Draft Land Expropriation Law

Amharic

English

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ማብራርያ
 

  1. የካሣ አዋጅ 455/1997 ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት

በሀገራችን የካሣ አዋጅ 455/1997 ተደንግጎ በስራ ላይ ከዋለ 13 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ወቅታዊነት የሚጎድለው ሆኖ ተገኝቷል። በአዋጁ መሰረት ለሕዝብ ጥቅም ቦታ በሚለቀቅበት ሂደት የበርካታ ዜጎች ሕይወታቸው የሚነካ ሲሆን በፕሮጀክትና በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሲታይ አነስተኛ ሊመስል ቢችልም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲወሰድ ልማቱ የሚነካው ሕዝብ እጅግ ብዙና በአመዛኙም ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማሕበረሰብን ነው።
በዚህ ዙሪያ በተለያዩ አካላት ሰፋፊ ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን በተለይ የፌዴራል ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከከተማ መስፋፋትና መልሶ መልማት ጋር በተያያዘ የቀረበው ጥናት፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር እና በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በኩል የተከናወኑት ጥናቶች ችግሩን በአግባቡ ለይተዋል። በተለይም መሬት ለሕዝብ ጥቅም ለልማት ሲመረጥ ከመነሻ ፕላን ጀምሮ የቦታው ነባር ተጠቃሚዎች አያያዝ፤ ካሣ እና ድጋፍ ዙሪያ የተስተዋሉት ችግሮች ካልተፈቱ ለልማቱ ቀጣይነት ትልቅ ተግዳሮቶች እንደሚሆኑ ለማየት ተችሏል፡፡
ነባሩ የካሣ አዋጅ 455/1997 በሥራ ላይ በዋለባቸው ዓመታት ለአፈፃፀም ግድፈት ምክንያት የሆኑትን የአዋጁን ድንጋጌዎች በማሻሻል፣ በጥናት የተለዩትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችሉ አዳዲስ ድንጋጌዎችን በማካተት፣ ባለይዞታዎች ለሕዝብ ጥቅም ቦታ እንዲለቁ ሲደረግ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጥ መንገድ ማየት እንዲሁም የመንግሥትን የማቋቋም ግዴታ ማካተት አስፈላጊ ነበር።
በመሆኑም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል። ይህ አዋጅ በከተማም ሆነ በገጠር ባለይዞታዎች ለሕዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቁ ሲደረግ የተነሺዎችን በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡ የመብት ድንጋጌዎችን ያከበረ እና በመሬት ዘርፍ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚደረገዉን ርብርብ የሚደግፍ የመንግሥትን ልማታዊነት ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ ተሻሽሎ ጥቅም ላይ እንዲውል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

  1. በካሣ አዋጁ ማሻሻያ የተደረገባቸው ድንጋጌዎች
    1.  በክፍል አንድ፡- ጠቅላላ

ይህ ክፍል የአዋጁን አጭር ርዕስ፣ ትርጓሜ፣ የተፈጻሚነት ወሰን እና መርሆዎችን ያካተተ ነው።

  • አጭር ርዕስ ላይ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 44 ን/አንቀጽ 2 ላይ መንግሥት በሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግሥት በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት አላቸው" በሚል በመደንገጉ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ለተነሺዎች የሚከፈለው የንብረት ካሣ ብቻ ሳይሆን የመፈናቀያ ካሣ ጭምር በመሆኑ ለንብረት ብቻ ቢባል የካሣን ትርጉም ስለሚያጠበው፣ እንዲሁም ማቋቋምን በማካተት “የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትንና ተነሺዎች የሚቋቋሙበትን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር…” በሚል ርዕሱ እንዲሻሻል ተደርጓል።
  • ትርጓሜ፡-  የትርጉም ድንጋጌ በሕግ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላትን፣ ሐረጎችን ከአሻሚነት ወይም ከአደናጋሪነት የጸዱ እንዲሆኑ፣ በአዋጁ ልዩ ልዩ ክፍሎች ያላቸው አረዳድ ወጥ እንዲሆን እና ለማጣቀስም አመቺ ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡
  • ተፈጻሚነት ወሰን፡- በሕገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥትን ሥልጣንና ተግባር በሚደነግገው አንቀጽ 51 በን/አንቀጽ 5 ላይ "የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመከተ ሕግ ያወጣል" ከሚል በመነጨ በመላ አገሪቱ ለሕዝብ ጥቅም መሬት ሲለቀቅ በከተማም ሆነ በገጠር በወጥነት እንዲመራ በማስፈለጉ ይህን የተፈጻሚነት ወሰን በግልጽ ማሳየት ለሕጉ አፈጻጸም መሠረታዊ በመሆኑ ነው።
  • መርሆዎች፡- በቀድሞው አዋጅ ባለመካተታቸው ምክንያት የአዋጁን አፈጻጸም ለማሻሻል የዳኝነት እና አስፈጻሚ አካላት ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ መርሆዎችን ታሳቢ ማድረግ እንዲችሉ የተካተተ ነው።
    1.  በክፍል ሁለት፡- መሬት ለማስለቀቅ ስለሚፈጸም ሥነ-ሥርዓት

