96628 law of succession/ property law/ estate of the deceased

ሟች በህይወት እያለ ከይዞታ ቦታው ላይ ለሌላ ሠው ቤት እንዲሠራፈቅዶ ቢሰጠው ሟች በሚሞትበት ጊዜ በሟች ፈቃድ ቤት የሠራው የቤቱ ባለቤት እንደሚሆንና ከሌላው ቦታ ጋር ሆኖ የውርስ ክፍል የሚሆን ስላለመሆኑ፣

የፍ/ህ/ቁ. 826/2/፣1179/1/

 

የሰ/መ/ቁ. 96628

 

ህዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- 1. አሳመነው ከበደ

 

2. ወ/ሮ ፍቅርተ ከበደ            ጠበቃ አቶ ፍሰሀ አለማየሁ ቀረቡ፡፡

 

3. አቶ ምንተስኖት ከበደ - ቀረቡ

 

4. ተማሪ ቀንአየሁ ከበደ

 

5. ተማሪ ብሩክ ከበደ

 

ተጠሪ፡- አቶ ዳንኤል ከበደ- ጠበቃ አቶ በየነ ታደሰ ቀረቡ፡፡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 38926 ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የፌዴራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 137992 ጥር 14 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የውርስ ንብረት ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ አመልካች አመልካችዎች  ተጠሪ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው ማመልከቻ ነው፡፡ ተጠሪ ወላጅ አባቴ አቶ ከበደ ሰለሞን ጥቅምት 22 ቀን 2003 ዓ.ም በሞት ተለይቶ ወራሸነታችንን አረጋግጠናል፡፡ ስለዚህ ውርስ አጣሪ ተመድቦ ውርሱ እንዲጣራ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ አመልካቾች ውርስ አጣሪ ቢመደብና የውርሱ ንብረት ተጣርቶ ቢቀርብ አንቃወምም በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ውርስ አጣሪ ከመደበ በኋላ ውርሱ ሲጣራ ተጠሪ ሟች በ 24/11/1980 ዓ.ም በተፃፈ የስጦታ ውል በ210 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ አንድ ክፍል ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ሰጥቶኝ አባታችን በህይወት እያለ ቆርቆሮ ቤቱን በማፍረስ ሁለት ክፍል የጭቃ ቤት ሠርቼ እየኖርኩበት እገኛለሁ፡፡ ቤቱ ዋናውን   568


ካሬ ሜትር ግቢው ውሰጥ የሚገኝና ቦታውም ራሱን የቻለ ካርታ የሌለው በመሆኑ ሁለት ክፍል የጭቃ ቤት 210 ካሬ ሜትርይዞታ ከውርስ ንብረቱ ተለይቶ እንድያዝልኝ በማለት ለውርስ አጣሪው ጥያቄ አቅርቧል፡፡አመልካቾች የይርጋ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ስጦታው በፍትሐበሔር ሕግ ቁጥር 2443 እና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 881 መስፈርቶች የማያሟላ በመሆኑ ህጋዊ ውጤት የለውም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ስጦታው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2443 እና በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 881 የተደነገገውን መስፈረት ስለማያሟላ፣ ስጦታው ፈራሽ ነው በማለት ወስኗል፡፡ ሆኖም ሁለት ክፍል ጭቃ ቤት የሥር አመልካቹ የአሁን ተጠሪ ያሰራው መሆኑን በሰውና በፅሑፍ ማሥረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ በ201 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ የተሠራው ሁለት ክፍል ቤት የውርስ ንብረት ሣይሆን የአመልካች /የተጠሪ/ የግል ንብረት ነው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

