100079 criminal law/ criminal responsibility of artificial persons

የህግ ሰውነት ያለው የንግድ ድርጅት በህግ በግልፅ በተደነገገ ጊዜ በዋና ወንጀል አድራጊነት ፣በአነሳሽነት ወይም  በአባሪነት ወንጀል ሊቀጣ የሚችል መሆኑ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች ህጉ በወንጀል የሚጠየቁ እንደሆነ በልዩ ሁኔታና በግልፅ ባልደነገገባቸው ወንጀሎች የወንጀል ተጠያቂነት እንደማይኖርባቸው በወንጀል ህጉ የተደነገገ ስለመሆኑ፡-

 

 

ህጋዊ ህልውና ያለው ድርጅት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣው በኃላፊዎቹ ወይም ከሰራተኞቹ አንዱ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የድርጅቱን ጥቅም በህገ ወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ወይም የድርጅቱን ህጋዊ ግዴታ በመጣስ ወይም ድርጅቱን በመሳሪያነት አለአግባብ በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት በአነሳሽነትና  በአባሪነት  ወንጀል  ሲያደርግ  መሆኑ  በወንጀል ህጉ በግልፅ የተደነገገ መርህ ስለመሆኑ።-

 

 

 

አንድ የንግድ ድርጅት የወንጀል ተግባር ከፈፀመና ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ከተረጋገጠ ለወንጀሉ አድራጎት ኃላፊ የሚሆኑት ሠራተኞችና ኃላፊዎች በወንጀል ከመጠየቅ ነፃ የማይሆኑ ሥለመሆኑ፡-

 

 

የወንጀል ህግ አንቀፅ 34

የሰ/መ/ቁ 100079

 

መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ዕቁባይ በርሀ ገ/እግዚአብሔር  - ጠበቃ ደሳለኝ መስፍን ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ገቢዎች ጉምሩክ ባለሥልጣን - ዐ/ህግ ወንድዬ ብርሃኑ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 176025 ታህሳስ 19/2005 ዓ/ም የሰጠው ፍርድና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመዝገብ ቁጥር 131320 ጥር 21 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታርምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው ጉዳዩ ተጠሪ አመልካች የአንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ ለግብር ስብሳቢው መሥሪያ ቤት አሳሳች ማስረጃ የማቅረብና ተጨማሪ እሴት  ታክስ የማሳወቅና የመክፈል ኃላፊነቱን ባለመወጠት ወንጀል ፈፅሟል በማለት ያቀረበውን ክስና ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ ተጠሪ በሜጋ ኪነ ጥበብ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና በአመልካች ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ ነው፡፡ ተጠሪ ባቀረበው የወንጀል ክስ

· በሥር አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ሜጋ ኪነ ጥበብ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀፅ 96 እና የወንጀል ህጉን አንቀፅ 34/1/ የተመለከተውን በመተላለፍ ከሀምሌ 1996 ዓ/ም እስከ 2002 ዓ/ም ባደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ለመንግስት ገቢ ማድረግ የነበረበት ብር 39,801.32 /ሰላሣ  ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ አንድ ብር ከሰላሣ ሁለት ሳንቲም/ በማሣወቅ መክፈል ሲገባው ግብሩን ያላሳወቀ በመሆኑ ወንጀል ፈፅሟል ሁለተኛው ተከሳሽ (አመልካችም) የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀፅ 86 እና አንቀፅ 102(1) በመተላለፍ የንግድ ድርጅቱ ሥራ-አስኪያጅ ሆኖ የንግድ ድርጅቱን ገቢ ባለማሣወቁ ወንጀል ፈፅሟል፡፡

· አንደኛ ተከሳሽ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286 /1994 አንቀፅ 97 ንዑስ አንቀፅ 3(ሀ) የተመለከተውን በመተላለፍ 1997 ዓ/ም ባከናወነው የንግድ እንቅስቃሴ ትርፍ አግኝቶ እያለ፤ ወጭውን ከፍ አድርጎ በማቅረብ ኪሣራ እንደደረሰበት አድርጎ በማሳወቁ፤ ለግብር


ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት አሳሳች ማስረጃ የማቅረብ ወንጀል ፈፅሟል ሁለተኛው ተከሳሽ (አመልካች) የአንደኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ሆኖ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀፅ 96 ንዑስ አንቀጽ 3(ሀ) አንቀፅ 102(1) የተመለከተውን በመተላለፍ አሳሳች ማስረጃ የማቅረብ ወንጀል ፈፅሟል፡፡

· አንደኛ ተከሳሽ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285 /94 አንቀፅ 49 እና በወንጀል ህግ አንቀፅ 34(ሀ) የተመለከተውን በመተለለፍ ከ1996 ዓ/ም እስከ 2002 ዓ.ም ባደረገው የንግድ እንቅስቃሴ የሰበሰበውን ብር 426.229.03 /አራት መቶ ሃያ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ዘጠኝ ብር ከዜሮ ሶስት ሣንቲም) ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግስት አሳውቆ ባለመክፈሉ ወንጀል ፈፅሟል፡፡ሁለተኛ ተከሳሽ (አመልካች) የአንደኛ ተከሳሽ ሥራ-አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ አንደኛ ተከሳሽ የሰብሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግስት አሳውቆ እንዲከፈል ባለማድረጉ በአዋጅ ቁጥር 285/1994 ዓንቀፅ 49 እና 56(1) በመተላለፍ ወንጀል ፈፅሟል በማለት ክስ አቅርቧል፡፡

