103448 criminal law/ sentencing/ sentencing guideline

በወንጀል የቅጣት አወሳሰን ጊዜ የቅጣት መነሻ ለማግኘት ቀላል
የእስራት ቅጣትን ወደ ፅኑ እስራት መለወጥ የሚያሥፈልገው
ወንጀለኛው ጥፋተኛ የተባለው በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ
ወንጀሎች ሲሆንና አንዱ ወንጀል በቀላል እስራት ሌላው ደግሞ በፅኑ
እስራት የሚያስቀጣ በሆነ ጊዜ ብቻ ስለመሆኑ፡-
የተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ.2/2006
የወ/ሕ/አንቀፅ 184(1(ለ))

የሰ/መ/ቁ/103448

የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዳኞች:-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ አገኘሁ አስፋው የቀረበ የለም

 

ተጠሪ፡- የፌዴራል አቃቤ ሕግ - ወይን ገ/እግኢአብሄር  ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ በሰው ሕይወትና አካል ላይ በቸልለተኝት ጉዳት ማድረስን የሚመለከት የወንጀል ክርክር ሲሆን ክርክሩ የጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ የመሰረተው በአምስት ምድብ የተከፈለ ክስ ነው፡፡

 

1ኛክስ፡-በ1996 ዓ.ም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(3) እና የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 208/2003 አንቀጽ 13(ሀ) የተመለከተዉን በመተላለፍ አመልካቹ አሽከርካሪ በመሆኑ የሌላን ሰዉ የሕይወት ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እያለባቸው በ03/06/2005 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 9፡40 ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ/ወረዳ 01 ልዩ ቦታዉ ቻይና ካምፕ መታጠፊያ አካባቢ የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-15006 ኦ/ሮ የሆነ ተሸከርካሪ ይዞ ከአየር ጤና ወደ ሳሪስ አቦ አቅጣጫ እያሽከረከረ ሲጓዝ ከተሸከርካሪ መንገድ ዉጭ በመዉጣት በእግረኛ መንገድ ላይ ስትጓዝ የነበረችዉን ህጻን ሕይወት ዳዲ የተባለችዉን በሚያሽከረክረዉ መኪና የፊት አካል ገጭቶ በመግደሉ በቸልተኝነት ሰዉ መግደል ወንጀል ፈጽሟል የሚል ነዉ፡፡

 

2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ክሶች በተመሳሳይ የወ/ሕ/ አንቀጽ 559(2) የተመለከተዉን በመተላለፍ በ1ኛ ክስ በተጠቀሰዉ ጊዜ፣ ቦታና እንዲሁም በቸልተኝነት የድርጊት አፈፃጸም በ2ኛ ክስ የግል ተበዳይ በነበረችው ህጻን ብሩክታዊት ተስፋዬ የጆሮ ታምቡር መቀደድ ጉዳት አድርሷል፣በ3ኛ ክስ ተበዳይ በነበረችዉ ህጻን ሳምራዊት በቀለ ላይ የለስላሳ ጡንቻ ጉዳት አድርሷል፤ በ4ኛ ክስ ተበዳይ በነበረችዉ ህጻን ቅድስት አስማማዉ ላይ የለስላሳ ጡንቻ ጉዳት አድርሷል፤ እንዲሁም በ5ኛ ክስ ተበዳይ በነበረችዉ ህጻን ዋጋዬ ወቼሬ ላይ የለስላሳ ጡንቻ ጉዳት አድርሷ የሚል ነው፡፡


