labor law dispute/ termination of contract of employment 108789

Labor dispute

Termination of contract of employment without notice

Execution of instruction of employer

Proclamation no. 377/2004 Art. 13/1/2/ and /7/ and 27/1/ g/

 

 

የሰ//.108789

 ሚያዝያ 13 ቀን 2007 .

ዳኞች--አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሡልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡-ሴንቸሪ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር -

ጠበቃ አሰፋ ዓሊ ቀረቡ

ተጠሪ፡-አቶ ገስጥ ንጉሴ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ 11/09/2006 . አዘጋጅተው ባቀረቡት ክስ ነው፡፡ የክሳቸውም ይዘት ባጭሩ፡-ከሳሽ 09/03/2006 . ጀምሮ በአሽከርካሪነት የስራ መደብ ላይ በወር ያልተጣራ ብር 1,900 (አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ) ደመወዝ እየተከፈላቸው በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በመስራት ላይ እያሉ ተከሳሽ ድርጅት ካለአንዳች ምክንያት 19/07/2006 . ከስራ ካገዳቸው በኃላ 24/08/2006 . በተጻፈ ደብዳቤ ከስራ ያሰናበታቸው መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ የስራ ስንብት እርምጃው ሕገወጥ ነው ተብሎ ሕገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን እና ተዛማጅ ክፍያዎችን በድምሩ ብር 21,850 (ሃያ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ) ድርጅቱ እንዲከፍላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡

ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ 26/09/2006 .. በሰጠው መልስ የከሳሽ የስራ ውል እንዲቋረጥ የተደረገው ከሳሽ ስራቸውን ለመስራት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣አሮጌ ተሽከርካሪ አላሽከረክርም በማለታቸው፣ከድርጅቱ ሰራተኞች ጋር ለመስራት ባለመቻላቸው፣በዚህም ምክንያት የድርጅቱ ሰራተኞች በከሳሽ ሾፌርነት በድርጅቱ ተሽከርካሪ ከመጠቀም ይልቅ በታክሲ መጠቀም ይሻለናል በማለታቸው እና ከሳሽ ተደጋጋሚ ምክር እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሊታረሙ ባለመቻላቸው በመሆኑ የስራ ውላቸው የተቋረጠው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13(2) መሰረት በአግባቡ ነው፣እስከሰሩበት መጋቢት 19 ቀን 2006 .. ድረስ ያለው ደመወዝ ተከፍሏቸዋል ፣ያልሰሩበት የሚያዝያ ወር ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፣የዘገየ ክፍያ የለም፣ በመሆኑም ክሱ ውድቅ ሊደረግልን ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡ 

