107990 contract law/ donation/ Maintenance obligation/ invalidation of donation

በግልፅ የሰፈረ የውል ቃል ባይኖርም ስጦታ ሰጪው በድህነት ላይ ወድቆ ሲገኝ ስጦታ ተቀባይ የመጦር ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ፣ ሥጦታ ተቀባይ ይህን ግዴታውን ካልፈፀመ ደግሞ ስጦታ ሰጪ ውሉ እንዲሻር መጠየቅ ስለመቻሉ፣

 

የፍ/ሕ/ቁ. 2458(1)፣ 2464(1)

የሰ/መ/ቁ. 107990

 

መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

 

 

አመልካች፡- እማሆይ ወ/ገብርኤል የቀረቡ የለም (ተወካይ) ተጠሪ፡- ደረጀ ደሳለኝ - የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረው በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ በጉራጌ ዞን አቤሸጌ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ ነበሩ፡፡ አመልካች ባቀረቡት ክስ በ1997 ዓ/ም የባለቤቴ ልጅ ባል የሆነው ቄስ ሀይሎም ተስፋዬ ይዞታዬን ወሮ ይዞብኝ ተጠሪ ረዳት መስሎ ቀርቦኝ ቦታውን በትክክል በማላውቀው ቦታ ወስዶኝ ልጄ ነው ብለሽ ፈርሚልኝ ብሎ ከ1999 ዓ/ም ጀምሮ በመሬቴ ላይ ያመረተውን ድርሻዬንና 1.65 ሄክታር ይዞታየን ነጥቆኛል በመሆኑም ይመልስልኝ በማለት ጠየቁ፡፡ ተጠሪም በሰጠው መልስ አመልካች በ23/07/98 ዓ/ም  በተደረገ  የስጦታ ውል በፍ/ብ/ህ/ቁ/ 2443(1) እና በ881 መሠረት የተፈጸመ ስጦታ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩን ያየው የወረዳ ፍርድ ቤት የግራቀኙን በማከራከር አመልካች የስጦታ ውሉ  አልተመዘገበም በማለት ያቀረቡት ክርክር ውድቅ ነው፤ መሬቱን ወደውና ፈቅደው በስጦታ ውል ሰጡ እንጂ በማታለል መሆኑ አልተረጋገጠም፣ ስለዚህ ተጠሪ መሬቱን ሊለቁ አይገባም በማለት ወስኗል፡፡ በመቀጠልም ጉዳዩን ያየው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ30/8/98 ለጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ የቀረበው የስጦታ ውል እና የቀበሌ መስተዳደር የተጻጻፉት ደብደቤዎች ውሉ መመዝገቡን የሚይሳይ ካለመሆኑም በላይ በቀላጤ የሰው ንብረት ማስተላለፍ ስለማይቻል የስር ፍርድ ቤት አመልካች ወደውና ፈቅደው የሰጡት የስጦታ ውል ነው፤ በመሆኑም መሬቱን ተጠሪ ሊለቁ አይገባም በማለት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የስጦታ ወሉ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2443 እና 881”ን” የተከተለ ባለመሆኑ ተንኮል ያለበት በመሆኑ ተጠሪ ሊለቁ ይገባል፤ የኪራይ ግምትም በአካባቢው ባህል መሠረት ይክፈሉ በማለት ወስኗል፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩ በመመርመር፤ በ23/7/98 የተደረገው የስጦታ ውል የፍ/ብ/ህ/ቁ. 881 እና 2443 ተከትሎ የተከናወነ፤ እንከን የማይወጣለት፣ የመመዝገብ ግዴታ የማይጥል በመሆኑ ተጠሪ ከ1998 ጀምሮ በስጦታው መሰረት ወደስሙ አዙሮ በጉልበቱ አለስልሶ፤   የሚጠቀምበትን


ይዞታ ግዴታህን አልተወጣህም ባልተባለበት ይልቀቅ መባሉ እንደማፈናቀል የሚቆጠር በመሆኑ ሊለቁ አይገባም በማለት የከፍተኛውን ውሳኔ በመሻር የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ የክልሉ ሰበር ችሎትም ቅሬታውን ባለመቀበል ሰርዞታል፡፡

