103910 contract/ interpretation of contract

አንድ ውልን ለመተረጎም አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም የውሉ ድንጋጌ መተርጎም ያለበት በውሉ አስገዳጅ የሆነው ወገን በሚጠቀምበት ሁኔታ ሳይሆን በውሉ ተገዳጅ ለሆነው ሰው ምቹ በሚሆንበት አኳኋን ስለመሆኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1738(1)

የሰ/መ/ቁ. 103910 ቀን 28/01/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ - አልቀረቡም

 

ተጠሪ፡- አቶ ሀብታሙ ተመስገን - ጠበቃ አቶ ሙሉ ገ/ስላሴ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 

        ር ድ

 

ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነው ለስልጠና የወጣ ወጪ በውሉ መሰረት ይመለሰልኝ በማለት አመልካች በተጠሪ ላይ ላቀረበው ክስ የተሰጠው ውሳኔ ነው፡፡

 

ከመዝገቡ መረዳት እንደሚቻለው በግራ ቀኙ መካከል በቅድሚያ ህዳር 9/2002 ዓ/ም በተደረገ ውል በአመልካች የስልጠና ት/ቤት ውስጥ የሚሰጠውን የቢ 737 አውሮፕላን አካላት ስልጠና ተጠሪ በመውሰድ ለ24 ወራት ለማገልገል ይህን ግዴታውን ባይወጣ ግን የስልጠናውን ወጪ ብር 50,000.00 ለአመልካች ለመክፈል ተስማምቶ ለ 9 ወራት ቀሪ አገልግሎት ሳይስጥ ስላቋረጠ ብር

16,664.00 እንዲመልስ ፣ በሌላም በኩል ሀምሌ 24 ቀን 2002 ዓ/ም በተደረገ ውል ተጠሪ በአሜሪካን ሀገር ቢሲያትል በሚገኘው የቦይንግ ስልጠና ማዕከል የሚሰጠውን የቢ 777 አውሮፕላን አካላት ስርዓተ ትምህርት ለመውሰድ የሚያስፈልገውን ወጪ ብር 389,059.23 አመልካች ለመሸፈን ተጠሪ ደግሞ ስልጠናውን ወስዶ ለ36 ወራት ለማገልገል ይህን ግዴታውን ባይወጣ ግን የስልጠናውን ወጪ ለመክፈል የተሰማማ ቢሆንም ስራውን ጥሎ ስልጠፋ የሁለተኛውን ውል የስልጠና ወጪ ብር 389,059.23 በአጠቃላይ ብር 407,806.23 ከነወለዱ እንዲከፈላቸው እንዲወሰን ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡


ክሱ የቀረበለት የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ተጠሪ የሰጡትን መልስ ፤ ውሎቹ የተደረጉበትን ጊዜና የውሎችን ይዘት በመመርመር ተጠሪ በቀደመው ውል መሰረት ግዴታውን በመፈጸም ላይ እያለ ለ2ኛው ስልጠና የተላከ በመሆኑ ፤ ሀምሌ 24 ቀን 2002 ዓ/ም የተፈረመው ውል አንቀጽ 7 ደግሞ ሰልጣኙ የቀድሞ ግዴታውን በመፈጸም ላይ እያለ ለሌላ ስልጠና ቢጠራ (ቢመደብ) ሰልጣኙ ለዚሁ ስልጠና አዲስ ውል እንደሚፈርምና የአገልግሎት ጊዜውም በዚሁ  ጊዜ የሁለቱንም ስምምነት ለመሸፈን እንደሚጠቃለል የሚደነግግ በመሆኑ ፤ ይህም በቀደመው ግዴታ መሰረት ሳይፈጽም የቀረውን ጊዜ ቀሪ የሚያደርገው በመሆኑ ከቀደመው ውል ሳይፈጸም ቀርቷል ተብሎ የተጠየቀውን የ9 ወራት የክፍያ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ፤ በ2ኛው ዙር በተደረገው ስምምነት መሰረት ስልጠናውን ወስዶ በውሉ ለተመለከተው ጊዜ ያላገለገለ በመሆኑ ለስልጠና የወጣውን ወጪ ብር 389,059.23 ክሱ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ ወለድ ጋር ተጠሪ እንዲከፍል ወስኗል፡፡

 

አመልካች የሁለቱም ውሎች ግዴታዎች በ2ኛ ውል እንደተጠቃለለ ተደርጎ ውሉ መተርጎሙን በመቃወም ይግባኝ ለፌ/ከፍ/ፍ/ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ በመጨረሻ ውሉ የተተረጎመበት መንገድ ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም በማለት የስር ፍ/ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ አጸንቷል፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ላይ ነው፡፡

 

አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ የስር ፍ/ቤቶች ውሉን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም የሰጡት ውሳኔ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ተብሎ እንዲሻርና ህዳር 9/2002 ዓ/ም በተደረገው ውል መሰረት ተጠሪ ላላገለገለበት ጊዜ የሚፈለግበትን ብር 16,664.00 ለአመልካች መክፈል አለበት ተብሎ በዚህ ነጥብ ላይ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ተሻሽሎ እንዲወሰን ጠይቀዋል፡፡

 

ቅሬታቸው ተመርምሮ ውሉ የተተረጎመበትን አግባብ ለመመርመር ሲባል ተጠሪ ቀርበው መልስ እንደሰጡበት ተደርጓል፡፡

 