2 አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ቀርቦ ወንጀሉን አልፈፀምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት የቀረበበትን ክስ ክዶ ተከራክሯል፡፡ ተጠሪ የአንደኛ ተከሳሽ የንግድ ፈቃድ፤ ሜጋ ኪነጥበብ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የመመሥረቻ ፅሑፍና መተዳደሪያ ደንብ የድርጅቱ ገቢ ኦዲት የተሰራበት ሪፖርትና የትርፍ ማስታወቂያ፣ ደረሰኝ የተተመበትን ሰነድና የሰው ምስክሮችን በማስረጃነት አቅርቧል፡፡ ተጠሪ ያቀረባቸው ሁለት ምስክሮች አንደኛ ተከሳሽ የመፍረስ ጥያቄ በማቅረቡ ከሳሽ መሥሪያ ቤት የድርጅቱን ሒሳብ ኦዲት እንዲያደርጉ መድቧቸው ሒሳቡን ኦዲት ያደረጉ መሆኑን ሂሳቡን  ኦዲት ያደረጉት የአንደኛ ተከሳሽ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሁለተኛ ተከሳሽ ያቀረበውን የሂሳብ ሰነድና አንደኛ ተከሳሽ ለከሳሽ መሥሪያ ቤት ሲያቀርብ የነበረውን  የሂሳብ ሪፖርት መሠረት በማድረግ እንደሆነ ገልፀው 1997 ዓ/ም አንደኛ ተከሳሽ ብር 15,748 /አስራ አምስት ሺህ ሰባት መቶ አርባ ስምንት ብር/ ኪሳራ የደረሰበት  መሆኑን  ለከሳሽ አሳውቋል፡፡ ሆኖም 1997 ዓ/ም አንደኛ ተከሳሽ ብር 132,673.06/አንድ መቶ ስላሣ ሁለት ሺ ስድስት መቶ ሰባ ሶስት ብር ከዜሮ ስድስት ሣንቲም/ አግኝቶ የነበረ መሆኑንና 1997 ዓ/ም አንደኛ ተከሳሽ 39.801 /ስላሳ ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ አንድ ብር) የንግድ ትርፍ ገቢ ግብር መክፈል የነበረበት መሆኑን በማረጋገጥ ወስነናል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ኪሣራ ደርሶብኛል በማለት ሪፖርት ያደረገው የድርጅቱ ሠራተኞች ባልሆኑ ሰዎች የከፈለው ደመወዝ የስልክ ወጭና የሌላ ድርጅት ንብረት የሆኑ መኪኖች የተሞላ ነዳጅ በወጭነት በማቅረብ ነው፡፡ ይህም የገቢ ግብር አዋጅንና አዋጁን ለማስፈፀም የወጣውን መመሪያ መሠረት ያላደረገ በመሆኑ በወጭነት አልያዝነውም፡፡ እኛ ሂሳብ ስንሠራ ወድቅ አድርገነዋል፡፡

3 ከላይ ከተገለፀው በተጨማሪ ተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ አንደኛ ተከሳሽ ለከሳሽ ባሣወቀውና አንደኛ ተከሳሽ ባከናወነው ግብይት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ መካከል ልዩነት መኖሩን አንደኛ ተከሳሽ ብር 429,172 /አራት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ብር/ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግስት አሳውቆ መክፈል ሲገባው፤ ይህንን የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግስት ያልከፈለ መሆኑን ባከናወኑት የኦዲት ሥራ ማረጋገጣቸውን ለሥር ፍርድ ቤት ያስረዱ መሆኑን በውሣኔው አስፍሮታል፡፡ ሶስተኛው የተጠሪ ምስክር አንደኛ ተከሳሽ የሂሳብ ሠራተኛ መሆኑን ገልፆ ሁለተኛው ተከሳሽ የአንደኛ ተከሳሽ ሥራ አስኪያጂ በመሆን 1997 ዓ/ም እስከ 2002 ዓ/ም የሠራ መሆኑንና 1ኛ ተከሳሽ 1998


ዓ/ም ከሜጋ ማስታወቂያ ጋር ሲዋሀድም 2ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ሆኖ የሰራ መሆኑን እንደመሰከረ የሥር ፍርድ ቤት በውሳኔው ፅፎታል፡፡

4   ሁለተኛ ተከሳሽ /አመልካች/ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሂሳብ ሠራተኞች  በየወሩ    ለከሳሽ

/ተጠሪ/ ሪፖርት ያደርጉ የነበረ መሆኑንና ገቢን አለማሳወቅና አሳሳች ማስረጃ ማቅረብ የተባለውም ገቢን አለማሣወቅና አሳሳች ማስረጃ የማቅረብ ወንጀል አልፈፀምኩም በኦዲት ተገኘ የተባለው የሂሳብ ልዩነት የተፈጠረው አንደኛ ተከሳሽና ሜጋ ማስታወቂያ 1998 ዓ/ም ጀምሮ በአንድ ሥራአስኪያጅ እየተመሩ አንድ ላይ ስራ ሲሳሩ የነበረ በመሆኑና በሜጋ ማስታወቂያ ሠረተኞች የስልክ ወጭና የሜጋ ማስታወቂያ መኪኖች ነዳጅ የወጣ ውጭ በመኖሩ ምክንያት ነው በማለት አምስት የመከላከያ ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ አንደኛው የአመልካች የመከላከያ ምስክር የአንደኛ ተከሳሽ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆኖ ሲሳራ ከፋይናንስ ክፍል ይሰጠው የነበረውን የተጨማሪ እሴት ተክስ ሪፖርት ለከሳሽ /ለተጠሪ/ ሲያደርስ እንደነበረና አንደኛ ተከሳሽ 1998 ጀምሮ ከሜጋ ማስታወቂያ ጋር ሲሰራ የሜጋ ማስታወቂያና መኪኖች በትውስት በመውሰድ ነዳጅ በመሙለት ሲጠቀም እንደነበረ የመሰከረ መሆኑን ሁለተኛ መከላከያ ምስክር የሒሳብ ባለሙያ መሆናቸውን ገልፀው ለአንደኛ ተከሳሽ የሂሳብ ሠራተኞች በ1996 ዓ/ም የሂሳብ አያያዝ ሥልጠና የሰጡ መሆኑን እንደመሰከረ፣ ሶስተኛ መከላከያ ምስክር የአንደኛ ተከሳሽ የሂሳብ ሠራተኛ እንደነበር 1997 ዓ/ም ጀምሮ የሽያጭ ወጭ ደረሰኞችን በመቀበል በየወሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሪፖርት ያዘጋጅ እንደነበር እንደመሰከሩ፤ አራተኛ የመከላከያ ምስክር የአንደኛ ተከሳሽ ሹፌር የነበረ መሆኑን ገልጾ፣ 1ኛ ተከሳሽ ይጠቀምበት የነበረውን ላንድክሩዘር ኮድ ሁለት የሆነ መኪና ያሽከረክር እንደነበርና ወጭውንም የሚሸፍነው አንደኛ ተከሳሽ እንደነበር እንደመሰከረ፣ 5ኛ የመከላከያ ምስክር የፋሲል ኮንሰልት ኃላ/የተ/የግል ማህበር የሂሳብ ሰራተኛ በመሆን የአንደኛ ተከሳሽ የሁለት አመት 1996ዓ.ም እና 1997ዓ.ም ሂሳብ የሰራ መሆኑንና የሂሳብ ሰነድ ወጭና ገቢ አያያዙ ጥሩ ሆኖ ማግኘታቸውንና ተከሳሽ ድርጅትም በኪሳራ ይንቀሳቀስ እንደነበር ያስረዱ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት በውሳኔው አስፍሮታል፡፡

