96041 contract/ evidence

በውል የተገባ አንድ ግዴታ መፈጸም ያለመፈጸሙን ለማጣራት የግራ ቀኙ ተዋዋይ ወገኖች የገቡት ግዴታ እና ያላቸው መብት የሚገልጽ የሰነድና የሰው ማስረጃ እንዲሁም የግዴታ ልዩ ባህርይ መሰረት በማድረግ ልምድን መዳሰስ የሚጠይቅ ስለመሆኑ ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ 246፣247፣248 እና 249

 

የሰ/መ/ቁ. 96041

 

ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኸሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የቀረበ የለም ተጠሪ፡- ወ/ሮ አልማዝ ግዛው ተወካይ ትዝታ አቡሌ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል

 

 ፍ ር ድ

 

የጉዳዩ መነሻ በፖስታ ቤት በኩል ወደ ኖርዌይ አገር እንዲላክ አመልከች የተረከበው እቃ አደራረስ ላይ በተነሳው ክርክር የግራቀኙ መብትና ግዴታ ምን እንደነበር ከመወሰን እንፃር የቀረበ ነው ፡፡ በሥር ፍርድ ቤት አመልካች ተከሳሽ ተጠሪ ከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል ፡፡ ጉዳዩን በየደረጃው የተመለከቱት የሥር ፍ/ቤቶች የአመልካች መከራከሪያ ነጥቦች ውድቅ በማድረግ የዕቃውን ዋጋ እንዲከፍል በመወሰናቸው ምክንያት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልከች ያቀረበው አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን የቀረበ ነው፡፡

 

የክሱ ይዘትም፡- አመልካች ወደ ኖርዌይ አገር ዕቃውን ለማድረስ ውል የገባ ቢሆንም ዕቃውን በውሉ መስረት ወደ ተባለው አገር ባለማድረሱ ነው የዕቃው ግምትና የማጓዣ ክፍያ በድምር ብር 9374.38 /ዘጠኝ ሺህሦስት መቶ ሰባ አራት 38/100) እንዲከፍላት ተጠሪ ዳኝነት መጠየቋን የሚያሳይ ነው ፡፡


የአሁኑ አመልካች በሰጠው መልስም በግራቀኙ ስምምነት መስረት ዕቃው ወደ ኖርዌይ ተልኮ ተቀባይ ካላገኘ እንደሚመጣ መፈረማቸው ዕቃው ወደ ተባለው አገር ተልኮ ተቀባይ ያጣ በመሆኑ ወደ ሀገር ቤት እንደተመለሰ ፤የተጠሪ ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ሲል ተከራክረዋል፡፡

 

የሥር ፍርድ ቤትም የግራቀኙ ክርክር ከመረመረ በኃላ አመልካች ዕቃው ወደ ኖርዌይ አገር ልኮት ተቀባይነት ካጣ መመለስ አልነበረበትም ከስምምነታቸው ውጭ እንዲመለስ ዕቃው ወደ ኖርዌይ አገር ስለመላኩ እና ዕቃውን የሚቀበል ሰው ስለመጥፋቱ ያቀረበውን ክርክር ውድቅ በማድረግ አመልካች ካሳ እንዲከፈል የካሳ መጠኑም ብር 5300 እንዲሁም ውጪና ኪሳራ ብር 750 እንዲሆን ፍርድ ሰጥቷል ፡፡ የአሁኑ አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቤቱታው የቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱም ግራቀኙን ካከራከረ በኃላ ዕቃውን ወደ ኖርዌይ አገር መላኩ አልተረጋገጠም በሥር ፍ/ቤት የተወሰነው የካሳ መጠን በማሻሻል ብር 5000 እና ወጪና ኪሳራ ብር 750 በድምር ብር 5750.00 አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል ወስኗል ፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪም ጥሪ ተደርጎላት ቀርባ ግራ ቀኙ የጽሐፍ ክርክር አድርጓል ፡፡ አመልካች በሰበር አቤቱታው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ዕቃ ወደ ኖርዌይ አገር አድርሶ ተቀባይ በማጣቱ ንብረቱ ወደ ኢትዮጵያ እንደ ተመለሰ ስለ ድርጅቱ አሠራር ለማስረዳት የቆጠራቸው ምስክሮች ሳይደመጡ ጉዳዩ መወሰኑ የመደመጥ መብቱ እንደሚጋፋ በመግለጽ ውሳኔ እንዲሻር ጠይቋል ፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው የሥር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን አጣርተው የወሰኑት በመሆኑ የሚነቀፍ ነገር የለውም የሚል ክርክር አቅርበዋል ፡፡ አመልካች የመልስ መልስም አቅርበዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም ግራቀኙ በጽሑፍ ያደረጉት ክርክር ፤ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነ ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዝብ እንዲሁም ጉዳዩ ለሰበር ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር እንደሚከተለው መርምሮታል ፡፡

