97094 civil procedure Evidence law temporary injunction attachment of property before judgment priority of creditors

civil procedure

Evidence law

temporary injunction

attachment of property before judgment

priority of creditors

በተያዘ ወይም በተከበረ ንብረት ላይ መብት አለን ብለው ተቃውሞ የሚያቀርቡ ሠዎች በንብረቱ ላይ ያላቸውን የቀዳሚነት መብት ወይም ባለይዞታነት ለማረጋገጥ በጽሁፍ ማስረጃ ብቻ ሳይወሠኑ ሌላ ማስረጃም ሊያቀርቡ የሚችሉ ስለመሆኑ፣

 

የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ.418/3/ እና የፍ/ህ/ቁ 1193/1//2/

 

የሰ/መ/ቁ 97094 ቀን 08/03/2ዐዐ7 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ወ/ሮ አስቴር አምባው - ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1. አቶ አበባው ክፍሌ የቀረበ የለም

2. ያሬድ አለማየሁ የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በከፋ ዞን የቦንጋ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች በስር ፍ/ቤት በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 418 በአፈፃፀሙ ጉዳይ ጣልቃ የገቡ ሲሆኑ 1ኛ ተጠሪ የአፈፃፀም ከሳሽ 2ኛ ተጠሪ የአፈፃፀም ተከሳሽ ነበሩ የአፈፃፀም ከሳሽ /የአሁንተጠሪ/ ለአፈፃፀም ይውሉ ዘንድ 1. የልብስ ስፌት ማሽን፣ ኮንትሮል ብፌ፣ የሴቶች ፀጉር ቤት ካስክ፣ ስሶት የፀጉር ማሽን፣ የፀጉር ቤት መስታወት፣ የመቀመጫ ወንበር፣ ባለ 21 ኢንች ቴሌቪዥን እና አራት የሶፋ ወንበሮች ተሽጦ እዳው ይከፈለኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የተጠቀሱት ንብረቶች ተገመተው እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ በመስጠቱ ምክንያት የአሁን አመልካች ንብረቶች የግሌ ናቸው በማለት ሊፈፀም አይገባም በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ. 418 መሰረት በመቅረቧ ፍ/ቤቱም አመልካች ተጠቃሹ ንብረቶች የራሳቸው ለመሆኑ ያቀረቡት የፅሁፍ ሰነድ የለም፣ በሰው ምስክር አስረዳለሁ ያሉትን ክርክር በስነ ስርዓት ህጉ 418/3/ መሰረት ተቀባይነት የለውም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጐታል፡፡ በየደረጃው ያሉትም የክፍሉ ፍ/ቤቶችም ይህንኑ ተቀብለውታል፡፡

 

የአመልካች አቤቱታም የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸውን ሲገልፁ 2ኛ ተጠሪ በእኔ ድርጅት ተቀጥሮ የሚሠራ ነው፤ ተጠቃሾቹ ንብረቶች የግሌ እና መጠቀሚያዎቼ ናቸው ብዩ ብቀርብምበሰው ምስክር ማስረዳት አይቻልም፤የፅሑፍ ሰነድ ካልሆነ በቀር በማለት ላቀርብ እችላለሁ ያልኩትን ሰነድ ሳይቀበለኝ ጥያቄየን ውድቅ ማድረጉ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊታረምልኝ ይገባዋል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

 

በዚህም መሰረት እኛም አመልካች በሰውና በሰነድ ንብረቶቹ የእኔ መሆናቸውን ላስረዳ እያሉ በሰው ማስረጃ ብቻ ማሰረዳት አይቻልም ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት በጭብጥነት በመያዝ


የግራ ቀኙ በቀረበው አቤቱታ ላይ መልስና የመልስ መልስ በፅሑፍ እንዲቀባበሉ ተደርጐ ተከራክረዋል፡፡

 

1ኛ ተጠሪ የሚሉት 2ኛ ተጠሪ የአመልካች ባል ናቸው በአካሌ ላይ ጉዳት አድርሶብኝ እንዲፈፀምልኝ ያቀረብኩትን ንብረቶች አመልካች ለማስቀረት በማሰብ ነው የእኔ ንብረቶች ናቸው የሚሉት የራሳቸው ለመሆኑ በሰነድ ማቅረብ ባለመቻላቸው እና በሰው ማስረጃ አስረዳለሁ ማለታቸው ውድቅ መደረጉ የሚነቀፍ አይደለም በማለት ነው፡፡የሚከራከሩት አመልካች በበኩላቸው በ2ኛ ተጠሪ ፍቃድ እኔ ንብረቶቹን አቀርቤ ቀጥሬያቸው ነው የሚሰሩት እንጂ የጋብቻ ግንኙነት የለኝም በስር ፍ/ቤት በሰነድና በሰው ማስረጃ ላስረዳ ብዬ እያመለከትኩ ይህ ታልፎ በሰው ማስረጃ ማስረዳት አይቻልም ተብሎ መወሰኑ ንብረቴን የሚያሳጣኝ ውሳኔ በመሆኑ ሊሻር ይገባዋል ሲሉ ክርክራቸውን አጠናክረዋል፡፡

