95069 contract law/ non-performance/ reinstatement/ currency exchange

ከውጪ አገር በዶላር የተላከ የውጭ ምንዛሬ ለተላከለት አላማ አልዋለም በሚል ገንዘቡ እንዲመለስ ክርክር ሲነሳ ገንዘቡ ሊመለስ የሚገባውዶላር በተላከበት ጊዜ በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ በተሠጠው ተመን መሠረት ስለመሆኑ፣

 

የፍ/ሕ/ቁ 1705፣1749፣1750፣1771

የሰ/መ/ቁ. 95069

 

ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- 1. ሴፍሜት አግሪ ቢዝነስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር

2. አቶ ወንድምአንተነህ መሸሻ                  ጠበቃ ውቤ አለነ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ብረቱ ሱኬሱ ጠበቃ ወንድአወክ አየለ ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ የገንዘብ ይመለስልኝ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የጀመረው የአሁኗ  ተጠሪ የአሁኑ አመልካቾችን እንደቅደምተከተላቸው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች፣ ወ/ሮ ትግስት ድረስ የተባሉትን ግለሰብ ደግሞ 3ኛ ተከሳሽ በማድረግ መጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ/ም በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የተጠሪ የክስ ይዘትም፡- 2ኛው ተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽን በአሽሙር ማህበር በመመስረት የጥቁር ድንጋይ ማምረቻ እናቋቁም በማለት ተጠሪዋን ባግባቧቸው መሰረት በሚኖሩበት ከኬኒያ ናይሮቢ ከተማ ሆነው በተለያዩ ጊዜያት ማለትም ነሐሴ 06 ቀን 2001 ዓ.ም 10,000 የአሜሪካ ዶላር፣ ነሐሴ 07 ቀን 2001 ዓ/ም 70,000 የአሜሪካ ዶላር፣ ነሐሴ 11 ቀን 2001 ዓ.ም ደግሞ 67,000 የአሜሪካ ዶላር በ1ኛ አመልካች ስም ናይሮቢ ከተማ በሚገኘው ዲያመንድ ትረስት ባንክ አማካኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው በአቢሲኒያ ባንክ ቦሌ ቅርንጫፍ በኩል እንደላኩና ለእነዚህ በተለያዩ ጊዜያት ለተላኩት ገንዘቦች ደግሞ በተከታታይ 204 ዶላር፣ 1429 ዶላር፣ 1367 ዶላር ኮሚሽን እንደከፈሉባቸውና በአጠቃለይም 150,000 የአሜሪካን ዶላር ልከው 2ኛው አመልካችም ይህን ገንዘብ መቀበላቸውን በደረሰኝ ያረጋገጡላቸው መሆኑን እንዲሁም እርሳቸው ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት የአሽሙር ማህበሩን ለማቋቋም ተጨማሪ ገንዘብ መስጠት አለብሽ በማለት 2ኛው አመልካች በጠየቋቸው መሰረት ጳጉሜ 4 ቀን 2001 ዓ.ም በተፃፈ ደረሰኝ አማካኝነት ብር 800,000 (ስምንት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር) የሰጧቸው መሆኑን፣ ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን 2ኛ አመልካችን ለማግኘት እንደተቸገሩና ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አግኝተዋቸው ሲጠይቋቸው ገንዘቡን ለሌላ ፕሮጀክት እንዳዋሉት እንደገለፁላቸው፣ እርሳቸውን በደንብ የሚያውቋቸውን የ2ኛ አመልካች ባለቤት የሆኑትን የሥር 3ኛ ተከሳሽ የነበሩትን ግለሰብ ሲጠይቋቸውም “ገንዘብሽን አንክድሽም፤ ጊዜ ስጭንና ከባንክ ተበድረን እንሰጥሻለን” እንዳሏቸውና እርሳቸውም ባዶ እጃቸውን ወደ ኬኒያ እንደተመለሱ እና አመልካቾችም ሆነ የሥር 3ኛ ተከሳሽ ገንዘባቸውን ሊመልሱላቸው እንዳልቻሉ በመዘርዘር አመልካቾች የወሰዱትን 150,000 የአሜሪካ ዶላር ክስ በቀረበበት ከመጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ/ም በነበረው የአንድ ዶላር ምንዛሬ ብር