በዚህ ክፍል የንብረት ካሣና የመፈናቀያ ካሣ ክፍያ ከመፈጸሙ በፊት ለሕዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቀቅ ሲደረግ የሚለቀቅበት አግባብን ማስቀመጥ ወሳኝ ነው። ለሕዝብ ጥቅም የሚለቀቅ መሬትን ማን ይወስን፣ ማን ያስለቅቅ፣ ለሕዝብ ጥቅም አይደለም የሚል አቤቱታ ሊቀርብ እንደሚችል፣ የተነሺዎች መረጃን ስለማጣራት፣ ለሕዝብ ጥቅም መሬት መልቀቅ እንዳለ ሆኖ ልማቱ የሚጠይቀውን ያህል ባለይዞታዎች  አቅም ካላቸው በአካታችነት ወደ ልማትን  ማምጣት አስፈላጊነት፣ መሬት የሚለቀቅበት ቅደም ተከተል ሥርዓት፣ ለልማት የሚለቀቅ መሬት ለተነሺው ካሣና ምትክ ባለመሰጠቱ ምክንያት ተነሺው በመሬት መጠቀም ሁኔታን ማስቀጠል የሚቻልበት አግባብ ማስቀመጥ፣ ማስለቀቂያ ትዕዛዙ በጥናት ተደግፎ በቀረበውን ምክረ-ሀሳብ ታሳቢ በማድረግ ለተነሺዎች በቂ የመልቀቂያ ጊዜ ማስቀመጥ፣ ለሕዝብ ጥቅም እንዲለቀቅ የሚፈለግ መሬትን ያለበቂ ምክንያት ለማስረከብ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ የፖሊስ ኃይል ትብብር አስፈላጊነት፣ መሬት የሚጠይቅ አካል ለሥራው የሚፈለገውን መሬት ሥራው ከመጀመሩ ከአንድ ዓመት በፊት ለይቶ የማቅረብና አስፈላጊውን የተነሺዎች ወጪ የሚሸፈንበት አግባብ እና ነባር መሠረተ ልማቶች በቀጣይ ልማት ላይ መጓተትን እንዳይፈጥሩ በኃላፊነት የሚነሱበት አግባብ መደንገግ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም በዚህ ክፍል በዋናነት መታየት የሚገባቸውን ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ተብራርተው ቀርበዋል።         

  • ለሕዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቀቅ የሚያስችሉ ወሳኝ ምክንያቶች፣ ለሕዝብ ጥቅም ቦታ እንዲለቀቅ የሚወስን አካል እንዲሁም መሬት እንዲለቀቅ የሚያደርግ አካል ሥልጣን በግልጽ ተደንግጓል። ምክንያቱም በህዝብ ጥቅም ስም ባለሙያዎች እንደሻቸው መሬት እንዲለቀቅ የሚያደርጉበትን አግባብ ለማስቀረትና በመሰል ሁኔታ ጥሰት ቢከሰት አቤቱታ ሊቀርብ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ በግልጽ የሚወስነውን አካል፣ በምን አግባብ እንደሚወስን እንዲሁም በተወሰነው መሠረት ቦታው እንዲለቀቅ የሚያደርጉ አካላትን ሥልጣን ማስቀመጥ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል።
  • በቀድሞው አዋጅ አካታችነት እንደቅኝት የተያዘ አልነበረም፡፡ ለልማት የተፈለገ ቦታ የነባሩ ተጠቃሚ ወገኖችን ማስነሳት አማራጭ እንደሌለው ስልት የማየት፤ ልማት ለህዝብ በመሆኑ የተወሰነ ወገን ቢጎዳ ችግር አይደለም በማለት የመግፋት ስልት አንዱ ችግር እንደነበር በጥናት ተለይቷል። በመሆኑም የመልሶ ማልማት ዕቅድ ባላቸው ከተሞች አፍርሶ መገንባት ትግበራ በተለያዩ ምክንያቶች ሊዘገይ ስለሚችል የከተማውን አስተዳደር ትግበራ ዕቅድን በመደገፍ በአካታችነት በራሳቸው አቅም በአፍርሶ መገንባት ክልል ውስጥ በሚሰጣቸው ቦታ ላይ ማልማት የሚችሉበት አግባብ፣ በሌላ በኩል የከተማውን የትግበራ ዕቅድ ሳይጠብቁ በፕላኑ የመሬት አጠቃቀምና ሽንሻኖ መሠረት በግልም ሆነ በጋራ በማልማት ልማቱንና ገጽታ ግንባታ ማፋጠን የሚችሉበት ዕድል መስጠት ተገቢ መሆኑን፤ በገጠርም በተመሳሳይ የመሬት አጠቃቀሙን ተከትሎ አርሶ አደሩን በማስለቀቅ ለተመሳሳይ ወይም ሌላ አገልግሎት ለባለሀብት ከመስጠት ይልቅ አርሶ አደሩ የመፈናቀያ ካሣ የማይጠይቅበትንና በመሬት የመጠቀም መብቱን በካፒታል መዋጮነት በመጠቀም ከባለሀብት ወይም በራሳቸው ምርታማነትን የሚጨምሩበት አግባብ በጥናት የተደገፈ ምክረ-ሀሳብ በማመላከቱ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት ተደርጓል።
  • መሬት በማስለቀቅ ሂደት ውስጥ መሬት የሚያስለቅቅ አካል ሥርዓቱን በቅደም ተከተል ማከናወን፣ በአጭሩ ካሣ ከፋዩ አካል ባለመብት የሆነውን ተከፋይ ለይቶ/አውቆ ካሣውን እንዲከፍለው ባለይዞታውን ማጣራት አስፈላጊ መሆኑ፣ መብት አለኝ የሚል አካል ለሕዝብ ጥቅም ይዞታውን የሚለቅብትን አግባብ አውቆ መብቱ ተጠብቆለት በሥርዓቱ መሠረት መስተናገድ እንዲችል፣ ለተነሺዎች በቂ የመልቀቂያ ጊዜን ከመስጠት አንጻር በቀድሞ አዋጅ በማስለቀቂያ ትዕዛዙ መሠረት ከነበረበት በአንድ ወር በማሻሻል ወደ 120 ቀናት እንዲያድግ ተደርጓል። ሆኖም ያለ በቂ ምክንያት ይዞታውን ለማስረከብ ፈቃደኛ ያልሆነን አካል እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ቦታ በመያዝ ንብረት ያሳረፈን አካል የ30 ቀን ገደብ ጠብቆ ቦታውን ለመረከብ የሚችልበት አግባብ የፖሊስ ኃይል ትብብር መጠየቅ የሚችልበት አግባብ ተደንግጓል።
  • ካሣና ምትክ ሳይሰጥ ተነሺዎች ይዞታቸውን እንዳይጠቀሙ ለረዥም ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ መደረጉ፣ ካሣ ሲከፈልም ከረጅም ጊዜ በፊት በተገመተ ዋጋ መሆኑ ቅሬታ የፈጠረ ስለመሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። በመሆኑም ለተነሺው የካሣ ግምት በጽሁፍ እንዲያውቅ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ተገቢው ካሣ ካልተከፈለው በመሬቱ ላይ ከቋሚ ተክልና ግንባታ በስተቀር ሌሎችን ሥራዎች እንዲሁም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ማንኛውንም ሥራ መስራት ይችላል፡፡
  • በማስለቀቂያ ትዕዛዙ መሠረት ካሣና ምትክ ተወስኖላቸው ተነሺዎች በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ቀርበው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይወስዱ ቢቀር የተዘጋጀው የካሣ ገንዘብ በባንክ ዝግ ሂሳብ እንዲገባ የሚደረግበት እንዲሁም በይዞታው ንብረት ካለ ካሣና ምትክ ከተቀበለ ወይም ካሣው በዝግ ሂሳብ ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ከ120 ቀን እና በቦታው ንብረት ከሌለ በ30 ቀናት ውስጥ ቦታውን የሚያስረክብበት አግባብ ተደንግጓል። 
  • በአዋጅ ቁጥር 455/1997 የሕዝብ ውይይትን አስመልክቶ ድንጋጌ አልተካተተም። ይሁን እንጂ በተግባር የሕዝብ ውይይት በብዛት የሚጠራው በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። በመሆኑም በዚህ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 5(1) እና አንቀጽ 9(1/ሀ) መሠረት በዕቅድ በመመራት ተነሺዎችን ማወያየት እንደሚገባ በግልጽ ተደንግጓል። በተጨማሪም የወረዳ ወይም የከተማ አስተዳደር መሬት የማስለቀቅ ሥልጣን ቢኖረውም የንብረትና መፈናቀያ ካሣ ለመሸፈን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ያለባቸው ከመሆኑ አንጻር መሬት እንዲለቀቅለት የሚፈልግ አካል ተገቢውን ካሣና እና መቋቋሚያ ድጋፍ ወጪ ገቢ ማድረግ እንደ ሚጠበቅበት እና ተነሺዎችም ክፍያው ካልተፈጸመ የከተማ ወይም የወረዳ አስተዳደር የማያስለቅቅ መሆኑ ተደንግጓል።
    1.  በክፍል ሦስት፡- የካሣ አወሳሰን፣ ምትክ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም

በዚህ ክፍል ለሕዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቀቅ ከማድረግ ጋር በተያያዘ የተነሺውን           ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚጠበቁበት ድንጋጌዎችን ለማካተት ተሞክሯል። በመሆኑም ለተነሺዎች ስለሚከፈል ካሣ፤ በከተማም ሆነ በገጠር የመሬት ይዞታ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት እንዲለቀቅ ሲደረግ ለተነሺው ስለሚከፈል የንብረት ካሣ እና ስለሚሰጥ ምትክ ቤት ወይም ቦታ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን በዝርዝር ለማየት ተችሏል። በተጨማሪም ተነሺዎች በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ የሚደረጉበት አግባብም እስከፈንድ ማቋቋም እንዲሁም በልማቱ ምክንያት የተፈናቀሉና የገቢ ምንጫቸውን ላጡ ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበት አግባብ ተደንግጓል። በዚህ ክፍል ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ ንብረትን መገመት የሚገባው አካልን አሁን ከአለው ነባራዊ ሁኔታ እና ወደፊት መሆን ከሚገባው አንጻር በአማራጭነት ማስቀመጥ፣ ከንብረት ግምት ጋር በተያያዘ ቅሬታና አቤቱታ የሚስተናገድባቸው አግባቦች እንዲሁም እነዚህ አግባቦች ተጠብቀው የቦታ ርክክብ የሚፈጠምበትን ሁኔታ በግልጽ ተቀምጠዋል።  
በመሆኑም በዚህ ክፍል በዋናነት መታየት የሚገባቸውን ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ተብራርተው ቀርበዋል።         

