Federal Court Case Tracker

114669 labor dispute/ termination of contract of employment/ arrest

አንድ ሠራተኛ በጊዜ ቀጠሮ ከ30 ቀን በላይ መታሰሩ እና ከስራ ገበታው መቅረቱ ከ30 ቀናት የሚበልጥ እስራት እንደተወሰነበት ተቆጥሮ የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ተገቢ ስላለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 /1/በ/

 

መ/ቁ.114669

ጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ተኸሊት ይመስል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- የኢትዮጲያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፓሬሽን የደብረ ማርቆስ መንገዶች ጥገና ዲስትሪክት ነገረ ፈጅ መሰረት አበራ

 

ተጠሪ፡- አቶ አስማረ ፈጠነ ቀረበ

 

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ የስራ ውል ማቋረጥ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአ.ብ.ክ.መ.የደብረማርቆስ ወረዳ ፍ/ቤት በአሁኑ አመልካች ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻነት ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ተጠሪ በአመልካች መስሪያ ቤት ከሚያዚያ 21 ቀን 1984 ዓ/ም ጀምሮ በጠቅላላ 22 ዓመት ሲያገለግሉ እንደቆዩ፤ መስሪያ ቤቱም በየጊዜው እድገት ይሰጣቸው እንደነበር፤ በሹፍርና ሙያ የስራ መደብ እስከ መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ/ም ድረስ ስራቸውን በተገቢው መንገድ እየፈጸሙ በነበሩበት ሁኔታ አመልካች ከመጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ/ም ጀምሮ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ክስ እስካቀረቡት ድረስ ከስራ ያገዳቸው በመሆኑ የስራ ውሉ የተቋረጠው በህገ ወጥ መንገድ ነው ተብሎ ወደ ስራ ገብታችሁ እንዲመለሱ፤ ይህ የማይወሰን ከሆነ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 377/96 የተፈቀዱትን የስራ ስንብት ክፍያ የ6 ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ደመወዝ በወቅቱ ባለመክፈሉ በድምር 60,601.70 /ስልሳ ሺህ ስድስት መቶ አንድ ብር ከሰባ ሳንቲም ከወጪና ኪሳራ ጭምር እንዲከፈል እንዲወሰንላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡


የአሁኑ አመልካች ባቀረበው መልስ የስራ ውሉ የተቋረጠው ተጠሪ ከስራ ገበታቸው ከ30 ቀን በላይ የቀሩ በመሆኑ ስንብቱ በህጉ አግባብ የተከናወ ነው ወደ ስራ ለመመለስ ያቀረቡት ጥያቄም የህግ መስረት የለውም፡፡ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሉአቸው ያቀረቡት ጥያቄም በአግባቡ አይደለም፡፡ የአመት እረፍት በተመለከተ የቀረበ የክፍያ ጥያቄም ተገቢነት የለውም፡፡ የስራ ልምድ የተሰጣቸው በመሆኑ ድጋሜ ሊጠይቁ አይገባም የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡

 

የስር ወረዳ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክር መርምሮ ተገቢ ነው ያለው ጭብጥ በመያዝ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የስር ፍርድ ቤት መዝገቡ ከመረመረ በኃላ የአሁን ተጠሪ ከባህር ዳር ወደ ደብረ ማርቆስ የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነው ሌላ አሽከርካሪ ከእንጅባራ ወደ ደብረማርቆስ በሚነዱበት ጊዜ የመኪና ግጭት ተከስቶ የአሁኑ ተጠሪ ጉዳዩ እስከሚጣራ በጊዜ ቀጠሮ ለ4 ወር ከ11 ቀን መታሰሩን ዓቃቤ ህግ ጉዳዩን ካጣራ በኃላ በተጠሪ ላይ የቀረበው ክስ አያስከስስም በማለት በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/42/1/ሀ/ መሰረት የዘጋው ሲሆን ተጠሪ ማረሚያ ቤት የገቡት ፍ/ቤት ጥፋተኛ ተብሎው ተፈርዶባቸው ሳይሆን በጊዜ ቀጠሮ እስከ ሆነ ድረስ በተባለው ጉዳትም ተጠያቂ የሆነው ሌላ መኪና ሲነዳ የነበረ ሹፌር በመሆኑ አመልካች ተጠሪን የ6 ወር ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደ ስራ እንዲመለስላቸው ወስኗል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች የስር ወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም አቤቱታው ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/በ/ በጊዜ ቀጠሮ ከ30 ቀን በላይ ለሚታሰሩ ሰራኞች የሚመለከት አይደለም፡፡ ተጠሪ በጊዜ ቀጠሮ መታሰራቸው ፍርዱ ወይም ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ ነው የሚያስብል አለመሆኑን ገልጾ የ6 ወር ውዝፍ ደመወዝ ይከፈላቸው የሚለውን የውሳኔ ክፍል በማሻሻል ወደ ስራ  እንዲመለሱ የተሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል፡፡ አመልካች የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው የሰበር አቤቱታ በድምጽ ብልጫ ውድቅ ተደርጓል፡፡ ሰበር ችሎቱ በፍርድ ወይም በውሳኔ ከ30 ቀን በላይ ያልታሰረው ሰራተኛ ስራ ሲሰራ በተፈጠረ አደጋ በምርመራ ላይ በእስር የቆየ ለመሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ የስራ ውል መቋረጥ ከህግ ውጭ ነው ወደ ስራ ይመለስ መባሉ በአግባቡ ነው በማለት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔዎች አጽንቷል፡፡

