103452 criminal procedure/ preliminary objection/ amendment of charge

አንድ በወንጀል ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው ቅጣት በሚያከብድ የህግ
ድንጋጌ ስለተከሰስኩ ክሱ ይሻሻልልኝ በማለት ተቃውሞ ካቀረበ
ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ፍ/ቤቱ የሚወስነው እንጂ ከጅምሩ ማስረጃ
ሳይሰማ አቋም የሚወሰድበት እና ክሱ ይሻሻል ተብሎ የሚታዘዝ
ስላለመሆኑ፣

የሰ/መ/ቁ 103452 ቀን ጥር 19/2007 ዓ.ም

ዳኞች፡-  አቶ አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ጥዑም ተኬ ገብራይ ጠበቃ ሀብታሙ ንጉሴ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- የፌዴራል ሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የዐቃቤ ሕግ የድሬደዋ ምድብ ዋልተንጉስ ፍቅሬ - ቀረቡ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬደዋ ምድብ ችሎት ነው ፡፡ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ያቀረበው ክስ የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 408(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ከግል ተበዳይ አቶ ንጉሴ ለማ ብር ሁለት ሺህ (2,000.00) ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዟል የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

 

አመልካች በአሁኑ ተጠሪ የተመሰረተበት የወንጀል ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርቦ የተከራከረ ሲሆን ተጠሪም የበኩሉን መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መሠረታዊ ይዘት በጉቦ መልክ ተቀብለው የተባለው  የገንዘብ መጠን ትንሽ መሆኑ፤የሥልጣን ደረጃውም በአዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀፅ 2(5) እንደማይካተት በመግለፅ ክሱ በወ/ሕ/ቁ 408(1) ሥር እንዲቀርብ ዐቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል እንዲታዘዝለት አመልክቷል ፡፡ ተጠሪ በበኩሉ በሰጠው መልስ አመልካች ስራ አስኪያጅ መሆኑን ፤በአዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት የመንግስት የልማት ድርጀት ስራ አስኪያጆች የመንግስት ባለ  ስልጣን በሚል ሥር ያካተታቸው በመሆኑ መቃወሚያው ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል፡፡

 

የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የግራቀኙ ክርክር ከመረመረ በኋላ አመልካች ከፍተኛ ባለ ስልጣን ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 433/97 አልተካተተም ፡፡ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንቀጽ 2/2006 ለወንጀል ሕግ አንቀጽ 407(2) የወንጀል ደረጃ እና የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን ሲያወጣ ከፍተኛ ሥልጣን ማለት በተሻሻለው የፌዴራል ስነ ምግባር እና ፀረሙስና ኮሚሽን አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 2(5) ውስጥ የተካተቱ ባለሥልጣኖች ያላቸው ስልጣን ማለት እንደሆነ ተመልክቷል ፡፡  በወ/ህ/አ. 407(2) እና 408(2) ላይ የተቀመጡ ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች


ተመሳሳይ በመሆናቸው ለቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንቀጽ 408(2)መወሰዱ ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ ተከሳሽ የመንግስት የልማት ድርጅት ስራ አስኬያጅ መሆናቸው የስልጣን ደረጃቸው ከፍተኛ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም፡፡ በጉቦ መልክ ተቀብለው የተባለው ገንዘብ ሁለት ሺህ ብር መሆኑ ሲታይ የተገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ነው፡፡ ኃላፊነት ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ የከባድ የሙስና ወንጀል መለኪያ መስፈርቶችን የሚያሟላ ሆኖም አልተገኘም ፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በወንጀል መቀጫ ሥነ ሥርዓት አንቀጽ 112 በሚያዘው መሠረት አሻሽሎ እንዲያቀርብ ብይን ሠጥቷል፡፡

 

ተጠሪ በሥር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ቅር በመሰኘት የይግባኝ ቅሬታው ወደ ፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የግራቀኙ ክርክር ከመረመረ በኃላ የዓቃቤ ሕግ ክስ ስለ ወንጀሉ የሚዘረዝረው ዝርዝር መግለጫ ከህጉ ጋር በእጅጉ የተራራቀ እስካልሆነ ድረስ ፍ/ቤት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ስም ገና ከጅምሩ አንቀጽ ቀይሩ እያለ መዝገብ የሚዘጋ ከሆነ ገና ክሱ ሳይጀምር ወደ ማያባራ ውዝግብ እና ይግባኝ የሚደረግ ነው፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከሰማ በኃላ ተጠሪ ተከላከል የሚል ከሆነ ሊከላከል የሚገባውም ከተከሰሰበት የህግ አንቀጽ ያነሰ የሚያስቀጣ ነው ብሎ ካመነ በዛን ግዜ አንቀጽን መቀየር የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ዓቃቤ ሕግ  በከሰሰበት የወ/ህ/አንቀጽ 408(2) ክሱ ሊቀጥል እና ማስረጃ ሊሰማ ይገባል በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ብይን ተሽሯል፡፡