  • ለተነሺዎች የሚከፈል ካሣ በዓይነት ለንብረትና በመሬት የመጠቀም መብት በመቋረጡ የሚፈጠር የመፈናቀያ ካሣ መሆናቸውን፣ ሁለቱ የተለያየ ባህሪ ስላላቸው በየዓይነታቸው መግለጽ አስፈላጊ በመሆኑ በአዲስ መልክ እንዲደነገግ ተደርጓል፡፡ የንብረት ካሣ በይዞታ ላይ ለሚገኝ የሚዳሰስ ንብረትን ብቻ እንጂ የማይዳሰሱ የንብረት ዓይነቶችን እንደ የመልካም ስምና የቦታ እሴት ጭማሪ ድርሻ እንዳያካትት ተደርጓል። ይህ የሆነበት ምክንያት የማይዳሰስ ንብረት ጥቅም ንብረቱ ካለበት መገኛ ቦታና ከሚኖረው መልካም ስም የተነሳ ሊኖረው የሚችለውን የገበያ ዋጋ መሠረት የሚያደርግ በመሆኑ በዚህ መሠረት ካሣው ቢሰላ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40(3) መሠረት መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ንብረት/ሀብት መሆን ጋር የሚጋጭና ብዙኃኑን ተጠቃሚ ስለማያደርግ፤ ከተቻይነቱም አንጻር አጠራጣሪ በመሆኑ በሚዳሰስ ንብረት ካሣ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ድንጋጌ እንዲደነገግ ሆኗል።
  • ሌላው ከንብረት ካሣ ጋር በተያያዘ በአዋጅ 455/97 “በአለበት ሁኔታ ለመተካት” የሚለው ከደንብ ቁጥር 135/1999 የካሣ ስሌት ቀመር ጋር ሲታይ ክፍተት ስላለበት “ንብረቱን በአዲስ ለመተካት” ተብሎ እንዲሻሻል ተደርጓል። ንብረቱን “በነበረበት ለመተካት” በሚለው ሐረግ መሠረት ንብረቱ ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውሮ እንደገና ሊተከልና እንደነበረ አገልግሎት ለመስጠት የማይችል ለምሳሌ ቤት ቢሆን የሚከፈለው የንብረት ካሣ ቤቱ ባለበት እንደሚተካ ታስቦ ዋጋው ስለሚሰላ የእርጅና ዋጋ መቀነስ ወይም በአሮጌ ዋጋ ማስላት የግድ ይላል፡፡ ለተነሺው በዚህ መሠረት ተሰልቶ በሚሰጠው የካሣ ክፍያ ተመሳሳዩን ቤት ምትክ በተሰጠው ቦታው ላይ ሊሰራ አይችልም፡፡ ይህ ማለት የፈረሰበትን ቤት አልተካንለትም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ችግር ለማስወገድ የሚከፈለው ካሣ “ንብረቱን በአዲስ ለመተካት” በሚል ሲሻሻል ቤቱ የተሰራበትን ግብዓት በጠበቀ መልኩ በአዲስ ቁስ ለመተካት እንደሆነ መረዳት የሚያስችል በመሆኑ ተሻሽሎ ተደንግጓል፡፡
  • የመፈናቀያ ካሣን አስመልክቶ ለሕዝብ ጥቅም መሬት በቋሚነት እንዲለቀቅ ሲደረግ ለከተማም ሆነ የገጠር ተነሺ ስለሚከፈል ካሣ እና ስለሚሰጥ ምትክ ቤት ወይም ቦታ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን በዝርዝር ለማየት ተችሏል። እነዚህ ድንጋጌዎች ባለይዞታው የመሬት ይዞታውን ሲለቅ በመሬቱ ላይ የመጠቀም መብቱ በመቋረጡ ምክንያት የሚደርስን ጉዳት ለማካካስ የሚከፈል ክፍያና በዓይነት የሚሰጥ ምትክ ናቸው። በመሆኑም፡-
  • የገጠር ባለይዞታዎች፡- ምትክ ተመጣጣኝ መሬት ሲሰጠው መሬቱን አልምቶ ምርት እስኪሰጠው ድረስ ላለው ጊዜ የሚቋቋምበት ድጋፍ “መሬቱን ከመልቀቁ በፊት ሶስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ከመሬቱ ሲያገኝ ከነበረው ከፍተኛውን የአንድ ዓመት ገቢ ብቻ” ድጋፍ ይሰጠዋል። ነገር ግን ምትክ መሬት ማግኘት ካልተቻለ በቋሚነት መሬቱን እንዲለቅ ይደረጋል። በሕገ-መንግሥቱ መሬት የማይሸጥ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት በመሆኑ የገጠር ባለይዞታዎች የነበራቸውን በጊዜ ያልተገደበ የመጠቀም መብት መቋረጥ ምክንያት የመፈናቀያ ካሣ ክፍያ በማካካሻ መልክ እንዲከፈል የሚደረግበት አግባብ ተፈጥሯል። በመሆኑም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር በቀድሞው በአዋጅ 455/97 አንቀጽ 8 ን/አንቀጽ 1 “አማካይ ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ” የሚለውን “ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ በ15 ተባዝቶ” በሚል እንዲሻሻል ተደርጓል።  
  • ከመኖሪያ ይዞታው የሚነሳና ምትክ ቦታ የሚሰጠው ከሆነ ክልሉ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን የመፈናቀያ ድጋፍ መከፈል አለበት፡፡ በሚሰጠው ምትክ ቦታ ላይ ቤት ገንብቶ ኑሮውን መምራት እስኪጀምር የሚደርስበትን ችግር ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ ክልሎች እንደተጨባጭ ሁኔታቸው በሚያወጡት መመሪያ የሚወሰን የመፈናቀያ ድጋፍ እንዲከፈል፣ በተጨማሪም ከነበሩበት አካባቢ ወደ ሌላ ሲዛወሩ እንደ ዕድር፣ ማህበርና የመሳሰሉ ማህበራዊ ትስስሮች ስለሚቋረጡ እና የሥነ-ልቦና ጉዳት የሚደርስባቸው በመሆኑ ይህንንም ጉዳት ለመካሳ አንዱ አማራጭ በገንዘብ መደገፍ ስለሆነ ተደንግጓል።
  • ይዞታ በጊዜያዊነት እንዲለቀቅ ሲደረግ ባለይዞታው መሬቱ እስኪመለስለት ድረስ ተፈናቃይ ሆኖ ስለሚቆይ በነባሩ በአዋጅ 455/97 አንቀጽ 8 ን/አንቀጽ 1 የተደነገገውን መሬቱን ከመልቀቁ በፊት በነበሩት “የአምስት ዓመት አማካኝ” በማሻሻል “ሶስት ዓመታት ውስጥ ያገኘው ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ” በሚል ተተክቷል። ይሁን እንጂ የገጠር መሬት ባለይዞታው በጊዜያዊነት የተወሰደበት መሬት ቢመለስለትም በፊት ይሰጥ በነበረው ልክ ምርት ላይሰጥ ስለሚችል የመፈናቀያ ካሣው መሬቱ የነበረውን ምርታማነት ለመመለስ የሚወስደውን ተጨማሪ ጊዜ ታሳቢ እንዲያደርግ፣ ሆኖም መሬቱ በፊት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት መስጠት የማይችል ከሆነ በቋሚነት እንደለቀቀ ተቆጥሮ የመፈናቀያ ካሣ ወይም ምትክ ቦታ መስጠት ተገቢ በመሆኑ በአዲስ መልክ ተደንግጓል፡፡
  • የወል ይዞታ መፈናቀያ ካሣን አስመልክቶ፡- በአዋጅ ቁጥር 455/1997 አንቀጽ 8(2) በተለየ ሁኔታ በቋሚነት ሲለቀቅ ምን ሊሆን እንደሚገባ የተደነገገ ነገር አልነበረም። በዚህ ረቂቅ አዋጅ አርብቶ አደሮችና ሌሎች በወል መሬት የሚጠቀሙ የህብረተስብ ክፍሎች በቋሚነት የወል መሬታቸው ሲወሰድ የመጠቀም መብታቸው በመቋረጡ ጉዳት እንደሚደርስባቸው ታሳቢ በማድረግ ድንጋጌ አስቀምጧል። ይሁን እንጂ በየክልሉ ያለው የወል ይዞታ አጠቃቀምና የሚሰጠው አገልግሎት የተለያየ በመሆኑ ወጥ አዋጅ መደንገግ ስለሚያስቸግር የካሣው ስሌት ክልሎች በሚያወጡት መመርያ እንዲወሰን ሥልጣን ሰጥቷል። ምክንያቱም አርብቶ አደሮች የወል መሬት ለግጦሽ የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንደሌላው አካባቢ ዓመቱን በሙሉ ሳይሆን ለተወሰኑ ወራት አንዱን አካባቢ ለግጦሽ ተጠቅመው ወደ ሌላ የወል መሬታቸው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ አንድን አካባቢ የወል መሬት በሚሰጠው ዓመታዊ የግጦሽ ሣር መጠን ተመስርቶ ካሣውን ማስላት ተጎጂ ስለሚያደርጋቸው እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አጠቃቀሙንና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ታሳቢ አድርጎ ማስላት ስለሚጠይቅ ነው።
  • በቋሚነት ለሚነሱ የከተማ ባለይዞታዎች፡- በቋሚነት በሚነሱበት ጊዜ በአዋጅ 455/97 አንቀጽ 8 ን/አንቀጽ 4(ሀ) መሠረት “ከሚከፈለው ካሣ በተጨማሪ የመኖርያ ቤት መስሪያ ምትክ ቦታ” እንደሚሰጥ ሲደነገግ መኖርያ ቤት የሚገነቡ ከተሞች ለተነሺዎች ያላቸውን ቤት የማቅረብ አማራጭ በመጠቀም ተነሺዎችን ማስተናገድ የሚችሉበትን መንገድ ማስቀመጥና የከተማ ውስን መሬትን አጠቃቀም ለማጎልበት ስለሚረዳ “ምትክ ቦታ ወይም መኖሪያ ቤት በግዥ” እንዲያገኝ በሚል በማሻሻል ተደንግጓል። ተነሺው ምትክ ቤት የሚሰጠው ከሆነ በተሰጠው ቤት ገብቶ ኑሮውን እስኪያደላድል ተጨማሪ ወጪዎችን ለምሳሌ የቤት ማጠናቀቂያ ሥራዎች፣ የመብራት፣ ውሃና አገልግሎት ክፍያዎች የመሳሰሉት ወጪዎችን መሸፈን እንዲችል የመፈናቀያ ድጋፍ ተደንግጓል። ሌላው ተነሺዎች ከነበሩበት አካባቢ ወደ ሌላ ሲዛወሩ በነበሩበት አካባቢ መስርተው የነበሩት እንደ ዕድር፣ ማህበር የመሳሰሉ ማህበራዊ ትስስሮች መቋረጥና ለሚደርስ የሥነ-ልቦና ጫና ጉዳት ካሣ በድንጋጌ እንዲካተት ተደርጓል።
  • በጊዜያዊነት ለሚነሱ የከተማ ባለይዞታዎች፡- ይህ አንቀጽ በአዋጅ 455/1997 ያልነበረ ቢሆንም በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት ምክረ-ሀሳብ መሠረት የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ምክንያት ከመኖሪያ ወይም ከሥራ ቦታቸዉ በጊዜያዊነት የመልቀቅ /የገቢ መቋረጥ ሁኔታዎች ይከሰታሉ። በመሆኑም ለተፈጠረ ጉዳት ማካካሻ ማግኘት እንዳለባቸዉ ስለታመነበት አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ዝርዝር ጉዳዮችን ክልሎች እንደተጨባጭ ሁኔታቸው መመሪያ በማዉጣት እንዲያስፈጽሙት በአዲስ መልክ ተደንግጓል፡፡
  • ገቢያቸው ለተቋረጠ ስለሚከፈል ካሣ፡- ይህ አንቀጽ በአዋጅ ቁጥር 455/97 ያልነበረና አዲስ የተካተተ ሲሆን ባለ ይዞታዎች በተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ምክንያት ከመኖሪያ ወይም ከሥራ ቦታቸዉ ባይነሱም ኢኮኖሚያዊ ገቢ ሊቋረጥ ስለሚችል በዚህ አግባብ ለታጣ ገቢ ጉዳት ማካካሻ ማግኘት እንዳለባቸዉ ስለታመነበትና በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናትም ስለተረጋገጠ በአዲስ መልክ ተደንግጓል፡፡  
  • ከገጠር ወደ ከተማ ለተካለሉ አካባቢዎች፡- ከተሞች እየሰፉ ሲሄዱ በገጠር ወረዳ አስተዳደር ስር የነበሩ ቦታዎች በከተማ አስተዳደር በመካተቱ ነዋሪዎቹ በከተሜነት ሕይወታቸውን መቀጠል እንዲችሉ ከማድረግ አኳያ ለሕዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቁ ሲደረግ በከተማው የመሬት ሽንሻኖ ደረጃ መሠረት ከ500 ሜ/ካሬ ያልበለጠ የመኖርያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ተደንግጓል። ድንጋጌው አዲስ ከተረቀቀው የሊዝ አዋጅ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ የተቀመጠ ነው። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመትና በላይ ለሆናቸውና የባለይዞታውን ገቢ በመጋራት አብረው የሚኖሩ አርሶ/አርብቶ አደር ልጆችም የመኖርያ ቦታ የሚያገኙበት አግባብ የተፈጠረ ሲሆን ይህም በባለይዞታው በመኖሪያነት ከያዘው መሬት ስፋት በላይ ባልበለጠ እንዲሆን ተወስኗል። ይህም ውስን የሆነውን የመንግሥትና የሕዝብ የመሬት ሀብት ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ ማደልን ለመገደብ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ ያስፈልጋል።
  • መልሶ ማቋቋም፡- ተነሺዎች በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ የሚደረጉበት አግባብም ከፈንድ የማቋቋም ጀምሮ በልማቱ ምክንያት የተፈናቀሉና የገቢ ምንጫቸውን ላጡ ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበት አግባብ ተደንግጓል። በመሆኑም በዚህ አንቀጽ በዋናነት መታየት የሚገባቸውን ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ተብራርተው ቀርበዋል።         
  • በአዋጅ ቁጥር 455/97 አንቀጽ 13(1) የወረዳ ወይም የከተማ አስተዳደሮች አቅም በፈቀደ መጠን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲሚያደርጉ ቢደነገግም “አቅም በፈቀደ” ስለሚል በአግባቡ ሳይሰራ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ተነሺዎች የተከፈላቸውን የካሣ ገንዘብ በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ለችግር መጋለጣቸውን በጥናት ተረጋግጧል። ስለዚህ የከተማም ሆነ የገጠር ተነሺዎች መልሰው ስለሚቋቋሙበት መደንገግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት በዚህ አዋጅ የክልል መንግሥታት እንዲሁም በቻርተር የተቋቋሙ ከተሞች ለተነሺዎች ካሣ ከመክፈል በተጨማሪ የማቋቋም ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
  • ተነሺዎችን ማቋቋም ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም ክልሎች ለመልሶ ማቋቋም የሚሆን ፈንድ ማቋቋም እንዳለባቸውም ተደንግጓል። ይህ ድንጋጌ ሲቀመጥ ታሳቢ የሆነው በአንድ ማዕከል የሚተዳደር የካሣና መልሶ መቋቋሚያ ፈንድ በማቋቋም እንጂ የየመስሪያ ቤቱና የክልሎች ድርሻ ብቻ አድርጎ መተው ስለማይቻል ነው። ይህ ፈንድ በአዋጅ ወይም ደንብ የሚቋቋም ሆኖ የገንዘብ ምንጩ ክልሎች ከበጀት በድርሻቸው የሚያዋጡት ወይም ከአለምአቀፍ ድርጅቶች ከሚገኝ ብድር ወይም የገንዘብ ድጋፍ ሊሆን ይችላል፡፡ የገንዘብ ምንጩ (ፈንዱ) በቦርድ ሊመራ የሚችልና በማንኛውም ክልል ሰፊ መሬት ሲወሰድና ብዛት ያላቸው ተነሺዎችን ለማቋቋም ድጋፍ ሲያስፈልግ ወጪ በማድረግ እየተፈጠረ የነበረውን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግርን የሚፈታበት አግባብ በመሆኑ በአዲስ መልክ ተደንግጓል።
  • ንብረት ስለመገመት፡- ንብረት ስለመገመት በአዋጅ ቁጥር 455/97 አንቀጽ 9 ን/አንቀጽ 1 እና 2 የተገለጸ ቢሆንም በዚህ ረቂቅ አዋጅም እንዲካተት ተደርጓል። በመሆኑም ንብረት እና መፈናቀያ ካሣ በሀገር አቀፍ ቀመር መሠረት እንዲገመት በመደንገግ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚነሱ ተነሺዎች በአንድ የካሣ ቀመር መሠረት እንዲካሱ በማድረግ ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ነው፡፡