በበኩላችን የተያዘውን ጭብጥ ግራ ቀኝ ወገኖች ካደረጉት ክርክር ፣ ቅሬታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከህጉ ጋር በማገናዝብ መርምረናል፡፡

 

ከክርክሩ መረዳት እንዲሚቻለው ለክሱ መነሻ የሆኑት ውሎች ስለመደረጋቸው ፤ ተጠሪም በሁለቱም ውሎች መሰረት ስልጠና መውሰዱ ፤ ሁለተኛው ስልጠና የጀመረው  ተጠሪ የቀደመውን ስልጠና አጠናቆ ግዴታውን በመወጣት ላይ እያለ ነገር ግን የቀደመውን ግዴታ ከማጠናቀቁ በፊት መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ከቀደመው ውል የሚጠበቀው የ9 ወራት የአገልግሎት ቀሪ ዋጋ ብር 16,664.00 ተጠሪ ሊከፍል አይገባም ተብሎ በስር ፍ/ቤት የተወሰነው ሁለተኛው የስልጠና እና የአገልግሎት ውል የቀረውን የቀደመ ግዴታ የሚጠቀልል እና ቀሪ


የሚያደርግ ነው በሚል ምክንያት ነው፡፡ አመልካች ይህን ውሳኔ የተቃወሙት በግራ ቀኙ መካከል የተደረገውን ውል እና ህጉን መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት ነው፡፡

 

ክርክሩ ሊወሰን የሚገባው በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የተደረጉትን ውሎችና ለጉዳዩ አግባብነት የሚኖረውን ህግ መሰረት በማደረግ ሲሆን አከራካሪ የሆነውን የውሉን አንቀጽ 7 ይዘት እና ተገቢነተ ያለውን የህጉን ድንጋጌ ተመልክተናል፡፡

 

አመልካች ክሱን ለማስረዳት ባቀረበው ውል አንቀጽ 7 እንደተመለከተው ሰልጣኙ (ተጠሪ) በቀዳሚው ውል የነበረበትን የአገልግሎት ግዴታ ሳይጨርስ ለሌላ ስልጠና ሊመደብ  እንደሚችል

፤ በዚህ ሁኔታ አዲስ ውል እንደሚፈረምና የአገልግሎት ጊዜውም በዚሁ ጊዜ የሁለቱም ስምምነት ለመሸፈን እንደሚጠቃለል ተደንግጓል፡፡

 

አመልካች ይህ የውሉ አንቀጽ ግልጽ እና ተጠሪ የሁለቱም ውሎች የአገልግሎተ ጊዜ አጠቃሎ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት የሚያመለክት ነው በማለት የተከራከሩ ሲሆን ተጠሪ በበኩላቸው ሁለተኛው የስልጠና የአገልግሎት ጊዜ የሁለቱም ስምምነቶች የሚሽፍን (የሚያጠቃልል) መሆኑን በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ የስር ፍ/ቤት የተጠሪን መከራከሪያ ተቀበሎ ወስኗል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም የውሉ ስምምነት በስር ፍ/ቤት የተተረጎመበት መንገድ ስህተት ሆኖ እንዳላገኘው በውሳኔው አመልክቷል፡፡

 

ከላይ እንዲተመለከተው የውሉ አንቀጽ 7 ተጠሪ የሚኖርበትን የአገልግሎት ጊዜ ግዴታ በተመለከተ አጠራጣሪ ይዘት ያለው ነው፡፡ እንዲህ አይነት አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም የውሉ ድንጋጌ መተርጎም ያለበት በውሉ አስገዳጅ የሆነው ወገን በሚጠቀምበት ሁኔታ ሳይሆን በውሉ ተገዳጅ ለሆነው ሰው ምቹ በሚሆንበት አኳኋን ነው፡፡ ይኸው የትርጉም መርህ በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1738(1) ስር ተደንግጓል፡፡

 

ከዚህ አንጻር ሲታይ በቀዳሚው ውል የነበረበትን የአገልግሎት ግዴታ ሳይጨርስ ለሌላ ስልጠና ሲመደብ እና አዲስ ውል ሲያዝ የአገልግሎት ጊዜ ግዴታን በተመለከተ የሚደነገግው የውሉ አንቀጽ 7 መተርጎም ያለበት አመልካችን በሚጠቅም መንገድ ሳይሆን በአንቀጹ ተገዳጅ የሆነውን ተጠሪን በሚጠቅም መንገድ ነው፡፡

 

በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች ጉዳዩን ከውል ድንጋጌዎች አተረጓጎም አንጻር አይተው አለመወሰናቸው የሚነቀፍ ቢሆንም በውጤት ደረጃ ተጠሪ ከቀዳሚው ስምምነት ሳይፈጸም ቀረውን የአገልግሎት ጊዜ ግዴታ በገንዘብ ተሰልቶ የቀረበውን ሊከፍል አይገባም በማለት የሰጡት ውሳኔ የሚነቀፍ ባለመሆኑ ተከታዩ ተወስኗል፡፡


 

 

 ው ሳ ኔ

 

1ኛ. የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 73094 የካቲት 19/2005 ዓ/ም ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሁም የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ.135184 ግንቦት 13/2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በውጤቱ ጸንቷል፡፡

 

2ኛ. የሰበር ክርክሩ ስላስከተለው ወጪ ግራ ቀኙ የራሳቸውን ይቻሉ፡፡

 

3ኛ. የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይተላለፍ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

ሃ/ወ