 

ከሥር የክርክር ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች እና ተጠሪ ዕቃን በፖስታ ቤት በኩል የመላክ ውል የተፈራረሙ ስለመሆኑ ያከራከረ ጉዳይ አይደለም፡፡

 

ግራቀኙ እያከራከረ ያለው መሠረታዊ ጭብጥ ለክርክር መነሻ የሆነውን ዕቃ በግራ ቀኙ ስምምነት መሠረት ወደ ኖርዌይ አገር ተልከዋል ወይስ አልተላከም ከተላከ በኃላ ተቀባይ በመጥፋቱ በእርግጥ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል ወይስ አልተመለሰም?የሚለው ነው፡፡ አመልካች    በገባው


ውል መሰረት ዕቃውን ወደ ኖርዌይ አገር እንደላከው እና ዕቃውን የሚቀበል ሰው በመታጣቱ የተላከው ንብረት ወደ አገር ቤት እንደተመለሰ ለዚህም የሰነድና የሰው ምስክሮች የቆጠረ ስለመሆኑ በአንድነት ተከራክሯል፡፡ ተጠሪ በአንፃሩ ንብረቱ ወደ ኖርዌይ አገር አልተላከም ንብረቱ የተላከ ቢሆን አንኳ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዳልነበረበት የበኩላቸውን ክርክር ማቅረባቸውን ተመልክተናል ፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም የግራቀኙ ክርክር ከመረመረ በኃላ ዕቃውን ወደ ኖርዌይ አገር ስለመላኩ አልተረጋገጠም  በሚል ምክንያት አመልካች ካሣ አንዲከፍል ወስነዋል፡፡

 

በመሰረቱ አንድ ግዴታ በአግባቡ መፈጸም ያለመፈጸሙን ለማጣራት የግራቀኙ ተዋዋይ ወገኖች የገቡት ግዴታ እና ያላቸውን መብት የሚገልጽ የሰነድና የሰው ምስክር እንዲሁም የግዴታው ልዩ ባሕሪ መሠረት በማድረግ አለም አቀፍ ልምዱ ጭምር መዳሰስ የሚጠይቅ ነው፡፡በተያዘው ጉዳይ አመልካች ዕቃውን ወደ ኖርዌይ አገር ለመላክ እንደተቀበለ የተካደ ባይሆንም ዕቃውን በእርግጥ ወደ ኖርዌይ አገር መላክ ያለመላኩን የሚያረጋግጠው በሚያቀርበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ እንዲሁም የድርጅቱ አሠራር አጠቃላይ ሁኔታ በመመልከት ነው ፡፡ አመልካች ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ዕቃ ወደ ኖርዌይ አገር ስለመላኩ ከዌብ ሳይት (ድሕረ ገጽ ) የተገኘው መረጃ አያያይዞ እንደቀረበ የሰው ምስክሮች እንደቆጠረ በሚከራከርበት ሁኔታ የሥር ፍርድ ቤቶች የቀረበው ሰነድ በዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ያለው ተቀባይነት እና ምስክሮች የሚሰጡት ቃል ይዘት ምን እንደሆነ ሳይቀበል ቀረበ በተባለው የሰነድ ማስረጃ ብቻ ተመርኩዞ ከድምዳሜ ላይ መድረሱ ጉዳዩን በአግባቡ በማጣራት ውሳኔ አለመስጠቱን የሚያሳይ ነው ፡፡ የአሁኗ ተጠሪ ዕቃውን ለፖስታ ቤት (አመልካች )ካስረከቡ በኃላ ዕቃውን በስምምነቱ መስረት አለመላኩን እቃው ተቀባይ አለማጣቱን የሚያስረዳ ነገር ስለማቅረበቀቸውም በሥር ፍ/ቤት የተመዘገበ ነገር የለም፡፡ ተጠሪ ዕቃውን በውላቸው መሠረት አለመላኩን መነሻ በማድረግ ክስ ማቅረባቸው ሲታይ የቀረበው ክስ በማስረጃ አስደግፈው የማስረዳት ግዴታቸው ሳይወጡ ወይም ፍ/ቤቱ  ዕቃው መላኩን የማስረዳት ግዴታው የአመልካች ነው ለማለት የሚያስችለው ሕጋዊ ምክንያት መኖሩን በውሳኔው ሳይገልጽ በደፈናው ዕቃውን በግራቀኙ ውል መሰረት አልተላከም ከሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱ በሕጉ የተዘረጋው የሙግት አመራር ሥርዓት የተከተለ ሆኖ አላገኘውም፡፡