16.7293 ሂሳብ ብር 2,509,395 (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠኝ ሺህ ሶስት መቶ ዘጠና አምስት ብር) እንዲሁም የዚህን ገንዘብ የመጨረሻ ክፍያ (67,000 ዶላር) ከተከፈለበት ከነሐሴ 13 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ክስ እስከቀረበበት እስከ መጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ 9% ወለድ ብር 368,159.20 ተጨምሮበት እንዲከፈላቸው፣ እንዲሁም ብር 800,000.00 (ስምንት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር) እና ይህ ገንዘብ ከተወሰደበት ከጳጉሜ 4 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት እስከ መጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ 9% ወለድ ብር 112,636.60 (አንድ መቶ አስራ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከስልሳ ሳንቲም) እንዲከፈሏቸው ጠቅሰው በአጠቃላይም ከላይ የተዘረዘረውን ገንዘብ ክስ እስከቀረበበት ጊዜ ያለው ብር 3,790,189.82 (ሶስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ዘጠና ሺ አንድ መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ብር ከሰማኒያ ሁለት ሳንቲም) ክሱ ከቀረበበት ከመጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ ከሚታሰብ ወለድ ጋር በውጭ ምንዛሬ የወሰዱትም በሚከፍሉበት ወቅት በሚኖረው ምንዛሬ ታስቦ እንዲከፍሏቸው፣ የጠበቃ አበል በውላቸው መሰረት፣ ሌሎች ወጪና ኪሳራዎች ደግሞ በሚያቀርቡት ዝርዝር መሰረት እንዲወሰንላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

 

የአሁኑ አመልካቾች ለክሱ በሰጡት መልስም፡- ከሳሿ የክስ ምክንያት የሌላቸው መሆኑን፣ ከሳሿ ገንዘቡን ያዋጡት ለአሽሙር ማህበር መዋጮ በመሆኑ 1ኛ አመልካችን የሚመለከት ክስ ከሚሆን በስተቀር 2ኛ አመልካችን እና የሥር 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት የመክሰስ ጥቅም እንዳላቸው ያለማረጋገጣቸውን፣ ገንዘቡ ገቢ የተደረገውና በ2ኛ አመልካች ወጪ የሆነው በኢትዮጵያ ብር በመሆኑ እርሳቸው ባሉበት የዶላር ምንዛሬ ሊጠይቁ እንደማይገባ፣ ገንዘቡን የላኩት በመዋጮ መልክ በመሆኑ ወለድ ሊታሰብላቸው እንደማይገባ፣ ከሳሽ በአጠቃላይ ያዋጡት ገንዘብ ብር 2,634,089.73 ሁኖ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም ብር 139,200.75 ከሳሿ መልሰው የወሰዱ በመሆናቸው ይህ ተቀንሶ የሚቀራቸው ብር 2,494,888.98 መሆኑንና ይህን ገንዘብ ብቻ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆን በመሰረቱት ክስ ወጪና ኪሳራ ሊከፍሉ እንደማይገባ  ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የሥር 3ኛ ተከሳሻም የአሁኑ 2ኛ አመልካች ባለቤት ከመሆናቸው ውጪ ለክሱ ኃላፊ የሚሆኑበት ሕጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን ጠቅሰው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም አመልካቾች ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ አድርጎ ፍሬ ነገሩን በተመለከተም ጉዳዩን መርምሮ ከሳሿ (ተጠሪ) በዶላር የላኩት ገንዘብ 2ኛ ተከሳሽ (የአሁኑ 2ኛ አመልካች) የተቀበሉት በብር ስለሆነ አሁን ባለው የብር ምንዛሬ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ክስ ውድቅ ነው፣ ከሳሿ ገንዘቡን የላኩት በራሳቸው ፈቃድ የአሽሙር ማህበር ለመመስረት አስበው ስለሆነ የወለድ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም፣ ተከሳሾቹ ባቀረቡት ክርክር ከሳሿ  ብር 139,200.75 መልሰው ወስደዋል የሚለውም ተቀባይነት የለውም፣ 3ኛዋ ተከሳሽ ለከሳሿ ገንዘብሽን እንመልስልሻለን ከማለት ውጭ በክሱ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ነገር ስላልተገኘ ከክሱ በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል፣ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ግን ከከሳሽ የተቀበሉትንና የወሰዱትን ብር 2,634,089.43 ዳኝነት ከፍለው መዝገቡን ካስከፈቱበት ከሚያዝያ 10/2003 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር በአንድነትና በነጠላ ለከሳሽ እንዲከፍሏቸው በማለት ወስኗል፣ እንዲሁም ከሳሿ በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ላይ 3ኛዋ ተከሳሽ ደግሞ በከሳሿ ላይ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብትም ጠብቋል፡፡


በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ በከፊል በመቃወም ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን ይግባኛቸው መሰረታዊ ነጥብም፡- በኬኒያ አገር ናይሮቢ ከተማ ሆነው በዶላር የላኩላቸው ገንዘብ ለእኔ ጥቅም ባላገለገለበት  ማለትም  ለአሽሙር ማህበሩ በመዋጮ መልክ ባልዋለበትና እቃም ባልተገዛበት በወቅቱ በነበረው የብር ምንዛሬ ብቻ እንዲከፈላቸው ተብሎ መወሰኑ የደረሰባቸውን ጉዳት ያላገናዘበ ነው፤ የሥር ተከሳሾችም ገንዘቡን ከወሰዱበት ጊዜ ጀምሮ ወለድ ሊታሰብልኝ እየተገባ ክሱ ከቀረበበት ከሚያዝያ 10 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ እንዲታሰብ መደረጉ ስህተት ነው፣ የስር 3ኛዋ ተከሳሽም ከሌሎች ተከሳሾች ጋር እኩል ኃላፊነት እንዳላቸው ሊወሰን ሲገባ መታለፉ ያላግባብ ነው የሚሉትን ነጥቦችን ዘርዝረው ይግባኙን ለማቅረብ የከፈሉትን ዳኝነት፣ የጠበቃና ሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎች የስር ተከሳሾች እንዲከፍሉ ሊወሰን ይገባል በማለት ዳኝነት መጠያቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎትም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ መልስ ሰጪዎች ለይ/ባይ ሊከፍሉት የሚገባው የዶላር ምንዛሬ መቼ በነበረው ነው? የሚለው ጭብጥ በተመለከተከፍ/ብ/ህ/ቁ 1750 ጋር አመሳስሎ በመተርጎም የአሁኑ አመልካቾች ለተጠሪ ሊከፍሏቸው የሚገባው የዶላር ምንዛሬ የስር ፍርድ ቤቱ ፍርድ በሰጠበት በታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ/ም በነበረው የዶላር የብር ምንዛሬ ተመን መሆን ይገባዋል በማለት የወሰነ ሲሆን አመልካቾች ገንዘቡን ከወሰዱት ጊዜ ጀምሮ ተጠሪ ክስ እስከመሰረቱባቸው ድረስ ላለው ጊዜ ወለድ ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በተመለከተ ደግሞ ተጠሪ ገንዘባቸው ከእጃቸው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ ገንዘብ ያገኙት ምንም አይነት ጥቅም እንደሌለ፣ በአንፃሩ ደግሞ የገንዘቡ ተጠቃሚዎች አመልካቾች የነበሩ መሆኑን በምክንያትነት ይዞ ወለዱ የማይከፈልበት ምክንያት የለም ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ ተጠሪ በክሳቸው እንደጠየቁት 150,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ የአሜሪካን ዶላር) በሚመለከት ከነሐሴ 13 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ክስ ወደ ፍርድ ቤት እስከቀረበበት እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ ላለው ጊዜም 9% ወለድ ሊከፈላቸው ይገባል፤ በተመሳሳይም አመልካቾቹ ብር 800,000 (ስምንት መቶ ሺህ ብር) ከተጠሪ ከወሰዱበት ከጳጉሜ 4 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ተጠሪ ክሱን በሬጅስትራር እስካስከፈቱበት እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ 9% ወለድ ሊከፍሏቸው ይገባል በማለት የስር ፍ/ቤቱ በዚህ ረገድ የሰጠውን ውሳኔ በማሻሻል ወስኗል፡፡ እንዲሁም የሥር 3ኛ ተከሳሽን በተመለከተም በባለቤታቸው በሁለተኛው አመልካች በቤተሰብ ህጉ ድንጋጌዎች መሰረት ተጠያቂ ሊያደርጋቸው የሚችል ሁኔታ ካለ ከተጠያቂነት የማያመልጡበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ለተጠሪ ክስ ግን በቀጥታ ፍርዱ ሊያርፍባቸው የሚያስችል ነገር የለም፣ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቱ በዚህ ረገድ የሰጠው ፍርድ የሚነቀፍ አይደለም በማለት በዚህ ረገድ የተሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡

 

የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ሲሆን የአመልካቾች የሠበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተገቢውን ጭብጥ ለጉዳዩ ሳይዝና አግባብነት የሌለውን ድንጋጌን መሰረት አድርጎ አመልካቾች ከኬንያ ናይሮቢ በአሜሪካን ዶላር ተልኮ በ2ኛ አመልካች ከአቢሲኒያ ባንክ በወቅቱ በነበረው የውጭ ምንዛሬ ተመን መሰረት ለተወሰደው ገንዘብ ለተጠሪ ገንዘቡን ሊመልሱ የሚገባው የስር  ፍርድ ቤት ውሳኔ በሰጠበት ጊዜ ባለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ነው በማለት  መወሰኑ አግባብነት የሌለው መሆኑን፣ ተጠሪ ወለድ የሚያገኙበት ሕጋዊ ምክንያትም የሌለ መሆኑን ዘርዝረው በዚህ ረገድ የተሰጠው የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ በአንፃሩ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው  ፍርድ  ቤት  ውሳኔ  እንዲፀናላቸው  ዳኝነት  መጠየቃቸውን  የሚያሳይ ነው፡፡


አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው አበይት ነጥቦች፡-

 

1. አመልካቾች ለተጠሪ ሊከፍሉት የሚገባው ገንዘብ በውጪ ምንዛሬ ነው? ወይስ በኢትዩጵያ ብር ነው?፣

2. አመልካቾች ገንዘቡን ከወሰዱት ጊዜ ጀምሮ ተጠሪ ክስ እስከመሰረቱባቸው ድረስ ላለው ጊዜ ወለድ ሊከፍሉ ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚሉት ሆነው ተገኝተዋል፡፡

 የ መጀ መሪያ ውን ጭብጥ በተመ ለከተ ፡- አመልካቾች ለተጠሪ የኢትዩጵያ ብር 800,000 እና 150,000 የአሜሪካን ዶላር በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ ሊከፍሏቸው እንደሚገባ ክርክር ያቀረቡበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው አመልካቾች ለተጠሪ መክፈል ያለባቸው 150,000 ዶላር ይኼው ገንዘብ በ2ኛ አመልካች ከአቢሲኒያ ባንክ ወጪ ሲሆን በኢትዩጵያ ብር ተመንዝሮ በተሠጠበት መጠን ነው? ወይስ በዶላር ነው? የሚል ሲሆን ይህ ጭብጥ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 246፣ 247 እና 248 ድንጋጌዎች አግባብ ሊመሰረት የሚገባው እና ተጠሪ በዶላሩ ነው ሊከፈላቸው የሚገባው የሚል ምላሽ ከተሰጠ ደግሞ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄው የዶላሩ ምንዛሬ መሆን ያለበት አመልካቾች ገንዘቡን በወሰዱበት ጊዜ ባለው የውጪ ምንዛሬ ተመን ነው?፣ ተጠሪ ክስ በመሰረቱበት ጊዜ ባለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ነው?፣ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ በሰጠበት ጊዜ ባለው የውጭ ምንዛሬ ተመን? ወይስ አመልካቾች ገንዘቡን ለተጠሪ በሚከፈሉበት ጊዜ ባለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ነው? የሚሉትና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

 

