101396 labor law dispute Independent contractor scope of labor proclamation

አንድ ባለሙያ በአሠሪው ቁጥጥር ሳይሆን በራሱ የሙያ ኃላፊነት የሙያ አገልግሎት ለመስጠት ከአንድ አሠሪ ጋር ውል ሲኖረው ጉዳዩ የሚገዛው በአሠሪና ሠራተኛ ህግ ስላለመሆኑ፣

-ከአንድ ባለሙያ ጋር የሙያ ግልጋሎት ውል ያለው አሠሪ ውሉን በማናቸውም ጊዜ ማፍረስ ሥለመቻሉ፣

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀስ /1//2/ የፍ/ህ/ቁ. 2140፣2646/1/፣ 2638/1/

 

የሰ/መ/ቁ. 101396

 

ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመሰል

አመልካች፡- አዲስ አጠቃላይ ሆስፒታል ጠበቃ አብደላ ዓሊ ቀረቡ ተጠሪ፡- ዶ/ር ምስራቅ ጥላሁን ጠበቃ አቶ ስመኘው አራጌ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 42275 ሐምሌ 9 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 135997 ግንቦት 18 ቀን 2006ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የሥራ ውል ከሕግ ውጭ በአሠሪው ተቋርጣል በማለት ያቀረቡትን ጥያቄየሚመለከት ነው፡፡

1. የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው የክስ ማመልከቻ ነው፡፡ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ውስጥ በወር ብር 8000,/ስምንት ሺ ብር/ እየተከፈለው በራዲያሎጅስት ሙያ ከጥር 1 ቀን 2000ዓ.ም ጀምሮ ሲያገለግሉ የቆዩ መሆኑን ገልፀው፤አሰሪው አመልካች ከሕግ አግባብ ውጭ ያቋረጠ ስለሆነ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች መሠረት የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍል ውሣኔ ይሰጥልኝ በማለት አመልክተዋል፡፡

አመልካች ተከሣሽ ሆኖ ቀርቦ ከከሳሽ/ተጠሪ/ጋር የሥራ ቅጥር ውል ግንኙነት የለንም፡፡ከሳሽ ጋር ያለን ግንኙነት፣ከሳሽ በትርፍ ሠዓታቸው የሙያ ግልጋሎት እየሰጡ ክፍያ የሚያገኙበት የውል ግንኙነት ነው፡፡ተከሳሽ ይህንን በትርፍ ሠዓት የሚሰጥ የሙያ ግልጋሎት ውል አላቋረጠም፡፡ ከሳሽ የሙያ ፈቃዳቸውን ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር ያላሳደሱ በመሆኑ ፈቃዳቸውን አድሰው ሲቀርቡ ሥራ የሚጀምሩ ፤መሆኑን ተገልፆላቸዋል ከሳሽ በድርጅታችን ውስጥ በቀን ሁለት ሰዓት የሚሠራ ሲሆን በጡረታ የተገለሉ በመሆኑ ከከሳሽ ጋር ቋሚ የሆነ የአሠሪና የሠራተኛ ግንኙነት የላቸውም በማለት ተከራክረዋል፡፡

2. የሥር ፍ/ቤት ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር ከመረመረ በኃላ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የከሳሽን ስም በመጥቀስ ጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም የፃፈው ደብዳቤና ሌሎች የፅሑፍ ሰነዶች በማስረጃነት ያቀረቡለት መሆኑን ጠቅሶ በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል የአሠሪና ሰራተኛ ግንኙነት አለ ከሳሽ የተከሳሽን የሥራ ውል ያቋረጠው ከሕግ አግባብ ውጭ ነው


በማለት ከሳሽ ለተከሳሽ የሥራ ስንብት ክፍያ የማስጠንቀቂያ ክፍያ የካሣ ክፍያና ክፍያ ለዘገየበት ክፍያና የፅሁፍ ክፍያ እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ አፅንቶታል፡፡

3. አመልካች ግንቦት 28 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው ከአመልካች ዘንድ በቀን ሁለት ሠዓት ብቻ የሚያገለግሉራዲዮሎጂስት ናቸው፡፡ ይህ ፍሬ ጉዳይ በተጠሪ አልተካደም ይህም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀጽ 2(1) የሚሸፈንና በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የአሠራና እና ሠራተኛ ግንኙነት የሌለ መሆኑን የሚያሳይ ሆኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች የሥራ ውል አላግባብ ተቋርጧል በማለት የተለያዩ ክፍያዎች እንድከፍል መወሰናቸው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ ተጠሪ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ እኔ በራሴ ኃላፊነት ሳይሆን በአመልካች ኃላፊነትና ቁጥጥር ሥር ሆኜ ሥራ የምሠራ ሠራተኛ ነኝ፡፡ ሬዲዮሎጅስት አገልግሎት የሚሰጥበት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ አመልካች ከሚገኘው ደመወዝ በየወሩ የሥራ ግብር 2,433.65(ሁለት ሺ አራት መቶ ሰላሣ ሶስት ብር ከስልሣ አምስት ሣንቲም ) እየቀነሰ ያስቀራል እንጅ በቀን ሁለት ሰዓት መስራት የአመልካችና የእኔን የስራ ውል ስምምነት  የሚያሳይ  እንጂ የአመልካች ሰራተኛ አለመሆኔን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ ይጽናልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካች ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

4. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን  እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች በአመልካችና በተጠሪ መካከል በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚሸፈን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት አለ፣ አመልካች ከሕግ አግባብ ውጭ የሥራ ውሉን አቋርጧል በማለት የተለያዩ ክፍያዎች አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል የሰጠው የሕግ መሠረት ያለው ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5. ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ “በሬድዮሎጂ” የሕክምና ሙያ የስልጠና በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለውና የደንብ ቁጥር 76/1994 አንቀፅ 20 በሚደነግገው መሠረት በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው አካል በሙያው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጠው ባለሙያ መሆኑ በግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ ከጥር 1 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በአመልካች ድርጅት በቀን ለሁለት ሠዓት ያህል በመገኘት ከአመልካች ጋር በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2641 በሚደነግገው መሠረት የሆስፒታል ውል ከተዋዋሉ የአመልካች ደንበኞች የሙያ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑና ተጠሪ ለሚሰጠው አገልግሎት አመልካች በየወሩ ብር 8000 /ስምንት ሺ ብር/ክፍያ ሲከፍለው  የኖረ መሆኑ በግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

6. አመልካች እና ተጠሪ ከላይ የተገለፀው አይነት የውል ግንኙነት የነበራቸው መሆኑ አያከራክርም፡፡ አከራካሪው ጉዳይ ይኽ በአመልካችና በተጠሪ መካከል ፀንቶ የኖረው ግንኙነት የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ነው ወይስ የዕውቀትና የሙያ ሥራ ለማከራየት የተደረገ የውል ግንኙነት ነው? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ይህንን ጭብጥ ለመወሰን በአመልካች ተጠሪና የሕክምና አገልግሎት በሚሰጣቸው ህሙማን /የአመልካች ደንበኞች


መካከል የሚኖረውን ግንኙነት መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከላይ እንደተገለፀው አመልካች በደንብ ቁጥር 76/94 አንቀጽ 20 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሠረት በሙያው የሕክምና ግልጋሎት ለመስጠት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያለው ባለሙያ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪ አመልካች የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2140 በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የሚጥለው ግዴታና በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2646(1) መሠረት ለሚሰጠው አገልግሎት የአመልካች ደንበኛ ከሚከፍለው ክፍያ ተጠሪ ምን ያህል ገንዘብ በወር ሊከፈለው እንደሚችል በውል በመስማማት፣ሙሉ በሙሉ በአመልካች ተቆጣጣሪነትና አሠሪነት እየተመደበ ሳይሆን ፣በቀን ለሁለት ሠዓቶች ሙያዊ አገልግሎትየሚሰጥ ባለሙያ መሆኑን የግራ ቀኙ ክርክርና በበታች ፍርድ ቤቶች የተረጋገጡት ፍሬ ጉዳዮች ያሳያሉ፡፡

7. የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ የተፈፃሚነት ወሰን በዝርዝር የሚደነግገው በአዋጅ ቁጥር 397/96 አንቀፅ 3 ፣ንዑስ አንቀፅ (1) አዋጅ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ የተመሠረተ የሥራ ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን በመርህ ደረጃ ደንግጓል፡፡ አዋጅ በዚህ ጠቅላላ መርህ የማይካተቱና የቅጥር ላይ የተመሰረቱ የሥራ ግንኘነቶች በአዋጅ ቁጥር 377 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 2 በልዩ ሁኔታና በዝርዝር ደንግጓል፡፡ የአዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 ድንጋጌ ቃል በቃል ሲነበብ ‹‹ይህ አዋጅ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት በቅጥር ላይ በተመሠረቱ የሥራ ግንኙነቶች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም ›› የሚል ይዘት ያለው ሲሆን በአዋጅ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 2 በዝርዝር ከተደነገጉ አዋጅ ተፈፃሚነት ከማይሆንባቸው ግንኙነቶች ውስጥ፤አንድ ተዋዋይ ወገን ዋጋ እየተከፈለው በራሱ የንግድ ሥራ ወይም በራሱ የሙያ ኃላፊነት የሚሠራ ስራ የሚያከናውን ሲሆን፣አዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሌላቸው መሆኑ በአዋጅ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 2(1) ተደንግጓል፡፡

