96168 criminal law/ sentencing/ extenuating circumstances/ evidence law/ sentencing guideline

በወንጀል ጉዳይ ጥፋተኛ የተባለ ሠው በቅጣት ማቅለያነት
እንዲያዝለት ያቀረበውን ምክንያት በማስረጃ ማስደገፍ እንዲችል በቂ
ጊዜ ባልተሠጠበት ሁኔታ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በሚል
የማቅለያ ምክንያቱን ውድቅ በማድረግ የሚሠጥ የቅጣት ውሣኔ
በወንጀል ህጉ እና በቅጣት አወሳሠን መመሪያው ሥለ ቅጣት
አወሣሠን የተቀመጡትን ድንጋጌዎች መሠረት ያደረገ ነው ለማለት
የሚቻል ስላለመሆኑ፣
የወ/መ/ሥ/ሥርዓት 149/3//4/

የሰ/መ/ቁ.96168 ህዳር 9 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ አርአያ ኪዳነ ቤተሰብ ነኝ በማለት መምህር ፍሰሐ ገ/መስቀል ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዐ/ሕግ - የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ተጠሪ ያቀረበባቸውን የኮንትሮባንድ የወንጀል ክስ የተመለከተው የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠባቸው እና በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የጸናው የጥፋተኝነት እና የተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

 

ተጠሪ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ በነበሩት የአሁኑ አመልካች እና የዕቃዎቹ ባለቤት ናቸው ተብለው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 141 መሰረት በብይን በተሰናበቱት 2ኛተከሳሽ ላይበ07/06/2005 ዓ.ም.አዘጋጅቶ ያቀረበው ክስ ይዘት ባጭሩ፡-ተከሳሾቹ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(3) እና በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 በአንቀጽ 91(2) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የጉምሩክ ስነ ስርዓት ያልተፈጸመባቸውን የቀረጥ እና የታክስ መጠናቸው ብር 136,657 የሆነ እና ንብረትነታቸው የ2ኛ ተከሳሽ የሆኑ የተለያዩ ዕቃዎችን 1ኛ ተከሳሽ ሲያሽከረክሩ በነበረው የሰሌዳ ቁጥሩ 2-A06860 አ.አ. በሆነ ተሽከርካሪ ለዕቃ መሸሸጊያ ተብሎ በተሰራ የመኪና አካል (ሻግ) ውስጥ ጭነው ከባሌ ሮቤ ወደ ሻሸመኔ በመጓዝ ላይ እያሉ በ15/05/2005 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 9፡00 ሰዓት በአዳባ ኬላ ላይ የተያዙ በመሆኑ የኮንትሮባንድ ወንጀል አድርገዋል የሚል ሲሆን አመልካች ተጠይቀው ወንጀሉን አላደረግሁም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ በተጠሪ በኩል የቀረቡ ሁለት የጉምሩክ ፖሊስ አባላትን ምስክርነት ከሰማ እና የተጠሪን የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኃላ 2ኛ ተከሳሽ የነበሩትን ግለሰብ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 141 መሰረት በነጻ በማሰናበት አመልካችን ግን ዐቃቤ ሕግ በክሱ መሰረት ያስረዳባቸው መሆኑን ገልጾ መከላከያቸውን ማሰማት እንዲጀምሩ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 142 መሰረት ትዕዛዝ በመስጠቱ አመልካች የተሳቢ መኪና ሾፌር  መሆናቸውን እና የተከለከሉ ዕቃዎችን  ጭኖአል የተባለውን  ተሽከርካሪ በዕለቱ  ሊይዙ የቻሉት ብር   500


