108933 Labor dispute Termination of contract of employment without notice Failure to discharge duties based job specification

Labor dispute

Termination of contract of employment without notice

Failure to discharge duties based job specification

Proclamation no. 377/2004 Art. 13(2) እና (7)

 

 

አንድ ሰራተኛ በስራ መዘርዝሩ በግልጽ የተሰጠውን /የተቀመጠለትን/ ግዴታዎቹን አለመወጣቱ የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ሊያቋርጥ የሚችል ስለመሆኑ፡- 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 13(2) እና (7)  

የሰ// 108933

ሐምሌ 30 ቀን 2007 .

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ተኽሊት ይመሰል

እንዳሻው አዳነ

ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ሠላም ቦሌ ሸማቾች .የተ.የህብረት ስራ ማህበር - የቀረበ የለም ከተባለ በኃላ ጠበቃ መለሰ ግርማይ - ቀረቡ

ተጠሪ፡አቶ እሸቱ አደፍርስ  - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

   

ጉዳዩ የግል ስራ ክርክር ሲሆን የተጀመረውም ተጠሪ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ ሰኔ 02 ቀን 2006 / ባቀረቡት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱም ይዘት ባጭሩ፡-ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ውስጥ 7/00/2003 / ጀምሮ በጉልበት ሰራተኝት የስራ መደብ ተቀጥረው በወር ብር 770.00 እየተከፈላቸው በመስራት ላይ እንዳሉ የአሁኑ አመልካች ከስራ መደባቸው ውጪ የሆነ ስራ ተጠሪ እንዲሰሩ በማድረጉ ተጠሪ የአመልካችን ትዕዛዝ ከስራ መዘርዝራቸው ውጪ ነው በሚል በመቃወማቸው ምክንያት ከስራ ያሰናበታቸው መሆኑን ዘርዝረው ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሏቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካቸ ለክሱ በሰጠው መልስም ተጠሪ የታዘዙት ከስራ መደባቸው ጋር ተያያዥነት ያለውንና በስራ መዘርዝሩ በተጠቀሰው አግባብ መሆኑን እንዲሁም በተደጋጋሚ በቅርብ አለቃቸው ሲታዘዙ ትዕዛዙን የማይቀበሉ መሆኑን ጠቅሶ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ሲል ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡ የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርን ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ ከአሰሪው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ያለመፈጸማቸው አከራካሪ ያለመሆኑን፣ተጠሪ የሚፈፅሟቸው ተግባራት በስራ መዘርዝሩ በግልጽ መመልከታቸውን፣በዚህም መሰረት ተጠሪ ውሃ ያላቸውን ለስላሳ ጠርሙሶችን ከስቶር ወደ ባር፣ባዶ ጠርሙሶችን ደግሞ ከባር ወደ ስቶር እንደሚመልሱ በስራ መዘርዝሩ ላይ ከመገለፁም በላይ በዚሁ ሰነድ ተራ ቁጥር 8 ስርም ከቅርብ አለቃቸው ሲታዘዙ ማንኛውንም የጉልበት ስራ ሊሰሩ እንደሚችሉ መጠቀሱን ከሰነዱ ይዘት መመልከቱንና ከዚህም ተጠሪ የታዘዙት  ከስቶር ወደ ባር ውሃ ያለበትን ጠርሙስ ወስደው ከባር ወደ ስቶርም ውሃ ያለበትን ጠርሙስ እንዲመልሱ በመሆኑ ስራው የስራ ድርሻቸው የሆነው የጉልበት ስራ መሆኑን መረዳቱን ከአረጋገጠ በኋላ ይህ ተግባር የስራ ውልን ያለማስንጠቀቂያ ሊያቋርጥ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ጥያቄ በማንሳት በስራ መዘርዝሩ መሰረት ያለመስራት ስራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት የሚያስችል ህጋዊ ምክንያት አይደለም በማለት ደምድሞ የአመልካችን እርምጃ ሕገ ወጥ ነው በማለት አመልካች ለተጠሪ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ብር 1540.00፣የካሳ ክፍያ ብር 4620.00፣የስራ ስንብት ክፍያ ብር 781.25፣የአመት ፈቃድ ክፍያ ብር 377.3 የገቢ ግብር ተቀንሶ እንዲከፈላቸውና የስራ ልምድ ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-ተጠሪ በስራ መዘርዝራቸው መሰረት የታዘዙትን ስራ ለመስራት ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ተረጋግጦ እያለ ተግባሩ ያለማስጠንቀቂያ ሊያሰናብት የሚችል አይደለም ተብሎ በበታች ፍርድ ቤቶች የተወሰነው የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 13(2) ድንጋጌን ያላገናዘበ ነው የሚል ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ በመሆኑ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነውም ተጠሪ በስራ መዘርዝሩ መሰረት ስራቸውን ያለመስራታቸው ተረጋግጦ እያለ ተግባሩ ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውሉን ሊያቋርጥ የሚችል አይደለም ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባ ሁኖ አግኝተናል፡፡

