104511 court jurisdiction/ jurisdiction of federal courts

የክርክሩ አጠቃላይ ይዘት የዕቁብ ገንዘብ ይከፈለኝ ጥያቄን መሰረት አድርጐ የቀረበ በንግድ ህጉየተመለከቱትን አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎችን አተገባበር ለመመርመር የሚያስችልና ቼክ እንደተራ ማሰረጃነት ሆኖ በክርክር ወቅት በቀረበበት ጊዜ ጉዳዩ የፌደራል ነው ተብሎ የማይወሰድ ሥለመሆኑ፡-

 

አዋጅ ቁጥር 25/1988

የሰ/መ/ቁ 104511

 

መጋቢት 30 ቀን 2007

 

ዳኞች፡- አልማዉ ወሌ ዓሊ መሀመድ

ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡-1. ዳኜ ሀይሉ          ጠበቃ ታየ ቀረበ 2. በከልቻ መኮንን

ተጠሪዎች፡-1. አለምሰገድ ሀብታሙ - የቀረበ የለም 2. ታሪኩ ተክሌ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረዉ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ቡሌ ሆራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካቾች ተከሳሽ ተጠሪዎች ከሳሾች ነበሩ፡፡ ተጠሪዎች ባቀረቡት ክስ 1ኛ አመልካች የዕቁብ ሰብሳቢ 2ኛ ተጠሪ ዳኛ እና ጸሀፊ፤ ተጠሪዎች አባል በመሆን1ኛ ተጠሪን በ01/01/2005 ብር 50000 ደርሶአቸዉ 2ኛ ተጠሪን 08/07/2005 ዓም ብር 60,000 ደርሷቸዉ ከቡሌ ሆራ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክእንዲወስዱ ቼክ ተሰጥቷቸዉ ወደ ባንክ ሄደዉ በቂ  ገንዘብ  የለም በመባላቸዉ አመልካቾች በጋራ እና በተናጥል ይክፈሉንበማለት ጠይቋል፡፡አመልካቾች ባለመቅረባቸዉ በሌሉበት በማየት ተጠሪዎች የእቁቡ አባል መሆናቸዉን በማረጋገጥ በተጠቃሹ ቼክ ባንክ ቤት ሄደዉ ገንዘቡን በማጣታቸዉና አመልካቾችም የዕቁቡ ሀላፊዎች በመሆናቸዉ 110,000.00 ብር ለተጠሪዎች የመክፈል ሀላፊነት አለባቸዉ በማለት ወስኗል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በማከራከር የስር ፍርድ ቤትን ዉሳኔ አጽንቶታል፡፡በመጨረሻም ጉዳዩን ያየዉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ የቼክ ክርክር በመሆኑ በአዋጅ ቁ. 25/1988 መሰረት የማየት ስልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

 

የአመልካቾች አቤቱታም የቀረበዉ ይህንኑ ዉሳኔ ለማስቀየር ነዉ፡፡በመሆኑም አመልካቾች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸዉን ሲገልጹ፡-በስር የቀረበዉ ክስ የነበረዉ ያልተከፈለኝ የእቁብ ገንዘብ እንዲከፈለን፤ የሚል ሆኖ ሳለ ክልሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩ የቼክ ክርክር በመሆኑ የማየት ስልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን የአዋጅ ቁ.25/88 አንቀጽ 5(7) መሰረት መዝጋቱ ባግባቡ አይደለም፤ አመልካቾች የእቁብ ጸሀፊና ሰብሳቢ ናቸዉ በማለት፤ በምስክር ሳይጣራ ክፈሉ መባላችን  ሊታረም ይገባል፤ ቼኩ የተፈረመዉ በስር ተከሳሽ  በነበሩት


አቶ ቦጋለ ግዛዉ ስም ነዉ፤አመልካቾች ከቼኩ ጋር ግንኙነት የለንም፤ አልሰበሰብንም፤  የዕቁቡ ዳኛ መሆኑንና የሚመለከተዉ መሆኑን አዉቆ ጠፍቶ እያለ የአሁን አመልካቾችን ሀላፊ ናችሁ መባላችን ስህተት ነዉ፣ የዕቁብ ደንብ ለዕቁብተኞች ዉል ነዉ ፤እኛ ደግሞ ከዉልም ሆነ ከህግ የመነጨ ግዴታ የለብንም፣ ስለዚህ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት አለባችሁ ተብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ጠይቀዋል፡፡

 

በዚህም መሰረት የአመልካቾች እና ተጠሪዎች ክርክር በቼክ አማካኝነት የተሰጠን የዕቁብ ገንዘብ በቂ ስንቅ ባለመኖሩ ሊከፈለን ባለመቻሉ ይከፈለን በማለት የጠየቁት ዳኝነት የክልሉ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአዋጅ ቁ.25/88 መሰረት ለማየት ስልጣን የለኝም ማለቱን አግባብነት በጭብጥነት በመያዝ ተጠሪዎች ባለመቅረባቸዉ መልስ መስጠት መብታቸዉ ታልፎ በአመልካቾች የቀረበዉን ቅሬታ እና የስር ክርክርን አይተናል፡፡