አመልካች የቀረበባቸዉ ክስ ደርሷቸዉ በግልጽ ችሎት ተነቦላቸው እንዲረዱት ከተደረገ በኃላ በሥር ፍርድ ቤት የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ሲጠየቁ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ ክደው የተከራከሩ ሲሆን ተጠሪም አሉኝ ያላቸውን የሠውና የሠነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ አቃቤ ሕግ እንደክሱ ማስረዳቱን በመገንዘብ አመልካች የመከላከያ ማስረጃ እንዲያስሙ መብታቸውን የጠበቀላቸው ሲሆን አመልካችም አሉኝ ያሏቸውን ማስረጃዎች አቅርበው አሰምተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግንና የአመልካችን የሰዉና የሰነድ ማስረጃዎች ሰምቶና መርምሮ አመልካችን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን በመከላከያ ማስረጃዎቹ ያለማስተባበላቸውን ጠቅሶ የመከላከያ ማስረጃዎቹን ክብደት ሳይሰጥ ያለፈ ሲሆን አመልካችን በዐቃቤ ሕግ ተጠቅሶ በቀረበባቸው ክሶች በመሉ ጥፋተኛ አድርጎ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለና ከወንጀል ሕጉ እንዲሁም ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ ጋር አገንዝቦ መመልከቱን ከጠቀሰ በኃላ አመልካችን በ6 ዓመት ጽኑ እስራት እና በብር 5,000 የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ከዚህም በኋላ አመልካች የይግባኝ አቤቱታቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱም ጉዳዩን መርምሮ 1ኛ ክስን በተመለከተ አመልካች ጥፋተኛ ሊባሉ የሚገባው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(3) ድንጋጌ ሳይሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(2) መሆኑን፣በ3ኛ እና 5ኛ ክሶችም በአቃቤ ሕግ ክሱ የተነሳ መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ ጥፋተኛ ሊባሉ እንደማይችሉ፣በ2ኛ እና በ4ኛ ክሶች ጥፋተኛ የተባሉት ግን ተገቢ መሆኑን ገልፆ የጥፋተኝነት ውሳኔ በዚህ አግባብ ከአሻሻለ በኃላ ቅጣቱን በተመለከተም አመልካች የወንጀል ሪከርድ ያልቀረበባቸው መሆኑና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው እንዲሁም ከግል ተበዳይ ህፃናት ወላጆች ጋር እርቅ መፈፀማቸውን በሶስት ቅጣት ማቅለያነት ሊያዝላቸው እንደሚገባ ጠቅሶ በአንደኛው ክስ በሶስት አመት እስራት፣በ2ኛ እና በ4ኛ ክሶች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው አንድ አመት እስራት ይዞና እነዚህን ጊዜያት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84(1(ለ) ድንጋጌ ደምሮ መነሻ ቅጣቱን አምስት አመት አድርጎ ይኼው መነሻ ቅጣት በእከርን ሃያ እንደሚያርፍና በሶስት ማቅለያ ምክንያቶች ደግሞ ወደ እርከን አስራ ሰባት እንደሚወርድ ጠቅሶ በዚሁ የቅጣት እርከን ውስጥ ካለው ሬንጅ ውስጥ አመልካች ሊቀጡ የሚገባው ሶስት አመት ከስድስት ወር እስራት ነው፣ የገንዘብ መቀጮውን በተመለከተ ደግሞ ብር 2000.00 ሊሆን ይገባል በማለት ወስኗል፡፡

 

የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ በወንጀል ሕጉም ሆነ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ላይ የተቀመጠውን ያላገናዘበ ነው የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በአመልካች ላይ የተጣለው የቅጣት ውሳኔ ሕጉን የተከተለ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርቦም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆኑትን የበታች ፍርድ ቤቶችን የውሳኔ ክፍሎችን አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስልጉ ጭብጮች፡-

 

1. አመልካች ለ2ኛ እና 4ኛ ክሶች ጥፋተኛ ተብለው በመነሻ ቅጣትን የተያዘው ጊዜ ወደ ፅኑ እስራት ሳይቀር ከ1ኛው ክስ ጋር ተደምሮ መነሻ ቅጣቱ መያዙ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም?


