99883 criminal procedure/ jurisdiction of court/ federal court jurisdiction/ consolidation of charges

በአንድ ተከሳሽ ላይ ከቀረቡት ከአንድ በላይ ከሆኑት ክሶች መካከል
ከፊሎች የሚወድቁት በፊዴራል ፍ/ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር
ከፊሎቹ ደግሞ በክልል ፍርድ ቤት የስረ- ነገር ስልጣን ስር በሆነ
ጊዜናበወንጀል ህግ ሥነ-ስርዓቱ የክስ አቀራረብ መርህ መሰረት
በቀጥታም ሆነ በውክልና በፌደራል ፍ/ቤት ቀርበው እንዲታዩ
ከተደረገ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የይግባኝ እና የሰበር ሥርዓታቸው
በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲቀርቡ እንደተደረገው ሁሉየፌደራል
ፍ/ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ሥርዓት ተከትለውና ተጠቃለው
መታየትያለባቸው ስለመሆኑ።- ወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 109(3)፣116(2)
አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 4(4)፣15(1)

የሰ/መ/ቁ/ 99883

 

ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶገ/ሥላሴ ገብሩ - ጠበቃ ገ/እግዚአብሔር ተስፋዬ ቀረቡ፣ ጠበቃ ሐና ዲግራንዲ ከመቀሌ በV.C. ቀረቡ፡፡

 

ተጠሪ፡- የትግራይ ብ/ክ/መንግስት ፍትሕ ቢሮ - ዐ/ሕግ ገ/እግዚአብሔር ተወልደብርሃን ከመቀለ በV.C. ቀረቡ፡፡

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ እና ቁጥራቸው 98349 እና 98350 በሆኑት በዛሬው ዕለት በዚሁ ችሎት ውሳኔ በተሰጠባቸው ሌሎች ሁለት መዝገቦች ለቀረበው የሰበር ክርክር ምክንያት የሆነው ጉዳይ የተጀመረው ተጠሪ በ19/08/2003 ዓ.ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ በትግራይ ክልል  በመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ በነበሩት የአሁኑ አመልካች እና 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በነበሩት ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ላይ ስድስት የወንጀል ክሶችን በማቅረቡ ሲሆን ይዘታቸውም በአጭሩ፡-

 

1. በአንደኛ ክስ ሶስቱም ተከሳሾች በገቢ ግብር አዋጅቁጥር 286/1994 በአንቀጽ 96 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በተለያየ የንግድ ስራ ዘርፍ ተሰማርተው ይሰሩ በነበረበት ጊዜ

 

· 1ኛ ተከሳሽ አቶ ገ/ሥላሴ ገብሩ ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ መክፈል ይገባቸው የነበረውን ግብር ብር 1,973,389.10 ባለመክፈላቸው፤

· 2ኛ ተከሳሽ ወ/ት ብርኽቲ ተስፋይ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ መክፈል ይገባቸው የነበረውን ግብር ብር 1,209,320.17 ባለመክፈላቸው፤

· 3ኛ ተከሳሽ አቶ ፍጹም አብርሃ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ መክፈል ይገባቸው የነበረውን ግብር ብር 25,102.93 ባለመክፈላቸው ሕግን በመጣስ ግብር ያለመክፈል ወንጀል አድርገዋል፤


2. በሁለተኛ ክስ ሶስቱም ተከሳሾች በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ  ቁጥር  285/1994 በአንቀጽ 49 ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ በተለያየ የንግድ ስራ ዘርፍ ተሰማርተው ይሰሩ በነበረበት ጊዜ፡-

 

· 1ኛ ተከሳሽ በገዛ ገብረስላሴ ባህላዊ ምግብ ቤት የወ/ሮ ከለላ ሃደራ ወኪል ሆነው በሰሩበት ጊዜ ከሚያዝያ እስከ የካቲት ወር 1999 ዓ.ም. ድረስ ለመንግስት ገቢ ማድረግ ይገባቸው የነበረውን ብር 2,195,929.51 የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ባለማድረጋቸው፤

·   2ኛ ተከሳሽ ከሐምሌ 1999 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ   ለመንግስት ገቢ ማድረግ ይገባቸው የነበረውን ብር 3,094,268.85 የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ባለማድረጋቸው፤እንዲሁም ከሐምሌ 1999 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ሲገባቸው ባለመመዝገባቸው፤

·   3ኛ ተከሳሽ ከሐምሌ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ   ለመንግስት ገቢ ማድረግ ይገባቸው የነበረውን ብር 199,334.17 የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ባለማድረጋቸው፤እንዲሁም ከሐምሌ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ሲገባቸው ባለመመዝገባቸው፤ሕግን በመጣስ ታክስ  ያለመክፈል ወንጀል አድርገዋል።

 