ከግመታ ጋር በተያያዘ በተመሰከረለት የግል ድርጅት እንዲገመት ይደረጋል ተብሎ ሲደነገግ ሁሉንም ሥራዎች ማለትም የልማት ተነሺዎችን የሚያስነሳው፣ ካሣ የሚገምተው እና ካሣ የሚከፍለው መንግስት ብቻ ከሚሆን ይልቅ ገማቹ የግል ድርጅት ቢሆን ከተወዳዳሪነትና ገለልተኛነትን ከማረጋገጥ አንጻር አስፈላጊነቱ ታይቶ ነው። ይሁን እንጂ የግል ድርጅት ከሌለ አማራጭ በማስቀመጥ ራሱን በቻለ በመንግሥት በተቋቋመ ተቋም እንዲገመት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ከሌለ ወይም የተጠቀሱት አማራጮች እስኪደራጁ ክልሉ ወይም በወረዳው ወይም በከተማ አስተዳደር በሚቋቋምና ተገቢው ሙያ ስብጥር ባለው ገማች ኮሚቴ እንዲሰራ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ የሚነሳው ንብረት የመንግሥት መሠረተ ልማት ወይም የአገልግሎት መስመር ከሆነ ግምቱ የሚዘጋጀው በንብረቱ ባለቤት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከግምት ጋር በተያያዘ የካሣ ግምት የሚሰላበት ነጠላ ዋጋ ቢበዛ በሁለት የዓመቱ መከለስ እንደሚገባው ተደንግጓል።  