2. አመልካቾች በዚሁ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኙን በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡ አመልካቾች ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ በ210 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አንድ ክፍል ቤት እንድሰራ በሰጦታ ተሰጥቶኝ ቤቱን አፍርሸ ሁለት ክፍል ቤት ሠርቻለሁ በማለት ክስ አቅርቧል፡፡ የስጦታ ውሉ የሕጉን ፎርም አያሟላም ተብሎ ውድቅ ተደርጓል፡፡ ይህ ከሆነ ተጠሪ አማራጭ የዳኝነት ጥያቄ ያላቀረበበትን የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179 ጠቅሶ መወሰኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት፡፡ ተጠሪ ቤቱን መሥራቱን አመልካቾች አላመኑም፡፡ ቤቱን መስራቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ስለዚህ ቤቱን ያሠራው ተጠሪ ነው መባሉ ስህተት ነው፡፡ ተጠሪ ሠራሁ የሚለውን ቤት ከ30 ካሬ ሜትር በማይበልጥ ቦታ ላይ ያረፈ ሆኖ እያለ 210 ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ የውርስ ንብረት ክፍል እንዳልሆነ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ  በማለት አመልክተዋል፡፡

 

3. ተጠሪ የካቲት 21 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች ቤቱንና ሽንት ቤቱን በግል የሠራሁት መሆኔን ገልጬ ያቀረብኩትን ክስ በግልፅ ክደው ክርክር አላቀረቡም፡፡ ተጠሪ 1179 ድንጋጌን በመጥቀስ በቃል ክርክርና በፅሑፍ ለሥር ፍርድ ቤት አማራጭ ክርክር አቅርቤያለሁ፡፡ አመልካቾች ቤት ያረፈበት በ3ዐ ካሬ ሜትር የሚሆነው ይዞታ እንጅ 21ዐ ካሬ ሜትር አይደለም በማለት ያቀረቡት ክርክር በሥር ፍርድ ቤት ያልቀረበ አዲስ የፍሬ ነገር ክርክር ነው፡፡ ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ እንዲፀናልኝ በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካቾች የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

4. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የቤት ቁጥር 429 ግቢና ስፋቱ 568 ካሬ ሜትር ቦታ ውስጥ የሚገኘው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤትና ቤቶቹ የተሰሩት 21ዐ ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ የውርስ ንብረት ሣይሆን የተጠሪ የግል ቤትና ይዞታ ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ የሕግ መሠረት አለው ወይስ የለውም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5. ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን ተጠሪ ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበውን የዳኝነት ጥያቄ መሠረታዊ ይዞታና በተጠሪና በአመልካቾች ክርክር   ማስረጃ


የተረጋገጡትን መሠረታዊ ፍሬ ጉዳዩች መመርመር ያስፈልጋል፡፡ተጠሪ ለሥር ፍርድ ቤትና ለውርስ አጣሪው ያቀረበው የዳኝነት ጥያቄ ሁለት መሠረታዊ መብቶች ተረጋግጠው በፍርድ እንዲወሰንለት የሚጠይቅ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሟች ወላጅ አባቴ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የቤት ቁጥር 429 ግቢ ውስጥ ሰርቶት የነበረውን አንድ ክፍል ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ሐምሌ 24 ቀን 1980 ዓ.ም ባደረገው የስጦታ ውል ሰጥቶኛል፡፡ ከዚህ በኂላ ሰጭው ወላጅ አባቴ በህይወት እያለ የሰጠኝን አንድ ክፍል ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት በማፍረስ ፣ በራሴ ወጪ ሁለት ክፍል ሰርቪስ የጭቃ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ገንብቼ የኖርኩበት ስለሆነ ሁለቱ ክፍል ሰርቪስ ቤቶችና አንድ ክፍል ሽንት ቤት የሟች የውርስ ንብረት ክፍል አለመሆኑ ተረጋግጦ ይወሰንልኝ የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ሁለተኛ የዳኝነት ጥያቄ ወላጅ አባቴ ሐምሌ 24 ቀን 1980 ዓ.ም ባደረገው የስጦታ ውል አንድ ክፍል ቆርቆር በቆርቆሮ የተሰራ ቤት ሣይሆን ሟች ከነበረው 568 ካሬ ሜትር የይዞታ መሬት210 ካሬ ሜትር ይዞታ  በስጦታ ያስተላለፈልኝና ይህ የይዞታ መሬት ከጠቅላላው 568 ካሬሜትር ይዞታ ያልተለየ በመሆኑ ተለይቶና ተከልሎ እንዲሰጠኝ ይወሰንልኝ የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