3 በሶስተኛ ክስ 1ኛ ተከሳሽ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 በአንቀጽ 98(1)(ሀ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በመቀሌ ከተማ ለሚያሰሩት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ከቀረጥ ነጻ ያስገቡት የተለያየ መጠን ያለው የቀረጥ መጠኑ ብር 8,741,024.44 የሆነ ቴንዲኖ በባለሙያዎች ተፈትሾ ባለመገኘቱ ከቀረጥ ነጻ ሆኖ ወይም በቅናሽ ቀረጥ የገባን ዕቃ ከቀረጥ ነጻ መብቱ ከተሰጠበት ዓላማ ውጪ ለሌላ አገልግሎት የማዋል ወንጀል አድረገዋል፤

4   በአራተኛ ክስ 1ኛ ተከሳሽ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 በአንቀጽ

60(1) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ መጀመርያ በሕንጻ ማከራየት የንግድ ዘርፍ ፈቃድ አውጥተው ከ2001 እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ባለመክፈል እና ባለማደሳቸው፤በከብት ማድለብ የንግድ ዘርፍ ፈቃድ አውጥተው ከ2001 እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ባለመክፈል እና ባለማደሳቸው፤ እንዲሁም በምግብ ቤት የንግድ ዘርፍ ፈቃድ አውጥተው ከ2001 እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ሳይከፍሉ እና የጸና/የታደሰ/ የንግድ ፈቃድ ሳይዙ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው የጸና የንግድ ፈቃድ ሳይዙ በንግድ ስራ ላይ የመሰማራት ወንጀል አድርገዋል፤

5   በአምስተኛ ክስ 1ኛ ተከሳሽ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994   በአንቀጽ

50(3)(ለ) ስር የተደነገገውን ተላልፈው በክሱ ዝርዝር የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት በመፈጸማቸው የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ የማቅረብ ወንጀል አድርገዋል፤

6 በስድስተኛ ክስ1ኛ ተከሳሽ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 በአንቀጽ 97(3)(ለ) የተደነገገውን ተላልፈው በክሱ ዝርዝር የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት በመፈጸማቸው የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃ የማቅረብ ወንጀል አድርገዋል፤የሚሉ ናቸው፡፡

1ኛ ተከሳሽ ያቀረቧቸው የመቃወሚያ ነጥቦች ውድቅ ከተደረጉ በኃላ ተጠይቀው ሶስቱም ተከሳሾች ወንጀሎቹን አላደረግንም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ በተጠሪ በኩል የቀረቡ በሁሉም ክሶች ኦዲተሮችን ጨምሮ በድምሩ የአስራ ሰባት ምስክሮችን ምስክርነት ከሰማ እና የኦዲት  ሪፖርትን


ጨምሮ የተጠሪን የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ተጠሪ በክሶቹ መሰረት አላስረዳባቸውም በማለት 1ኛ ተከሳሽን ከአምስተኛ እና ከስድስተኛ ክሶች በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 141 መሰረት በማሰናበት እና ቀሪዎቹን ክሶች በተመለከተ ግን ዐቃቤ ሕግ በክሱ መሰረት ያስረዳባቸው መሆኑን ገልጾ ሶስቱም ተከሳሾች መከላከያቸውን ማሰማት እንዲጀምሩ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 142 መሰረት ትዕዛዝ በመስጠቱ ሶስቱም ተከሳሾች የተለያዩ የመከላከያ ጭብጦችን በማስያዝ በጋራ እና በተናጠል በመሆን በድምሩ አስራ አምስት የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው ያሰሙ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ሰነዶችንም በመከላከያነት አቅርበዋል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም በሁለቱ ወገኖች የቀረበውን አጠቃላይ ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአንደኛ ክስ በተጠሪ የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ በመከላከያቸው ያስተባበሉ መሆኑን ገልጾ በአንደኛ ክስ ከተመለከተው የወንጀል ክስ በነጻ ያሰናበታቸው ሲሆን ይከላከሉ በተባሉባቸው በቀሪዎቹ ክሶች ግን ሶስቱም ተከሳሾች ባሰሟቸው የመከላከያ ምስክሮች በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተመሰከረባቸውን ፍሬ ነገር ለማስተባበለል አልቻሉም በማለት በየክሶቹ በተጠቀሱባቸው ድንጋጌዎች ስር የጥፋተኝነት ውሳኔ በማስተላለፍ ግራ ቀኙ የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡ በመቀጠልም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ካመዛዘነ በኃላ፡-

 

·   1ኛ ተከሳሽ በአንደኛ ክስ ስር በሁለት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት፤በሁለተኛ   ክስ ስር በሶስት ዓመት ጽኑ እስራት፤በሶስተኛ ክስ ስር በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት፤በአራተኛ ክስ ስር በአራት ዓመት ጽኑ እስራት በብር 200,000 መቀጮ በድምሩ በአስራ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እና በብር 200,000 መቀጮ፤