5 የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽና ሜጋ ማስታወቂያ አግባብነት ባለው ሕግ መሰረት ያልተቀላቀለ መሆኑ፣ አንደኛ ተከሳሽ በሜጋ ማስታወቂያ ሰራተኞች የከፈለው ደመወዝና የስልክ ወጭ የአንደኛ ተከሳሽ ሕጋዊ ወጭ ተደርጎ ሊያዝ የማይችል መሆኑን የተሽከርካሪ ትውስት የተባለውም ተቀባይነት ያለውን የሂሳብ አሰራር ያልተከተለ በመሆኑ ተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ፣ በየወሩ ሪፖርት ይደረግ የነበረ መሆኑን በመከላከያ ማስረጃ ከማስረዳት ውጭ አንደኛ ተከሳሽ የሰበሰበውን ብር 426,229.03 ተጨማሪ እሴት ታክስ ለከሳሽ መስሪያ ቤት ያላሳወቀና ገቢ ያላደረገ መሆኑን በማረጋገጥ በከሳሽ (ተጠሪ) በኩል ያቀረበውን ማስረጃ የሚያስተባብል ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ስለዚህ አንደኛ ተከሳሽ 1997ዓ.ም ትክክለኛ ገቢውን ባለማሳወቁና ኪሳራ እንደደረሰበት ሪፖርት በማድረጉ እንደዚሁም አንደኛ ተከሳሽ ከ1996ዓ.ም እስከ 2002ዓ.ም የሰበሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ሙሉ ለሙሉ ለተጠሪ (ለከሳሽ) ባለማሳቁና ገንዘቡንም ገቢ ባለማድረጉ ሁለተኛ ተከሳሽ  በስራ አስኪያጅነቱ በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 96 እና አንቀጽ 97 ንዑስ አንቀጽ 3(ሀ) የተመለከተውን በመተላለፍና በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት የቅጣት ውሳኔ በመወሰንና በመገደብ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

6 በዚህ ውሳኔ አመልካችና ተጠሪ ቅር በመሰኘት አመልካች በመዝገብ ቁጥር 131320 ተጠሪ በመዝገብ ቁጥር 131160 ያቀረቡትን ይግባኝ ቅሬታ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት


በመዝገብ ቁጥር 131320 በማጣመር፣ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ በማጽናት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

7 አመልካች የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡትን የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማስለወጥ ሚያዚያ  17 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የወንጀል ክስ ከመመስረቱ በፊት የንግድ ድርጅት ስራ አስኪያጅነት መልቀቄን ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ እኔ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በወንጀል ጥፋተኛ ልባል ከሚገባው በመጀመሪያ በስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው የንግድ ድርጅት ተጠርቶ፣ ቀርቦ ተከራክሮ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የሌለ መሆኑን ተጠሪ የወንጀል ክስ ሲመሰርት ያውቃል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የፈረሰና ህጋዊ ህልውና የሌለው በመሆኑ በወንጀል ሊከሰስና ጥፋተኛ ተብሎ ሊቀጣ አይችልም፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በወንጀል ሊጠየቅ የማይችል ከሆነ ስራ አስኪያጅ በወንጀል ሊጠየቅ አይችልም ፡፡ የአንደኛ ተከሳሽ ሂሳብ ኦዲት የተደረገው በ2003 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም አመልካች ድርጅቱን ከለቀቀ ከአስር ወር በኋላ ነው፡፡ ሜጋ ማስታወቂያና ሜጋ ኪነጥበባት፣ በኋላ የተቀላቀሉ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ስራ አስኪያጅ የነበረው አመልካች በተጨባጭ ለስራ ያወጣው ወጭ ውድቅ ተደርጎ አሳሳች ማስረጃ አቅርቧል፣ ተጨማሪ እሴት አሳውቆ ገቢ አላደረገም ተብሎ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

