96310 criminal procedure/ confession by accused/ effect of confession on co-accuseds

አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሒደትም ሆነ ክሱን
ለሚሠማው ፍ/ቤት የሚሠጠው የእምነት ቃል ውጤት በራሱ በቃል
ሠጪው ላይ ተወስኖ የሚቀር ከመሆኑ ውጪ ወንጀሉን
አልፈፀምኩም ብሎ በሚከራከር ሌላ ተከሣሽ ላይ ህጋዊ ውጤት
ሊያስከትል የማይችል ሥለመሆኑ፣
የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 27፣35 እና 134

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል


የሰ/መ/ቁጥር 96310

ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም.


 

አመልካች፡-አቶ ጉዲና ለማ ገዛኸኝ - አባት ነኝ በማለት አቶ ለማ ገዛኸኝ ከጠበቃ ልዑል አያለው ጋር ቀረቡ

ተጠሪ፡- የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት የስ/ፀ/ሙስና ኮሚሽን ዐ/ሕግ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ተጠሪ ያቀረበባቸውን በስራ ተግባር ላይ የሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ከባድ የሙስና የወንጀል ክስ የተመለከተው በቤንች ማጂ ዞን የቤንች አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠባቸው እና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች በትዕዛዝ የጸናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

 

ተጠሪ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ በነበሩት የአሁኑ አመልካች እና በሌሎች አምስት ሰዎች ላይ ያቀረበው አንደኛ ክስ ይዘት ባጭሩ፡-ተከሳሾቹ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)፣33 እና413(2) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በሚዛን አማን ሆስፒታል  ውስጥ

1ኛ ተከሳሽ የዋናው መድኃኒት ቤት ጠባቂ፤2ኛ ተከሳሽ የመድኃኒት ማሰራጫ ክፍል ባለሙያ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ የግዢና የፋይናንስ የስራ ሂደት ባለቤት ሆነው በመስራት ላይ በነበሩበት ጊዜ በወንጀሉ ስራና በሚሰጠው ውጤት በመስማማት 1ኛ ተከሳሽ ይሰራበት ወደነበረው የመድኃኒት መጋዘን በ13/03/2005 ዓ.ም. ገቢ የተደረጉትን ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች 2ኛ ተከሳሽ ይሰራበት ወደነበረው የመድኃኒት ማሰራጫ እንዲገቡ ካደረጉ በኃላ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች እነዚህኑ መድኃኒቶች በ17/04/2005 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 1፡00 ሰዓት ላይከአማን ከተማ በሆስፒታሉ ተሽከርካሪ ጭነው በማውጣት እና ወደ ሚዛን ከተማ በማጓጓዝ ወደ ባጃጅ አዛውረው በማጓጓዝ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ለተጠቀሱት ተከሳሾች በብር 23,200 ከሸጡ በኃላ መድኃኒቱ ከ5ኛ ተከሳሽ እጅ፤የሽያጩ ገንዘብ ደግሞ ከ2ኛ ተከሳሽ እጅ የተያዘ በመሆኑ በስራ ተግባር ላይ የሚፈጸም የመውሰድ እና የመሰወር ከባድ የሙስና ወንጀል አድርገዋል የሚል ሲሆን ሁለተኛ ክስ የቀረበው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)እና 420(1)ተጠቅሶ መድኃኒቶቹ ወጥተዋል በተባለበት ጊዜ በስራ ላይ በነበሩት የሆስፒታሉ የጥበቃ ሰራተኞች ላይ ነው፡፡አመልካች ተጠይቀው ወንጀሉን አላደረግሁም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ የሌሎቹንም ተከሳሾች የእምነት ክደት ቃል ጠይቆ ከመዘገበ በኃላ በተጠሪ በኩል የቀረቡ በአንደኛ ክስ አስራ ሁለት፤በሁለተኛ ክስ ደግሞ አንድ በሁለቱም ክሶች በድምሩ የአስራ ሶስት ምስክሮችን ምስክርነት ከሰማ እና  የተጠሪን


የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኃላ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በክሱ መሰረት ያስረዳባቸው መሆኑን ገልጾ መከላከያቸውን ማሰማት እንዲጀምሩ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር142 መሰረት ትዕዛዝ በመስጠቱ አመልካች ከዋናው የመድኃኒት ስቶር የመድኃኒቶችን የአወጣጥ ስርዓት ያስረዱልኛል ያሏቸውን ሁለት የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው አሰምተዋል፡፡

 

ከዚህ በኃላ ፍርድ ቤቱ የቀሪዎቹንም ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ከሰማ በኃላ በሁለቱ ወገኖች የቀረበውን አጠቃላይ ክርክር እና ማስረጃ መርምሮ አመልካቹ ባሰሟቸው የመከላከያ ምስክሮች በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተመሰረተባቸውን ፍሬ ነገር ለማስተባበል አልቻሉም በማለት ከ1ኛ እስከ 3ኛ በተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ በክሱ በተጠቀሰባቸው ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ውሳኔ በማስተላለፍ ግራ ቀኙ የቅጣት አስተያየታቸውን በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡በመቀጠልም በክሱ የተመለከተው ወንጀል በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ደረጃ ያልወጣለት መሆኑን ገልጾ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች የተሰጣቸውን መንግስታዊ አደራ ወደ ጎን በመተው ወንጀሉን የፈጸሙት ለሕዝብ ጥቅም  ተብሎ ወደ ሆስፒታሉ በገባው መድኃኒት ላይ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሶ ወንጀሉን በክብደቱ እና በአፈጻጸሙ በከባድ ደረጃ በመመደብ ቅጣቱ በአባሪ አንድ በእርከን 29 ስር የሚወድቅ መሆኑን፣ተጠሪ በጠየቀው እና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 84(1)(ሀ)(ለ)እና(መ) ስር በተመለከተው መሰረት በሶስት የማክበጃ ምክንያቶች እርከኑ ከ29 ወደ 32 ከፍ የሚል መሆኑን እና የአመልካች የቀድሞ ጠባይ መልካምነት በአንድ የማቅለያ ምክንያትነት ሲያዝ ቅጣቱ ከእርከን 32 ወደ 30 ዝቅ የሚል መሆኑን ገልጾ ቅጣቱን በመመሪያው መሰረት በማስላት በአባሪ አንድ በእርከን 30 ስር አመልካች በአስራ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች የቀረበላቸውን እንደቅደም ተከተሉ ይግባኝ እና አቤቱታ ዘግተው በማሰናበታቸው ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ የስር 2ኛ ተከሳሽ የሰጠውን የተከሳሽነት ቃል መሰረት በማድረግ አመልካቹ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 413(2) ስር ጥፋተኛ የመባሉን እና የተጠቀሰበትን አንቀፅ አግባብነት ተጠሪው ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት አመልካች ተጠይቀው ወንጀሉን አላደረግሁም በማለታቸው ተጠሪው አቅርቦ ካሰማቸው አስራ ሶስት ምስክሮች መካከል፡-

 

· 1ኛ ምስክር የሆስፒታሉ ሾፌር መሆኑን፣በዕለቱ ምስክሩ ይዞት የነበረውን ሌላ ተሽከርካሪ አቁሞ አምቡላንሱን እንዲይዝ 3ኛ ተከሳሽ ወደ አመሻሽ አካባቢ እንደነገረው፣በኃላም ጊዜው ያለፈበት ስለሆነ ችግር የለበትም በማለት 3ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ሆነው 2ኛ ተከሳሽ ከሚሰራበት የመድኃኒት ማሰራጫ መጋዘን ውስጥ በሶስት ካርቶን ያሉ መድኃኒቶችን በአምቡላንሱ ውስጥ እንደጫኑ፣2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጥበቃዎቹ እንዳይጠረጥሩን በማለት በእግራቸው ወጥተው ውጪ እንደጠበቁት እና ከግቢው ውጪ እንደተሳፈሩ፣በመንገድ ላይ ሲደርሱ 2ኛ ተከሳሽ ከአምቡላንሱ ወርዶ በባጃጅ እንደተሳፈረ፣3ኛ ተከሳሽ ግን አብሮት መሄድ እንደቀጠለ፣ የተወሰነ ቦታ ሲደርሱ 3ኛ ተከሳሽ በጠየቀው መሰረት    አምቡላንሱን


