102512 labor law dispute/ review of labor board decison by court/ error of law

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሠራተኛ ጉዳይ ወሣኝ ቦርድ የወሰነውን ጉዳይ በይግባኝ ሲያይ የህግ ስህተት መኖሩን እና አለመኖሩን ከማረጋገጥ ባለፈ የፍሬ ጉዳይ እና የማስረጃ ምዘናን በተመለከተ የማየት እና የማረም ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ፣

 

አንድ አሠሪ የሠራተኛ ቅነሳ በሚል ምክንያት ሠራተኞችን ከሥራ ሲያሰናብት በአዋጁ የሠራተኛን ቅነሳ በተመለከተ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች መሠረት ማድረግ ያለበት ስለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28(2)(ሐ) ፣29፣140

 

የሰ/መ/ቁጥር 102512

 

ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

 

 

አመልካቾች፡-

 


1.አቶ ብርሃኑ ቢኔ

2. አቶ ሞላ ደሴ

3. አቶ ተስፋዬ ሐበና

4. ወ/ሮ ጀማነሽ መንገሻ

5. አቶ ጉልትነህ ታደሰ

6. አቶ ወርቁ አይዴ

7. አቶ መኮንን ሙሉ

8. ወ/ሮ ክብነሽ ዋጤሮ

9. ወ/ሮ ታየች አሰፋ

10. አቶ አጫ አይሳሮ

11. ወ/ሮ ፀዳለ ቸችሮ

12. አቶ ሐይሌ አረጋዊ

13. አቶ ጠብቀው ሳንፎ

14. ወ/ሮ ለተብርሃን መኮንን

15. አቶ ዘሪሁን ደግፌ

16. አቶ በርሔ አሰፋ

17. ወ/ሮ አቦነሽ ሳካሎ

18. አቶ ዋህድ ካሳዬ


19. አቶ ግዛቸው ካሳ

20. አቶ አበራ ሐይሌ

21.አቶ ደምመላሽ ካሳዬ        ደመነ ቱኔ

22. ወ/ሮ መስከረም ካንኮ       የ34ቱም

23. አቶ ሙሉጌታ መቺሶ         ጠበቃ

24. አቶ ሱልጣን ሐሰን

25. አቶ ጌታሁን ሐይሌ

26. ወ/ሮ ዓለሚቱ ገብሬ

27. ወ/ሮ ባዩሽ በቀለ

28. አቶ ደሳለኝ ትንታግ

29. አቶ እንግዳ እሸቱ

30. ወ/ሮ ጀማነሽ መንገሻ

31. ወ/ሮ አየለች ባልቻ

32. አቶ መንበረ ጌታቸው

33. አቶ መተኪያ ፀጋዬ

34. አቶ አብዮት ጌታሁን


ተጠሪ፡- የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካአ/ማ- ነ/ፈጅ ሹፋያን ሱልጣን ቀረቡ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139151 ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የስራ ውል መቋረጥን የሚመለከት ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በደቡብ ክልል የሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ነው፡፡ በክልሉ የሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አመልካቾች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

1. አመልካቾች በተጠሪ ድርጅት ከሃያ ዓመት በላይ በታማኝነት ያገለገሉ መሆኑን ገልፀው ተከሳሽ (ተጠሪ) አዲስ መዋቅር አስጠንቻለሁ በማለት የስራ መደባችሁ ታጥፏል በሚል ሰበብ በሕግ አግባብ የሰራተኛ ድልድልና ምደባ ሳያደርግ ቅነሳ በሚል ሀሰተኛ ምክንያት መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓ/ም እና ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የስራ ውላችንን ከሕግ ውጭ ያቋረጠ በመሆኑ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ይወሰንልን በማለት አመልክተዋል፡፡ ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚታይ ነው በማለት የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ያቀረበ ሲሆን፣ በአማራጭ ሰራተኞቹ የተቀነሱት የድርጅቱ መዋቅር በገለልተኛ ባለሙያ ከተጠና በኋላ ከሳሾች መዋቅሩ የሚጠይቀውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ያልተደለደሉ በመሆኑና ድልድሉ የሰራተኞች ተወካይ ባለበት በግልጽ መስፈርት ሰራተኞች ተወዳድረው የተመደቡ በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡

2. የክልሉ ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ተጠሪ አመልካችዎችን ከስራ ያሰናበተበት አግባብ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 29 የተደነገጉትን መስፈርቶች የማያሟላና ከሕግ ውጭ በመሆኑ ተጠሪ በሕጉ መሰረት ሁሉንም ሰራተኞች ባሳተፈ መልኩ እንደገና የሰራተኛ ድልደላ ይፈፅም፡፡ ተጠሪ እንደገና ለመደልደል ካልፈለገ ስንብቱ ሕግን ያልተከተለ በመሆኑ ከሳሾችን/ አመልካቾችን/ ወደ ስራ ይመልስ፡፡ ተጠሪ ከሳሾችን ወደ ስራ ካልመለሰ በሕግ አግባብ ካሳ በመክፈል እንዲያሰናብታቸው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ይግባኝ ባይ (ተጠሪ) ሠራተኞችን የደለደለው በትምህርት ደረጃ፣ በስራ ልምድ፣ በማህደር ጥራትና የስራ አፈፃፀም ውጤት በመሆኑ ስንብቱ በህግ አግባብ የተፈፀመ ነው በማለት የክልሉ ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

3. አመልካቾች ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ/ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ያስጠናው መዋቅር ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 20 የስራ መደብ ያለው ቢሆንም ሰራተኛ ድልድል የፈፀመው ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ባለው የሥራ መደብ ላይ ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪ ካሉት 674 ሠራተኞች አስር ፐርሰንት የሚሆኑ አልቀነሰም፡፡ መዋቅሩ ሠራተኞች ቁጥር እንዲጨምር የሚያደርግ ነው፡፡ ተጠሪ እኛን በሕግ አግባብ በማወዳደር ሠራተኞችን ያልደለደለ መሆኑን በማረጋገጥ ቦርዱ የሰጠውን ውሳኔ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አላግባብ መሻሩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል፡፡ ተጠሪ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ/ም በተፃፈ መልስ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ባለው የስራ መደብ


ሠራተኞች በአግባቡ ተወዳድረው ተመድበዋል፡፡ ከደረጃ 13 እስከ ደረጃ 20 ያለው የስራ መደብ የስራ መሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ከስራ የተሰናበቱት ሰራተኞች 10% በታች መሆኑ ስንብቱን ህገ ወጥ አያደርገውም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ  ቤት የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ እንዲፀናልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካቾች ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ/ም በተፃፈ የመልስ መልስ ተጠሪ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ሰራተኞች ተወዳድረው ተመድበዋል ያለው ሀሰት ነው፡፡ ምክንያቱም በድርጅቱ ንብረትና ፋይናንስ ዘርፍ የሥራ መደቦች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች በድልድል አልተካተቱም፡፡ ተጠሪ ከደረጃ 13 እስከ ደረጃ 20 ያሉት የስራ መደቦች የስራ መሪ የስራ መደብ ነው በማለት ያቀረበው ክርክር እውነትነት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ እንዲወስንልን በማለት ተከራክረዋል፡፡

4. ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ የአመልካቾችን የስራ ውል ያቋረጠው በሕግ አግባብ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5. ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተገለፀውን ጭብጥ ለመወሰን፣ በመጀመሪያ ፍሬ ጉዳይ የማጥራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን በሕግ የተሰጠው የሠራተኞች ጉዳዮች ወሳኝ ቦርድ የግራ ቀኙን የሰውና የፅሁፍ ማስረጃ ሰምቶ፣ መርምሮና መዝኖ የደረሰባቸውን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያዎች ከሕጉ ድንጋጌ ጋር ማገናዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ የክልሉ ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ተጠሪ ምርታማነትን ለማሳደግና አሰራር ለመለወጥ አዲስ መዋቅር ያስጠና መሆኑና በአዲሱ መዋቅር መነሻ በማድረግ አመልካቾችን ከስራ የቀነሰ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሆኖም ተጠሪ ካሉት 674 ሠራተኞች ቅነሳ በሚል ምክንያት ከስራ ያሰናበተው ከአስር ፐርሰንት የማይሆኑ ሠራተኞችን እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የስራ ምደባው ከተወዳደሩ በኋላ በውድድሩ ያላለፉ ሠራተኞችን ተጠሪ ከደረጃቸው ዝቅ አድርጎ የመደበና ያላሰናበተ መሆኑን በማስረጃ መረጋገጡንና የሥራ ድልድሉ ሁሉንም ሰራተኞች የማይመለከት በተለይ ንብረትና ፋይናንስ ክፍል የሚሰሩ ሰራተኞችን የማይመለከት መሆኑን  በማስረጃ እንደተረጋገጠ ቦርዱ በግልጽ በውሳኔው ውስጥ አስፍሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከደረጃ 13 እስከ ደረጃ 20 ያሉ የስራ መደቦች ሰራተኞች በውድድር ያልተመደቡባቸው መሆኑን፣ በማስረጃ እንደተረጋገጠ በውሳኔው አስፍሯል፡፡ ይህም የሠራተኛ ቅነሳ ነው በማለት ተጠሪ ያከነወነው ተግባር የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት አያሟላም በማለት የሠራተኛ ውሳኝ ቦርዱ መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡

6. ከላይ የሰራተኛ ወሳኝ ቦርዱ በማስረጃ ያረጋገጣቸው ጉዳዬች አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች አንጻር መርምረናል፡፡ በመጀመሪያ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) አሰሪው የድርጅቱን አቋም ወይም የስራ እንቅስቃሴ ምክንያት በማድረግ በተለይም የድርጅቱን ምርታማነት የማሳደግ አሰራር ዘዴዎች ለመለወጥ ወይም አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሲባል ሠራተኞችን የመቀነስ ውሳኔ ሊያስተላልፍ እንደሚችልና ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ሰራተኞችን ሊያሰናብት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በዚህ መስረት የስራ መደብ መሰረዝ ሠራተኞችን የሚነካ ሲሆንና በአዋጁ አንቀጽ 29(1) መሰረት የሠራተኛ ቅነሳ የሚያስከትል ሲሆን የስራ ውሉ የሚቋረጠው በአዋጅ አንቀጽ 29 ንዑስ  አንቀጽ 3 ሁኔታዎች በማሟላት መሆን እንዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 3 ተደንግጓል፡፡

7. ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች ባስጠናው አዲስ መዋቅር ምክንያት ካሉት ሠራተኞች አስር ፐርሰንት የሚሆኑትን የስራ ውል ያላቋረጠና ይህም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ  29(1)


የተቀመጠውን መስፈርት የማያሟላ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ አመልካች ካሉት ሠራተኞች አምስት ፐርሰንት የማይሆኑትን የስራ ውል ለማቋረጥ በአዋጅ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 3 የተደነገገውን አስገዳጅ መስፈርት የመከተል ግዴታ አለበት፡፡ ሆኖም አመልካች በመጀመሪያ ደረጃ ከአመልካቾች ያነሰና ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም ያላቸውን ሠራተኞች በተጠሪ ኃላፊዎች ትዕዛዝ በስራ እንዲቀጥሉ አድርጎ አመልካቾችን ያሰናበተ መሆኑ የሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ የግራ ቀኙን ምስክሮች የሰራተኛ ደልዳይ ኮሜቴ አባላት የምስክርነት ቃል በመስማትና በመመዘን አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የስራ ድልድልና ቅነሳው ተጠሪ ያሉትን ሁሉንም የስራ መደቦች የማያካትትና ሁሉንም የስራ ክፍሎች የማይመለከት መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡በአጠቃላይ ተጠሪ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 29/3/ የተደነገጉትን መስፈርቶች በመጠቀም የአመልካቾችን የስራ ውል ያላቋረጠ መሆኑ ፍሬ ጉዳይ የማጣራት እና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባለው የሠራተኛ ጉዳይ ቦርድ ተረጋግጧል፡፡

8.  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ያረጋገጣቸውን ፍሬ  ጉዳዮች እና የደረሰበትን የፍሬ ጉዳይ እና የማስረጃ መደምደሚያ በመቀበል፤ሕጉን መሰረት ያደረገ መሆኑን ከመመዘን ያለፈ፣ የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና ስህተት በይግባኝ የማየትን የማረም ሥልጣን ከአዋጅ አንቀጽ 140 ንዑስ አንቀጽ 1 አልተሰጠውም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ተጠሪ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ሰራተኞች ለመደልደል በተጠቀማቸው አራት መስፈርት ከአመልካቾች ጋር ተወዳድረው ዝቅተኛ ነጥብ ያመጡ ሰዎች በስራ እንዲቀጥሉ ያደረገና የተሻለ ውጤት ያመጡትን አመልካቾች ያሰናበተ መሆኑን በማስረጃ እንዳረጋገጠ የገለጸውን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያ የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት ሳይመረምርና ሳይመዝን በማለፍ ተጠሪ ሠራተኞችን የደለደለው አራት መስፈርቶች ተጠቅሞ ነው በማለት ስንብቱ ህጋዊነው በማለት መወሰኑ በመዝገቡ የሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በማስረጃ ያረጋገጣቸውን ፍሬ ጉዳዮች በማለፍ የተሰጠና የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) እና ንዑስ አንቀጽ 3 እንዲሁም የአዋጁን አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 40(1) ድንጋጌዎችን የሚጥስና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

 ው ሳኔ

 

1.  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል፡፡

2. የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሠራተኞች ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ በመዝገብ ቁጥር 0002/05 መሰከረም 24 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል፡፡

3. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