 

የሰበር አቤቱታ የቀረበው የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ለማስለወጥ ነው፡፡

 

አመልካች በሥር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተፈጽሟል ያሉትን የህግ አተረጓጐም ስህተት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ዋና ፍሬ ነገሩ ፈጸሙት የተባለው ድርጊት በተከሰሱበት የሕግ አንቀጽ ሥር የተቀመጡትን ማቋቋሚያ ፍፌ ነገሮች የማያሟላ በመሆኑ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል የተሰጠ ትዕዛዝ ተገቢ ሆኖ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻር የሚጠይቅ ነው ፡፡ ተጠሪ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲጸና አመልክቷል ፡፡የአመልካች የመልስ መልስም የሰበር ቅሬታቸውን የሚያጠናክር ነው፡፡

 

ከሥር የክርክሩ አመጣጥ በሰበር ግራ ቀኙ በፅሑፍ ያደረጉት ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የተነሱትን ክርክሮች ከተያዘው ጭብጥ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም የሥር ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥር ከፍተኛ  ፍርድ ቤት ብይን በመሻር ዓቃቤ ሕግ በከሰሰበት የወ/ሕ/ቁ.408(2) ክሱ ሊቀጥል እና ማስረጃ ሊሰማ ይገባል በማለት መወሰኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን ያለመሆኑን በመመርመር ለተያዘው ጉዳይ ዕልባት መስጠት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

 

በዚሁ መሰረት ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አመልካች ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ አጥብቆ የሚከራከረው የተመደበበት የኃላፊነት ደረጃ ይሁን በወንጀል ድርጊቱ ተገኘ የተባለው ጥቅም አነስተኛ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ማቅረብ የነበረበት በወ/ሕ/ቁ. 408 (1) ሥር መሆን ነበረበት በሚል ነው ፡፡ተጠሪ በበኩሉ የአመልካች ሥራ አስኪያጅ በመሆናቸው በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የሚመደብ በመሆኑ የተገኘው ጥቅም አነስተኛ መሆን የተከሰሰበት የሕግ አንቀጽ ለመቀየር የሚያስችል አይደለም በማለት ተከራክረዋል ፡፡


የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓቃቤ ሕግ የሚያቀርበው ክስ ማሟላት ያለበት መሰረታዊ ነጥቦች ምን እንደሆኑ ደንግጓአል፡፡ ተከሳሹ የቀረበበት ክስና ማስረጃ ዝርዝር አውቆና ለይቶ እንዲከላከል በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 111፣112 የተዘረዘሩት መሠረታዊ ፍፌ ነገሮች በዓቃቤ ሕግ ክስ መገለጽ አለባቸው፡፡ ዓቃቤ ሕግ የሚያቀርበው ክስ የወንጀል ድርጊት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ድርጊት መሆኑ የሚደነግጉ ፍሬ ነገሮች ተከሳሹ ፈጸመው ከተባለው ድርጊት የሚዛመድ መሆኑ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ፡፡ በእንግሊዘኛው (“such description shall follow as closely as may be the words of the law creating the offence`) በማለት ተገልጿል ፡፡ በአግባቡ የቀረበ ክስ ደግሞ ተከሳሹ የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት ዝርዝር ጉዳይ አውቆ የመከላከያ ማስረጃው እንዲያዘጋጅ ፍርድ ቤትም የጠራ ግንዛቤ በመያዝ ክርክሩን በሕጉ መሰረት ለመምራት የሚያስችለው እንደሆነ ከወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ111፣112 እና ከአጠቃላይ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ መሠረታዊ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡

 

አመልካች የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ ስለመሆናቸው በሙስና የተጠረጠሩትም ሁለት ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅከፍንጅ የተያዙ እንደሆኑ መሰረት በማድረግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 408(2) የተጠቀሰባቸው ስለመሆኑ ከሥር ፍርድ ቤት የክርክር ሂደት መገንዘብ ይቻላል ፡፡ የአመልካች የኃላፊነት ደረጃ በአዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 2(5) ሥር በግልጽ የተጠቀሰ ባይሆንም በተመሳሳይ ደረጃ የሚታዩ ኃላፊዎች በዚህ ትርጓሜ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚችሉ በአዋጅ የተጠቀሰ በመሆኑ ከወዲሁ የኃላፊነት ደረጃቸው ከፍተኛ ነው ወይስ ዝቅተኛ