እንዳቆመው፣2ኛ ተከሳሽም በባጃጅ እንደደረሰባቸው፣ቀጥሎም መድኃኒቱን ሁለቱ ተከሳሾች ወደ ባጃጁ እንዳዛወሩት፣ምስክሩ በዚሁ እንደተለያቸው፣በሚዛን ከተማ ውስጥ ሲዘዋወር አደባባይ አካባቢ በዚያኑ ምሽት በፖሊሶች ተይዞ ስለጫናቸው  መድኃኒቶች ሲጠየቅ ዝርዝሩን እንደነገራቸው  በመግለጽ ምስክርነት መስጠቱን፤

· 7ኛ ምስክር የሆስፒታሉ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ከስራ ሰዓት ውጪ ምሽት አካባቢ በግቢው ውስጥ 2ኛ ተከሳሽ ከሚሰራበት መድኃኒት ማሰራጫ አካባቢ መቆየታቸውን፣በወቅቱም 1ኛ ምስክር የሆስፒታሉን አምቡላንስ ይዞ እዚያው አካባቢ የነበረ መሆኑን እና በእለቱ 1ኛ ተከሳሽን በአካባቢው እንዳላየው በመግለጽ ምስክርነት መስጠቱን፤

· 2ኛ ምስክር በመንገድ ላይ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአምቡላንስ ውስጥ የነበረውን  መድኃኒት 2ኛ ተከሳሽ ተሳፍሮ ወደመጣበት ባጃጅ ሲያዛውሩ አይቶ ለፖሊሶች ጥቆማ እንደሰጠ በመግለጽ ምስክርነት መስጠቱን፤

· 11ኛ እና 13ኛ ምስክሮችም 2ኛ እና  3ኛ  ተከሳሾች  በአምቡላንስ  ውስጥ የነበረውን መድኃኒት ወደ ባጃጅ ሲያዛውሩ ማየታቸውን በመግለጽ ምስክርነት መስጠታቸውን፤

· 3ኛ፣4ኛ፣እና 12ኛ ምስክሮች ከ2ኛ ምስክር በተሰጠው ጥቆማ መሰረት ተገቢውን ክትትል አድርገው መድኃኒቶቹን ከ5ኛ ተከሳሽ እጅ፤የሽያጭ ገንዘቡን ደግሞ በነጋታው ከ2ኛ ተከሳሽ ቤት መያዛቸውን በመግለጽ ምስክርነት መስጠታቸውን፤

·     8ኛ ምስክር ቃላቸውን የሰጡት በ2ኛ ክስ በተከሰሱት የጥበቃ ሰራተኞች ላይ መሆኑን፤

· 1ኛ ተከሳሽ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የነበረው ስለመሆኑ ወይም በዕለቱ የወንጀሉ አፈጻጸም ተጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ከ2ኛ እና ከ3ኛ ተከሳሾች ጋር ታይቶ የነበረ ስለመሆኑ ከላይ ከተዘረዘሩት ምስክሮች መካከል አንዳቸውም የጠቀሱት ነገር አለመኖሩን፤

የመዝገቡ ግልባጭ የሚያመለክት ሲሆን የስር ፍርድ ቤቶችም ከላይ በተጠቀሱት ምስክሮች በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የተሰጠ ምስክርነት ስለመኖሩ በውሳኔአቸው ላይ አልገለጹም፡፡