 

በአጠቃላይ የክርክሩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተጠቀሰዉን ይመስላል፡፡ በመሆኑም የግራቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌ አንጻር መዝገቡን መርምረናል፡፡

 

እንግዲህ ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር የስር ክርክርን እንዳየነዉ ተጠሪዎችባቀረቡት ክስ በአመልካቾች ሰብሳቢነት፤ ጸሀፊነት እና የስር 2ኛ ተከሳሽ ዳኛ በሆኑበት የእቁብ አባል በመሆን እቁብ ደርሷቸዉ ተጠቃሹን ገንዘብ እንዲወስዱ ቼክ ተሰጥቷቸዉ ወደ ቡሌ ሆራ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በመሄድ በቂ ስንቅ ባለመኖሩ መዉሰድ ባለመቻላቸዉ አመልካቾች በቼክ የተጠቀሰዉን ገንዘብ በአንድነትና ነጠላ እንዲከፍሏቸዉ በጠየቁት መሰረት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በማከራከር ዳኝነት ቢሰጡም በመጨረሻ ጉዳዩ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ችሎት ክርክሩ ከቼክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የማየት ስልጣን የለኝም በማለት አዋጅ ቁ 25/88 5(7) በመጥቀስ ቅሬታዉን ሰርዞታል፡፡በዚህም ችሎት ሊታይ የሚገባዉ ነጥብ ሆኖ የተገኘዉ የሰበር ችሎቱ ጉዳዩን ያለማስተናገዱን አግባብነት ነዉ፤ በመሆኑም የግራቀኙ መሰረታዊ ክርክር ዕቁብን ተከትሎ ያዋጡት ገንዘብ የመከፈያ ቀኑ ደርሶ አመልካቾች የእቁቡ አመራር በመሆናቸዉ ተጠቃሹን ገንዘብ የመክፈል ሀላፊነት ስላላቸዉ ቼክ ቆርጠዉ በሰጧቸዉ መሰረት ወደ ባንክ ቤት በመሄድ ገንዘባቸዉን ባለማግኘታቸዉ የዕቁቡን ግንኙነታቸዉን መሰረት አድርጎ እንዲመለስላቸዉ የቀረበ ዳኝነት እንጂ የክርክሩ መሰረት  ቼክ ነዉ በማለት አይደለም፡፡ ቼክ የዕቁብ ገንዘቡ ላለመከፈሉ ማረጋገጫ ሆኖ በተራ ሰነድ ማስረጃነት የቀረበ እንጂ በዋናነት ቼኩ ራሱ በንግድ ሕጉ የተመለከቱትን አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎችን አተገባበር ለመመርመር የሚያስችል ክርክር በሚያስነሳ መልኩ የቀረበ ያለመሆኑን ከክርክሩ ይዘት ለመረዳት የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡ የክርክሩ አጠቃላይ ይዘት የእቁብ ገንዘብን ይከፈለኝ ጥያቄ መሰረት አድርጎ ቼኩን በተራ የሰነድ ማስረጃነት የቀረበበት ሁኖ ሳለ የክልሉ ሰበር ችሎት የግራቀኙን የተጠየቀዉን ዳኝነት እና የክርክሩን አቅጣጫ ባላገናዘበ  መልኩ  ጉዳዩ በአዋጁ ቁ.25/88 ስር የሚታይ ነዉ ሲል የሰበር አቤቱታውን ሳይመለከተው መዝገቡን መዝጋቱ ስነ ስርዓታዊ ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

ባጠቃላይ ክልሉ ከፍተኛ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በቀረበላቸዉ የዳኝነት ጥያቄ አከራክረዉ ዉሳኔ ላይ ቢደርሱም የክልሉ ሰበር ችሎት  የቀረበለትን የዳኝነት ጥያቄ ከወዲሁ  ስልጣኔ  አይደለም ,በማለት መዝገቡን  መዝጋቱ  የክርክሩን  ይዘት  ያላገናዘበ


በመሆኑ ትዕዛዙ መሰረታዊ የሆነ ህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ዉ ሳ ኔ

 

1.  በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁ 08843 በቀን 18/10/2005  ዓ/ም እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ 168299 በቀን 26/9/2006 ዓ/ም የሰጡትን ዉሳኔ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠዉ ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 34(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

 

2. ጉዳዩ በክልሉ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት በክልሉ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የታዬ በመሆኑ የክርክሩ ይዘትም የፌዴራል ጉዳይ ሊባል የማይችል፣የቼክ ጉዳይ ባለመሆኑ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ብለናል፡፡ በመሆኑም የክልሉ ሰበር አጣሪ ችሎት በበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት መሆን ያለመሆኑን በመመርመር ተገቢውን ዳኝነት እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይፃፍ፡፡

 

3. የግራቀኙ የወጪ ኪሳራቸዉን ይቻቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ዉሳኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