88275 family law/ divorce/ partition of property/ priority to purchase

የባልና ሚስት ጋብቻ ፈርሶ የጋራ የሆነ ንብረት  ክፍፍል በሚፈፀምበት ጊዜ በፍ/ሕጉ ላይ የተቀመጡት በቅድሚያ የመግዛት መብት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሌላቸው ስለመሆኑ

 

የፍ/ሕ.ቁ. 1386፣1388፣1391፣1392፣1393፣(1)፣1397

የሰ/መ/ቁ.88275

ጥር 19 ቀን 2007.ዓ.ም

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ኃይለሚካኤል ልኬ ሎሶ - የቀረበ የለም ተጠሪ ፡- 1. አቶ መኮነን በለጠ - ጠበቃ መለሰ ጦና ቀረቡ

2. ወ/ሮ አምሳለች ዘበን - አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ የቅድሚያ ግዥ መብት ጥያቄ የሚስተናገድበትን የሕግ አግባብ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረውም በሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአፈፃጸም ከሳሽ የሆኑት የአሁኗ 2ኛ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ በዋናው ፍርድ መሰረት እንዲፈፅምላቸው ባቀረቡት የአፈጻም ክስ መነሻ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካችና 2ኛ ተጠሪ ባልና ሚስት የነበሩ ሲሆን ጋብቻው በፍርድ ቤት ውሳኔ ፈርሶ የጋብቻ ውጤት ከሆኑት ንብረቶች መካከል ለአሁኑ ክርክር መነሻ የሆነውን መኖሪያ ቤት በክልሉ የቤተሰብ ሕግ መሰረት የተቀመጡት የክፍፍል ስርዓቶችን መሰረት በማድረግ ቤቱ በግልጽ ጨረታ መሸጥ እንደአለበት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳርፎ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ የአሁኑ 1ኛ ተጠሪተወዳድረው የጨረታ አሸናፊ በመሆን የቤቱ ገዥነታቸው ከታወቀ  በኋላ የአሁኑ አመልካች ቤቱን የመልሶ መግዛት መብት እንደአላቸው ጠቅሰው ቤቱን እንዲያስቀሩ እንዲወሰንላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተው የአሁኑ ተጠሪዎች ይህንኑ የአመልካችን ጥያቄ ተቃውመው የመልሶ መግዛት መብት ለአመልካች ሊሰጣቸው አይገባም የሚለውን መከራከሪያ ሁለቱም ተጠሪዎች ከማቅረባቸውም በተጨማሪ የአሁኗ 2ኛ ተጠሪ አመልካች አዲስ አበባ ውስጥ መንግስት በሰጣቸው ደረጃውን በጠበቀ ቤት እንደሚኖሩና ራሳቸው ግን ሁለት ልጆችን ይዘው ቤት የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰው የመልሶ መግዛት መብት ለራሳቸው እንዲጠበቅላቸው ጭምር ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡የሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የአመልካች ጥያቄ ተቀባይነት የለውም በማለት ውደቅ አድርጎ የጨረታውን ውጤት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡በዚህ የስር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩ በክልሉ የቤተሰብ ሕግ የሚገዛ ቢሆንም የክልሉ የቤተሰብ ሕግ ስለመልሶ የመግዛት መብት የሚደነግገው ጉዳይ ያለመኖሩንና በዚህ ሁኔታ ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕጉ የጋራ ንብረትን መልሶ ስለመግዛት የተደነገጉትን ድንጋጌዎችን ተፈፃሚ ማድረግ በሕግ አተረጓጎም መርህ ተገቢ መሆኑን ጭምር ዘርዝሮ የአመልካች ቤቱን መልሶ የመግዛት መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል በማለት የስር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ሽሮታል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪዎች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ   ችሎት