  • አቤቱታ ሰሚ አካል እና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ስለማቋቋም፡- የማስለቀቂያ ትዕዛዝ የደረሰው ወይም ትዕዛዝ በተሰጠበት ንብረት ላይ መብቴ ወይም ጥቅሜ ተነክቷል የሚል ማንኛውም ሰው በቀጥታ ወደ ፍ/ቤት ከማምራቱ በፊት አቤቱታውን ለአስተዳደሩ ማቅረብ የሚችልበትን አግባብ ክልሎች የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች አቤቱታ ሰሚ እና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ እንዲያቋቁሙ፣ የጉባኤውን ተደራሽነት ለማረጋገጥም ሲባል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲቋቋም ማድረግ እንደሚቻል መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከእነዚህ ተቋማት ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው ተደንግጓል።
  • አቤቱታን አስመልክቶ በአንድ በኩል በአዋጅ የክርክር መንስኤዎችን ዘርዝሮ መጨረስ የማይቻል በመሆኑ፣ በሌላ በኩል መሬት ለሕዝብ ጥቅም ከመወሰዱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታና አቤቱታዎች በተቻለ መጠን በአስተዳደራዊ አካል ለተቋቋመ አቤቱታ ሰሚ አካል ቀርበው እንዲታዩ ማድረግ፣ እነዚህ አካላት በሌሉበት ደግሞ በመደበኛ ፍ/ቤት እንዲታዩ በማድረግ የተነሺዎችን መብት ያለገደብ እንዲከበር ድንጋጌዎቹ ተቀምጠዋል። የቀናት ገደብም የተበጀው አቤቱታ ሰሚ አካሉ የአስተዳደራዊ አካል በመሆኑ ፈጥኖ ውሳኔ እንዲሰጥ በማድረግ የልማቱ ስራ እንዳይጓተት በሚል ታሳቢ ተደንግጓል።