ተከፍሎአቸው ተሽከርካሪውን ሻሸመኔ ድረስ እንዲያደርሱ ደላሎች በነገሯቸው መሰረት መሆኑን ያስረዱልኛል በማለት ሁለት የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው አሰምተዋል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም በሁለቱ ወገኖች የቀረበውን አጠቃላይ ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ አመልካቹ ባሰሟቸው የመከላከያ ምስክሮች በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተመሰረባቸውን ፍሬ ነገር ለማስተባበለል አልቻሉም በማለት በክሱ በተጠቀሰባቸው ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠባቸው በኃላ ግራ ቀኙ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡በመቀጠልም በክሱ የተመለከተው ወንጀል በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ደረጃ ያልወጣለት መሆኑን ገልጾ በክብደቱ እና በአፈጻጸሙ በመካከለኛ ደረጃ መድቦ አመልካች የቀድሞ ፀባያቸው መልካምነት እና የቤተሰብ አስተዳዳሪነታቸው በማቅለያ ምክንያትነት እንዲያዙላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በሚል ምክንያት ሳይቀበል ቀርቶ ቅጣቱን በመመሪያው መሰረት በማስላት በአባሪ አንድ በእርከን 27 ስር በአስር ዓመት ጽኑ እስራት እና በብር 15,000 መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት ይግባኙን የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአመልካቹ የዘወትር ፀባይ መልካምነት በማቅለያ ምክንያትነት ሳይያዝ የቀረው አላግባብ መሆኑን ገልጾ የጽኑ እስራት ቅጣቱን በሶስት እርከን ዝቅ በማድረግ በእርከን 24 ስር ወደ ሰባት ዓመት አሻሽሎ ቀሪውን ውሳኔ በማጽናቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ የጥፋተኝነት ውሳኔውን አግባብነት ተጠሪ ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመከለተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት አመልካች በክሱ የተመለከተውን ወንጀል አላደረግሁም በማለት ክደው የተከራከሩ ቢሆንም ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት በአመልካቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠው ተጠሪ ባሰማቸው ሁለት ምስክሮች እና ባቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 141 ስር በተቀመጠው መስፈርት መሰረት አመልካቹን ጥፋተኛ በሚያደርግ ደረጃ በክሱ መሰረት ማስረዳቱን፣አመልካች መከላከያቸውን እንዲያሰሙ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 142 መሰረት በተሰጠው ትዕዛዝ አመልካች አቅርበው ያሰሟቸው ሁለት የመከላከያ ምስክሮች የምስክርነት ቃል በተጠሪ ምስክሮች እና ሰነዶች በአመልካቹ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ፍሬ ነገሮች ማስተባበል ያልቻለ መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ነው፡፡አመልካች ሲያሽከረክሩት በነበረው ተሽከርካሪ የተጫኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በጉምሩክ ኬላ መያዛቸውን ሳይክዱ አጥብቀው የሚከራከሩት ተሽከርካሪውን ከባሌ ሮቤ እስከ ሻሻመኔ ለማድረስ በብር 500 ተስማምቼ ከማሽከርከር በቀር ተሽከርካሪው የጉምሩክ ስነ ስርዓት ያልተፈጸመባቸውን ዕቃዎች ጭኖ የነበረ ስለመሆኑም ሆነ የዕቃ መደበቂያ ሻግ የነበረው ስለመሆኑ የማውቀው ነገር ያልነበረ በመሆኑ በወንጀሉ ጥፋተኛ የተባልኩት አላግባብ ነው በማለት መሆኑን የአቤቱታው ይዘት ያመለክታል፡፡

 

ይሁን እንጂ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈው አመልካች በክሱ የተመለከተውን ወንጀል ማድረጋቸው በተጠሪ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው እያለ ይህንኑ በመከላለከያ ማስረጃ አለማስተባበላቸውን መሰረት በማድረግ ከመሆኑም በላይ ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው  የክልሉ


ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልካች በጥፋተኛነት ውሳኔው ላይ ያቀረቡትን ቅሬታ ሳይቀበል የቀረው ዕቃዎቹ ስለመጫናቸው የማውቀው ነገር የለም ይበሉ እንጂ 1ኛ የተጠሪ ምስክር በሰጡት ምስክርነት ቃል ውስጥ አመልካች በተሽከርካሪው ላይ የዕቃ መሸሸጊያ ቦታ (ሻግ) ካለ ተጠይቀው ሌላ ሻግ ከተሽከርካሪው ሳልቫቲዮ ውስጥ መኖሩን አሳይተውኛል የሚል ምስክርነት እንደሰጡ ከይግባኙ ግልባጭ መገንዘቡን ጭምር በመጥቀስ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ ተጠሪ ይህንኑ ሁኔታ በመጥቀስ በሰበር መልሱ ላቀረበው ክርክር የምስክሩ ቃል እርስ በርሱ የሚጋጭ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ከማለት በቀር የዚህ ዓይነት ምስክርነት ስለመሰጠቱ አመልካች ያቀረቡት ማስተባበያ አለመኖሩን ከመልስ መልሳቸው ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ፍሬ ነገርን አጣርተው እና ማስረጃን መዝነው በአመልካች በኩል የቀረበውን መከላከያ ውድቅ በማድረግ  የሰጡት የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ባለመገኘቱ አመልካች የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠብኝ አላግባብ በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ በነጻ እንድሰናበት ሊወሰንልኝ ይገባል በማለት ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