· 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በሶስት ዓመት ጽኑ እስራት(የቅጣት መጠኑን በተመለከተ ብቻ በአብላጫ ድምጽ)፤እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ሶስቱም ተከሳሾች በአንድነት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 54809 ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ከተሰጠው ውሳኔ መካከል በከፊሉ ቅር በመሰኘት በመዝገብ ቁጥር 54810 ይግባኝ አቅርቦአል፡፡ ፍርድ ቤቱም በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለተኛ ክስ በተሰጠባቸው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ሶስቱም ተከሳሾች ያቀረቡትን ይግባኝ በትዕዛዝ የዘጋ ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ እና በተጠሪ መካከል በሁለቱም መዝገቦች የቀረበለትን ክርክር በተመለከተ ግን ክርክሩን በአንድነት ከመረመረ በኃላ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አድርጎ የ1ኛ ተከሳሽን የይግባኝ ክርክር በመቀበል በከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንደኛ፣በሶስተኛ እና በአራተኛ የወንጀል ክሶች ተሰጥቶባቸው  የነበረውን የጥፋተኛነት እና የቅጣት ውሳኔ ሽሮ በነጻ አሰናብቷቸዋል፡፡

ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው በማለት ተጠሪ ባቀረበው አቤቱታ ሳቢያ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 በአንቀጽ 98(1)(ሀ) ተጠቅሶበት የቀረበው ሶስተኛው ክስ ሁለተኛ ይግባኝ ያለው በመሆኑ ምክንያት በሰበር ሊያየው እንደማይችል ገልጾ በማለፍ በአንደኛ እና በአራተኛ የወንጀል ክሶች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ በማጽናት እና በ4ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የተሰጠው የቅጣት መጠን አንሷል በሚል የቀረበውን የዐቃቤ ሕግ አቤቱታ በመቀበል እና ለ4ኛ የወንጀል ክስ ቅጣቱን በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት በማስላት የመቀጮ ውሳኔውን ሳይነካ 1ኛ ተከሳሽ በሁለተኛ ክስ የተሰጠባቸውን የሶስት ዓመት ጽኑ እስራት ጨምሮ በድምሩ በአስራ አራት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ


የሰጠ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ በዚህ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 99883 አቤቱታ ያቀረቡትም ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ በስር የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጣምረው ከቀረቡት ክሶች መካከል አንዱ የተጨማሪ እሴት ታክስን የሚመለከት ከመሆኑ አንጻር ጉዳዩን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ስልጣን ያለው መሆን አለመሆኑን ተጠሪው ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት በአመልካቹ ላይ ከቀረቡት ስድስት የወንጀል ክሶች መካከል ሶስቱ ማለትም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 ተጠቅሶበት የቀረበው ሁለተኛ ክስ፣ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 98(1)(ሀ) ተጠቅሶበት የቀረበው ሶስተኛ ክስ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 50(3)(ለ) ተጠቅሶበት የቀረበው አምስተኛ ክስ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4(4) እና 15(1) ድንጋጌዎች  መሰረት የሚወድቁት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር መሆኑ፣እነዚህ ክሶች ለመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የቻሉትም በሕገ መንግስቱ  በተሰጠው የስልጣን ውክልና መሰረት መሆኑ፣ቀሪዎቹ ሶስት ክሶች በክልሉ የወረዳ ፍርድ የስረ ነገር ስልጣን ስር የሚወድቁ ሆነው ነገር ግን በስልጣን ውክልና መሰረት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ከቀረቡት ክሶች ጋር ተጠቃለው ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 109(3) ድንጋጌ መሰረት መሆኑ እና ይህም ተገቢነት ያለው የክስ አቀራረብ ስርዓት መሆኑ ያላከራከረ ጉዳይ ነው፡፡ ይልቁንም አከራካሪ ሆኖ የቀረበው በአንድ ተከሳሽ ላይ ከቀረቡት ከአንድ በላይ ከሆኑ ክሶች መካከል ከፊሎቹ  የሚወድቁት  በፌዴራል ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር፣ከፊሎቹ ደግሞ በክልል ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር በሆነ ጊዜ እና ነገር ግን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 109(3) ድንጋጌ ስር በተመለከተው የክስ አቀራረብ መርህ መሰረት ተጠቃለው በቀጥታም ሆነ በውክልና በፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲታዩ ተደርገው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ በተመለከተው ፍርድ ቤት በአንድ ወይም በሌላ አግባብ ውሳኔ ከተሰጠባቸው በኃላ ወደ ይግባኝ እና ወደ ሰበር የክርክር ደረጃ ሲደርሱ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደተደረገው ሁሉ ተጠቃለው የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ስርዓት ተከትለው መጠናቀቅ አለባቸው ወይስ እንደየሚወድቁበት የስረ ነገር ስልጣን ሁኔታ ተነጣጥለው ከፊሎቹ የክልል ፍርድ  ቤቶችን፣ከፊሎቹ ደግሞ በፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ስርዓት ተከትለው መጠናቀቅ አለባቸው? የሚለው ዓቢይ ነጥብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ የወጣው በሀገሪቱ ውስጥ የፌዴራል የአስተዳደር ስርዓት እና ይህንኑ ተከትሎ አዲስ የፍርድ ቤቶች አወቃቀር ስርዓት ከመዘርጋቱ ከበርካታ ዓመታት በፊት በመሆኑ የስነ ስርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች በዚህ መዝገብ አከራካሪ ሆኖ ለቀረበው ነጥብ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በመሆኑም የሀገሪቱን አዳዲስ ሁኔታዎች ያገናዘበ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ተቀርጾ ተግባራዊ እስከሚደረግ ድረስ አከራካሪ ሆኖ ከቀረበው ነጥብ ጋር ግንኙነት ያላቸው አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀል የስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ከፌዴራሊዝም ስርዓት እና ይህንኑ ተከትሎ ከተዘረጋው የፍርድ ቤቶች አወቃቀር ጋር በተቻለ መጠን ሁሉ ሊጣጣም በሚችል ሁኔታ እየተተረጎሙ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከማድረግ ውጪ የተሻለ አማራጭ አይኖርም፡፡