 

የአመልካችም አቤቱታ የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡ አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸውን ሲገልጹ፡- የስር ፍርድ ከጠየቅኩት ዳኝነት ውጭ ጭብጥ በመያዝ በወረራ ተያዘብኝ ያልኩትን ይዞታ፤በስጦታ አስታኮ መወሰናቸው፤ እንዲጦረኝ ሰጥቸው ሲጦረኝ ቆይቶ አታሎኝ ስጦታ አስፈረመኝ እያልኩ ከዚህ ጭብጥ ወጥቶ መወሰኑ እና ለረጅም አመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ይዞታዬን እንዲነጠቅ መወሰናቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ጠይቋል፡፡ በዚህም መሰረት ችሎቱም አከራካሪውን መሬት ባለይዞታው ማነው? የሚለውን ለማስረዳት የቀረበው የስጦታ ውል በማስረጃነት ያለውን ተቀባይነት ለመመርመር በጭብጥነት በመያዝ የግራቀኙ በጽሁፍ መልስና የመልስ መልስ በማቀባበል አከራክሯል፡፡

 

ተጠሪም በሰበር መልሳቸው አመልካች የተገኘውን ምርት አላካፍል አለኝ አሉ እንጂ ስጦታ መስጠታቸውን አልካዱም፤ የቀበሌው አመራሮች ባሉበት በሰነዱ ላይ ወደው ፈቅደው ሰጥቶኛል፤ ግዴታህን አልተወጣህም ከተባልኩ እንድወጣ ማድረግ እንጅ ውሉን የማያፈርሰው ነው፡፡ በመሆኑም የወረዳውና የጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የይግባኝ ሰሚውና የሰበሩ ውሳኔዎች ሊጸና ይገባል በማለት ጠይቀዋል፡፡ አመልካች በበኩላቸው ከተጠሪ ጋር ዝምድና የሌላቸውና በቤተክርስቲያን ቀርበን አብረን ለመጠቀም ነበር የተስማማነው፤ የስጦታ ውሉ የማላውቀውና  በተንኮል የተገኘነው፤ በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 110/99 አንቀፅ 8/5‚6 መሰረት ለቤተሰብ፤ ወይም ለወራሽ ካልሆነ በቀር ማስተላለፍ ስለማይቻል ሊሻር ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

ባጠቃላይ የክርክሩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰው ሲመስል፡- እኛም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካለው የህግ ድንጋጌ አንፃር መዝገቡን መርመረናል፡፡

 

በመሆኑም ከተያዘው ጭብጥ አንፃር የስር የግራ ቀኙን ክርክር የተሰጠውን ዳኝነት እንዳየነው፤ የአመልካች ጥያቄ የነበረው ከሟች ባለቤታቸው የተላለፈላቸው የእርሻ መሬት ወሮ ይዞብኛል፤ በማላቀው ሰነድ አታሎም አስፈረመኝ ድርሻየን እና ምርቱን ያካፍለኝ በማለት በመጠየቃቸው ምክንያት መሆኑን ከተያዘው ክርክር የምንገነዘበው ሲሆን ተጠሪም፤ ይዞታውን አመልካች በ23/7/98 በተደረገ የስጦታ ውል መያዙን ገልጸው ተከራክረዋል፡፡ እንግዲህ አመልካች እንዲመለስላቸው የሚጠይቁት 1.65 ሄ/ር ቦታን አስመልክቶ ይህ ተጠሪ ረዳት በመምሰልና ባልታወቀ ቦታ ወስዶአቸው አብረን እንበላለን ልጄ ነው ብለሽ ፈርሚ ብሎኝ ነው የፈረምኩት በማለት አሁን ተጠሪ የሚያቀርቡትን የስጦታ ሰነድ እየተቃወሙት ያሉት፤ በተጨማሪም ሲረዳኝ ቆይቶ አቅመ ደካማ መሆኔን አይቶ እርዳታውን በማቆሙ ረዳት አጥቼ ወደ ቤተክርስቲያን በመግባት በመጠለል እገኛለሁ በማለት ገልጸው በሰው ምስክርም አስረድቷል፡፡ ተጠሪ የሚለው አመራሮች ባሉበት ፈቅደው ሰጥተውኛል፤ ግዴታህን አልተወጣህም የሚባል ከሆነ ግዴታዬን ከመወጣት በቀር በፍ/ህ/ቁ 2442 መሰረት በይርጋ ይቀራል፣ ሊጠይቁኝ አይችሉም በስሜ አዙሬ እየተጠቀምኩበት ነው የሚል መከራከሪያ ነው የሚያቀርበው፤ ይሁን እንጁ ይህ የአመልካች ክርክር የሚያሳየው የተጠቀሰው ይዞታ በእጁ መሆኑን እና ከመሰረቱ የመጦር ግዴታ የለብኝም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአመልካች እድሜና አቅመደካማነትን፤ በአሁኑ ጊዜ ያለረዳት በረሀብ ላይ