8 ሰኔ 27 ቀን 2006ዓ.ም በተጻፈ መልስ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት በራሱ ወንጀል የመፈጸም ሃሳብ የሚፈጥር ባለመሆኑ፣ ድርጅቱ ወንጀል የሚፈጽመው ከድርጅቱ ኃላፊዎች ወይም ሰራተኞች አንዱ የድርጅቱን ህጋዊ ግዴታ ባለመወጣት ወይም የድርጅቱን ጥቅም በህገ ወጥ መንገድ ለማራመድ ተንቀሳቅሰው በተገኙ ጊዜ ነው፡፡ ከስር ሁለተኛ ተከሳሽ የነበሩት አመልካች አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ መሆናቸው በወንጀል ሕጉ የተቀመጠውን መርህ የተከተለ ነው፡፡ ከስር አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት በህጋዊ መንገድ የፈረሰ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የለም፡፡ ተጠሪ የወንጀል ክሱንና መጥሪያውን ለማድረስ ጥረት አድርጎ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በጋዜጣ ጥሪ አድርጎለት አልቀረበም ከዚህ አንጻር የስር ፍርድ ቤት በጋዜጣ አለመጥራት እንደ ስነ- ስርዐት ስህተት ከሚታይ በስተቀር በአመልካች ላይ የተሰጠውን ውሳኔ የሚያስለውጥ አይደለም፡፡ የድርጅቱም ሂሳብ በአግባቡ የተጣራና ወንጀሉ የተፈጸመ መሆኑ ተረጋግጦ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ የአመልካች፣ የሰበር አቤቱታ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ ሁለተኛ ተከሳሽ (አመልካች) በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ የሚረጋገጠው አንደኛው  ተከሳሽ በአግባቡ ተጠርቶ፣ ተከራክሮ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ሲፈረድበት ነው፡፡ ይህ ሳይደረግ ሁለተኛው ተከሳሽ ጥፋተኛ ተብሎ ሊፈረድበት አይችልም፡፡ የስር ፍርድ ቤት ድርጅቱንና ሁለተኛ ተከሳሽን ጥፋተኛ ናቸው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ ተገቢ ያልሆነና የወንጀል ህግን መሰረታዊ መርህ የሚጻረር ውሳኔ ነው፡፡ ምክንያቱም በስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽን በመጥሪያም ይሁን በጋዜጣ አልተጠራም፣  አልቀረበም በሌለበት ይታያል ተብሎ አልተያዘም፡፡ 1ኛ ተከሳሽ ያፈረሰ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ ሁለተኛ ተከሳሽ የለብኝም የሚልና ሌሎች በሰበር አቤቱታው ያነሳቸውን መከራከሪያዎች የሚያጠናክር ክርክር አቅርቧል፡፡

9 ከስር የክርክሩ አመጣጥና ግራ ቀኙ በዚህ ሰበር ችሎት ያቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች የሜጋ ኪነጥበባት ኃላፊነቱ


የተወሰነ የግል ማሕበር ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ፣ የንግድ ትርፍ ገቢ በትክክል አለማሳወቅና የንግድ ትርፍ ገቢ ግብር አለመክፈል፣ አሳሳች ማስረጃ የማቅረብና የንግድ ድርጅቱ በፈጸማቸው ግብይቶች ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሰበሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ በተሟላ ሁኔታ አለማሳወቅና ገቢ ያለማድረግ ወንጀል ፈጽሟል በማለት የሰጡት የጥፋተኝነት ውሳኔ በሕግ አግባብ የተሰጠ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

10 ጉዳዩን እንደመረመርነው የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ሜጋ ኪነጥበባት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር በንግድ ህግ አንቀጽ 542 እና አንቀጽ 543 መሰረት ያልፈረሰ ወይም የንግድ ህጉ ከአንቀጽ 544 እስከ አንቀጽ 554 በተደነገጉት ድንጋጌዎች መሰረት ከሌላ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር በተለይም ከሜጋ ማስታወቂያ ጋር በሕግ የተደነገገውን ስርዓት በማሟላት ያልተቀላቀለ መሆኑ የስር ፍርድ ቤት በውሳኔው በማረጋገጥ ውሳኔ ሰጥቷል የስር አንደኛ ተከሳሽ በህግ አግባብ ካልፈረሰ ወይም ከሌላ የንግድ ድርጅት ጋር አለመቀላቀሉ ካልተረጋገጠ፣ ህጋዊ ህልውና ያለው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ እንደሆነ ከህጉ ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ የስር አንደኛ  ተከሳሽ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በመሆኑ ከመፍረሱ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር ከመቀላቀሉ በፊት ይከናወን ያላቸው ተግባራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ተግባራት መካከል የማኃበሩ ሒሳብ የማጣራት ስራ ነው፡፡ ተጠሪ የአንደኛ ተከሳሽ ሂሳብ ኦዲት ያደረገው አንደኛ ተከሳሽ የመፍረስ ጥያቄ በማቅረቡ እንደሆነ፣ ተጠሪ ያቀረባቸው ምስክሮችና የአንደኛ ተከሳሽን ሒሳብ ያጣሩት ባለሙያዎች የገለጹ መሆኑን በስር ፍርድ ቤት በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ይህም የአንደኛ ተከሳሽ ሒሳብ በተጣራበት ጊዜ አንደኛ ተከሳሽ የመፍረስ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም በሕግ አግባብ ሒሳቡ ተጣርቶ የመፍረስ ውሳኔ ያልተሰጠና ህጋዊ ሕልውና ያለው ድርጅት የነበረ መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣናቸው ያረጋገጡት በመሆኑ አመልካች አንደኛ ተከሳሽ ሕጋዊ ሕልውናው የከተመ ወይም የፈረሰ ድርጅት ነው በማለት ያቀረበው ክርክር የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡

11 .አንደኛ ተከሳሽ የሕግ ሰውነት ያለው የንግድ ድርጅት ነው፡፡ የሕግ ሰውነት ያለው የንግድ ድርጅት በሕግ በግልጽ በተደነገገ ጊዜ በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ወንጀል ሊቀጣ የሚችል መሆኑ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች ሕጉ በወንጀል የሚጠየቁ እንደሆነ በልዩ ሁኔታና በግልጽ ባልደነገገባቸው ወንጀሎች የወንጀል ተጠያቂነት እንደማይኖርባቸው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 1 በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ማንኛውም የንግድ ድርጅት በዓመት ውስጥ ያገኘው ትክክለኛ ትርፍ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት የማሳወቅ ግብር የመክፈል ኃላፊነት እንዳለበትና ይህንን ኃላፊነቱን በመጣስ በተለይም አሳሳች የሆኑ ማስረጃዎችን በማቅረብ ግብር የማጭበርበር ተግባር ከፈጸመ በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ከአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 96 እና አንቀጽ 97(1) ድንጋጌዎች ተደንግጓል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በ1997ዓ.ም ብር 132673.06 /አንድ መቶ ሰላሳ ሁለት ስድስት መቶ ሰባ ሶስት ብር ከዜሮ ስድስት ሳንቲም/ ከንግድ ስራ ትርፍ አግኝቶ እንደነበር ነገር ግን አንደኛ ተከሳሽ በሕግ አግባብ ላልተቀላቀለው ሜጋ ማስታወቂያ ሰራተኞች የከፈለውን ደመወዝ በስልክ ክፍያና የነዳጅ ወጭ አንደኛ ተከሳሽ ለእራሱ ስራ ያወጣው ህጋዊ ወጭ አስመስሎ በማቅረብና 1997ዓ.ም ከንግድ ስራ ትርፍ እንዳላገኘና ኪሳራ እንደደረሰበት ለተጠሪ ያሳወቀ መሆኑ ተጠሪ ባቀረበው የጽሑፍና የሰው ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ  በተጨማሪ አንደኛ  ተከሳሽከ1996  እስከ  2002  ዓ.ም ባከናወነው


ግብይት ብር 426299.03 /አራት መቶ ሃያ ስድስት ሺ ሁለት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ብር ከዜሮ ሶስት ሳንቲም/ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቦ ለተጠሪ ይህንን ተጨማሪ እሴት ታክስ ገንዘብ የሰበሰበ መሆኑን እንዳላሳወቀና ገንዘቡንም ገቢ እንዳላደረገ ተጠሪ ባቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የተረጋገጠ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና  ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ሕግን በመጣስ የሰበሰበውን ታክስ ያላሳወቀ ወይም የሚፈለግበትን ታክስ ያልከፈለ እስከ አምስት አመት ሊቀጣ የሚችል መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 የተደነገገ ሲሆን የንግድ ድርጅት ይህንን አዋጅ በመተላለፍ ለሚፈጸመው ጥፋት የወንጀል ተጠያቂነት  የሚኖርበት ስለመሆኑ ከአዋጁ ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡

12 .በስር አንደኛ ተከሳሽ የነበረው የንግድ ድርጅት ለሌላ ድርጅት ሠራተኞች  ሜጋ ማስታወቂያ ሠራተኞች የከፈለውን ደመወዝና የስልክ ወጭ የንግድ ተግባሩን ሲያከናውን ያወጣው ወጭ መሆኑን በሚገልጽ መንገድ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ሪፖርት በማቅረብ 1997ዓ.ም ትርፍ አግኝቶና ካገኘውም ትርፍ 39,801.32 የንግድ ስራ ትርፍ ገቢ ግብር መክፈል ሲገባው ኪሳራ እንደደረሰበት አድርጎ ሪፖርት ማቅረቡና ይህም ሪፖርት ለሌላ ንግድ ድርጅት ወጭ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመሸፈን የወጣ ወጭ እንደ ሕጋዊ ወጭ በማቅረብ የተፈጸመ መሆኑ በኦዲት የተረጋገጠ መሆኑን እንደዚሁም አንደኛ ተከሳሽ ከ1996 እስከ 2002 ዓ.ም የሰበሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ለተጠሪ ያላሳወቀና ገንዘቡንም ገቢ ያላደገረገ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

13 .አመልካች 1997ዓ.ም አንደኛ ተከሳሽ ትርፍ አግኝቶ እያለ ትርፍ እንዳላገኘና ኪሳራ እንደደረሰበት ሪፖርት በማድረግ በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 96 እና አንቀጽ  97 (1) (ሀ) የተመለከቱትን የወንጀል ድርጊቶች ሲፈጽም የአንደኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ የነበረ መሆኑ በተጣራ ማስረጃ ብቻ ሳይሆን አመልካች ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች የተረጋገጠ መሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ያሳያል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ከላይ የጠቀስናቸውን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ወንጀል የፈጸመ መሆኑ ከተረጋገጠ ስራ አስኪያጁ በወንጀሉ ተጠያቂ እንደሚሆን በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል፡፡ እንደዚሁም አንደኛ ተከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 የተመለከተውን በመተላለፍ ከ1996 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ባከናወነው ግብይት የሰበሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ለተጠሪ ያላሳወቀና ገንዘቡንም ገቢ ያላደረገ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 ድንጋጌ የሚጥስ የወንጀል ተግባር በፈጸመበት ጊዜ አመልካች የአንደኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ እንደነበር በተጣራ ማስረጃ ብቻ ሳይሆን አመልካች ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ተረጋግጧል፡፡ አንደኛ ተጠሪ ወንጀሉን የፈጸመው ከ1996ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ አመልካች የአንደኛ ተከሳሽ ሂሳብ በተጠሪ በሚጣራበት 2003ዓ.ም እኔ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አልነበርኩም በማለት የሚያቀርበው ክርክር አንደኛ ተከሳሽ በስራ አስኪያጅነት በሚሰራበት ወቅት ለተፈጸመው ወንጀል በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 56 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ተጠያቂ መሆኑን የሚያስቀር ባለመሆኑ የአመልካች ክርክር ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡

14 .የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ ከክርክሩ ውጭ እንዲሆን አላደረገም፡፡ የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ እና በአመልካች ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ እና ማስረጃ ከሰማና የአመልካችን መከላከያ ከመረመረ በኋላ ‘’ስለሆነም ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የሚያስተባብል ማስረጃ ያላቀረቡ በመሆኑ በ1997ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ ባከናወነው የንግድ


