Labor dispute
Termination of contract of employment
Termination without notice
Leave payment
Provident payment
አንድ አሠሪ ሠራተኛው ህጋዊ የመብት ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት የስራ ውሉን ማቋረጥ ህገወጥ ተግባር ስለመሆኑ
አዋጅ ቁ.377/96 አንቀፅ 26(2)(ሐ)
የሰ/መ/ቁ.102994
ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም
ዳኞች-፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ
ሡልጣን አባተማም
ሙስጠፋ አህመድ
ተኽሊት ይመሰል
አመልካች፡- ዳሽን ባንክ አክሲዮን ማህበር - ነ/ፈጅ ሰለሞን አያኖ - ቀረቡ፡፡
ተጠሪዎች፡- 1. አቶ ተፈሪ አሳልፈው
2. አቶ አየለ ገብረሃና
3. አቶ በኃይሉ ዓለማየሁ
ጠበቃ ሳህሉ ሀብቴ ጋር - ቀረቡ፡፡
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የአሠሪና ሠራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሾች የነበሩት የአሁኖቹ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ በ07/08/2005 ዓ.ም አዘጋጅተው ባቀረቡት ክስ ነው፡፡የክሳቸውም ይዘት ባጭሩ፡-ከሳሾች በተከሳሽ ድርጅት ተቀጥረው ቄራ አካባቢ በሚገኘው መጋዘን በመስራት ላይ እያሉ ከመጋዘኑ ግቢ ያልወጣን ንብረት “ለግል ጥቅማችሁ አውላችኃል” በማለት ከ13/07/2005 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ውላቸውን ያቋረጠ መሆኑን፣ከሳሾቹ ንብረት ከመመዝገብ በስተቀር ንብረት የመያዝም ሆነ የመጠበቅ ኃላፊነት እና የስራ ድርሻ የሌላቸው መሆኑን፣ንብረት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ሠራተኛ በስሩ የሚገኘውን ንብረት ለአጠባበቅ ያመቸኛል በማለት ከመደበኛ ቦታ ውጭ በማስቀመጡ ድርጅቱ እርምጃ መውሰድ የሚገባው ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘው ሠራተኛ ላይ ብቻ ሆኖ እያለ ከሳሾቹን ጭምር በማሰናበት የወሰደው እርምጃ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27 (1) (መ) እና የድርጅቱን የሕብረት ስምምነት አንቀጽ 36 (1.3) የሚቃረን መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ የስራ ስንብት እርምጃው ሕገወጥ ነው ተብሎ ድርጅቱ ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደስራ እንዲመልሳቸው፣ይህ የሚታለፍ ከሆነም ሕገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን እና ተዛማጅ ክፍያዎችን እንዲከፍላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡
ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ17/10/2005 ዓ.ም በሰጠው መልስ ከሳሾቹ ከብር 180,000 በላይ ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ ዕቃዎች እርስ በርስ በመመሳጠር በስቶር ክለርክነት ከሚሰሩበት የዕቃ ግምጃ ቤት ሰርቀው በመውሰድ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ በመደበቅ እና የመጸዳጃ ቤቱን በመቆለፍ የቆጠራ ሠራተኞች እንዳያገኟቸው ያደረጉ መሆኑን፣ንብረቶቹ ለተለያዩ የአካባቢ ባንኮች እና የስራ ክፍሎች የተሰራጩ ተደርገው የሚታወቁ መሆኑን፣ከሳሾቹ ንብረቶቹን ከሚሰራጩት ዕቃዎች ቀንሰው ያጠራቀሟቸው እንደሆነ መረጋገጡን፣ስለጉዳዩ ሲጠየቁም እርስ በርስ የሚጋጭ መልስ መስጠታቸውን፣እንዲሰናበቱ የተደረገውም በፈጸሙት የስርቆት እና የማጭበርበር ድርጊት በአዋጁ አንቀጽ 27 (1) (ሐ) እና (ተ) እና በሕብረት ስምምነቱ አንቀጽ 36 /1.1 እና 36 /1.2/ መሰረት በአግባቡ መሆኑን፣የሚፈለግባቸውን ዕዳ በማቻቻል ተራፊ ገንዘብ ካለ ከሁለት ዓመት በላይ ያልተላለፍ የዓመት ዕረፍታቸውን ድርጅቱ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑን፣የፕሮቪደንት ፈንድ የለም እንጂ አለ ከተባለ ድርጅቱ ክፍያውን ለመክፈል የሚገደደው ከሳሾቹ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በመወጣት ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ብቻ በመሆኑ ከሳሾቹ ይህንን ግዴታ ተወጥተው ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ጥያቄ ባላቀረቡበት ሁኔታ ድርጅቱ የሶስት ወር ደመወዝ ለመክፈል የሚገደድበት ምክንያት አለመኖሩን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል፡፡