በመሰረቱ በአንድ ተከሳሽ ላይ ከአንድ በላይ የሆኑ የወንጀል ክሶች በቀረቡ ጊዜ ክሶቹ በመርህ ደረጃ በአንድነት መታየት የሚገባቸው ስለመሆኑ በስነ ስርዓት ህጉ በቁጥር 116(2) ስር የተቀመጠው ድንጋጌ ዓይነተኛ ዓላማ በአንድ በኩል በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እና መዝገቦች በአንድ ተከሳሽ ላይ ለየብቻ የቀረቡትን ከአንድ በላይ የሆኑ ክሶች በማስተናገድ ሊባክን ይችል የነበረውን ጊዜ እና ሀብት በማዳን ለተከራካሪ ወገኖችም ሆነ ለምስክሮች ምቹ በሆነ ሁኔታ የተቀላጠፈ ፍትሕ እንዲሰጥ ለማስቻል እና በሌላ በኩል ደግሞ በክሶቹ ተነጣጥሎ መታየት ሳቢያ በክሱ ክትትል ረገድም ሆነ የጥፋተኝነት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ በቅጣት አጣጣል ረገድ በተከሳሽ ወገን ላይ ሊደርስ የሚችለውን አላስፈላጊ ጉዳት በተቻለ መጠን ለማስወገድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 109(3) ድንጋጌ ስር ከተመለከተው የክስ አቀራረብ መርህ አንጸር ከላይ የተጠቀሰው የቁጥር 116(2) ድንጋጌ ዓላማ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ ተጠቃለው የታዩት ክሶች ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ በተመለከተው ፍርድ ቤት በአንድ ወይም በሌላ አግባብ ውሳኔ ከተሰጠባቸው በኃላ ወደ ይግባኝ እና ወደ ሰበር የክርክር ደረጃ ሲደርሱ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደተደረገው ሁሉ ተጠቃለው የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ስርዓት ተከትለው እልባት እንዲያገኙ ሲደረግ ነው፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ የመቀሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሶቹን አጠቃሎ የተመለከተው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣኑ መሆኑን በመግለጽ የክልሉ ሰበር ችሎት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቅ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ ከአመልካች የቀረበለትን መቃወሚያ ሰበር ችሎቱ ሳይቀበል የቀረው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቁ ናቸው ከተባሉት መካከል 2ኛውን ክስ አስመልክቶ የቀረበለት አቤቱታ አለመኖሩን እና 3ኛው ክስ ደግሞ የይግባኝ ስርዓቱ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ምክንያት በሰበር ሊታይ የማይችል መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ ይህ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አቋም ደግሞ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ በተመለከተው ፍርድ ቤት ተጠቃለው እንዲታዩ የተደረጉት የወንጀል ጉዳዮች በይግባኝ እና በሰበር የክርክር ደረጃ ሲደርሱ  እንደየሚወድቁበት የስረ ነገር ስልጣን ሁኔታ ከፊሎቹ የክልል ፍርድ ቤቶችን፣ ከፊሎቹ ደግሞ በፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ስርዓት ተከትለው እና ተነጣጥለው የሚታዩበትን አሰራር የሚፈጥር በመሆኑ እና የስነ ስርዓት ሕጉን ቁጥር 109(3) እና 116(2) ድንጋጌዎች ዓላማ የሚያሳካ ባለመሆኑ የተሻለ የክርክር አመራር አማራጭ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡

 

ሲጠቃለል የመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣኑ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 109(3) እና 116(2) ድንጋጌዎች መሰረት አጠቃሎ በማየት በአንድ ወይም በሌላ አግባብ ውሳኔ የሰጠባቸው ከፊሎቹ በክልል፣ከፊሎቹ ደግሞ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር የሚወድቁ የወንጀል ጉዳዮች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑ በይግባኝ አይቶ በአንድ ወይም በሌላ አግባብ ውሳኔ ከሰጠባቸው በኃላ ቀጥሎ ባለው የክርክር ሂደት መታየት የሚገባቸው በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደተደረገው ሁሉ ተጠቃለው የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ስርዓት ተከትለው መሆን ሲገባው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የቀረበለትን መቃወሚያ ባለመቀበል በክልሉ ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር የሚወድቁ ናቸው በማለት የቀረበለትን የሰበር አቤቱታ ተቀብሎ በከፊሎቹ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠቱ በክርክር አመራር ረገድ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡


 

 

 

 

 

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የትግራይ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 63092 በ12/07/2006 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ ከላይ በተጠቀሰው ስነ ስርዓታዊ ምክንያት በአብላጫ ድምጽ ተሽሯል፡፡

2. የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣኑ ከፌዴራል ጉዳይ ጋር በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 109(3) ድንጋጌ መሰረት አጠቃሎ ያየውን የክልል ጉዳይ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር የማየት ስልጣን የለውም በማለት ወስነናል፡፡

3. በአንድ ተከሳሽ ላይ ከቀረቡት ከአንድ በላይ ከሆኑ ክሶች መካከል ከፊሎቹ የሚወድቁት በፌዴራል ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር፣ከፊሎቹ ደግሞ በክልል ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር በሆነ ጊዜ እና ነገር ግን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 109(3) ድንጋጌ ስር በተመለከተው የክስ አቀራረብ መርህ መሰረት ተጠቃለው በቀጥታም ሆነ በውክልና በፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲታዩ ተደርጎ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ በተመለከተው ፍርድ ቤት በአንድ ወይም በሌላ አግባብ ውሳኔ ከተሰጠባቸው በኃላ ወደ ይግባኝ እና ወደ ሰበር የክርክር ደረጃ ሲደርሱ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደተደረገው ሁሉ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የይግባኝ እና የሰበር ስርዓት ተከትለው እና ተጠቃለው መታየት አለባቸው በማለት ወስነናል፡፡

4. እንዲያውቀው የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለትግራይ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ይላክ፡፡

5.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 የሃ ሳብ ል ዩነ ት

 

እኔ ስሜ በተራ ቁጥር ሁለት የተገለጸው ዳኛከአብላጫው ድምጽ በተሰጠው የህግ ትርጉምና ውሳኔ ያልተስማማሁ በመሆኔ በሃሳብ ተለይቻለሁ፡፡ የስራ ባልደረቦቼ ከሰጡት የህግ ትርጉምና ከደረሱበት መደምደሚያ የተለየሁባቸውምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

1. ከአብላጫው ድምጽ በውሳኔ እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና  ጉምሩክ ባለስልጣን ውክልና ያለው የክልሉ ዐቃቤ ህግ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 622/2001 የተመለከተውን በመተላለፍ፣ ከግብር ነጻ ያስገባውን የግንባታ ማቴሪያል፣ ለሌሎች ሰዎች  አሳልፎ በመስጠት ወይም በመሸጥ ወንጀል እንደፈጸመና፣ የአዋጅ ቁጥር 285/1994 ድንጋጌዎች እንደተሻሻሉና አዋጅ ቁ.286/1994 የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል የፈጸመ መሆኑን፣የአዋጅ ቁጥር 686/2002 ድንጋጌ በመተላለፍ የጸና ንግድ ፍቃድ ሳይኖረው የንግድ ስራ በማከናወን ወንጀል የፈጸሙ መሆኑን የሚዘረዝር የወንጀል ክስ ለመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል የክልሉ አቃቤ ህግ በአመልካች ላይ ያቀረባቸው የወንጀል   ክሶች


መካከል ከፊሎቹ በፌዴራል ፍ/ቤቶች የወንጀል የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቁና ክፊሎቹ ደግሞ በክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት /የወረዳ ፍ/ቤት/ የዳኝነት የስር ነገር ስልጣን ስር የሚወድቁ መሆናቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡

2. እያከራከረ ያለው፣ የክልሉ አቃቤ ህግ በክልል ፍ/ቤቶች የወንጀል የዳኝነት ስልጣን ስር እና በወረዳው ፍ/ቤት የዳኝነት የስር ነገር ስልጣን ስር የሚወድቁትን የወንጀል ክሶች፣ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 109 ንዑስ አንቀጽ 3 እና የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 117 በሚደነገገው መሰረት በአንድ ላይ አጠቃልሎ ለመቀሌ ከተማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ማቅረብና የዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትም ያቀረበለትን የወንጀል ክሶች በመቀበል ፣የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ ውሳኔ መስጠቱ፣ ጉዳዩ በይግባኝ እና በሰበር ታይቶ በሚወሰንበት ስርዓትና በክልል ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ላይ የሚኖረው ውጤት ምንድን ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡

 

3.  ተጠሪ የፌዴራል ወንጀል የሆኑትንና የክልሉን ወንጀል የሆኑትን ጉዳዮች በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.