እንቅስቃሴ ገቢን አሳውቆ ባለመክፈልና ተከሳሾች አሳሳች መረጃ በመስጠትና ኪሳራ ሪፖርት በማድረግና ከ1996ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የተሰበሰበውንየተጨማሪ እሴት ታክስ የሰበሰቡትን በሙሉ ሪፖርት ባለማድረጋቸው ሁለተኛው ተከሳሽ (አመልካች) በስራ አስኪያጅነታቸው አንደኛ ተከሳሽ ለፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ በመሆናቸው ተከሳሾች በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 96 እና አንቀጽ 97 ንዑስ አንቀጽ 3 (ሀ) አንደዚሁም በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ጥፋተኛ ናቸው’’ በማለት ውሳኔ እንደሰጠ ከስር ፍርድ ቤት ከሰጠው ፍርድ በስምንተኛው ገጽ በአራተኛው ፓራግራፍ በግልጽ ሰፍሯል፡፡

15 ይህም የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ ከላይ በገለጽናቸው አዋጆች የተመለከቱትን የሕግ ድንጋጌዎችና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገውን በመተላለፍ ወንጀል የፈጸመ መሆኑን በማረጋገጥ የጥፋተኛነት ውሳኔ የሰጠ መሆኑንና  አንደኛ ተከሳሽ ወንጀሉን በሚፈጽምበት ጊዜ ሁለተኛ ተከሳሽ አመልካች የአንደኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 102 እና የአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 56 ድንጋጌዎች መሰረት ሜጋ ኪነጥበባት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በስራ አስኪያጅነት ሲመራ በነበረበት ጊዜ በድርጅቱ ለተፈጸመው ወንጀል በኃላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን በማረጋገጥ የተሰጠ ውሳኔ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ  አመልካች  የንግድ ድርጅቱ ወንጀሉን የፈጸመ መሆኑ ሳይረጋገጥ አና ለወንጀሉ ኃላፊ ተብያለሁ በማለት የሚያቀርበው ክርክር በመዝገቡ ያለውን እውነታ የሚያንጸባርቅ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ከአመልካች ጋር ለተፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ መሆኑን የስር  ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 176025 ታህሳስ 19 ቀን 2004ዓ.ም በሰጠው ፍርድ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡

16 አመልካች የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽን በአግባቡ ሳይጠራ አንደኛ ተከሳሽ በክርክሩ ተካፋይ ሳይሆን ወይም ጉዳዩ አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት  እንዲታይ  ትእዛዝ ሳይሰጥ የወንጀል ክሱን ሰምቶ የወሰነ መሆኑ የሕግ ስህተት ያለበት መሆኑን መከራከሪያ አድርጎ አቅርቧል፡፡ አመልካች ከ 2003ዓ.ም ጀምሮ የአንደኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ እንዳልሆነና አንደኛ ተከሳሽንም ወክሎ ክርክር ለማቅረብ እንደማይችል በስር ፍርድ ቤት የገለጸ መሆኑን ግራ ቀኙ ካቀረቡት ክርክር ተገንዝበናል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የወንጀል ጉዳይ የታየው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ አንቀጽ 162 አንቀጽ 167 እና ሌሎች ድንጋጌዎች ከሚደነግጉት ውጭ ነው ብሎ ካለ የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት አይቶ የሰጠው ፍርድ እንዲነሳለት ከሚያመለክት በስተቀር አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት ታይቶ መወሰኑን አመልካች መከራከሪያ አድርጎ ሊያቀርብ የሚችል አይደለም፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በመወከልም አንደኛ ተከሳሽ በሌለበት ታይቶ የተሰጠው ፍርድ እንዲነሳ ለመከራከር የሚያስችለው ውክልና ወይም ስልጣን የለውም ስልጣንም ቢኖረው ክርክሩ መቅረብ የሚገባው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ሕግ ከአንቀጽ 197 እስከ አንቀጽ 102 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ መሆን የሚገባው በመሆኑ አመልካች ያቀረበው ክርክር የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡

17 አንደኛ ተከሳሽ አግባብነት ባላቸው የንግድ ህግ ድንጋጌዎች መሰረት መፍረሱ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር መቀላቀሉን የሚያሳይ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ይህም አንደኛ ተከሳሽ ሕጋዊ ህልውና ያለው ድርጅት መሆኑን ያሳያል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በህግ አግባብ ሳይፈርስ ወይም ሌላ ድርጅት ጋር ተቀላቅሎ ህጋዊ ህልውናውን ሳያጣ አንደኛ ተከሳሽ በእውን እንዳይኖር የፈጸመበትን የንግድ ዓላማ የማይፈጽምና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደግ በማድረግ