 

  • ቦታ ስለመረከብ በዋናነት እንዲካተት የተደረገው ለህዝብ ጥቅም ሲባል የከተማ ቦታን ከማንኛውም ይገባኛል ነጻ በማድረግ የከተማ ወይም የወረዳ አስተዳደር መቼና እንዴት መረከብ እንዳለበት መደንገግ በማስፈለጉ ነው፡፡ አግባብ ያለው አካል የሕግ ሂደቱን ተከትሎ እንዲለቀቅ የተፈለገው መሬት ለታለመው ልማት ሳይውል እንዳይቀር ለማድረግ ነው፡፡
    1.  በክፍል አራት፡- ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
  • ሥልጣንና ተግባር፡- ክልሎች በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 52 ን/አንቀጽ 2(መ) የፌዴራል መንግስት በሚያወጣው ሕግ መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል በሚል ተደንግጓል፡፡ የካሣ አዋጅ 455/1997 የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አዋጁን በማስፈጸም ሥልጣን የነበረው ቢሆንም አንዳንድ የአዋጁ ድንጋጌዎች ወቅታዊነት የሚጎድላቸው ስለመሆናቸው በጥናት መለየቱን ተከትሎ በቀጣይ ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በከተሞች የከተማ ልማትና ኮንስትሪክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም በገጠር የግብርና ሚኒስቴር እንደሆኑ ተለይተዋል። ክልሎች የወረዳ ወይም ከተማ አስተዳደሮች አዋጁን በማስፈጸም ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንዲችሉ ሥልጣን ተግባር የተሰጠበት አግባብ ተካቷል።
  • የመተባበር ግዴታ፡- ማንኛውም ሰው ይህንን አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመተባበር ግዴታ እና የአዋጁን ድንጋጌዎችን የጣሰ ወይም አፈፃፀማቸውን ያሰናከለ ማንኛውም ሰው አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን የተደነገገበት ነው።
  • የመሸጋገሪያ ድንጋጌ፡- ይህ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ክስ ቀርቦባቸው ውሳኔ ያላገኙ ጉዳዮች በቀድሞው አዋጅ 455/1997 መሠረት እንደሚስተናገዱ የተደነገገበት አግባብ ነው።

3.ማጠቃለያበሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ የመሬት አጠቃቀም ሕግ የማውጣት ሥልጣን ተከትሎ የካሣ አዋጅ 455/1997 ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ለንብረት ካሣ የሚከፈልበትን ሁኔታ ወጥቶ የነበረው አዋጅ በከተሞች ልማትና ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ በማበርከት ረገድ የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ በስራ ላይ በዋለባቸዉ ዓመታት በአዋጁ አፈጻጸም የታዩትን ክፍተቶች ለማረም፣ ከአዋጁ ድንጋጌዎች ዉስጥ ለከተሞች ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የሆኑትን ድንጋጌዎች በመለየትና በማስተካከል እንዲሁም በጥናት ምክረ-ሀሳቦች መሠረት ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መቃኘት ያለባቸውን ጉዳዮች በማካተት የካሣ አዋጁን ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በመሆኑም አዋጁን በማሻሻል እና በተሟላ ሁኔታ በመተግበር ለተነሺዎች ተጠቃሚነት የሚያመጡ እና በዘለቄታነት እንዲቋቅሙ የሚያስችላቸውን አስገዳጅ ድንጋጌዎች በማካተት፣ በመንግሥትም ደረጃ ለካሣ ክፍያም ሆነ ተነሺዎችን በዘለቄታነት ለማቋቋም የሚያስችል ፈንድ ማቋቋም እንዳለበት በመደንገግ ለሕዝብ ጥቅም የተለቀቀውንና ዉስን የሆነዉን መሬት ለላቀ ልማት እና ለሀገራችን ሕዳሴ የድርሻዉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