 

ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር ግንኙነት ያለው ምስክርነት የሰጡት 5ኛ፣6ኛ፣9ኛ እና 10ኛ ምስክሮች ናቸው፡፡5ኛ እና 6ኛ ምስክሮች በሆስፒታሉ ውስጥ በቀን ሠራተኝነት የሚያገለግሉ ሲሆኑ እነዚህ ምስክሮች ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት 1ኛ ተከሳሽ 5ኛ ምስክርን ጠርቶ  መድኃኒቶቹን 2ኛ ተከሳሽ ወደሚሰራበት ማሰራጫ እንዲወስድ በነገረው መሰረት ሁለቱ ምስክሮች 1ኛ ተከሳሽ ወደሚሰራበት ዋና መጋዘን ሄደው በካርቶን የተደረጉ መድኃኒቶችን 2ኛ ተከሳሽ ወደሚሰራበት ማሰራጫ መውሰዳቸውን እና ይህ ስራ ሁል ጊዜም የሚያከናውኑት የተለመደ ስራ መሆኑን በመግለጽ የመሰከሩ ናቸው፡፡9ኛ ምስክር በሙያው ፋርማሲስት ሆኖ ቀድሞ የሆስፒታሉ ሰራተኛ የነበረ እና 10ኛ ተከሳሽ ደግሞ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ሲሆን የሰጡት ምስክርነት ይዘትም በዕለቱ 1ኛ ተከሳሽ ከሚሰራበት መጋዘን ወጪ ተደርገው 2ኛ ተከሳሽ ወደሚሰራበት ማሰራጫ ከተወሰዱት መድኃኒቶች መካከል አንደኛው ዓይነት መድኃኒት ወጪ የተደረገው ማሰራጫ መቀመጥ ከሚገባው መጠን በላይ መሆኑን እና መድኃኒቶቹ ወጪ  የተደረጉበት ሰነድም ስርዝ ድልዝ የሚታይበት መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡በተጠሪ በኩል የቀረበው አጠቃላይ የሰው ማስረጃ ከላይ የተመለከተው ሲሆን በማስረጃነት ከቀረቡት ሰነዶች መካከል 1ኛ ተከሳሽን የሚመለከተው መድኃኒቶቹ የተጠየቁበት እና ወጪ የተደረገበትሰነድ መሆኑንም ከመዝገቡ ግልባጭ መገንዘብ ይቻላል፡፡በመሰረቱ 1ኛ ተከሳሽ የዋናው መድኃኒት ቤት መጋዘን ኃላፊ ሲሆኑ የስራ ድርሻቸውም በሆስፒታሉ የበላይ አመራር ተፈቅዶ፣ተፈርሞ እና ተረጋግጦ በሚደርሳቸው ሰነድ መሰረት መድኃኒቶችን ማስረከብ ከመሆኑ በቀር መድኃኒት ወጪ እንዲሆን የመፍቀድ


ወይም መጠኑን የመወሰን የስራ ድርሻ ያላቸው ስለመሆኑ፣ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት መድኃኒቶች ከ1ኛ ተከሳሽ መጋዘን ወጪ የተደረጉት ይህንን የተለመደ አሰራር በሚጥስ ሁኔታ በሆስፒታሉ የበላይ አመራር በጽሁፍ የተሰጠ ትዕዛዝ ሳይኖር ስለመሆኑ እንዲሁም ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት መድኃኒቶች 1ኛ ተከሳሽ ከተረከቧቸው መድኃኒቶች መካከል በጉድለት የተገኙ ስለመሆኑ በተጠሪ በኩል የቀረበ ክርክርና ማስረጃ ስለመኖሩ የመዝገቡ ግልባጭ አያመለክትም፡፡

 