በቁሙ ማክሰም የሚቻል መሆኑና አመልካችም አንደኛ ተከሳሽ በህግ አይን የፈረሰ ድርጅት ነው ባይባልም በእውኑ ዓለም የሌለና የከሰመ ድርጅት ነው የሚል መከራከሪያ ያቀረቡ መሆኑን ተረድተናል፡፡ በመሰረቱ አንድን ድርጅት በቁሙ አንዲከስም በማድረግ ድርጅቱ ህጋዊ ህልውና ኖሮት ተግባራዊ የንግድ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በነበረበት ጊዜ ለተፈጸመ ወንጀል የንግድ ድርጅቱንም ሆነ በወቅቱ ወንጀሉ በተፈጸመበት ጊዜ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የነበረውን ሰውና የሌሎች ሰራተኞች የወንጀል ተጠያቂነት ለማስቀረት አይቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕጋዊ ህልውና ያለው ድርጅት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣው በሃላፊዎቹ ወይም ከሰራተኞች አንዱ ከድርጅቱ ስራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የድርጅቱን ጥቅም በሕገ ወጥ መንገድ ለማራመድ  በማሰብ ወይም የድርጅቱን ህጋዊ ግዴታ በመጣስ ወይም ድርጅቱን በመሳሪያነት አላግባብ በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት በአነሳሽነትና በአባሪነት ወንጀል ሲያደርግ መሆኑ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 2 በግልጽ የተደነገገ መርህ ነው፡፡ አንድ የንግድ ድርጅት የወንጀል ተግባር ከፈጸመና ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ከተረጋገጠ በኋላ ድርጅቱ የወንጀሉን ፍርድ ሊፈጽም የማይችልበት ሁኔታ በቁም እንዲከስም መደረጉ ለወንጀሉ አድርጎት ኃላፊ የሚሆኑትን ሰራተኞችና ኃላፊዎች በወንጀል ከመጠየቅ ነጻ የማያወጣ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ በአመልካች ላይ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2 (ለ) 2  መሰረት ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌዴረል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ)2 መሰረት በድምጽ ብልጫ ጸንቷል፡፡

2.  መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

 የ ል ዩነ ት ሐሳብ

እኔ ስሜ በተራ ቁጥር አምስት የተሰየምኩት ዳኛ አብላጫው ድምጽ ከሰጠው ውሳኔ ባለመስማማት የሚከተለው የልዩነት ሐሳብ አስፍሬአለሁ፡፡

 

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ አንደኛ ተከሳሽ ሜጋ ኪነጥበብ ማዕካል ኃ/የተ/የግል ማህበር 2ኛ ተከሳሽ የአሁኑ አመልካች በማድረግ ስድስት ክሶች ያቀረበ ሲሆን በአመልካች ላይ ያቀረበው ክስ ገቢን አለማሳወቅ፣ ትርፍ አሳውቆ አለመክፈል፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ አለመክፈል የሚሉ ናቸው፡፡ አመልካች ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው የግራ ቀኙ ማስረጃዎች ተሰምተው ጥፋተኛ ተብሎው የእስራት ቅጣት ተወስኖ የተገደበላቸው ስለመሆኑ ከሥር ፍርድ ቤት መዝገብ መረዳት ይቻላል፡፡ አመልካች በየደረጃው ጉዳዩን በተመለከቱት ፍርድ ቤቶች ያቀረቡት ቅሬታ መሠረታዊ ይዘት በሥር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ጥፋተኛ ሳይባል መቀጣታቸው መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑ የሚያሰይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ አንደኛ ተከሳሽ ጥፋተኛ እንደተባለ እና ስለ መፍረሱ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን አመልካች ድርጁቱን ወክለው ባይከራከሩም ለምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ በማቅረብ የተከራከሩ በመሆኑ የተጣበበ መብት የለም የሚል ነው፡፡


በሥር ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ሜጋ ኪነጥበብ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቀርቦ እንዲከራከር በሕጉ አግባብ ጥሪ የተደረገለት ስለመሆኑ ጉዳዩም በሌለበት እንዲታይ ግልጽ ትዕዛዝ የተሰጠ ስለመሆኑ የወሳኔው ይዘት አያሳይም ፡፡

 

ጉዳዩ በይግባኝ ሥልጣኑ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሥር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው የሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል በሕጉ አግባብ እንዳልተጠራ በዚህ ምክንያት መዝገቡ ወደ ሥር ፍርድ ቤት መመለሱ ውጤት እንደሌለው በመግለጹ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች በሕግ በግልጽ በተመለከተ ጊዜ የወንጀል ተጠያቂነት ያለባቸው ስለመሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሬ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 34 ተመልክቷል፡፡ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 102 እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285 /1994   አንቀጽ

56(1) እንደተመለከተው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት የወንጀል ጥፋት ከፈፀመ የድርጅቱ ስራአስኪያጅ ተጠያቂ እንደሚሆን ተደንግጓአል፡፡ የዚህ ድንጋጌ የእንግሊዝኛ ትርጉም ``subject to sub-Article (3) where an entity commits an offence every person who is manager of that entity at that time is treated as having committed the offence and is liable penalty under this proclamation`` የሚል ነው፡፡ ከዚህ የህግ ድንጋጌ መሠረታዊ ይዘት ዓላማና መንፈስ መረዳት የሚቻለው የአንድ ድርጅት ሥራአስኪያጅ ኃላፊ የሚሆነው ድርጅቱ በሕግ አግባብ ጥፋተኝነቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ሲንመጣ ድርጁቱ በህግ አግባብ መጥሪያ የደረሰው ስለመሆኑ አልተረጋገጠም፡፡ የአሁኑ አመልካችም ድርጅቱ ከለቀቁ ከአንድ ዓመት በኃላ ክስ የተመሰረተባቸው ስለመሆኑ እየተከራከሩ ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች የአሁኑ አመልካች ጥፋተኛ ከተባሉ ድርጅቱም ጥፋተኛ ነው በሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ከውሳኔያቸው ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁንና የስር ፍርድ ቤቶች ድምዳሜ የህግ መሰረት ያለው አይደለም፡፡ ሕግ አውጪው ከላይ በጠቀሱኩዋቸው አዋጆች ላይ በግልጽ እንዳመለከተው ቅድሚያ መረጋገጥ ያለበት የድርጅት ጥፋት መኖር ያለመኖር ነው፡፡ አንድ ድርጅት ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም ወደ ሚለው ድምዳሜ ለመድረስም በህጉ የተዘረጋው የሙግት አመራር ሥርዓት በጥብቅ ተግባራት መደረግ ነበረበት፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት ሕጋዊ ሰውነት ያለውና ያልከሰመ መሆን ያለመሆኑን በአግባቡ ሰያጣሩ ጥሪ ቢደረግለትም አይቀርብም በሚል ሰበብ እውነት የማፈለግ ግዴታቸው (truth finding) ወደ ጎን በመተው ሕጉን የዘረጋው የሙግት አመራር ሥርዓት ሳይከተሉ ከውሳኔ ላይ መደረሳቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸማቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ድርጅቱ ጥፋተኛ ሳይባል ስራአስኪያጅ ነበሩ የተባሉ የአሁኑ አመልካች በወንጀል ተጠያቂ ማድረግ በአዋጅ ቁጥር 285 እና 286/1994 የተደነገገው የድርጅት እና ሥራአስኪያጅ የተጠያቂነት አወሳሰን ቅደም ተከተል ያዛባ ሂደት ነው፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች ይሁን አብላጫው ድምጽ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የገቢ አዋጆች ስለ ድርጅት እና ሥራአስኪያጅ የወንጀል ተጠያቂነት አወሳሰን ማለትም የድርጅቱ ጥፋተኝነት በቅድሚያ የማረጋገጥ ሕጋዊ ግዴታ ታልፎ አመልካች ጥፋተኛ ናቸው በማለት የሰጡት ውሳኔ የአዋጆች ዓለማና ግብ ያላገነዘበ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