109 ንዑስ አንቀጽ /3/ መሰረት በማጣመር ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበው ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በኢ.ፈ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80 ንዑስአንቀጽ 4 ከክልል የዳኝነት ስልጣን በተጨማሪ የተሰጠው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ስልጣኑ በመጠቀም የወንጀል ክሶቹን አይቶ እንዲወስንና ከዚህ ጎን ለጎን በኢፊዲሪ ህግ መንግስት አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 7 በክልሉ ህገ መንግስትና በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በተሰጠው ክልልዊ የዳኝነት ሥልጣኑ መሠረት የፌዴራሉንና የክልሉን የወንጀል ጉዳዮች ጎን በጎን እውነት ፍርድ እንዲሰጥባቸው በማሰብ እንደሆነ ተጣምረው ከቀረቡለት የወንጀል ክሶች ይዘት ሙሉ መሠረታዊ ባህሪ፤ ከሕገ መንግስቱና ከአዋጅ ቁጥር 25/1988 ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡

4. በእርግጥ የክልል ዐቃቤ ህግ የፌዴራል የክልል የወንጀል ጉዳዮች አጣምሮ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለማቅረብ መሠረት አድርጎ የሚከራከረው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በጠቅላላውና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 109 ንዑስ አንቀፅ 3፣ አንቀፅ 117 እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች አገሪቱ፣ አህዳዊ ቅርፀ መንግስት ትተዳደር በነበረበት ጊዜና የዳኝነት ሥልጣንም በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ተጠቃሎ ተይዞ በነበረበት 1954 ዓ/ም የታወጁ ናቸው፡፡ እነዚህን እድሜ ጠገብ ድንጋጌዎች የመንግስት ስልጣን በፌዴራልና በክልል በተዋቀረበትና የዳኝነት ሥልጣንም በፌዴራልና በክልል ደረጃ ተከፍሎ ተግባራዊ በሆነበት ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ተፈፃሚ ሲያረጉ በሕገመንግስቱ አንቀፅ 50 ንዑስ አንቀፅ 2 እና ንዑስ አንቀጽ 7 አንቀጽ 78 እንደዚሁም የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀፅ 2 እና ንዑስ አንቀጽ 3 (ለ) ንዑስ አንቀጽ 3 እና ንዑስ አንቀጽ 4 የተደነገጉትን መሠረታዊ መርሆች  በማይጥስ  ወይም በማይሸራርፍ መንገድ መተርጎምና ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል የሚል እምነት አለኝ፡፡

5. ከዚህ አንፃር ሲታይ የመቀሌ ከተማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 109 ንዑስ አንቀፅ 3 እና የወ/መ/ሥ/ሥ/ ሕግ ቁጥር 117 መሠረት አጣምሮ ካቀረበለት የወንጀል ክሶች መካከል፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል የዳኝነት ሥልጣን ስር የሚወድቁትን የወንጀል ክሶች በሕገመንግስት አንቀፅ 88 ንዑስ አንቀፅ 4 ካለው ክልልዊ የዳኝነት ሥልጣን በተጨማሪ ተደርቦ የተሰጠውን የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን በመጠቀም አይቶ አከራክሮና መርምሮ ፍርድ ሰጥቶበታል ተብሎ ሊያዝ የሚገባው ነው፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ሥር ከሚወድቁ የወንጀል ጉዳዮች ጋር በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 109 ንዑስ


አንቀፅ 3 መሠረት ተጣምረው የቀረቡትን በክልል የዳኝነት ስልጣን ሥር የሚወድቁ የወንጀል ክሶች የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 50 ንዑስ አንቀፅ 2 እና ንዑስ አንቀጽ 7 በክልሉ ሕገ መንግስትና ሌሎች ክልላዊ የሕግ ማዕቀፎች የተሠጠውን ክልላዊ የዳኝነት ስልጣን በመጠቀም ጉዳዮችን አይቶ አከራክሮና በማስረጃ አጣርቶ ፍርድ ሰጥቶበታል የሚል ግንዛቤ ሊይዝ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

6. የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያለውን የፌዴራልና የክልል የዳኝነት ስልጣን መሰረት በማድረግ የሰጠው ፍርድ በይግባኝ አይቶ የወሰነው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ ይግባኙን መርምሮ ውሳኔ የሰጠው በሕገ መንግስቱና ሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ድርብ የዳኝነት ሥልጣን መሰረት በማድረግ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 4 እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 የተሰጠውን የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣኑ አይቶ በሰጠው ፍርድ ላይ ተጠሪ ያቀረበውን የይግባኝ ቅሬታ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 2 በተጨማሪነት በተሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣኑንና በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 5 የተሰጠውን የፌዴራል የይግባኝ የዳኝነት ስልጣን በመጠቀም ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ በሌላ በኩል የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከፌዴራል የወንጀል ክሶች ጋር ተጣምረው በቀረቡለት የክልል የወንጀል ክሶች ላይ በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት የቀረበለትን የይግባኝ ቅሬታ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 7፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 6 በክልሉ ሕገ መንግሰትና በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሰጠውን ክልላዊ የይግባኝ የዳኝነት ስልጣኑን መሰረት በማድረግ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