ፍርድ ቤቱም ክሱን እና የተከሳሽ ድርጅትን ሶስት ምስክሮች ከሰማ በኃላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ በስቶር ውስጥ በነበረው ዕቃ ጉድለት ያልተገኘ ቢሆንም ከሳሾች በመመካከር ዕቃዎቹ ከመጸዳጃ ቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጋቸውን ተከሳሽ ድርጅት ያስረዳ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ ከሳሾቹ ዕቃዎቹ ትርፍ መሆን አለመሆናቸው ወይም በመጠየቂያ መሰረት ያልተሰጡ ዕቃዎች መሆን አለመሆናቸው እስኪለይ ድረስ አስቀምጠናቸዋል በማለት ለተከሳሽ ድርጅት ምስክሮች በቃል እና በጽሁፍ ከሰጡት መግለጫ አንጻር ከሳሾቹ ዕቃዎቹን ከመደበኛ ቦታቸው ውጪ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ማስቀመጣቸው አግባብ አይደለም ከሚባል በቀር ከሳሾቹ በመመካከር ዕቃዎቹን ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በማሰብ ከሚላኩ ዕቃዎች ቀንሰው አውጥተው ወስደዋል ለማለት የሚያስችል አለመሆኑን ገልጾ ከሳሾቹ የስርቆት እና የማጭበርበር ድርጊት ፈጽመዋል በማለት ተከሳሽ ድርጅት የወሰደው የስንብት እርምጃ ሕገወጥ ነው በማለት ለእያንዳንዳቸው የስድስት ወር ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደ ስራ እንዲመልሳቸው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩል የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት የተሰጠውን ውሳኔ ሲያጸናው ተጠሪዎቹ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏቸው ወደስራ እንዲመለሱ የተሰጠውን የውሳኔ ክፍል ግን በመሻር ሕገወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸው ክፍያዎች፣የፕሮቪደንት ፈንድ እንዲሁም ያልተጠቀሙበት የዓመት ዕረፍት ክፍያ ለ1ኛ ተጠሪ የ27 ቀናት፣ለ2ኛ እና ለ3ኛ ተጠሪዎች ለእያንዳንዳቸው የ15 ቀናት ክፍያ ተፈጽሞላቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ይዘቱ ከላይ የተመለከተው የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ተጠሪዎች በነበራቸው የስራ ግንኙነትና አጋጣሚ የአመልካች የሆኑ ለልዩ ልዩ ቅርንጫፎች የሚታደሉ በመጋዘን ውስጥ የነበሩ ንብረቶችን ከመጋዘን አውጥተው በግቢው ውስጥ ባለ መጸዳጃ ቤት ውስጥ አስቀምጠውት የነበረው ንብረት በጠቋሚዎች አማካኝነት በፍተሻ መያዙን የስር የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በማስረጃ ካረጋገጠ በኃላ ንብረቶቹን መጋዘኑ ካለበት ግቢ አውጥተው ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ አድራጎታቸው እንደስርቆት እንደማይቆጠር ገልጾ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት የመወሰኑን እና ውሳኔውም በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመጽናቱን አግባብነት ተጠሪዎቹ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ሊከፈለኝ የሚገባው የዓመት ዕረፍት የ71 ቀናት ሆኖ ሳለ የ27 ቀናት ብቻ ታስቦ የ44 ቀናት የታለፈብኝ አላግባብ ነው በማለት 1ኛ ተጠሪ ያቀረቡት መስቀልኛ የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ አመልካች መልስ እንዲሰጥበት በ13/06/2007 ዓ.ም. በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በመስቀልኛ አቤቱታው ጉዳይም አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በጉዳዩ እልባት ማግኘት የሚገባቸው ነጥቦች፡-
1. አመልካች አቤቱታ ያቀረበበት የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ወይስ አይደለም?