እንዳሉ ከተገለፀው ፍሬ ነገር አንፃር ስንመለከተው ተአማኝነት የለውም፤ ላለመጦር ይዞታቸውን ይለቃሉ ተብሎም አይገመትም፤ ሌላው፤ የፍ/ብ/ህ/ቁጥር 2458/1/ ድንጋጌም እንደምንረዳው፤ በግልፅ የሰፈረ የዉል ቃል ባይኖርም ስጦታው ሰጪ በድህነት ላይ ወድቆ ሲገኝ፤ የመጦር ግዴታም እንደለበት ተደንግጎል፤ ይሁን እንጂ ተጠሪ ከዚህም አልፎ ይዞታውን ይዘው እንኳንስ መጦር በውለታ ቢስነት ይዞታውን ስመሃብቱን ወደስማቸው ያዞሩት መሆኑን ከክርክሩ የምንረዳው ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አመልካች ያለመጦራቸውን ባረጋገጡበት ጊዜ ይዞታቸውን ማስመለስና ስጦታውንም እንዲሻር የመጠየቅ መብቱን ሊነፈጉ አይችሉም የፍ.ብ.ህ.ቁ. 2464(1) ይህንኑ ያመላክታል አመልካች ከይዞታቸው ያለመፈናቀል ሕገመንግስታዊ መብትም አላቸው፡፡ በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ/ ሃዋሳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚውና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አከራካሪውን ይዞታ ተጠሪ በስጦታ ያገኙትና ጉልበታቸውን አፍሰው አለስልሶ ወደስማቸው አዙሮ እየተጠቀሙበት በመሆኑ በስጦታ ያገኙትን ይዞታ ሊለቁ አይገባም ሊፈናቀሉ አይገባም በማለት የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ማጽናታቸው ሊታረም የሚገባው ነው ብለናል፡፡

 

ባጠቃላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚውና የሰበር ሰሚው ችሎት ተጠሪው አከራካሪውን ይዞታ ሊለቁ አይገባም በማለት የከፍተኛው ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር የደረሱበት ድምዳሜ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳኔ

 

1. የደ.ብ.ብ.ህ.ክ.መ. የአበሸጌ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ.ቁ. 06347 በቀን 15/05/06 የሰጠው የጉ/ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁ. 08153 በቀን 28/06/06 የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ በመ.ቁ. 03248 በቀን 09/10/06 የስር ውሳኔን በመሻር የሰጠውና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 03727 በቀን 10/3/07 ቅሬታውን ባለመቀበል የሰጡት ትእዛዝ ተሽሯል፡፡

2.  የጉ/ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 08153 በቀን 28/06/06 የሰጠው ውሳኔ ጸንቷል፡፡

3.  ተጠሪ በስጦታ ውል ያዝኩት የሚሉትን ይዞታ ለአመልካች ሊለቁ ይገባል ብለናል፡፡

4. የግራ ቀኙ የወጪ ኪሳራቸውን የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ውሳኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