ከክርክሩ መረዳት እንደተቻለው ተጠሪ ገንዘቡን ከኬኒያ ወደ ኢትዮጵያ ለአመልካቾቹ የላኩላቸው አብረው የንግድ ማህበር ለማቋቋም በመዋጮነት ቢሆንም ማህበሩም አልተመሰረተም፣ ገንዘቡም ለአመልካቾች ጥቅም የዋለ ነው ከሚባል በስተቀር ተጠሪ በዚህ ገንዘባቸው ያገኙት እንዳችም ጥቅም የሌለ መሆኑን፣ ተጠሪ በገንዘባቸው ምንም አይነት ጥቅም ሳያገኙ  በአንፃሩ ግን አመልካቾች ይህንን ገንዘብ ከተጠሪ ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ ለራሳቸው ጥቅም በማዋል ከፍተኛ ገቢ እንዳገኙበት የሚገመት መሆኑን፣ ተጠሪ ገንዘቡ ለራሳቸው ንግዳዊ ስራ ወይም ለሌላ አገልግሎት አውለውት ቢሆን ኖሮ በወቅቱ ከፍተኛ ጥቅም ሊያገኙበት  ይችሉ እንደነበር የሚገመት መሆኑን፣ ተጠሪ የገንዘባቸው ዋጋ ሳይወርድ አቻው የብር ምንዛሬ እስካላገኙበት ድረስ ገንዘባቸውን በተሟላ ሁኔታ አግኝተዋል ሊባሉ የሚችሉ ያለመሆኑን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በምክንያትነት ይዞ የስር ፍ/ቤቱ አመልካቾች ለተጠሪ የብር ምንዛሬው መክፈል ያለባቸው ገንዘቡን ሲወስዱ በነበረው የብር ምንዛሬ ነው ማለቱ የተጠሪን ጥቅም የሚያጓድል፣ አመልካቾችን ደግሞ አላግባብ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ደምድሞ እና ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1750 ጋር አመሳስሎ በመተርጎም አመልካቾች ለተጠሪ ሊከፍሏቸው የሚገባው የዶላር ምንዛሬ የስር ፍርድ ቤቱ ፍርድ በሰጠበት በታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ/ም በነበረው የዶላር የብር ምንዛሬ ተመን መሆን ይገባዋል በማለት መወሰኑን ነው፡፡

በመሰረቱ ተጠሪ እንዲመሰርት የፈለጉትና ጥቅም አገኝበታለሁ ብለው የነበሩት ድርጅት ባለመቋቋሙ አመልካቾች ገንዘቡን እንዲመልሱላቸው ዳኝነት መጠየቃቸው ግልጽ ሲሆን  ዶላሩን


ከኬንያ አገር ወደ ኢትዩጵያ ቢልኩም 2ኛ አመልካች ገንዘቡን ከባንክ ወጪ አድርገው ሲወስዱ የተከፈላቸው በወቅቱ በነበረው የምንዛሬ ተመን ወደ ኢትዩጵያ ብር ተለውጦ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ በሚገባ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ከውጪ አገር የተላከ የውጭ ምንዛሬ ኢትዩጵያ ውስጥ በጊዜው በነበረው ተመን ታስቦ ክፍያ የተፈፀመበት ከሆነ ዶላሩ ለተላከበት አላማ አልዋለም በሚል ክርክር ሲነሳ ገንዘቡ ሊመለስ የሚገባው ዶላሩ ሲላክ በነበረበት የውጪ ምንዛሬ ተመን ሊሆን አይገባም የሚል የሕግ መሰረት የለም፡፡ ተጠሪ ከአመልካቾች ጋር ያለው ውል በመፍረሱ ምክንያት የደረሳባቸውን የጉዳት አይነትና መጠን በግልጽ ጠቅሰውም አልተከራከረም፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1750 ድንጋጌ ከገንዘብ እዳ ጋር ተይይዞ የሚነሳውን የውል አፈፃጸም ለመግዛት ታስቦ የወጣ ድንጋጌ መሆኑን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1749 ድንጋጌ ጋር ተጣምሮ ሲነበብ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1749(1) ድንጋጌ ገንዘብን የሚመለከት እዳ ሲሆን እዳው የሚከፈለው በአገሩ መገበያያ ገንዘብ መሆኑን በመርህ ደረጃ የደነገገ ሲሆን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1750 ድንጋጌ ደግሞ እዳው በሚከፈልበት ቦታ ውሉ ሕጋዊ ዋጋ የሌለው ገንዘብ ጠቅሶ እንደሆነ ውሉ ቃል በቃል እውነተኛ ዋጋ ወይም ይህንኑ የመሰለ ቃል ከሌለበት በቀር እዳው በሚከፈልበት ቀን ዋጋ ልክ በአገሩ ገንዘብ ሊከፈል እንደሚችል የሚያስቀምጥ ነው፡፡ በመሆኑም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1750 ድንጋጌ በአመልካቾችና በተጠሪ መካከል ላለው ጉዳይ ቀጥታም ሆነ በማመሳሰል የትርጉም መርህ ተፈፃሚ የሚሆንበት አግባብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የገንዘብ ክፍያ ውል መሰረት ያደረገ የገንዘብ እዳ ክፍያን የሚመለከት ካለመሆኑም በላይ አመልካቾች ከተጠሪ የተላከላቸውን የአሜሪካን ዶላር በቀጥታ የተቀበሉ ሳይሆን ዶላሩ በጊዜው በነበረው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን መሰረት ተሰልቶ ወደ ኢትዩጵያ ብር ተመልሶ አመልካቾች መቀበላቸው የተረጋገጠ ጉዳይ ነውና፡፡ በአገሪቱ የገንዘብ ስርዓት መሰረት መንግስትና ሕዝብ በጊዜው  በነበረው የውጪ ምንዛሬው ተመን ላገኙት ጥቅም ደግሞ ወደ ኢትዩጵያ ብር የተመነዘረ ዶላር ለተጠሪ ሊያስገኝ ይችል የነበረው ጥቅም ግምት ውስጥ ገብቶ ምንዛሬው ተመን የሚታሰብበት የሕግ አግባብም የለም፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካቾች ያላግባብ ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉበትን አጋጣሚ ግምት ውስጥ አስገብቶ ዶላሩ በተላከበት ጊዜ በኢትዩጵያ ብር ተመንዝሮ ለአመልካቾች መሰጠቱ በተረጋገጠበት ሁኔታ ለተጠሪ ዶላሩ ከተላከበት ጊዜ በኋላ ያለው የምንዛሬ ተመን  በከፍተኛ ሁኔታ የተለዋወጠ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገባ ተመኑ ለተጠሪም የሚያስገኘው ጥቅም ሕጋዊ አድርጎ መውሰዱ አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ጭብጥ ሳይመሰርትና በክርክሩ ሂደት የተረጋገጠው ፍሬ ነገር በመተው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1750 ድንጋጌን ያለቦታው ጠቅሶ አመልካቾች 150,000.0 የአሜሪካን ዶላር ለተጠሪ ሊመልሱ የሚገባው በታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ/ም ባለው የውጪ ምንዛሬ ነው በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት አመልካቾች ይህንኑ ዶላር ለተጠሪ ሊከፍሉ የሚገባው 2ኛው ተጠሪ ከአቢሲኒያ ባንክ ሲወስዱ በተከፈላቸው የውጪ ምንዛሬ ተመን ሊሆን የሚገባ ሁኖ አግኝተናል፡፡