 

በሥር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት /ሜጋ ኪነጥበባት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በዚህ አገር በንግድ ህግ ተመዝግቦ የሚሰራ ድርጅት ከነበረ ስለ ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት ያለው መሆን ያለመሆን ከከሰመም መቼና በማን ውሳኔ የሚሉ ነጥቦች ሊጣሩ የሚገባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አመልካች ድርጅቱ ከመሰከረም 5/2002 ጀምሮ የፈረሰ   ስለመሆኑ


ሲከራከሩ ተጠሪ በበኩሉ ድርጅቱ አልፈረሰም ተሰውሯል በማለት መልስ አቅርበዋል፡፡ ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት በእርግጥ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ህያው ድርጅት ከሆነ ከሚመለከታቸው አካላት በማጣራት እውነት የማፈላላግ ሥራ መከናወን ነበረበት፡፡ በሌላ በኩል ድርጅቱ ሜጋ ማስታወቂያ ከተባለው ድርጅት የተዋሃደ/የተቀለቀለ / Amalgamation merge /ስለመሆኑ በክርክር ሂደት ተነስቷል፡፡ ይህ በተመለከተም ሁለቱም ድርጅቶች ተዋህደው ከሆነ መቼ እና በማን ውሳኔ ሰሚነት ተዋሀዱ የሚለው መጧራት ነበረበት፡፡ አመልካች እንደሚሉት በክርክር ጊዜ አግባብነት ያላቸው ሰነዶች ለማግኘት እንደተቸገሩ በተለይም ድርጅቱ ህያው ካልሆነ እና የድርጅቱ ሕጋዊ ሠራሽ የሆነው ድርጅት ወይም ግለሰብ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ካልተከራከሩ ዞሮዞሮ የአመልካች የመከላከል ሕግ መንግስታዊ መብት ማጣበቡ የማይቀር ነው፡፡ የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች በተጠሪ ምስክሮች መሰቀለኛ ጥያቄ በማቅረብ ስለተከራከሩ የተጣበበ መብት የለም በማለት በውሳኔው ያሳፈረ ቢሆንም ክርክሩ ግለሰባዊ ጉዳይ ሳይሆን የአንድ ድርጅት ጥፋተኛ መሆን ያለመሆን ብሎም የድርጅቱ ሥራአስኪያጅ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ጉዳይ በመሆኑ ድርጅቱ እና የአሁኑ አመልካች ፈጸሙት የተባለው የወንጀል ድርጊት ለመከላከል መቅረብ ያለባቸው ሕጋዊ ሰነዶች እና የክርክር ነጥቦች ከድርጅቱ የተያያዙ አይደለም የሚለው ድምዳሜ የህጉን አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው የሥር ፍርድ ቤት ይሁን ጉዳዩ በይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሥር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት ህያው ድርጅት ነው ወይስ የከሰመ ድርጅት? የከሰመ ድርጅት ከሆነ መብትና ግዴታው ለማን ተላለፈ? የሚሉትና ተያያዥ ነጥቦች በማጣራት ድርጅቱ ጥፋተኛ ነበር ወይስ አልነበረም? የሚለው በቅድሚያ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

 

በማጠቃለል በሥር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ሜጋ ኪነጥበበት ማዕከል ኃ/የተ የግል ማህበር በቅድሚያ በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጎለት ራሱ ወይም ህልውናው የከሰመ ከሆነ መብትና ግዴታው የወረሰው ድርጅት/ተቋም/ ግለሰብ ሳይጣራ እና በአግባቡ ተጣርቶ ጥፋተኛ ሳይባል አመልካች ጥፋተኛ ናቸው ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ አይደለም፡፡ በሥር አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ድርጅት ህልውና ካበቃ ወይም መብቱና ግዴታው የተላለፈለት ድርጅት/ግለሰብ ከሌለ በእርግጥ በሥራ አስኪያጅ የወንጀል ተጠያቂነት ያስከትላል ወይ የሚለውም ከወንጀል ቅጣት ዓላማና ግብ መታየት ነበረበት፡፡ ሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ሜጋ ማስታወቂያ ድርጅት በሕጉ አግባብ ያልተዋሀዱ ከሆነ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትለው ውህዳቱን የወሰኑ እና ያስፈጸሙ የየድርጅቱ ባለቤቶች ናቸው ወይስ  ሥራ  አስኪያጅ ነው ተጠያቂ መሆን ያለበት? የሚለውን በአግባቡ የተጣራ ጉዳዩ አይደለም፡፡ በእነዚህ  ሁሉ ምክንያቶች የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊሻር ይገባ ነበር በማለት በሐሳብ ተለይቻለሁ፡፡

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