2. እያንዳንዱ ቅጣት ማቅለያ የሚያስቀንሰው 1 እርከን ወይስ 2 እርከን ነው? የሚሉት ሁነው አግኝቷል፡፡

 የ መጀ መሪያ ውን ጭ ብጥ በተመ ለከተ፡ -

 

አመልካች በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(2) እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 559(2) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል ተብለው በሶስት ክሶች ነው፡፡እነዚህ ድንጋጌዎች የሚያስቀጡት በቀላል እስራት መሆኑን ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡በመሆኑም የመነሻ ቅጣቱ ሲወሰን ለእያንዳንዱ የወንጀል ድንጋጌ ከተለየ በኋላ ተደምሮ የሚመጣው ውጤት ሲሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84(1(ለ)) ድንጋጌ መሰረት እንደተመለከተው በቅጣት አደማመር ጊዜ በጽኑ እስራትና ቀላል እስራት በሚያስቀጡ ድንጋጌዎች አንድ ሰው ጥፋተኛ ከተባለ በቅድሚያ የቀላል እስራት ቅጣት ወደ ጽኑ እስራት መለወጥ አለበት፡፡ይህ ስሌት ተፈጻሚ መሆን እንደአለበትም ተሻሽሎ የወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያም በአንቀጽ 22 ስር ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡የወንጀል ሕጉም ሆነ የቅጣት መመሪያው አንድ ሰው በቀላል እስራት በሚያስቀጡ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ አድራጎቶች ጥፋተኛ ከተባለ ለእያንዳንዱ አድራጎት የሚጣለው ቅጣት ወደ ጽኑ እስራት መለወጥ ያለበት መሆኑን አይገልፁም፡፡በመሆኑም አመልካች ጥፋተኛ የተባሉባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(2) እና 559(2) ድንጋጌ የሚያስቀጡት በቀላል አስራት በመሆኑ ለእያንዳንዱ ድንጋጌ መነሻ ቅጣቱ ተወስኖ ከሚደመሩ በስተቀር የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 559(2) ድንጋጌ ቅጣት ወደ ፅኑ እስራት ተቀይሮ ለወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(2) ለመነሻነት ከተያዘው ቅጣት ጋር የሚደመርበት የሕግ አግባብ የሌለ በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ቅሬታ አልተቀበልነውም፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በ ተመ ለከተ፡ -አመልካች ጥፋተኛ የተባሉባቸው የህግ ድንጋጌዎች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሻሽሎ በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 የወንጀሉ ደረጃ የወጣላቸው ሲሆን የስር ፍርድ ቤትም ሆነ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ቅጣቱን በዚህ መመሪያ መሰረት ማስላቱን ተመልክተናል፡፡በክስ አንድ አመልካች የፈፀሙት አድራጎት የወንጀሉ ደረጃ አራት ሲሆን ይህም የቅጣት መነሻ እርከኑ 16 ስር የሚወድቅ ነው፡፡ለ2ኛ እና 4ኛ ክሶች ደግሞ ደረጃ 1 እርከን 7 የሚያርፍ ነው፡፡በእነዚህ እርከኖች ፍርድ ቤቶች ለእያንዳንዱ መነሻ ቅጣት ከለየ በኋላ ድምሩ አምስት አመት እስራት መሆኑን የገለፀ ይህም በእርከን ሃያ ስር የሚወድቅ ሁኖ በዚህ እርከን ስር ደግሞ ለፍርድ ቤቱ የተተወው ፍቅድ ስልጣን አራት አመት ከአምስት ወር እስከ አምስት አመት ከአራት ወራት እስራት ነው፡፡ይህንኑ ይዘን ወደ ቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች ስንመጣ በተጠሪ በኩል የቀረበ ማክበጃ ምክንያት የሌለ ሲሆን አመልካች ሪኮርድ የሌለባቸው መሆኑን፣ከግል ተበዳይ ህፃናት ወላጆች ጋር መታረቃቸውና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በቅጣት ማቅለያ ምክንያትነት ተይዞላቸዋል፡፡በመሆኑም አመልካች የሚኖራቸው የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ብዛት ሶስት ይሆናሉ፡፡እነዚህ ማቅለያ ምክንያቶችም በመመሪያ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ 23(4) ድንጋጌ መሰረት በጠቅላላው ሶስት እርከን የሚያስቀንሱ ይሆናል፡፡ ሆኖም አመልካች ጥፋተኛ የተባሉባቸው ድንጋጌዎች ድርጊቱ በተፈጸመበት የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ/ም ተፈጻሚነት በነበረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት የቅጣት ማቅለያ ዋጋ አያያዝ ከተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ የተለየ ነው፡፡በዚህም ምክንያት እኛም የቅጣት ማቅለያ ዋጋ አያያዝን ከወንጀል ሕጉ አንቀፅ 6 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አንጻር ለአመልካች የተሻለ ሁኖ ያገኘነው ነባሩ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ በመሆኑ የቅጣቱን መጠን ከዚሁ አንፃር ተመልክተናል፡፡


ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች እንዲቀጡ በመነሻነት የሚያዘው እርከን 20 በመሆኑ በዚህ እርከን መነሻ ሲያዝ የቅጣት መጠኑ ከአንድ አመት በላይ እና ከሰባት አመት በታች በመሆኑ አመልካች ያላቸው ሶስት የቅጣት ማቅለያዎች በመመሪያ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 16(6) ድንጋጌ መሰረት እያንዳንዳቸው ሶስት እርከን የሚያስቀንሱ በመሆኑ ከእርከን 20 ወደ እርከን 14 መውረድን፣ በዚህ እርከን ውስጥ ተገቢውን ቅጣት መወሰን የሚጠይቅ ነው፡፡

 

በዚሁ መሰረት ቅጣቱን ስናሰላው አመልካች ሊቀጡ የሚገባው በእርከን 14 ስር ለፍርድ ቤቱ በተተወው የፍቅድ ስልጣን ማለትም ከሁለት አመት ከስድስት ወር እስከ ሶስት አመት እስራት ውስጥ ነው፡፡ከእነዚህ የእስራት ጊዜያት አመልካችን ያርማል፣ሌሎች መሰል አጥፊዎችን ከወዲሁ ያስጠንቅቃል ብለን ያመነው ሶስት አመት ቀላል እስራት ሁኖ አግኝተናል፡፡ሲጠቃለልም ከላይ በዝርዝር በተመለከቱት ህጋዊ ምክንያቶች የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው  ሳ ኔ

 

1. በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 133523 ጥር 21 እና 29 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 98818 ግንቦት 29 ቀን 2006 ዓ/ም ተሻሻሎ የተወሰነው ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195(2)(ለ-2) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. አመልካች በ1ኛ፣ በ2ኛ እና 4ኛ ክሶች በተናጠል ጥፋተኛ መባላቸው ተገቢ ነው ብለናል፡፡ቅጣቱን በተመለከተም ለእያንዳንዳቸው መነሻ ቅጣቱ ከተለየ በኋላ ወደ ፅኑ እስራት ሳይቀየር መደመራቸው ተገቢ ነው ብለናል፡፡የቅጣት ማቅለያ ዋጋ አያያዝን በተመለከተ ግን ሶስት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች የሚያስቀንሱት ስድስት እርከን በመሆኑ ከእርከን 20 ወደ አርከን 14 በመውረድ በዚሁ እርከን ውስጥ በሶስት አመት እስራት እንዲቀጡ ብለናል፡፡የገንዘብ መቀጮውን በተመለከተ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ጸንቷል፡፡

3. አመልካች በጉዳዩ የታሰሩት የሚታሰብላቸው ሁኖ በዚህ ችሎት በተወሰነው የእስራት ቅጣት መሰረት ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ይገለጽለት ብለናል፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

 

ሩ/ለ