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተመ ለከተ፡ - ተጠሪ ገንዘባቸው ከእጃቸው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ ገንዘብ ያገኙት ምንም አይነት ጥቅም ያለመኖሩ፣ በአንፃሩ ደግሞ የገንዘቡ ተጠቃሚዎች አመልካቾች በመሆናቸው ተጠሪ ይህ ገንዘብ ከእጃቸው አላግባብ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያጡት ጥቅም በወለድ ክፍያ ሊካካስላቸው የሚገባ መሆኑን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ አመልካቾች በዚህ ሰበር ደረጃ የሚከራከሩት ለተጠሪ ሕጋዊ ወለድ የሚታሰብበት አግባብ የለም በሚል ሲሆን ለዚህም እንደ ሕጋዊ ምክንያት የሚያቀርቡት ተጠሪ ለአመልካቾች ማስጠንቀቂያ ያልሰጡ መሆኑንና ጉዳዩ የገንዘብ ብድርን መሰረት ያላደረገ መሆኑን ነው፡፡


ይሁን እንጂ ይመሰረታል የተባለው ድርጅት ሳይመሰረት መቅረቱን አመልካቾች የሚክዱት ፍሬ ነገር አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በተጠሪ ቋሚ ሃብት ወይም ጥቅም ላይ መቀነስን የሚያስከትል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ በተጠሪ ላይ ቀጥተኛ የሆነ የገንዘብ ኪሳራ የደረሰባቸው መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ተጠሪ ለአመልካቾች ማስጠንቀቂያ የሚሰጡበት ምክንያት የለም፡፡ አመልካቾች ያመኑትን ገንዘብ ያህል ተጠሪ ለመውሰድ ፈቃደኛ ሊሆኑ ያለመቻላቸውንም በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጡት ጉዳይ አለመሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ በመሆኑም ተጠሪ ይመሰረታል በማለት የጠበቁት ድርጅት ሳይመሰረት ከቀረ ለአመልካቾች በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1771 እና 1705 ድንጋጌዎች አግባብ ማስጠንቀቂያ ሊሰጡ ይገባ ነበር ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡ እንዲሁም የወለድ ገንዘብ በብድር ጊዜ ብቻ ተፈፃሚነት የሚሆን ነው በሚል የቀረበው የአመልካቾች ክርክር ሲታይም የሕግ መሰረት የሌለው ነው፡፡ ወለድ በሕጉ አግባብ የተዘረጋው ስርዓት እንደተጠበቀ ሁኖ በስምምነት ወይም ያለስምምነት ሊከፈል የሚችል ገንዘብ ነው፡፡ ወለድ ተበዳሪ የወሰደውን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ባለመመለሱየተነሳ የሚከፈል የገንዘብ ካሳ ነው፡፡ ሌላው አይነት ወለድ አንድ ሰው ግዴታውን ባለመፈፀሙ ወይም በማዘገየቱ የተነሳ የሚከፈለው ካሳ እኩያ ነው፡፡ ስለሆነም ወለድ ለገንዘብ ብድር ብቻእንዲከፈል የሚደረግ የካሳ አይነት አይደለም፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1803(3) ድንጋጌ አንፃር ሲታይም ተጠሪ አመልካቾች የውል ግዴታቸውን ባለመፈመፀማቸው የተነሳ የካሳ እኩያ የሆነው ወለድ የማያገኙበት የሕግ ምክንያት አላገኘንም፡፡