8. ከላይ እንደተገለፀው ተጠሪ ሙሉ በሙሉ በአመልካች መሪነትና ቁጥጥር ሣይሆን በአመልካች ድርጅት ውስጥ በቀን ለሁለት ሠዓት ያክል ከአመልካች ጋር የሆስፒታል ውል ለተዋዋሉ የአመልካች ደንበኞች የራድዮሎጅ የሙያ ግልጋሎት በራሱ የሙያ ኃላፊነት የሚሰጥ ነው፡፡ አመልካች ተጠሪ ይህንን የሙያ ግልጋሎቱን ሌላ ቦታ የሚገኝ የህክምና ተቋም ወይም ከአመልካች ጋር ምንም አይነት የሆስፒታል ውል ግንኙነት ለሌላቸውና የአመልካች የህክምና ካርድ ላልያዙ ሰዎች እንዲሰጥናየሥራ ስምሪት መስጠትና አመልካችን ተቆጣጥሮ ማሠራት አይችልም፡፡ ከዚህ  በተጨማሪ ተጠሪ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 61 እና ተከታታይ ድንጋጌዎች መሠረት በቀን ሥምንት ሠዓት በሣምንት አርባ ሥምንት ሠዓት ከሥራ ቦታ እንዲገኝ ለማስገደድና ተቆጣጥሮ ማሰራት እንደማይችል የግራ ቀኙ ክርክርና ከበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ተረድተናል፡፡

9. የሥር ፍ/ቤት ተጠሪ በቀን ለሁለት ሠዓት ብቻ አገልግሎት መስጠቱ፤ ከአመልካች ጋር በአዋጅ ቁጥር 377/96 የሚሸፈን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ከመመስረት አይገድበውም በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም ይህ የስር ፍርድ ቤት የሰጠው የሕግ ትርጉምና ውሳኔ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 ከአንቀፅ 61 እስከ አንቀፅ  64 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች ይዘትና ውጤት ያገናዘበ ካለመሆኑም በላይ ፣በአዋጅ አንቀጽ 65 ልዩ ድንጋጌ ያገናዘበ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በአዋጅ አንቀጽ 65 መሠረት በሥራ ውሉ  ወይም በህብረት ስምምነት በሌላ አኳኃን ካልተወሰነ በስተቀር ፣የአዋጁ የስራ ሰዓት የሚመለከቱት ከአንቀጽ 61 እስከ አንቀጽ 64 የተደነገጉት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የማይኖራቸው በንግድ መልዕክተኞች በንግድ ወኪሎች ላይ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጎአል፡፡ ከዚህ አንፃር


የሥር ፍርድ ቤት የአዋጅ የሥራ ሠዓት ድንጋጌዎች ተጠሪ የአመልካች ቅጥር ሰራተኛ ነው ብሎ ለመወሰን ተፈፃሚነት እንደሌላቸው በመግለፅ የሰጠው ትርጓሜ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 65 ልዩ ድንጋጌ ያላገናዘበና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

10. ከላይ በዝርዝር የተገለፁት ምክንያቶች ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀፅ 2/1) መሠረት ከአመልካች ቁጥጥርና የሥራ አለመረዳት ሣይገደብ በራሱ የሙያ ኃላፊነት በቀን ለሁለት ሠዓት የራዲዮሎጅ የሙያ አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ እንጅ የአመልካች ሠራተኛ አይደለም፡፡ ተጠሪ ለአመልካች የሚሰጠው የእውቀት  ግልጋሎት እና ሥራ ውል በመሆኑ አመልካች በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማፍረስ የሚችል መሆኑን በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2638 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል፡፡ ይህም በመሆኑ አመልካች አግባብነት ያለውንና ተፈፃነሚነት ያለውን የህግ ድንጋጌ መሠረት በማድረግ አለኝ የሚለውን መብትና ጥቅም ከሚጠይቅ በስተቀር ተጠሪ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 ድንጋጌዎች መሠረት የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍለው የመጠየቅ መብት የለውም ። በመሆኑም የበታች ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ከላይ በዝርዝር የጠቀስናቸውን የሕግ ድንጋጌዎች የሚጥስና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 ው ሣ ኔ

 

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ ተሸሯል ፡፡

2. ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3 ንዑስ 2(1) መሠረት በራሱ የሙያ ኃላፊነት በቀን ለሁለት ሠዓት የሙያ አገልግሎት የሚሠጥ በመሆኑ የአመልካች ቅጥር ሠራተኛ ሣይሆን የዕውቀት ሥራና ግልጋሎት ለመሰጠት የተዋዋለ ባለሙያ ነው በማለት ወስነናል፡፡

3. አመልካች ከተጠሪ ጋር የነበረውን የሙያ (ዕውቀት)ሥራ ግልጋሎት ውል ያቋረጠው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2637 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት ነው በማለት ወስነናል፡፡

4. ይኽ ውሣኔ ተጠሪ የሙያ ግልጋሎት ውሉ በመቋረጡ ምክንያት አለኝ የሚለውን የመብት ጥያቄ ከማቅረብ የሚገድበው አይደለም ብለናል፡፡

5.  በዚህ ፍርድ ቤት የወጣውን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ፡፡