አቅርበው ተቀባይነት ያጡ ሲሆን የሰበር አቤቱታቸውን በተናጠል ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ መዝገቦችን አጣምሮ በመመርመር የአሁኑ አመልካች የመልሶ መግዛት መብት አላቸው ተብሎ የተሰጠውን የከተማውን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ እና ይህንኑ ውሳኔ ያጸናውን የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትዕዛዝ ሽሮ የከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ አፅንቶታል፡፡የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ  ይዘትም፡- የጋብቻ ውጤት የሆነውን ቤት መልሶ ለመግዛት በፍትሃ ብሔር ሕጉ በአንቀጽ 1261፣ከአንቀፅ 1386- 1409 ስር የተጠቀሱት ድንጋጌዎች መብት የሚሰጣቸው ሁኖ እያለ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ በክልሉ የቤተሰብ ሕግ መሰረት የሚዳኝ እንጂ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች የሚዳኝ አይደለም በማለት የሰጠው ውሳኔ ተገቢውን የሕግ አተረጓጎምና አተገባበር ያልተከተለ ከመሆኑም በላይ በዚህ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 37297 የተሠጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ያላገናዘበ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡የሰበር አቤቱታቸው ተመርምሮም ከተጠቃሽ ድንጋጌዎችና ከክልሉ የቤተሰብ ሕግ አንጻር የአመልካች ጥያቄ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን የጽሁፍ ክርክር የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ጉዳዩ ለሰበር ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ የአሁኑ አመልካች የጋራ ንብረት ነው የሚለውን ቤት ከ1ኛ ተጠሪ መልሶ የመግዛት መብት ያለው መሆኑ አለመሆኑን፣ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1394፣ ከቁጥር 1405-1408 ከተመለከቱት ድንጋጌዎች እና የፍትሐብሔር ሕጉ ስለ ጋራ ባለሃብትነት በቁጥር 1257 እና የሚቀጥሉት አንቀጾች የደነገገውን ከክልሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 103(2) እና 102 ድንጋጌዎች አኳያ ለመመርመር ተብሎ በመሆኑ ከዚሁ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው ተመልክተናል፡፡

በክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካችና 2ኛ ተጠሪ በቤቱ ላይ እኩል መብት ያላቸው መሆኑን፣የቤቱ የክፍፍል ስርዓት እንዲፈጸም የተደረገውም የክልሉን የቤተሰብ ሕግ መሰረት በማድረግ መሆኑን፣አመልካች አሁን አጥብቀው የሚከራከሩት የክልሉ የቤተሰብ ሕግ ስለመልሶ መግዛት የሚያስቀምጠው መፍትሄ ስለሌለ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ያሉት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት ሊኖራቸው ይገባል በማለት መሆኑን፣2ኛ አመልካችም ቤቱን መልሶ የመግዛት መብት ሊጠበቅልኝ ይገባል በማለት ያቀረቡት ጥያቄ እስከዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ተቀባይነት ያጣ መሆኑን የሰ/መ/ቁጥር 90586 የሚያሳይ መሆኑን፣1ኛ አመልካች አከራካሪውን ቤት የገዙት በግልጽ በተደረገው ጨረታ ተወዳድረው ጨረታው ሕጋዊነቱ ተረጋግጦ መሆኑን ከመሆኑም በላይ በዚህ የጨረታ ሂደት አመልካችም ሆነ የአሁኗ 2ኛ ተጠሪ እንዲሳተፉ ጨረታው እንዲከናወን ያዘዘው የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያልሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡

በመሰረቱ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ክፍፍል ስርዓት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስትም ሆነ በክልል ሕግጋት መንግስታት የተረጋገጠውን የእኩልነት መብት መሰረት አድርጎ መከናወን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ክፍፍል ስርዓት የሚከናወንበትን መንገድ የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 በቅደም ተከተል ያስመቀጣቸው መንገዶች ከአንቀፅ 90 እስከ 93 ድረስ ባሉት የሰፈሩ ሲሆን ስራ ላይ ያሉት የክልል የቤተሰብ ሕግጋትም አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎችን ይዘው እናገኛለን፡፡ ለተያዘው ጉዳይ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ያለው የክልሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 75/1996 ሲታይም የባልና ሚስት ንብረት የሚከፋፈልበትን ሥርዓት ከአንቀፅ    101


እስከ 105 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች አካቶ ይዟል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለውም የጋብቻ ውጤት የሆነው የጋራ ንብረት ክፍፍል ሊከናወን የሚገባው የእኩልነት መርህን መሰረት አድርጎና የተጋቢዎችን ፈቃድ በመመርኮዝ መሆኑን ነው፡፡የተጋቢዎች ስምምነት ከሌለ ደግሞ ክፍፍሉ መፈፀም ያለበት በሕጉ የተመለከተውን ቅደም ተከተል መሰረት አድርጎ ሊሆን እንደሚገባ ሕጉ ያስገነዝባል፡፡በመሆኑም የጋብቻ ውጤት የሆነውን ንብረት ለማከፋፈል የበላይነት ያለው የቤተሰብ ህጉ ነው፡፡

 