 

በአጠቃላይ የክርክሩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሱትን ይመስላል፡፡ በመሆኑም ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መርምሯል፡፡

 

እንግዲህ አመልካች ተጠቃሾቹ ንብረቶች የእኔ ለመሆናቸው “ሰነድ” ማቅረብም እችላለሁ ስል እንዳቀርብ ከተፈቀደልኝ በኋላ ነው፡፡ ይህ ታልፎ በፅሁፍ ማስረጃ ብቻ ነው እንጂ በሰው ማስረጃ ማስረዳት አትችይም የተባልኩት ነው የሚሉት፡፡ በመሰረቱ የፍ/ብ/ህ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 418 ድንጋጌ አስፈላጊነት የክርክሩ አካል ያልሆኑና ፍርድ ያላረፈባቸው የ3ኛ ወገን ንብረት ሳይረጋገጥ የፍርዱ ማስፈፀሚያነት እንዳይውሉ ለመከላከልና ባንጻሩ ፍርዱን የመፈፀም ለማስተጓጉል (እንዳይፈፀም ለሚቀርቡት በቂ ላልሆኑ አቤቱታዎችም (መቃወሚያ) እልባት የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም በተያዙት ንብረቶች ላይ መብት አለኝ የሚል ወገን የሚያቀርበውን መቃወሚያና አቤቱታ ተቀብሎ መመርመር እንዳለበት የተጠቀሰው ድንጋጌም በግልፅ ያሰፈረውነው፡፡ ይህ ከሆነ የዚሁ አንቀጽ 418(3) የአራተኛው ቅጂ ባለይዞታነትን ለማስረዳት የፅሁፍ ማስረጃ መቅረብ እንዳለበትየሚደነግግ ቢሆንም የእንግሊዘኛው ቅጂ የስነ- ስርዓት ህጉደግሞ ይህንኑ  አንቀጽ ሲገልጽ The Claimant or 0bjector Shall adduce evidence to Show that and the date of the attachment he had Some interest in or was possessed of the property attached ይላል፡፡ እንግዲህ ከዚህኛው የእንግሊዘኛ ቅጂ የምንረዳው “ማስረጃ በማቅረብ ለአፈጻጸም የቀረበውን ንብረት ማስረዳት እንደሚቻል የሚገልጽ ነው፡፡ የአማርኛው ቅጂም ቢሆን ከፍ/ህ/ቁ/1193 (1) እና (2) ድንጋጌዎች ጋር ተደምሮ ሲታይ ሌላውን የማስረጃ አይነት በግልጽ እንዳይቀርብ የከለከለው ሆኖ አይታይም፡፡በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች አመልካች አካራካሪውን የሚንቀሳቀስ ንብረት በሰው ማስረጃ ሊያስረዱ አይችሉም ሲሉ ያደረሱበትን ድምዳሜ የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 418 ድንጋጌ መሰረታዊ አላማና የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ ሀብቶችን ባለ ሃብትነት ለማስረዳት የሚጠቅሰውን የማስረጃ ዓይነት ያገናዘበ ሁኖ አልተገኘም በመጨረሻ በስር ፍ/ቤት አመልካች ያቀረቡትን የሰው ማስረጃ ከወዲሁ ሳይሰማ ሰነድ አልቀረበም በማለት ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረጉ የማስረጃ አቀራረብ ስርዓትን ያልተከተለ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኘተነዋል ፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ተወስኗል፡፡


 

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ ዐ64ዐ3 በቀን 11/ዐ4/2ዐዐ6 ዓ.ም የሰጠው የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 1ዐዐ82 በ3ዐ/ዐ4/2ዐዐ6 ዓ.ም እና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ ዐ1555 በቀን ዐ9/ዐ5/2ዐዐ6 ዓ.ም የተሰጡት ውሳኔዎች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1/መሰረት ተሽረዋል፡፡

2. የቦንጋ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በጉዳዩ የቀረበውን  የሰው  ማስረጃ በመስማት አግባብነት ያላቸውን ሰነዶች በመመርመር ተገቢነት ያለውን ውሳኔ እንዲሰጥ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343/1/ መሰረት መዝገቡን መልሰን ልከናል፡፡ ይፃፍ፡፡

3.  የወጪ ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::