የፍሬ ጉዳይ ክርክሩን በተመለከተ አመልካች አላግባብ ከስራ አስናብቶኛል በማለት ተጠሪ ላቀረቡት ክስ  አመልካች በሰጠው መልስ ተጠሪው ከስራ ማሰናበቱን አምኖ ያሰናበተው ግን ተጠሪው እንደሚሉት አላግባብ ሳይሆን የተጠሪ የቅርብ አለቃ በሰጣቸው ትዕዛዝ እና በስራ መዘርዝሩ መሰረት ተጠሪ የስራ ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት መሆኑ በሚገባ ተረጋግጧል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ተጠሪው የተሰናበቱት በስራ መዘርዝሩ በተገለፀው አግባብ የስራ ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው በመሆኑ ውጤቱ ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13(2) እና (7) ድንጋጌዎች ይዘት እና መንፈስ እንዲሁም አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሰረታዊ አላማ መታየት ያለበት ነው፡፡ ተጠቃሹ አዋጅ መሰረታዊ አላማ ከያዛቸው ነገሮች ውስጥ የኢንዱስትሪ ሰላምን በማስፈን ምርትና ምርታማነትን በማሳዳግ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ መሆኑን የአዋጁ መግቢያ ያሳያል፡፡ ይህንኑ ለማሳካትም ሕጉ በአሰሪውም ሆነ በሰራተኛው ላይ ለይቶ ያስቀመጣቸው ግዴታዎች መኖራቸውን የአዋጁ አንቀጽ 12 እና 13 ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም አሰሪውም ሆነ ሰራተኛው በሕጉ የተጣለባቸውን ግዴታ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለውና ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለውን ነጥብ በተመለከተ ስናይም አዋጁ ሰራተኛው በአሰሪው የተሰጠውን ሕጋዊ የስራ ትዕዛዝ በአግባቡ የመወጣት ግዴታ ያለበት መሆኑን በአንቀፅ 13(2) እና (7) ስር ከተቀመጡት ድንጋጌዎች ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው አዋጁ አካቶ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል የስራ ውል የሚቋርጥባቸው መንገዶችና ምክንያቶች ይገኙበታል፡፡ የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ የሚችልባቸው ምክንያቶች በአዋጁ አንቀፅ 27(1) ስር በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ስር የተመለከቱት የስራ ውል ማቋረጫ ምክንያቶች ግን አንድ ሰራተኛ የስራ ግዴታውን ያለመወጣቱ ሲረጋገጥ የስራ ውሉን ለማቋረጥ ማስጠንቀቂያ መስጠትን በቅድመ ሁኔታነት የሚያስቀምጡ አይደለም፡፡ ስለሆነም ግልጽ ደንብ ወይም መመሪያ መኖሩ በተረጋገጠበት ሁኔታ ሰራተኛው የስራ ግዴታውን ካልተወጣ አሰሪው ሰራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ የማያሰናብትበት ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተውም ተጠሪ በስራ መዘርዝራቸው በግልጽ የተቀመጠመውን ግዴታቸውን ያለመወጣታቸው ተረጋግጦ የተከናወነው ስንብት ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 13(2) እና (7) ድንጋጌዎች እና ከአዋጁ መሰረታዊ አላማ አንፃር ሲታይ ህጋዊ ነው ከሚባል በስተቀር ሕገ ወጥ የሚባልበትን አግባብ አላገኘንም፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ከዚህ አንፃር መመልከት ሲገባቸው ከአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሰረታዊ አላማ በመውጣት የስራ ግዴታውን ያለመወጣቱ የተረጋገጠውን ተጠሪ መሰናበት የነበረበት በማስጠንቀቂያ ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል፡፡ 

1.    በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 90184 ሐምሌ 03 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 155790 ታህሳስ 20 ቀን 2007 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2.    ስንብቱም ህገወጥ ነው በማለት በስር ፍ/ቤቶች የሰጡት የውሳኔ ክፍል ተሽሮ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ብለናል፡፡

3.    አመልካች ለተጠሪ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣የስራ ስንብት ክፍያና የካሳ ክፍያ ለመክፈል አይገደድም፣ የአመት ፈቃድ ክፍያ ብር 377.3 ግን ለተጠሪ ሊከፍል ይገባል፣የስራ ልምድ ምስክር ወረቀትም ሊሰጥ ይገባል ብለናል፡፡

4.    በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