ፍርድ ቤቱም ክሱን እና የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኃላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ  ከሳሽ ባላቸው የማሽከርከር ሙያ በተቀጠሩበት የስራ መደብ ሰራተኞችን ወደ ስራ ቦታ በሰዓቱ ወስደው በሰዓቱ መመለስ እና የሚሰጣቸውን ትዕዛዝም መፈጸም እንዳልቻሉ እንዲሁም ተሽከርካሪው መስራት የሚችል ሆኖ እያለ በአሮጌ ተሽከርካሪ አልሰራም በማለት አቁመው እንደሄዱ ከግራ ቀኙ ምስክሮች ቃል መገንዘብ መቻሉን፣አንድ ሰራተኛ በአሰሪው የሚሰጠውን ትዕዛዝ የመፈጸም ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13 (2) ስር ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑን፣ይሁን እንጂ ከሳሽ መፈጸማቸው የተረጋገጠው ጥፋቶች በአዋጁ አንቀጽ 27 መሰረት ካለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብቱ አለመሆኑን ገልጾ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት ተከሳሽ ድርጅት ሕገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች ለከሳሽ እንዲከፍል እና የስራ ልምድ ማስረጃ እንዲሰጣቸው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ዘግቶ በማሰናበቱ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ተጠሪው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13 የተመለከተውን ግዴታ ሊፈጽም ያልቻለ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ቢሆንም የዚህ ግዴታ መጓደል ካለማስጠንቀቂያ የስራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ስር ስላልተካተተ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ትርጉም አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ  ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት በአንድ በኩል ተጠሪው ባላቸው የማሽከርከር ሙያ በተቀጠሩበት የስራ መደብ ሰራተኞችን ወደ ስራ ቦታ በሰዓቱ ወስደው በሰዓቱ መመለስ እና የሚሰጣቸውን ትዕዛዝም መፈጸም እንዳልቻሉ እንዲሁም ተሽከርካሪው መስራት የሚችል ሆኖ እያለ በአሮጌ ተሽከርካሪ አልሰራም በማለት አቁመው እንደሄዱ በግራ ቀኙ ምስክሮች መረጋገጡን እና አንድ ሰራተኛ በአሰሪው የሚሰጠውን ትዕዛዝ የመፈጸም ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13 (2) ስር  ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑን በውሳኔው ላይ ከገለጸ በኃላ በሌላ በኩል ግን ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት ለተጠሪው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሉ ውሳኔ የሰጠው ተጠሪው መፈጸማቸው የተረጋገጠው ጥፋቶች በአዋጁ አንቀጽ 27 መሰረት ካለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብቱ አይደሉም በማለት ነው፡፡በመሰረቱ የስራ ውል ማለት ማንኛውም ሰው ደመወዝ እየተከፈለው በአሰሪ መሪነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ወይም የተወሰነ ስራ ለአሰሪው ለመስራት ግዴታ የሚገባበት ውል ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 4 (1) ስር የተመለከተ ሲሆን የዚህ ዓይነት የውል ግዴታ የገባ ሰራተኛ በስራ ውሉ ላይ የተመለከተውን ስራ ራሱ የመስራት፣በስራ ውሉ እና በስራ ደንቡ መሰረት በአሰሪው የሚሰጠውን ትዕዛዝ መፈጸም እና የአዋጁን ድንጋጌዎች፣የሕብረት ስምምነትን፣የስራ ደንብን እና በሕግ መሰረት የሚተላለፉ መመሪያዎችን እና ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 13 (1) (2) እና (7) ድንጋጌዎች ስር ተመልክቷል፡፡በተጠሪው መፈጸማቸው በግራ ቀኙ ምስክሮች እንደተረጋገጡ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የተገለጹት ፍሬ ነገሮችም ተጠሪው ከላይ በተጠቀሱት የአዋጁ ድንጋጌዎች የተመለከቱትን ግዴታዎች መፈጸም አለመቻላቸውን በግልጽ የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ተጠሪው እነዚህን ግዴታዎች ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ደግሞ ከአመልካች ጋር የገቡትን የስራ ውል መሰረታዊ ዓላማ እና ይዘት የሚጻረር እና የስራ ውሉን ተግባራዊነት የሚያሰናክል ከመሆኑም በላይ ድርጊቶቹም በባህሪያቸው ሆን ተብለው የሚፈጸሙ በመሆኑ እንደተራ ጥፋት ተቆጥረው በቀላሉ ሊታለፉ የሚገባቸው አይደሉም፡፡ በተጠሪው መፈጸማቸው የተረጋገጡት ጥፋቶች ካለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብቱ ናቸው ተብለው በአዋጁ አንቀጽ 27 (1) ስር ከተዘረዘሩት ጥፋቶች ውስጥ በግልጽ ባይጠቀሱም በአሰሪው ንብረት ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው በማናቸውም ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ካለማስጠንቀቂያ ከስራ ሊያሰናበት የሚችል ጥፋት ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 27 (1) (ሸ) ስር ተመልክቷል፡፡በመሰረቱ …”የአሰሪው ንብረት…” በሚል በዚህ ድንጋጌ ስር የተቀመጠው አገላለጽ መተርጎም የሚገባው ግዙፍነት ያለው ቁሳዊ አካል ብቻ ተደርጎ ሳይሆን ለአሰሪው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ማናቸውንም ሌላ ነገር በሚያካትት አግባብ ነው፡፡በተያዘው ጉዳይ በተጠሪው መፈጸማቸው የተረጋገጡት ጥፋቶች የአሰሪውን የስራ እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ውጤት ያስከተሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ይህ መሆኑ ደግሞ ተጠሪው ሆነ ብለው በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡በመሆኑም ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት ተጠሪው በአዋጁ አንቀጽ 13 (1) (2) እና (7) ድንጋጌዎች ስር የተመለከቱትን ግዴታዎች አለመወጣታቸው የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት በአዋጁ አንቀጽ 27 (1) (ሸ) ስር ከተመለከተው ድንጋጌ አንጻር አይቶ መተርጎም ሲገባው ተጠሪው በአዋጁ አንቀጽ 13(2) ስር የተመለከቱትን ግዴታዎች አለመፈጸማቸው ካለማስጠንቀቂያ የስራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችሉ ናቸው ተብለው በአዋጁ አንቀጽ 27 (1) ስር ከተዘረዘሩት ጥፋቶች ስር በግልጽ አልተጠቀሱም ከሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት የሰጠው እና በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተቀባይነት ያገኘው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

ሲጠቃለል ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት ሕገ ወጥ የስራ ስንብት እርምጃ የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች አመልካች ለተጠሪው እንዲከፍል በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ የሚከተለው  ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

1. ንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት ሕገ ወጥ የስራ ስንብት እርምጃ የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች አመልካች ለተጠሪው እንዲከፍል በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 13619 29/11/2006 . ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 155925 20/04/2007 .. በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሮአል፡፡

2.    በአመልካች የተወሰደው የስራ ስንብት እርምጃ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13 (1)

(2)    እና (7)  እና 27 (1) () መሰረት ሕጋዊ ነው በማለት ወስነናል፡፡

3.    የተጠሪውን የስራ መደብ፣የደመወዝ መጠን እና የአገልግሎት ዘመን በመጥቀስ አመልካች የስራ የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የውሳኔ ክፍል አልተነካም፡፡

4.    እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ፡፡

5.    የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

6.    ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