7. ተጠሪ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ላይ የቀረበውን ጥቅል የይግባኝ ቅሬታ አይቶ ውሳኔ ሲሰጥ፣ ይግባኝ ሰሚው ችሎት በፌዴራል የይግባኝ የዳኝነት ስልጣኑ አይቶ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ተፈፅሟል የሚለውን መሰረታዊ የሕግ ስህተትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት በክልል የይግባኝ የዳኝነት ስልጣኑ አይቶ ውሳኔ በሰጠባቸው ክልላዊ የወንጀል ጉዳዮች  ላይ ፈፅሟል የሚለውን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት፣ በሰበር አይቶ እንዲያርምለት ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን መዝገቡ ያሳያል፡፡ ሆኖም የክልሉ ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በተጠሪ በኩል የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ይዘትና ከላይ የገለፅናቸውን የሕገመንግስቱን ድንጋጌዎች በማገናዘብ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ስልጣኑ አይቶ ውሳኔ የሰጠባቸውና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ይግባኝ የዳኝነት ስልጣኑ አይቶ ያሻሻላቸው ወይም በሻራቸው የፌዴራል የወንጀል ጉዳዮች በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እንዲታይለት ተጠሪ ማቅረቡ ህጋዊ መሰረት የሌለውና ተጠሪ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 5 በተደነገገው መሰረት ይግባኙን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማቅረብ እንዳለበት ገልፆ የተጠሪን የሰበር አቤቱታ ውድቅ ያደረገው መሆኑን ፣የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተደራቢ የዳኝነት ስልጣኑ አይቶ ውሳኔ በሰጠባቸው የፌዴራል ወንጀሎች ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በክልል የዳኝነት  ሥልጣኑ በተጨማሪነት በተሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌዴራል የይግባኝ ሥልጣኑ መሠረት አይቶ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል ዳኝነት ሥልጣኑ የሰጠውን ውሳኔ ባፀናባቸው  ጉዳዮች

፣ጉዳዩን በሰበር አይቶ የመወሰን ሥልጣን የሌለው መሆኑንና የሰበር አቤቱታው   መቅረብ


የሚገባው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እንደሆነ በመግልፅ የወሰነ መሆኑን መዝገቡ ያሣያል

8. የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ፣ተጠሪ የሰበር አቤቱታ ካቀረበባቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ፍርድ ከሰጡባቸው የወንጀል ጉዳዮች ውስጥ በሰበር አይቶው ውሣኔ የሰጠበት ተጠሪ ከፌዴራል የወንጀል ጉዳዮች ጋር በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 109 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት አጣምሮ ክስ ያቀረበባቸውን በክልሉ ፍርድ ቤቶች የወንጀል የዳኝነት ስልጣን ሥር የሚወድቁ ክልላዊ የወንጀል ጉዳዮች ላይ የሆኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክልላዊ የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣኑን በመጠቀም ይግባኝ ሰሚው ችሎት ደግሞ ክልላዊ የይግባኝ የዳኝነት ሥልጣኑን በመጠቀም በሰጡት ፍርድ ላይ የተፈፀመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለመሆኑን በማጣራት ነው፡፡ ይህም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 80 ንዑስ አንቀፅ 2 የተሰጠውን በክልል ጉዳይ ላይ ያለውን የበላይና የመጨረሻ ሥልጣንና በሕገ መንግስቱ አንቀፅ  80 ንዑስ አንቀፅ 3(ለ) የተሰጠውን የሰበር ሥልጣን መሠረት ያደረገና የሕግ ስህተት የሌለበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

9. የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነውን ውሳኔ የሰጠው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 109 ተጣምረው  ከቀረቡላቸው የፌዴራልና የክልል የወንጀል ክሶች፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት በሕገ መንግስቱ ተደርቦ የተሰጣቸውን የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃና የይግባኝ የዳኝነት ሥልጣን መሠረት በማድረግ ፍርድ የሰጡባቸውን የፌዴራል የወንጀል ጉዳዮች በሰበር አይቶ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የሌለው መሆኑን በግልፅ ለይቶ አውጥቶ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የሌለው መሆኑን በመወሰንና ከተጣመሩት የወንጀል ክሶች ውስጥ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት በክልል የዳኝነት ሥልጣናቸው አይተው ውሣኔ የሰጡባቸውን የወንጀል ጉዳዮች ላይ የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ብቻ በመመርመር ነው፡፡ በእኔ እምነት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 109 ንዑስ አንቀፅ /3/ እና በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 117 መሰረት ተጣምረው ያቀረቡለትን የፌዴራልና የወንጀል ክሶችን በአንድ ላይ አይቶ የመወሰን ድርብ የዳኝነት ስልጣን ላለው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጣምረው መቅረባቸው፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል የወንጀል ክሶችን ከክልል የዳኝነት ስልጣኑ  በተጨማሪ በሕገ መንግስቱ በተሰጠው የፌዴራል የዳኝነት ስልጣኑ፣ የክልል የወንጀል ክሶችን ደግሞ በክልል የወንጀል የዳኝነት ስልጣን አይቶ ውሳኔ ለመስጠት፣ በሁሉም የወንጀል ጉዳዮች የሚቀርበውን ክርክር አንድ ላይና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመስማትና የመወሰን እድል ከመፍጠር ውጭ ከፌዴራል የወንጀል ክስ ጋር ተጣምሮ የወንጀል ክስ የቀረበበትን የክልል የወንጀል ጉዳይ ወደ ፌዴራል ወንጀልነት የመቀየር ውጤት አይኖረውም፡፡