በመሰረቱ በፍ/ብ/ሕጉ አንቀጽ 1386 እና ተከታዩቹ የተመለከተው ድንጋጌ ተፈፃሚነት የሚኖረው የጋራ ባለሐብቶች ለሆኑ ወገኖች እንዲሁም የጋራ ባለሐብት የሆኑ ወራሾች መካከል ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕግ ድንጋጌ ቁጥር 1388 እና 1392 ይዘት ያመለክታል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ የመግዛት መብት በሕግ ጥበቃ የተደረገለት መብት ሲሆን ሕጉ ሊያሳካ ያሰበው አላማም ከዘር የወረደ ንብረትን በተመለከተ ዘመዳሞች የሚኖራቸውን ስሜት ለመጠበቅና ከቤተሰቡ እጅ ወጥቶ ወደ ሌላ ወገን እንዳይተላለፍ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡በዘመዳሞች መካከል ይህ መርህ ተፈጻሚ የሚሆነው በውርስ ሀብት ላይ ሲሆን መብቱን ተግባራዊ የሚያደርጉትም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1391 ስር እንደተመለከተው በወራሽነት ቅደምተከተላቸው መሰረት ነው፡፡ ለቅድሚያ ግዥ መብት የሚወዳደሩት  በእኩል የዝምድና ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሆኑ እንደሆነ በመሬቱ ላይ የሚኖረውና የሚጠቀምበት ሰው ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1392 ስር በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይህ ካልተቻለ ደግሞ መሬቱን በአንድነት እንደሚሰሩበት እኩል በሆነ ድርሻ የጋራ ባለሃብቶች እንደሚሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1393(1) ድንጋጌ ያሳያል፡፡በሌላ በኩል ሕጉ በባለጥቅሞቹ ላይ ያስቀመጠው ገደብም ያለ መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1397 ድንጋጌ ያሳያል፡፡በዚህ ድንጋጌ መሰረት ባለጥቅሞቹ በቀዳሚነት የመግዛት መብትን ለሌላ ሰው ሊያስተላልፉ እንደማይችሉና እንዲሁም በእዳ ሊያዝ እንደማይችል አስገዳጅነት ባለው ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ሌላው ስለቅድሚያ የመግዛት መብት በሕጉ የተቀመጠው ጉዳይ የመብቱ የተፈፃሚነት ጊዜ ነው፡፡በዚህም መሰረት በቅድሚያ የመግዛት መብት ተፈጻሚ የሚሆነው ባለሃብቱ ሀብቱን ወይም የሀብቱን አላባ በዋጋ በሚሸጥበት ጊዜ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1398 ድንጋጌ የሚያመላክት ሲሆን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1407(1) ድንጋጌም ንብረቱ የተላለፈው ያለ ዋጋም ቢሆንም ግምቱን በመክፈል ይገባኛል ባዩ ሊገለገልበት እንደሚችል ያስረዳል፡፡እንዲሁም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1400 ድንጋጌ ማንም ሰው በቀዳሚነት ይገባኛል በማለት መብት ሊገለገልበት የፈለገ እንደሆነ ንብረቱ በሀብትነት ወይም በአላባነት ለገዥ ወይም በሐራጅ ለሚገዛው ሰው የተላለፈ መሆኑ ለይገባኛል ባዩ ከተነገረበት ቀን አንስቶ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በመብቱ ሊገለገልበት የፈለገ መሆኑ ካስታወቀ መብቱ እንደሚቀርበት አስገዳጅነት ባለው ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1401 ደግሞ በቀዳሚነት ይገባኛል በማለት መብት እንዲገለገልበት ለመጠየቅ የማስተላለፍያ ማስታወቂያ ሳይነገር የቀረ እንደሆነ የጋራ ባለሃብቶቹ በማያጠራጥር አኳኋን ንብረቱ ለሌላ ሰው የተላለፈ መሆኑን ካወቁበት ቀን አንስቶ በሚቆጠር በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በቀዳሚነት ይገባኛል  በማለት በመብታቸው ሊገለገሉበት የፈለጉ መሆናቸውን ማስታወቅ እንደአለባቸውና የስጋ ዘመዳሞች ከሆኑ ደግሞ አዲሱ ባለሃብት ወይም የአላባ ጥቅም ተቀባዩ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት እጅ ካደረገበት ቀን አንስቶ በሚቆጠር በስድስት ወር ጊዜ ውሰጥ በቀዳሚነት ይገባናል በማለት መብታቸውን ሊገለገሉበት የፈለጉ መሆናቸውን ማስታወቅ እንደአለባቸው እንደቅደምተከተሉ በተጠቃሹ ቁጥር ንዑስ አንቀጽ አንድ እና ንዑስ አንቀጽ ሁለት ድንጋጌዎች ስር በሕጉ የተመለከተውን ጊዜ ያለማስታወቅ እና ውጤቱን በተመለከተ ደንግገው እናገኛለን፡፡