6. ተጠሪ መብት አግኝበታለሁ የሚሉት የስጦታ ውል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር  2443 እና በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 881 የተደነገጉትን መስፈርቶች የማያሟላ መሆኑ ፍሬ ነገር የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ምክንያት ተጠሪ የግል ንብረቴ ናቸው የሚላቸውን ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶችና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ላይ መብት ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሥጦታ ውሉ መሠረት እንደማይሆንና የሥጦታ ውሉ ህጋዊ መብት እንደሌለው የበታች ፍርድ ቤቶች ወስነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ የውርስ ንብረት ከሆነው የቤት  ቁጥር 429 አጠቃላይ 568 ካሬ ሜትር ስኩየር የይዞታ ቦታ 21ዐ ካሬ ሜትር ስኩዌር በስጦታ ይተላለፍልኝ የግል ይዞታዬ ነው በማለት ያቀረበው ክርክር የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው በመባሉ ምክንያት የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ተጠሪ የስጦታ ውሉን መነሻ በማድረግ ሰርቪስና ሽንት ቤቱ በ 21ዐ ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ ላይ ያቀረበው የመብት ጥያቄ፣የስጦታ ውሉ የሕጉን ፎርም ያላሟላ ፈራሽ ነው በመባሉ ምክንያት ውሉ በሙሉ ውድቅ የተደረገ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

7. የሥር ፍርድ ቤት በሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና በአንድ ክፍል ሽንት ቤት የተጠሪ የግል ንብረት ነው በማለት መደምደሚያ ላይ የደረሰው፣ ተጠሪ ቤቶቹን የአመልካችዎች አውራሽና ወላጅ አባት ሣይቃወመው በራሱ ወጭና ገንዘብ የሠራቸው መሆኑ በማስረጃ ተረጋጋጧል በማለት ነው፡፡ በእርግጥ ተጠሪ ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት የአመልካቾችና የተጠሪ ወላጅ አባትና አውራሽ ፈቃድና ያለምንም ተቃውሞ ተጠሪ በራሱ ውጭ የገነባቸው መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች በማስረጃ አረጋገጠዋል፡፡ በአንድ ሰው የይዞታ መሬት ላይ ባለይዞታው ሣይቃወም ህንፃ የገነባ ሰው የህንፃው ባለቤት እንደሚሆን፣ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179 ንዑስ አንቀጽ 1 ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ሁለቱ ክፍል ሰርቪስ ቤቶችና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ከጅምሩ የአመልካቾች አውራሽ የግል ሀብት ሣይሆኑ የተጠሪ የግል ንብረት መሆናቸውን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች የደረሱበትን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179 ንዑስ  አንቀጽ 1 ድንጋጌ በማጣመር ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሟች ሲሞት ለሟች ወራሾች የሚተላለፈው በሟች መሞት ምክንያት የማይቋርጡ መብቶችና ግዴታዎች መሆናቸው በፍትሐበሔር


ሕግ ቁጥር 826 ንዑስ አንቀጽ 2 ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የአመልካችዎች አውራሽ ተጠሪ በራሱ ወጭ በሰራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶች እና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ላይ የባለሀብትነት መብት የሌለው በመሆኑ፣ አውራሻቸው የሌለው መብት ለአመልካች ወራሾች ሊተላለፍ የሚችልበት የሕግ መሠረት የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ተጠሪ የሠራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሰርቪስ ቤት የውርስ ንብረት ክፍል ሣይሆን የተጠሪ የግል ንብረት ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 826 ንዑስ አንቀጽ 2 እና የፍትሐበሔር ሕግ ቁጥር 1179(1) ድንጋጌ መሠረት ያደረገ በመሆኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ተጠሪ ቤቶቹን የሠራኃቸው እኔ ነኝ የሚል ጥያቄ ያቀረበ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን የሕግ ድንጋጌ ማለትም የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179(1) በመጥቀስ የሰጡት ውሳኔ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 182(2) ድንጋጌ የሚጥስ ነው በማለት አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሠረት የሌለው በመሆኑ አልተቀበልነውም ፡፡

