107166 criminal law/ rape

በወንጀለኛ ህግ ቁጥር 627(2) መሰረት በክብረ ንህፅና ላይ የሚደረግ ድፍረት የተበዳይ ክብረ ንፅህና በጥቃቱ መገርሰስ ወይም አለመገርሰስ እንደ መስፈርት ሊቆጠር የሚገባው ስላለመሆኑ

 

የሰ/መ/ቁ. 107166

ቀን ጥቅምት 4/2008 ዓ.ም

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብራሃ መለሰ

አመልካች ፡- መኳንንት ማሞ - አልቀረቡም ተጠሪዎች፡- የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ - አልቀረቡም መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

የሰበር አቤቱታው የቀረበው አመልካች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 627(1) ተላልፎ እድሜዋ 8 ዓመት የሆናት የግል ተበዳይ ሕፃን ያብስራ አብይ ላይ የግብረሥጋ ግንኙነት ፈፅሟል ተብሎ የቀረበበት ክስ የሥር ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ እና የ16 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ወስኖበት በየደረጃው ያሉት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ስለፀኑበት ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈፀመበት ስለሆነ ይታረምልኝ ሲል አመልካች ስለጠየቀ ነው፡፡

 

የአመልካች የቅሬታ ነጥብ የግል ተበዳይ ክብረ ንፅህና ያልተገረሰሰ ስለሆነ በሙከራ ደረጃ የቀረ ስለሆነ የጥፋተኝነት ውሳኔም ሆነ ቅጣቱ እንዲሻሻል የሚል ነው፡፡

 

ይህንኑ ጉዳይ ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል ተብሎ ዐቃቤ ሕግ መልስ ሰጥቷል ፡፡ ዐቃቤ ሕግም የአመልካች ድርጊት በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ተበዳይን ጨምሮ የተረጋገጠ መሆኑን ጠቅሶ በሥር ፍርድ ቤት የተላለፈው የጥፋተኝነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔ በአግባቡ ነው ተብሎ አንዲፀና ተከራክሯል ፡፡በእኛ መኩል ጉዳዩን ከሕጉ ጋር በማገናዘብ መርምረናል አመልካች የሚከራከረው የሕፃኗ ክብረ ንፅህና አለመገርሰሱ በህክምና ማስረጃ ተረጋግጧል በሚል  ምክንያት


ድርጊቱ በሙከራ ቀርቷል በማለት ነው፡፡ከመዝገቡ መገንዘብ የተቻለው አመልካች የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር (ድርጊት) ስለመፈፀሙ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተረጋገጠ ስለመሆኑ ፍሬ ነገር የመመርመርና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን የተሰጣቸው የሥር ፍርድ ቤቶች ያረጋጡት ጉዳይ ነው ፡፡ የድርጊቱ አፈፃፀም ሲታይ አመልካች የወንድ ብልቱን በሕፃኗ የሴት ብልት ውስጥ ማስገባቱ በግል ተበዳይ የተመሰከረ ሲሆን በዚህም ምክንያት ማህፀኗ ላይ የመቅላት ምልክት የታዬ ስለመሆኑ በህክምና ማስረጃ የተረጋገጠ ሲሆን ክብረንፅህና አለመገርሰሱ ድርጊቱን በሙከራ የቀረ ነው የሚያሰኝ ባለመሆኑ የአመልካች ክርክር ተቀባይነት የለውም ፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 627(1) ድንጋጌም ክብረ ንፅህና መኖር አለመኖር ወይም መገርሰስ አለመገርሰስ እንደ መስፈርት ያስቀመጠው ጉዳይ ባለመሆኑ ክርክሩ የሕግ መሠረት የለውም ብለናል፡፡

 

በቅጣት ረገድ አመልካች ጥፋተኛ የተባለበት አንቀጽ 627(1) ከአሥራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት (15-25) በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን የሥር ፍርድ ቤት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወጣውን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት በማድረግ በሕግ ተቀባይነት ያለው እና በማስረጃ የተደገፈ የቅጣት ማቅለያ ተቀብሎ የድንጋጌው መነሻ የሆነ ቅጣት አሥራ ስድስት ዓመት (16) ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ መሠረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈፀመበት ነው የሚያስኝ የሕግ ምክንያት አልተገኘም ፡፡

 

በመሆኑም ተከታዩ ተወስኗል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ/ቁጥር 186777    

20/01/07 የሰጠው ትዕዛዝ ፣የኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት   በመ/ቁጥር

122177 በ 22/11/06 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ እና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 11654 በ 08/09/06 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195/2-.ለ-.2/ መሠረት ፀንቷል፡፡

2.  መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ይፃፍ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ት/ጌ