እንግዲህ በቀዳሚነት የመግዛት መብትን አድማስ በተመለከተ በሕጉ የተቀመጡ ሁኔታዎች ከላይ የተቀመጡ ከሆኑ አሁን የተያዘው ጉዳይም እልባት ማግኘት ያለበት ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መሰረታዊ አላማ እንዲሁም ጉዳዩን በተለይ ለመግዛት የወጣው ህግ ድንጋጌዎች አንፃር ነው፡፡ከዚህ አኳያ ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካችና 2ኛ ተጠሪ በንብረቱ ላይ እኩል መብት ያላቸው ቢሆንም አንዱ ከሌላው በቅድሚያ ቤቱን መልሶ የመግዛት መብት የሚያገኝበት አግባብ የለም፡፡ የክልሉ የቤተሰብ ሕጉ በአንቀጽ 102 ስር ክፍፍሉ መሰረት ከሚያደርግባቸው ሁኔታዎች አንዱ ንብረቱ የተለየ ጥቅም የሚሰጠውን ተጋቢ መለየት እንደሆነ በተመለከተው አግባብም ለአመልካች ቤቱ እንዲሰጥ የሚደረግበት ህጋዊ ምክንያት መኖሩ አልተረጋገጠም፡፡ጉዳዩን የሚገዛው ልዩ ሕግ ስለ አንድ ክርክር መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ድንጋጌ ባልያዘበት ሁኔታ አግባብነት ያላቸው ሌሎች ሕጎች ስር ያሉትን ድንጋጌዎችን መሰረት አድርጎ ለአንድ የክርክር ጭብጥ መፍትሔ መስጠት ተገቢ መሆኑን ተቀባይነት ያላቸው የህግ አተረጓጎም ደንቦች የሚያስገነዝቡን ጉዳይ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ግን በክልል የቤተሰብ ሕግ የጋብቻ ውጤት የሆነው ንብረት ክፍፍል የሚፈፀምበትን አግባብ በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑና ተጋቢዎች ግራ ቀኙ በሚያደርጉት ስምምነት መሰረት ክፍፍሉ ሊፈጸም ያልቻለ ከመሆኑም በላይ 2ኛ ተጠሪም የመልሶ መግዛት ጥያቄ ያቀረቡ በመሆኑ የአሁኑ አመልካች ንብረቱን መልሰው የመግዛት መብት የሚያገኙበት አግባብ ከፍትሃ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች አንፃር የሚታይበት አግባብ የለም፡፡ጨረታው እንዲከናወን ያደረገው የሥር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ተጋቢዎች መብት አነጻጽሮ በጨረታው ላይ እንዲሳተፉና መልሶ የመግዛት መብት እንደሚኖራቸው ከመነሻውም ግልጽ ትዕዛዝ ያልሰጠበት መሆኑን ክርክሩ ያሳያል፡፡ በዚህ አግባብ በጨረታው ላይ ተወዳድሮ የጋብቻ ውጤት የሆነውን ንብረት የገዛ ተጫራች የጨረታው ውጤት ከታወቀ በኋላ ንብረቱን ለጋራ ባለሃብት መልሶ እንዲሸጥ ማድረግ የባልና ሚስት ንብረት በሐራጅ እንዲሸጥ በሚደረግበት ጊዜ ተወዳዳሪ እንዲቀርብ ያለማድረግ ውጤት የሚያስከትል በመሆኑ ተቀባይነት አግኝቶ ሊተገበር የሚገባው አይደለም፡፡ስለሆነም ጉዳዩ ልዩ ሕግ በሆነው የክልሉ የቤተሰብ ሕግ የሚዳኝ እና በዚህ ሕግ የተቀመጡ የክፍፍል ስርዓቶች ደግሞ የጋራ ባለሃብት መብቱን እንዲጠቀም የሚያስችሉ ቅደም ተከተል ያላቸው በመሆኑ አመልካችና 2ኛ ተጠሪ በዚህ በህጉ በተቀመጡ ቅደም ተከተሎች መጠቀም ሳይችሉ ከቀሩ በኋላ በጨረታው ላይ የመልሶ መግዛት መብት እንዳላቸው ባልተቀመጠበትሁኔታ ሶስተኛ ወገኖች ተወዳድረው አሸናፊው ከተለየ በኋላ ንብረቱን መልሰን እንግዛ ሲሉ ጥያቄው በዚህ ረገድ በተደነገጉት የፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች የሚታይበት አግባብ የሌለ ሁኖ አግኝተናል፡፡ሲጠቃለለም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በጉዳዩ ላይ የሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ እንጂ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡


 

 

 ው ሣ ኔ

 

1. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 58418 መጋቢት 06 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. አመልካች አከራካሪውን ቤት የመልሶ መግዛት መብት የላቸውም ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል፡፡

3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ውጪ እና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 ት ዕ ዛዝ

ነሐሴ 07 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ይጻፍ፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ::

 

 

መ/ተ