 

በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቱ ገንዘቡ ለተጠሪ ጥቅም ያለማዋሉን አረጋግጦ እያለ ገንዘቡን የላኩት ለንግድ ማህበር ማቋቋሚያ በመዋጮነት በመሆኑ ወለድ አይገባቸውም የሚል ምክንያት አሳማኝ ሆኖ ባለመገኘቱ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ያለመቀበሉ ተገቢ ሁኖ አግኝተናል፡፡ ስለሆነም ተጠሪ በክሳቸው እንደጠየቁት 150,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ የአሜሪካን ዶላር) በሚመለከት 2ኛ ተጠሪ ከአቢሲኒያ ባንክ ወጪ አድርገው ከወሰዱበት ጊዜ ጀምሮ ክስ ወደ  ፍርድ ቤት እስከቀረበበት እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ ላለው ጊዜም 9% ወለድ ሊከፈላቸው ይገባል፤ በተመሳሳይም አመልካቾቹ ብር 800,000 (ስምንት መቶ ሺህ ብር) ከተጠሪ ከወሰዱበት ከጳጉሜ 4 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ተጠሪ ክሱን በሬጅስትራር እስካስከፈቱበት እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ 9% ወለድ ሊከፍሏቸው ይገባል በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

ሲጠቃለልም ከላይ በተገለፁት ሕጋዊ ምክንያቶች የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ሊሻሻል የሚገባው ሁኖ ስለአገኘን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው  ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ 88280 ጥቅምት 08 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች 150,000 የአሜሪካን ዶላር ለተጠሪ ሊከፍሉ የሚገባው ይኼው ዶላር ከኬንያ ናይሮቢ ወደ ኢትዩጵያ ተልኮ በአቢሲኒያ ባንክ በኩል በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ በተሰጠው ተመን መሰረት ነው ብለናል፡፡


3. ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች ለተጠሪ በሚከፍሉት ገንዘብ ላይ ክሱ ከቀረበበት ከሚያዝያ 10 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስኪያልቅ ከሚታሰብ 9% ወለድ አክለው እንዲከፍሉ የሚለውን የስር  ፍርድ  ቤትን ውሳኔ በማሻሻል የሠጠውን ውሳኔ ይህ ችሎትም በማሻሻል አመልካቾች 150,000 ዶላሩን በሚመለከት ከላይ በተራ ቁጥር 2 መሰረት በሚገኘው የብር ስሌት ላይ ከነሐሴ 13 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ 9% ወለድ በማከል እንዲሁም ብር 800,000 (ስምንት መቶ ሺህ ብር) በሚመለከት ደግሞ አመልካቾች ገንዘቡን ከወሰዱበት ከጳጉሜ 4 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስኪያልቅ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር ለተጠሪ እንዲከፍሏቸው ወስነናል፡፡

4.  የሥር 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከትይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ አልተነካም፡፡

5. በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ለተደረገው ክርክር ወጪና ኪሳራ በሚመለከት አመልካቾች ለተጠሪ በዚህ ሰበር ችሎት በተወሰነው የገንዘብ መጠን መሰረት የዳኝነት ገንዘብ ይክፈሏቸው ብለናል፡፡ ሌሎች ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና በዚህ ችሎት ክርክር የወጡትን ወጪና ኪሳራዎችን የያራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

 

መዝገቡ ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::