2. 1ኛ ተጠሪ ያቀረቡት መስቀልኛ የሰበር አቤቱታ ያቀረቡበት የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ወይስ አይደለም?
የሚሉ መሆናቸውን በመገንዘብ ጉዳዩን ከእነዚሁ ነጥቦች አንጻር መርምረናል፡፡
በዚህም መሰረት የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ ተጠሪዎቹ በአመልካች ድርጅት ውስጥ ይሰሩ የነበሩት በስቶር ክለርክነት መሆኑ፣በዚሁ የስራ መደብ ከሚሰሩበት የዕቃ ግምጃ ቤት ወጪ ተደርገው ለባንኩ የተለያዩ አካባቢዎች እና የስራ ክፍሎች እንደተሰራጩ ተደርገው የተመዘገቡትን የተለያዩ ዕቃዎች ከንብረት ጠባቂው ጋር በመተባበር ከሚሰራጩት ዕቃዎች ቀንሰው በመጸዳጃ ቤት ውስጥ በመደበቅ እና የመጸዳጃ ቤቱን በመቆለፍ የቆጠራ ሰራተኞች እንዳያገኟቸው ያደረጉ መሆኑ፣ንብረቶቹን ለተለያዩ የአካባቢ ባንኮች እና የስራ ክፍሎች የተሰራጩ እንደሆኑ አድርገው የመዘገቡትም እነዚሁ ተጠሪዎች መሆናቸው በስር ፍርድ ቤቶች በማስረጃ የተረጋገጡ ፍሬ ጉዳዮች መሆናቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ተጠሪዎቹም እኛ ንብረት ከመመዝገብ ባለፈ ንብረቱን የመያዝ እና የመቆጣጠር የስራ ድርሻ እና ኃላፊነት የሌለን ስለሆነ ለዕቃዎቹ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ተደብቀው መገኘት በኃላፊነት የምንጠየቅበት ምክንያት የለም፣ዕቃዎቹም የተገኙት ከግቢው ሳይወጡ ነው፣በግቢው መውጫ ላይ የሚደረገው ፍተሻ ዕቀዎቹን ከመጋዘኑ ግቢ ለማውጣት የሚያስችል አይደለም በሚል ከመከራከር በቀር በስር ፍርድ ቤቶች ስለተረጋገጡት ከላይ ስለተጠቀሱት ፍሬ ነገሮች ያቀረቡት የማስተባበያ ክርክር የለም፡፡ከንብረት ጠባቂው ጋር በመሆን ዕቃዎቹን ከመደበኛ ቦታቸው ውጭ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ቆልፎ ለማስቀመጥ ያስቻላቸው ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ስለመኖሩም ገልጸው አልተከራከሩም፡፡
የስር ፍርድ ቤቶች ይዘቱ ከላይ የተመለከተው ፍሬ ነገር መረጋገጡን ከተቀበሉ በኃላ ስንበቱ ሕገወጥ ነው ለማለት የቻሉት በዋነኛነት ዕቃዎቹ የተገኙት በግቢው ውስጥ እንዳሉ በመሆኑ ተጠሪዎቹ ዕቃዎቹን ወስደዋል ማለት አይቻልም በማለት መሆኑን ከውሳኔዎቹ ይዘት ተገንዝበናል፡፡በእርግጥ ዕቃዎቹ በመጸዳጃ ክፍል ውስጥ ተቆልፈው እንዳሉ በጥቆማ ተይዘዋል ከመባሉ በስተቀር ከግቢ ውጪ አልተወሰዱም፡፡አመልካችም ቢሆን ዕቃዎቹ ከግቢ ውጪ ተወስደዋል በማለት አልተከራከረም፡፡ይሁን እንጂ ተጠሪዎቹ ዕቃዎቹን ወጪ ተደርገው ለተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች እና የስራ ክፍሎች እንደተሰራጩ አድርገው በመመዝገብ እና ከተሰራጩት ዕቃዎች በመቀነስ ከመደበኛ የዕቃ ማከማቻ ቦታ ውጭ በመጸዳጅ ክፍል ውስጥ ቆልፈው ያስቀመጡበት ሕጋዊ ምክንያት መኖሩን አስካላስረዱ ድረስ የፈጸሙት አድራጎት በድርጅቱ ላይ የተፈጸመ የማጭበርበር ድርጊት ነው ሊባል የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ዕቃዎቹ ከግቢው ሳይወጡ ድርጊቱ በሙከራ ደረጃ ላይ እንዳለ የተደረሰበት መሆኑ እና በግቢው መውጫ ላይ ፍተሻ የሚደረግ መሆኑም ተጠሪዎቹ ዕቃዎቹን ከግቢው አውጥተው ለግል ጥቅማቸው የማዋል ሀሳብ አልነበራቸውም ወደሚል ድምዳሜ ሊያደርስ የሚችል አይደለም፡፡በመሆኑም ተጠሪዎቹ ዕቃዎቹን ከመደበኛ ቦታቸው ውጪ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ማስቀመጣቸው አግባብ አይደለም ከሚባል በቀር በመመካከር ዕቃዎቹን ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በማሰብ ከሚላኩ ዕቃዎች ቀንሰው አውጥተው ወስደዋል ለማለት እና በስራቸው ላይ የስርቆት እና የማጭበርበር ድርጊት ፈጽመዋል ለማለት የሚያስችል ባለመሆኑ ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የደረሱበት ድምዳሜ በክርክሩ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጭ በመሆኑ ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንደጥፋቱ ክብደት ሰራተኛው በስራው ላይ የሚፈጽመው የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር ደግሞ ካለማስጠንቀቂያ የስራ ውል ለማቋረጥ የሚያበቃ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 27 (1) (ሐ) ስር ተመልክቷል፡፡በመሆኑም የመጀመሪያው ጭብጥ ሲጠቃለል ስንብቱ ሕገወጥ ነው በሚል በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት እና ሊታረም የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ሁለተኛውን ነጥብ በተመለከተ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለ1ኛ ተጠሪ የ27 ቀናት የዓመት ፈቃድ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈል በሚል ውሳኔ የሰጠው ተጠሪው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ ላይ ያላቸው የዓመት ፈቃድ ወደ ገንዘብ ተለውጦ እንዲከፈላቸው በደፈናው ከመጠየቅ ውጭ ያላቸውን የዓመት ፈቃድ መጠን ጠቅሰው እና ለይተው አለማቅረባቸውን በመግለጽ እና በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 77 (1)፣(5) እና 79 (5) ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች መሰረት አድርጎ ተገቢ ነው ያለውን ግምት በመውሰድ ነው፡፡በሰበር ክርክራቸውም ቢሆን ያላቸውን የዓመት ፈቃድ መጠን በክሳቸው ለይተው አቅርበው የነበረ ስለመሆኑ ተጠሪው ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመዝገቡን ግልባጭ እና የግራ ቀኙን ክርክር መሰረት አድርጎ ለተጠሪው ሊከፈል የሚገባው የዓመት ዕረፍት መጠን የ27 ቀናት ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡በመሆኑም በዚህ ረገድ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡
ሲጠቃለል የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት እና ሊሻሻል የሚገባው ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡
ው ሳ ኔ
1. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 08897 በ15/04/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139478 በ09/10/2006 ዓ.ም. ተሻሽሎ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡
2. በአመልካች የተወሰደው የስንብት እርምጃ ሕገወጥ ነው በሚል የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል፡፡
3. በተጠሪዎቹ መፈጸሙ የተረጋገጠው ጥፋት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 27 (1) (ሐ) ድንጋጌ መሰረት የስራ ውላቸውን ካለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ወስነናል፡፡
4. ስንበቱ ሕጋዊ በመሆኑ አመልካች ለተጠሪዎቹ የካሳ ክፍያ እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ሊከፍል አይገባም በማለት ወስነናል፡፡
5. አመልካች ለተጠሪዎቹ የዓመት ዕረፍት ወደገንዘብ ቀይሮ እንዲከፍላቸው የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል፡
6. አመልካች ለተጠሪዎቹ የፕሮቪደንት ፈንድ ሊከፍል የሚገባው ተጠሪዎቹ ባዋጡት መጠን ብቻ ነው በማለት ወስነናል፡፡
7. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 14377 የተያዘው አፈጻጸም ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዝገብ በ17/11/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡ይጻፍ፡፡
8. እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ፡፡
9. የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡
10. ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