከበር በሚያስችለው አግባብ ለመጠየቅ ከአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 55፣አንቀጽ 110 እና በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 454 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌዎች የሚፈቅድለት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡

10. ከዚህ በተጨማሪ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 35 ድንጋጌ፣ ከአንድ ሰው አንድ አይነት መብትና ጥቅም የሚጠይቁ ካሉ ከሳሾች፣ መብትና ጥቅማቸውን እነሡን በመወከል የሚጠይቅ በህግ ዕውቅና የተሰጠውና ህጋዊ ህልውና ያለው ማህበር በማቋቋም፣ በማህበሩ መብታቸውን እንዲጠይቅላቸው በማህበሩ መመሥረቻ ፅሑፍ በሙሉ ፈቃድና ስምምነት በማፅደቅ የሚሰጡትን ስምምነት ዋጋ በሚያሳጣ ሁኔታ መተርጐም ያለበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በአንፃሩ የህግ ህልውና ያገኙ የሲቪል ማህበራት ፣የተቁቋሙለትን ዓላማ ለማሣካትና፣ ሲያከራክሩት የሚፈልጉትን የአባላታቸውን መብትና ጥቅም  ለማሰከበር፣ ለፍርድ ቤት ለግልግል ተቋም ወይም ለሌሎች የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጣቸው አካላት ጥያቄዎችን  ለማቅረብ  በሚያስችል  መንገድ  የሕጉን  ድንጋጌዎች  መተርጐም   በግልና


በተናጠል እንዲሁም በራሳቸው ችሎታ ተከራክረው መብትና  ጥቅማቸውን ለማስከበር ከፍተኛ ወጭና ጊዜ የሚጠይቃቸው ግለሰቦች፣ ለዚህ ዓላማ በመሠረቱት ማህበር በኩል መብትና ጥቅማቸውን በቀላሉ ለማስከበር የሚችሉበትን ዕድል በሚያሰፋና የሰዎችን ፍትህ የማግኘት መብት የሚያረጋግጥ አግባብ መተርጐም ያለበት ሆኖ አገኘተነዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ተጠሪ በሕግና በሚመለከተው የመንግስት አካል ዕውቅና የተቋቋሙ ማህበራት፣ የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት፣ የሚያስችላቸው የዳኝነት ጥያቄ የማቅረብ  መብት የላቸውም በማለት ያቀረበው መቃወሚያ ከላይ በዝርዝር የጠቀስናቸውን የሕግ ድንጋጌዎች ይዘትና ተግባራዊ ተፈፃሚነት ያላገናዘበ በመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡

11. የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከላይ በዝርዝር የገለጽናቸውን ድንጋጌዎች ይዘትና ተግባራዊ ውጤት ሣያገናዝቡ አመልካች የግልግል ዳኛ እንዲሰየምለት ለማቅረብ አይችልም በማለት የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

 ው ሣኔ

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ትእዛዝ ተሽሯል፡፡

2. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 197501 ታህሳስ 1 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡

3.  በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

4.  መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