ይልቁንም ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው የቤንች አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ ክሱን እንዲከላከሉ ብይን የሰጠውም ሆነ ተከሳሹ የቀረበባቸውን ማስረጃ አላስተባበሉም በማለት የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ወንጀሉን ስለማድረጋቸው በምስክሮች ወይም በሰነድ ማስረጃ ተመስክሮባቸዋል በሚል ሳይሆን 2ኛ ተከሳሽ ወንጀሉን ያደረገ ስለመሆኑ እና ያደረገውም በ1ኛ ተከሳሽ ጠንሳሽነት ወይም አነሳሽነት ስለመሆኑ በመግለጽ በምርመራ ጊዜ እንዲሁም ክሱ በተሰማበት ጊዜ የሰጠውን የእምነት ቃል ዋነኛ ማስረጃ አድርጎ በመቀበል ስለመሆኑ በውሳኔው ላይ በግልጽ ያሰፈረው ሲሆን በበኩላችን አንድ ተከሳሽ የሰጠው የእምነት ቃል በሌላኛው ተከሳሽ ላይ በማስረጃነት ሊወሰድ የሚችልበት የሕግ አግባብ መኖር አለመኖሩ እና በዚህ ዓይነቱ ማስረጃ ዐቃቤ ሕግ በክሱ መሰረት አስረድቷል ለማለት የሚቻል መሆን አለመሆኑ በአግባቡ መጤን የሚገባው ሆኑ አግኝተናል፡፡

 

በመሰረቱ አንድ ሰው ወንጀል አደረገ የሚባለው ሕገወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ የተደነገገን ድርጊት ፈጽሞ በተገኘ ጊዜ መሆኑ እና አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለውም ወንጀሉን የሚቋቁሙት ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23(1) እና (2) ስር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን ማንም ሰው በዋና ወንጀል አድራጊነት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣው በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር ወንጀሉን ያደረገ በሆነ ጊዜ ወይም ወንጀሉን እርሱ በቀጥታ ባያደርገውም እንኳን በመላ አሳቡና አድራጎቱ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ድርጊቱን የራሱ ያደረገ በሆነ ጊዜ ስለመሆኑም በዚሁ ሕግ በአንቀጽ 32(1) ስር ተደንግጓል፡፡ በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ የክስ ማመልከቻ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል እንዲሁም የወንጀሉ መሰረታዊ ነገርና ሁኔታዎች የተገለጹበት ሊሆን እንደሚገባ እና ስለ ወንጀሉና ስለሁኔታው የሚሰጠው ዝርዝር መግለጫ ተከሳሹ ፈጸመ የተባለውን ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን እንደሚገባው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና 112 ድንጋጌዎች ላይ የተደነገገውም ከሳሹን ወገን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23(2) ስር የተመለከቱት የወንጀል ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸውን ለማስረዳት እንዲያስችለው መሆኑን ከድንጋጌዎቹ ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡በሌላ አነጋገር ከሳሽ ወገን በክሱ መሰረት የማስረዳት ግዴታ ተወጥቷል ሊባል የሚችለው ቀደም ሲል በተጠቀሱት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና 112 ድንጋጌዎች መሰረት አዘጋጅቶ ባቀረበው የክስ ማመለከቻ መሰረት ተከሳሹ ወንጀል መፈጸሙን ማስረዳት በቻለ ጊዜ ነው፡፡ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ተከሳሹ መከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ክሱን እንዲከላከል በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 142 መሰረት ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚችለው ከሳሽ ወገን ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያደርገው መሆኑን ሲያረጋግጥ ስለመሆኑ በዚሁ ሕግ በቁጥር 141 ስር በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

 

እንደሚታወቀው አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሂደትም ሆነ ክስ ከቀረበበት በኃላ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት የሚሰጠው የእምነት ቃል በሕግ ተቀባይነት ካላቸው የማስረጃ