10. የክልሉ ጉዳዮች ከፌዴራል የወንጀል ጉዳይ ጋር ተጣምሮ ክስ ያቀረበበት መሆኑ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክልላዊ የዳኝነት ስልጣኑ አይቶ ውሳኔ በሰጠባቸው የክልል የወንጀል ክሶች ላይ የሰጠውን ፍርድ፣ ክልላዊ የሆነ የይግባኝና የሰበር የዳኝነት ስልጣን ያላቸው የክልሉ ፍርድ ቤቶች፣ ክልላዊ የሆነ በይግባኝና በሰበር አይተው ጉዳዩን ከመወሰን የሚገድባቸው አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ በዚህ ጉዳይ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 8ዐ ንዑስ አንቀፅ 2 እና ንዑስ አንቀፅ 3/ለ/ የተሰጠው ክልላዊ የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቁ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ውሳኔዎች በሰበር በማየትና ክልላዊ የዳኝነት ስልጣኑን በአግባቡ ከመጠቀም ውጭ የፈፀመው መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለ ብዬ ስለማላምን በሃሳብ ተለይቻለሁ፡፡


በዚህ ጉዳይ የቀረበው አከራካሪና መሰረታዊ የክልልና የፌዴራል የዳኝነት ስልጣን ጭብጥ፣ ይኽ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 91327 ውሳኔ ከሰጠበት ጉዳይ የሚለይባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ይኽው የሰበር መዝገብ ቁጥር 91327 የቀረበውን ጉዳይ በመጀመሪያ አይቶ ውሳኔ የሰጠው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወ/መሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 109 ንዑስ አንቀፅ 3 መሰረት ተጣምረው የቀረቡለትን ሁሉንም የፌዴራልና የክልል የወንጀል ጉዳዮች በዳኝነት አይቶ ለመወሰን የማያስችለው ድርብ የዳኝነት ስልጣንና የስረ ነገር ስልጣን የሌለው መሆኑ ነው፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ሕግ አንቀፅ 24ዐ ተጠቅሶና ከክልል የወንጀል ጉዳይ ጋር ተጣምሮ የቀረበለትን የወንጀል ክስ፣ አይቶ የመወሰን ስልጣን በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 8ዐ ንዑስ አንቀፅ 4 መሰረት ያልተሰጠው ቢሆንም፣ ከሌሎች የክልል ጉዳዮች ጋር አጣምሮ በማየት ውሣኔ ሰጥቶበታል፡፡ይህንን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕግ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን ሥር የሚወድቅ የፌደራል ወንጀል የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አይቶ መወሰኑ ስህተት መሆኑን በመረዳት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት ስህተቱንየማረምስራባለመሻራቸውናበፍርድ የፈፀመውን ስህተት  ባለማረማቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ዉሣኔ የዚህ ሰበር ችሎት ሙሉ በሙሉ እንዲሻር ውሣኔ የተሰጠበት መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡

 

11. በያዝነው ጉዳይ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ተጣምሮ የቀረበውን የወንጀል ክስ በዳኝነት አይተው ውሣኔ የሰጡት ፣ጉዳዩን ለማየት ክልላዊ የዳኝነት ሥልጣንና በተደራቢ የሆነ የፌደራል የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ ነው፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎትም በሰበር አይቶ የወሰነው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በክልል የዳኝነት ሥልጣናቸው አይተው የወሰኗቸዉን የክልል የወንጀል ጉዳዬች ብቻ ለይቶና መርጦ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ተጠሪ የወንጀል ክሱንም ሆነ የይግባኝ ቅሬታውን እንደወንጀሎች መሠረታዊ ባህሪ በመለየት፣በሁለት የተለያዩ መዝገቦች አለማቅረቡና የወንጀል ክሶችን አጣምሮ በአንድ ላይ ማቅረቡ ጉዳዬቹን አይቶ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ናቸው ከሚለው መደምደሚያ ላይ ያደርሳል የሚል እምነት የሌለኝ በመሆኑ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የተሰጠው ውሣኔ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 7 የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 2 እና ንዑስ አንቀፅ 3 (ለ) መሠረት ያደረገ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሌለበት ነው በማለት በሀሳብ ተለይቻለሁ፡፡

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ብ/ግ