የቅጣት ውሳኔውን በተመለከተ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክሱ የተመለከተው ወንጀል በወቅቱ በስራ ላይ በነበረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 ደረጃ ያልወጣለት መሆኑን ገልጾ በክብደቱ እና በአፈጻጸሙ በመካከለኛ ደረጃ ለመመደብ ምክንያት ያደረገው ዕቃዎቹ በተሽከርካሪው ውስጥ ተደብቀው የተገኙት ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ ልዩ የመሸሸጊያ ስፍራ መሆኑን ነው፡፡በመዝገቡ በማስረጃ የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት ወንጀሉን በመካከለኛ ደረጃ መመደቡ የመሰረታዊ የሕግ ስህተት ጥያቄን የሚያስነሳ ባለመሆኑ ወንጀሉ ሊመደብ ይገባው የነበረው በዝቅተኛ ደረጃ ነው በማለት አመልካች ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ በአመልካቹ ላይ የቀረበ የማክበጃ ምክንያት የሌለ ሲሆን የቀድሞ ፀባያቸው መልካምነት እና የቤተሰብ አስተዳዳሪነታቸው በማቅለያ ምክንያትነት እንዲያዙላቸው አመልካች ያቀረቡትን ጥያቄ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በሚል ምክንያት ሳይቀበል የቀረ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበ ተቃራኒ ክርክር እና ማስረጃ እስከሌለ ድረስ የአመልካቹ የቀድሞ ጸባይ መልካምነት ግምት የሚወሰድበት መሆኑን ገልጾ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅለያ ምክንያትነት ተቀብሎ ቅጣቱን አሻሽሏል፡፡

 

ይሁን እንጂ የቤተሰብ አስተዳዳሪነታቸው በማቅለያነት ሊያዝላቸው እንደሚገባ  አመልካች አሁንም ድረስ እየተከራከሩ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የቀረበውን ክርክር ያለፈው በምን ምክንያት እንደሆነ ውሳኔው በግልጽ አያመለክትም፡፡ቀደም ሲል እንደተገለጸው በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረቡትን ጥያቄ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳይቀበል የቀረው የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላቀረቡም በማለት ነው፡፡የጥፋተኛነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔው የተሰጠው በአንድ ቀን ስለመሆኑ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያመለክት በመሆኑ አመልካች አለኝ የሚሉትን የቅጣት ማቅለያ ምክንያት በማስረጃ ለማስደገፍ ጊዜ ወይም ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበረ ስለመሆኑ የመዝገቡ ግልባጭ አያመለክትም፡፡

 

በመሰረቱ በወንጀል ጉዳይ የጥፋተኛነት ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ ግራ ቀኙ አሉን የሚሏቸውን የማክበጃ እና የማቅለያ ምክንያቶች የማቅረብ እና አስፈላጊ ሲሆንም በማስረጃ የማስደገፍ መብት ያላቸው ስለመሆኑ ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 149 (3) እና (4) ድንጋጌ አጠቃላይ ይዘት እና መንፈስ መገንዘብ የሚቻል ሲሆን ፍርድ ቤቶችም የእነዚህን መብቶች


ተግባራዊነት ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ ለተከራካሪ ወገኖች ጊዜ ወይም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡በመሆኑም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ አመልካች የቤተሰብ አስተዳዳሪታቸውን በማስረጃ ማስደገፍ የሚችሉ መሆን አለመሆናቸውን ሳያረጋግጥ የማቅለያ ምክንያቱ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በማለት ወዲያውኑ የቅጣት  ውሳኔ  ወደ መስጠት ማምራቱ ተገቢነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ በወንጀል ጉዳይ ጥፋተኛ የተባለ ሰው በቅጣት ማቅለያነት እንዲያዝለት ያቀረበውን ምክንያት በማስረጃ ማስደገፍ እንዲችል በቂ ጊዜ ባላገኘበት ሁኔታ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በሚል የማቅለያ ምክንያቱን ውድቅ በማድረግ የሚሰጥ የቅጣት ውሳኔ ደግሞ በወንጀል ሕጉ እና በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ስለ ቅጣት አወሳሰን የተቀመጡትን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡

 

ሲጠቃለል በቅጣት አወሳሰን ረገድ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት  ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 17056 በ13/12/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 168474 በ12/03/2006 የተሻሻለው ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ  ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 195(2)(ለ)(2) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2.  በአመልካቹ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ፀንቷል፡፡

3.  አመልካቹ ላይ የተጣለው የቅጣት ውሳኔ ተሽሯል፡፡

4. የአመልካቹ የዘወትር ጸባይ መልካምነት በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በማቅለያ ምክንያትነት የተያዘው በአግባቡ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አመልካች የቤተሰብ አስተዳዳሪ ስለመሆናቸው አለኝ የሚሉትን ማስረጃ እንዲያቀርቡ ካደረገ በኃላ ተገቢውን - የቅጣት ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ ጉዳዩ ለምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲመለስ ወስነናል፡፡

5. የዚህ ውሳኔ ግልባጭ በውሳኔው መሰረት ተገቢውን መፈጸም  ያስችለው ዘንድ ለምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤እንዲያውቁት ደግሞ ለኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በሚገኙበት ማረሚያ ተቋም  በኩል ለአመልካቹ ይላክ፡፡

6.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