 

በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች ግራቀኙ እያከራከረ ያለው የውል አፈፃፀም ክርክር በተገቢ ሁኔታ ለመወሰን በሕጉ አግባብ የሚያከራክረው ጭብጥ ተለይቶ የግራቀኙ ማስረጃ ተመዝኖ መሆን ሲገባው የአመልካች የሰው ምስክሮች ቃል ሲያዳምጥ ቀረበ የተባለው የሰነድ ማስረጃም ከዓለም አቀፍ ልምድ ያለው ተያያዥነት በባለሙያ አስተያየት ተደግፎ ማብራሪያ ሳይሰጥበት ፍ/ቤቱ በራሱ ጊዜ ውድቅ ማድረጉ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 246 ፣247፣248 እና 249  የተመለከቱት መሠረታዊ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ነው፡፡በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 136 እና 264(1) እና (2) ድንጋጌዎች በሚያዙት አግባብ ተገቢ    ነው


ያለው ማስረጃ በማስቀረብ እና ጉዳዩን በማጣራት መወሰን እየቻለ ከዚህ በተቃራኒ ቀረበ የተባለው የሰነድ ማስረጃ ብቻ መሰረት በማድረግ አመልካች ግዴታውን አልተወጣም በማለት የደረሰበት ድምዳሜ በሕጉ አግባብ አይደለም ብለናል ፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የሥር ፍ/ቤቶች ጉዳዩን በአግባቡ ሳያጣሩ ውሳኔ ላይ መድሳቸውን የተረዳን በመሆኑ ውሳኔውን ተሽሮ በድጋሚ ተጣርቶ ሊወሰን የሚገባው ነው ፡፡ በመሆኑም የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የፈጸመውን ስህተት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳያርም ውሳኔው ማጽናቱ መሠረታዊ የህግ ስህተት መፈጸሙን የሚያሳይ በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው  ሳ  ኔ

 

1. የባሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ16237 በ 23/11/2005 የሰጠው ፍርድ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 168408 በ 15/04/2006 የሰጠው ውሳኔ ተሸሯል፡፡

2. የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍርድ ይዘቱ እንደተገለፀው ግራቀኙ የሚከራከሩበት ዕቃ ወደ ኖርዌይ አገር ተልኳል ወይስ አልተላከም ? ወደ ኖርዌይ አገር መላኩ ከተረጋገጠ ወደ ኢትዮጲያ የተመለሰው ተቀባይ በመጥፋቱ ነው ወይስ አይደለም ? በአመልካች የቀረበውና ከዓለም አቀፍ ዌብይት ተገኘ የተባለው የሰነድ ማስረጃ ይዘት እና በዓለም አቀፍ ስለፖስታ አላላክ ያለው ልምድ ምን ይመስላል ?በግራቀኙ የውል ስምምነት ዓለም አቀፍ ልምድ ዕቃው የሚላክበት ሥርዓትና አፈፃፀሙ ምን ይመስላል?የሚሉና ተያያዥ ነጥቦች አመልካች የቆጠራቸው ምስክሮች እና በተጠሪ በኩል የሚቀርብ ማስረጃም ካለ አንዲሁም ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ የሚጠቅም ከሆነ በፍ/ቤቱ አነሳሽነት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተገቢ ሕጋዊ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ ይፃፍ፡፡

3.  የዚህ ፍ/ቤት ክርክር ላስከተለው ወጪና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ


-   ዕግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡

-   መዝገቡ ወደ መዝብ ቤት ተመልሷል፡፡ መ/ተ


 

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