8. ተጠሪ የውርስ ንብረት በሆነው የቤት ቁጥር 429 ግቢ ውስጥ የሠራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት የግል ባለሀብት ነው የተባለው በስጦታ ውሉ ሳይሆን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179(1) መሠረት ባለይዞታው ሣይቃወመው በግል ገንዘቡ የሠራው ነው ተብሎ ነው፡፡ ይህ ከሆነ አመልካች በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179(1) መሠረት ባለመብት የሚሆነው የአመልካቾች አውራሽ ሳይቃወመው በራሱ ወጭ በሠራቸው ቤቶችና ቤቶቹ በተሰሩበት ወይም ባረፉበት ቦታ ላይ እንጅ፤ ቤቶቹን ከሠራበት ቦታ ውጭ ባለው የይዞታ ቦታ ላይ ባለመብት የሚሆንበት ድንጋጌ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር የበታቸ ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በግቢው ውስጥ በ 210 ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ ላይ መብት አግኝቼበታለሁ የሚለው የስጦታ ውል ፈራሽነው በማለት ከወሰኑ በኃላ ተጠሪ 210 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የይዞታ መብት እንዳለው ገልፀው የሰጡት ውሳኔ የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1179(1) እና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 826(2) ድንጋጌ መሠረት ያላደረገና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

9. ከዚህ አንፃር ቢታይ ተጠሪ ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ግንባታ ካከናወነበትና ቤቱ ካረፈበት ቦታ ውጭ በ210 ካሬ ሜትር ቦታ  ላይ ባለይዞታ የሚሆንበት የሕግ መሠረት የሌለ በመሆኑ ፣የበታች ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179 (1) ድንጋጌ ይዘት በአግባቡ ሣይገነዘቡ ተጠሪ በራሱ ወጭ የሰራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤት፣ አንድ ክፍል ሽንት ቤትና 210 ካሬ ሜትር ይዞታ የውርስ ንብረት አይደለም በማለት የሰጡት ውሣኔ በከፊል መሠረታዊ የሕግ ስህተት  ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 ው ሣኔ

 

1. የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ተሻሽሏል፡፡

2. የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በራሱ ውጭ የሠራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት የውርስ ንብረት ክፍል ሣይሆኑ የተጠሪ የግል ንብረት ናቸው በማለት የሰጡት ውሣኔ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1179(1) መሠረት ያደረገ በመሆኑ ፀንቷል፡፡

3. ተጠሪ በቤት ቁጥር 429 ግቢ ውስጥ 210 ካሬ ሜትር ቦታ ባለ ይዞታ ሆኜበታለሁ የሚለው የስጦታ ውል ፈራሽ የሆነ በመሆኑና ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል


ሽንት ቤት ከገነባበትና ቤቱ ካረፈበት ውጭ ያለው 210 ካሬ ሜትር ቦታ የውርስ ንብረት ክፍል አይደለም በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት  የውሣኔ ክፍል ተሽሯል፡፡

4.  ተጠሪ  ሰርቪስ ቤቱና ሽንት ቤቱ ከገነባበትና ቤቱ ካረፈበት ቦታ ውጭ ባለው  ይዞታ ቦታ ላይ የይዞታ መብት የለውም ብለናል፡፡ ተጠሪ ሰርቪስ ቤትና ሽንት ቤት ከገነባበትና ቤቱ ካረፈበት ቦታ ውጭ ያለው የቤት ቁጥር 429 ይዞታና ቤቱ ላይ አመልካችና ተጠሪ እኩል የወራሽነት መብት አላቸው በማለት ወስነናል፡፡

5.  በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

6. ይህ ውሣኔ ተጠሪ በአፈፃፀም ወቅት የመውጭያና የመግቢያ መብት ይከበርልኝ የሚለበትን ጥያቄ ከማቅረብ አያግደውም፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ አምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ብ/ግ