ዓይነቶች ውስጥ የሚካተት መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 27፣35 እና 134 ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ የዚህ ዓይነቱን የእምነት ቃል የሚሰጠው የራሱን አጥፊነት አምኖ በመቀበል እንደሆነ የሚገመት በመሆኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ተከሳሾች ወይም ማናቸውም ሌላ ሰው በወንጀሉ አደራረግ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ በእምነት ቃሉ ውስጥ የሚገልጻቸው ፍሬ ነገሮች ምናልባት ለቀጣይ ምርመራ ፍንጭ ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል ከሚባል በቀር በማናቸውም ሰው ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡በሌላ አነጋገር አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሂደትም ሆነ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት የሚሰጠው የእምነት ቃል ውጤት በራሱ በቃል ሰጪው ላይ ተወስኖ የሚቀር ከመሆኑ ውጪ ወደሌሎች ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች ሊተላለፍ የሚችል አለመሆኑን ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች አነጋገር እና ይዘት መገንዘብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ ወንጀሉን የፈጸሙት በጋራ ወይም በመተባበር መሆኑን በማመን አንደኛው ተከሳሽ የሚሰጠው የእምነት ቃል ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ በሚከራከረው ሌላኛው ተከሳሽ ላይ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትል የማይችል ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 94450 በ25/07/2006 ዓ.ም. የሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በተያዘው ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

 

ሲጠቃለል የክልሉ የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን ዐ/ሕግ በአመልካቹ ላይ ባቀረበው በስራ ተግባር ላይ የሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሰረት ለማስረዳት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ባልወጣበት ሁኔታ ክሱን የተመለከተው በቤንች ማጂ ዞን የቤንች አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ተከሳሽ ወንጀሉን ያደረገው በ1ኛ ተከሳሽ አነሳሽነት መሆኑን ገልጾ የሰጠውን የእምነት ቃል በሕግ ከተደነገገው ውጪ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ጭምር በማስረጃነት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሰጠው ትዕዛዝም  ሆነ በመጨረሻ የሰጠውና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች በትዕዛዝ የፀናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በቤንጅ ማጂ ዞን የቤንች አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 11935 በ21/09/2005 ዓ.ም. ከሰጠው እና በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች እንደቅደም ተከተሉ በመዝገብ ቁጥር 00918 በ28/10/2005 ዓ.ም. እና በመዝገብ ቁጥር 01110 በ22/02/2006 ዓ.ም. በትዕዛዝ ከጸናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ውስጥ የስር 1ኛ ተከሳሽ (የአሁኑ አመልካች) አቶ ጉዲና ለማ ገዛኸኝን የሚመለከተው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ክፍል በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 195(2)(ለ)(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪ ባቀረበው የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ አመልካች ወንጀሉን ማድረጋቸውን  ያላስረዳ እና በሕግ የተጣለበትን የማስረዳት ግዴታ ያልተወጣ በመሆኑ አመልካች አቶ ጉዲና ለማ ገዛኸኝ ከተከሰሱበት በስራ ተግባር ላይ የሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ከባድ የሙስና የወንጀል ክስ በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል በማለት ወስነናል፡፡


 

 

3. በአመልካች ላይ ተጥሎ የነበረው የአስራ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት የተሻረ በመሆኑ የሚፈለጉበት ሌላ ጉዳይ አለመኖሩን አረጋግጦ አመልካች አቶ ጉዲና  ለማ ገዛኸኝን ወዲያውኑ ከእስር እንዲለቃቸው አመልካቹ ለሚገኙበት በኦሮሚያ ማረሚያ  ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ለኢሉባቦር ዞን ማረሚያ ቤቶች ጽ/ቤት ትዕዛዝ ይተላለፍ፡፡ይፃፍ፡፡

4. እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ በቤንጅ ማጂ ዞን ለቤንች  አካባቢ ከፍተኛ ፍርድቤት፣ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ለኢሉባቦር ዞን ማረሚያ ቤቶች ጽ/ቤት ይላክ፡፡ለአመልካቹም በማረሚያ ቤት በኩል ይድረስ፡፡

5.  ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