95751 extra-contractual liability/ insurance/ liability beyound insurance policy

አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ በውል የመነጨውን ግዴታውን በወቅቱባለመወጣቱ ለተከሰተው ተጨማሪ ወጪ ተጠያቂ ሊሆን የሚችል ስለመሆኑ

የን/ሕ/ቁ 665

የሰ/መ/ቁ. 95751

መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም


 

 ፍ ርድ

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል የአዳማ ወረዳ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁኑ አመልካች ተከሳሽ ሲሆኑ የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ከሳሽ 2ኛ ተጠሪ ጣልቃ ገብ ነበሩ፡፡ ከሳሽ በቀረቡት ክስ ባለቤቴ ሟች ወንደሰን ከፍያለው በተከሳሽ መኪና የታርጋ ቁጥሩ 323459 በሆነው ላይ በአሽከርካሪነት ተቀጥሮ በወር 1000 እየተከፈለው ሲሰራ በደረሰው የመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 110/1/ ለከሳሽ እና የሟች ልጅ ለሆነው (ዳግም ወንድወሰን) ጭምር በድርጅታችን 60,000 (ስልሣ ሺ) ይከፈለኝ በተጨማሪም የጠበቃ አበል 10% እና ውጪ ኪሣራ ይከፈለኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡ አመልካችም በሰጡት መልስ ተጠቃሹ መኪና የኢንሹራንስ ሽፋን ያለው መሆኑን በመግለፅ ግሎባል ኢንሹራንስ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር በጠየቁት መሠረት ይኸው አካል ወደ ክርክሩ በመግባት እስከ 60,000 ብር ድረስ ሽፋን መስጠቱን በመጥቀስ ከውላቸው ውጭ የመክፈል ኃላፊነት የሌለበት መሆኑን ገልፆ ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን ያየው የወረዳው ፍ/ቤት ግሎባል ኢንሹራንስ በሰጠው ሽፋን ልክ ይክፈል፡፡ በወቅቱ ባለመክፈሉ ምክንያት ለደረሰው ወጪና ኪሣራ እና የጠበቃ አበል ይክፈል በማለት ወሰነ፡፡ የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ለደረሰው ጉዳት ይከፈል የተባለውን 60,000 በማጽናት የጠበቃ አበል፣ የወጪና ክሣራ አስመልክቶ ሊከፍል አይገባም በማለት አሻሽሎ አፀና በመጨረሻም 1ኛ ተጠሪ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ቅሬታዋን በማቅረብ የሰበር ሰሚውም ሽፋን ከተሰጠው በላይ የአሁን 2ኛ ተጠሪ /ግሎባል/ ሊከፍል አይገባም ከሽፋኑ በላይ የሆነውን የአሁን አመልካች ተተክተው ሊከፍሉ ይገባል ሲል አሻሽሎ አፅንቷል፡፡

የአመልካች የሰበር አቤቱታም ይህንኑ የሰበር ውሣኔ ለማሳረም ነው፡፡

አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ 2ኛ ተጠሪ (ግሎባል ኢንሹራንስ) ለደረሰ ጉዳት ተተክቶ ሊከፍልእና በውላችን መሠረት ግዴታውን ለመወጣት ተስማምቷል (ውል ገብቷል) ይሁን እንጂ 2ኛ ተጠሪ በፍርድ ካልተገደድኩ በማለት በወቅቱ ግዴታውን ባለመወጣቱ ለቀረበዉ ክስ ሽፋንከሰጠው በላይ ልገደድ አይገባውም ተብሎ አመልካች የወጪ ኪሣራና የጠበቃ አበል ትክፈል ተብሎ መወሰኑ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል በማለት ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም የግራ ቀኙ ለአመልካች አቤቱታ መልስ በፅሑፍ በማቅረብ ክርክራቸውን አድርገዋል፡፡


በዚሁ መሠረት 2ኛ ተጠሪ ለአመልካች ከሰጠው ሽፋን በላይ የወጪ ኪሣራ እና የጠበቃ አበል ሊከፍል አይገባም ተብሎ አመልካች እንዲከፍሉ የመወሰኑን አግባብነት በጭብጥነት ተይዞ ቀርቧል፡፡

ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካለው ህግ አኳያ መርምረናል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰውን ይመስላል፡፡ እንግዲህ ለጉዳዩ መነሻ የሆነው የሥር ከሳሽ የአሁን 1ኛ ተጠሪ የሆኑት በባለቤታቸው ላይ በደረሰው የሞት አደጋ ምክንያት የአዋጅ 377/96 አንቀጽ 110(2) ሀ,ለ መሠረት 60,000 ብር እንድከፍላቸው በአሁኑ አመልካች ላይ ክስ በማቅረባቸው ምክንያት የአሁን 2ኛ ተጠሪ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ ቁ. 43 መሠረት ወደ ክርክሩ እንድገባ ተደርጐ ለደንበኛው በሰጠው የኢንሹራንስ ሽፋን መሠረት 60,00ዐ ብር እና የጠበቃ አበል 10% እና የወጪ ኪሣራ 1000 ብር እንዲከፍል በመወሰኑና በየደረጃው ባሉት የክልሉ ፍ/ቤቶች እያዩት የክልሉ ሰበር ሰሚ ደረሶ ግሎባል ኢንሹራንስ ከሰጠው የኢንሹራንስ ሽፋን በላይ የጠበቃ እና የወጪ ኪሣራ ልከፍል አይገባም የአሁን አመልካች ኢንሹራንስ ከከፈለው በላይ ያለውን 8000 ብር ይክፈሉ በመባሉ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የክልሉ ሰበር አመልካች ሊከፍሉ ይገባል ሲል የሠጠው የአሁን 2ኛ ተጠሪ (ግሎባል ኢንሹራንስ የንግድ ህጉን አንቀጽ 665(2) መሠረት ግዴታው ከውላችን ላይ ካለው የሽፋን መጠን ልበልጥ አይገባውም የሚለውን ክርክር በመቀበል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እንግዲህ የግራ ቀኙ መብትና ግዴታ የሚመነጨው በመሀከላቸው ከተቋቋመው ውል መሆኑ ይህ ችሎትም የሚቀበለው ጉዳይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በተያዘው ጉዳይ የአመልካች ደንበኛ (ግሎባል ኢንሹራንስ) በአመልካች መኪና በደረሰው የሞት አደጋ በወቅቱ አግባብነት ያለውን ክፍያ ባለመፈፀሙ ምክንያት የአሁን 1ኛ ተጠሪ የመኪናውን ባለቤት የሆኑትን አመልካች ለመክሰስ ተገደዋል፡፡ ስለሆነም ለተለያዩ (ላልታሰበ) ወጪ መዳረጋቸው ያልተካደና የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነው፡፡ በመሆኑም ግሎባል ኢንሹራንስ ምንም እንኳ የሰጠው የኢንሹራንስ ሽፋን የተገለፀ ቢሆንም ከውል የመነጨውን ግዴታውን በወቅቱ ባለመወጣቱ ለተከሰተው ተጨማሪ ወጪ የአሁን አመልካች የሚቀጡበት የህግ አግባብ አይኖርም፡፡ በዚህ ሁሉ ምከንያት የሞት ካሣውን የገንዘብ መጠን 60,000 ብር ላይ የጠበቃ እና የወጪ ኪሣራውን ግሎባል ኢንሹራንስ ሊከፍል የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ባጠቃላይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሥር ውሳኔዎችን በማሻሻል ከ60,000 ብር በላይ የተጠየቀውን ተጨማሪ ወጪ አመልካች ሊከፍሉ ይገባል ማለቱ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ተከታዩን ውሣኔ ሰጥተናል፡፡

 ው ሳኔ

1. የአዳማ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ.63103 በቀን 27/3/05 የልዩ ዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ.15437 በ29/08/05 እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 164154 በቀን 23/03/2006 የሰጡት ውሣኔዎች ተሻሽሎ ፀንቷል፡፡

2. የጠበቃ አበል እና የወጪ ኪሣራን ግሎባል ኢንሹራንስ /8000/ብር ለ 1ኛ ተጠሪ ሊከፍል ይገባል ብለናል፡፡

የሰበሩን ክርክር አስመልክቶ ግራ ቀኙ የወጪ ኪሣራ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