? የሚለው በግልፅ የተወሰነ አይደለም ፡፡ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጠሪ ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ምን እንደሚወሰን ስለማይታወቅ ከወዲሁ የአመልካች የኃላፊነት ደረጃ  ወስኖ ወደ ክርክር መግባት ሥነሥርዓታዊ ነው ለማለት የሚቻል አይሆንም፡፡በሌላ በኩል በወ/ሕ/ቁ/408(2) የተዘረዘሩት የማቋቋሚያ ነጥቦች ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ ፤የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ ፣በህዝብ ወይም በመንግስት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት ናቸው ፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ዋና ሥራ አስኪያጅ ከፍተኛ ኃላፊ ነው ወይስ አይደለም የሚለው በአዋጅ በግልጽ ባልተሸፈነበት ፍርድ ቤቱ ክርክሩ ሲመረምር ግለሰቡ ከተሰጣቸው ኃላፊነት አንፃር እንደየአግባብነቱ የሚወሰን እንጂ ከወዲሁ የሰበር ሰሚ ችሎቱ አቋም የሚወሰድበት አይሆንም ፡፡ ሌሎች የማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮችም መኖር አለመኖራቸው በክርክር ሂደት ነጥረው የሚወጡ እንጂ ከወዲሁ ድርጊቱ የተፈፀመው ለዚህ ዓላማ ነበር ተብሎ ድምዳሜ የሚያዝበት ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ ምንድነው? የሚለው ምናልባት ለወደፊት ዓቃቤ ሕግ እንደክሱ የሚያስረዳ ከሆነ በሥር ፍርድ ቤት የሚታይ እንጂ ክርክሩ አሁን ባለበት ደረጃ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም ፡፡በተያያዘው ጉዳይ ተፈፀመ በተባለው ድርጊት በግለሰብ ወይም በህዝብ ወይም በመንግስት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ምንድን ነው ? የሚለውም ዓቃቤ ሕግ እንደክሱ አቀራረብ የሚያስረዳ ከሆነ የሥር ፍርድ ቤት ከክርክር በኃላ የሚወሰነው እንጂ ከወዲሁ አቋም የሚያዝበት አይደለም ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ደምረን ስንመለከታቸው አቃቤ ሕግ ተፈፀመ ያለው የወንጀል ድርጊት በወ/ሕ/ቁ. 408(2) ሥር የሚወድቅ ነው ብሎ ካመነ እና ለዚሁም መነሻ የሆኑ ነጥቦች በክሱ መግለጹ ከተረጋገጠ ፍርድ ቤት ጉዳዩን  ተቀብሎ ከማስተናገድ ውጭ ክርክሩ አሁን ባለበት ደረጃ የወ.ሕ..ቁ 408(2) ማቋቋሚያ ፍሬነገሮች አያሟላም ብሎ ክሱን ውድቅ የሚያደርግበት ሥርዓታዊ ሂደት አይኖርም፡፡ በሌላ በኩል የሥር ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ በሚመረምርበት ወይም ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ አስረድቷል


የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሰም የመከላከያ ማስረጃ በሚመረምረበት ጊዜ ሁሉ በአመልካች ላይ የተጠቀሰው የህግ አንቀጽ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ከመመርመር የሚገደበው  ሥርዓት አይኖርም ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ክርክሩ አሁን ባለበት ደረጃ ዓቃቤ ሕግ  በአመልካች  ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስ በወ/ህ/ቁ.408(1) የተዘረዘሩት የማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮችን አያሟሉም ተብሎ ወደ ወ/ህ/ቁ.408(1) እንዲቀየር የሚያስችል የህግ መሰረት የለውም ፡፡ በመሆኑም የሥር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክሩ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ መሰረት እንዲቀጥል መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

 

ሲጠቃለል አመልካች የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት በወ/ሕ/ቁ.408(2) እንዲቀጥል በፌዴራል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት መወሰኑ መሰረታዊ የህግ  ስህተት የተፈፀመበት አይደለም ብለናል ፡፡ የአመልካች የኃላፊነት ደረጃ ኃላፊነቱ እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ ፤በግለሰብ በህዝብ ወይም በመንግስት የደረሰው ጉዳት ምንድነው የሚለው ዓቃቤ ሕግ በሚያቀርበው ማስረጃ ይዘት የሚመዘን ምናልባት የሥር ፍርድ ቤት ድርጊቱ የተፈጸመበት ሁኔታ ከለየ በኋላ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ከሆነ የሚያቀርቡት የመከላከያ ማስረጃ ተመዝኖ የሚወሰን እንጂ ክርክሩ አሁን ባለበት ደረጃ አቋም የሚወሰድበት ባለመሆኑ የአመልካች ክስ ይሻሻልኝ ጥያቄ አልተቀበልነውም ፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ወስነናል፡

 

 ው ሳኔ

 

1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.101820 ሐምሌ 10 ቀን 2006ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን በመሻር የሰጠው ውሳኔ ጸንቷል፡፡

 

2. ተጠሪ በአመልካች ላይ ባቀረበው የወ/ሕ/ቁ.408(2)ሥር ክርክሩ እንዲቀጥል መታዘዙ በአግባቡ ነው ብለናል ፡፡

 

3. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የጸና ስለመሆኑ ለሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና አመልካች በሚገኝበት አድራሻ የፍ/ቤት ውሳኔ ግልባጭ ይድረሳቸው ፡፡  ይፃፍ፡፡መዝገቡ ተዘጋ፤ወደ መ/ቤት ተመለሰ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ት/ጌ