 

ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር አድርጓል /ተለዋውጧል/፡፡ አመልካች ያቀረበው የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘት፡- ተጠሪ በጊዜ ቀጠሮ ከ30 ቀን በላይ ታስረው ከስሩ የቀሩ መሆኑን ተረጋግጦ ስንብት መከናወኑ በአግባቡ ነው፡፡ የስር ፍ/ቤት ውሳኔዎች ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ/37256 የሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ያላገናዘበ ነው፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው አመልካች የስራ


ውሉ ያቋረጠው ከህግ ውጭ ነው፡፡ የሰበር ውሳኔው በጭብጥ ከተያዘው ጉዳይ ግንኙነት እንደሌለው፤ በጊዜ ቀጠሮ ታስረው እንደተለቀቁ ጉዳዩም አያስከስስም ተብሎ በዓ/ህግ መወሰኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲጸና ጠይቋል፡፡ የአመልካች የመልስ መልስም አቤቱታውን የሚያጠናክር ነው፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ በማገናዘብ መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነውም የዚህ ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ጭብጥ፡- ተጠሪ ፈጸሙት በተባለው ወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ ከ30 ቀን በላይ ታስረው ከተፈቱ በኃላ ወደ ስራ እንዲመለሱ መወሰኑ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/በ/ ያገናዘበ ነው ወይስ አይደለም?  የሚለው ነው፡፡

 

ከክርክር ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ ከባህር ዳር ወደ ደብረማርቆስ በሚያሽከርክሩበት ጊዜ ከሌላ መኪና ጋር ግጭት በመፍጠሩ ጉዳዩ ለማጣራት በጊዜ ቀጠሮ 4 ወር ከ11 ቀን ከታሰሩ በኃላ የዓቃቤ ህግ ጉዳዩን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/42/1/ሀ/ አያስከስስም በማለት የዘጋው በመሆኑ ከእስር እንደተለቀቁ እና በፍርድ ቤት ክስ አቅርበው በጊዜ ቀጠሮ ከ30 ቀን መታሰር የሰራተኛው የስራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል አይደለም ተብሎ በፍርድ ቤት ውሳኔ ወደ ስራ እንዲመለሱ መወሰኑ ያከራከረ ጉዳይ አይደለም፡፡ አመልካች ከስር ፍርድ ቤት ጀምሮ አጥብቆ የሚከራከረው ተጠሪ በወንጀል ተከሰው ጥፋኛ መሆን አለመሆናቸው ሳይሆን ከ30 ቀን በላይ ከስራ በመቅረታቸው ምክንያት ከስራ ለማሰናበት በቂ ስለመሆኑ ነው፡፡ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠው ጉዳይ ተጠሪ በጊዜ ቀጠሮ ከ30 ቀን በላይ ከመታሰራቸው ውጭ ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ጥፋተኛ አልተባሉም፡፡

 

አንድ አሰሪ ሰራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ከሚያሰናብትባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰራኛው  ከ30 ቀን በላይ የእስራት ፍርድ ተወስኖበት ከስራ መቅረቱን ሲረጋገጥ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 /1/በ/ ተመልክቷል ፡፡ የድንጋጌው ሙሉ ይዘት “በሰራተኛው ላይ 30 ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእስራት ፍርድ ተወስኖበት ከስራ ሲቀረ” የሚል ሲሆን የእንግሊዘኛው ቅጂ ደግሞ “absence from work due to sentence of imprisonment passed against the worker for more than 3 days” በማለት ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋ መረዳት የተቻለው አንድ ሰራተኛ ከ30 ቀናት የሚበልጥ እስራት ተወስኖበት ከስራ መቅረቱን ሲረጋገጥ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ እንደሚሰናበት የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ከስራ መቅረታቸው ሳይካድ የቀሩበት ምክንያት ግን  በወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ ታስረው ስለነበር ነው፡፡ ስልጣን ያለው የዐቃቤ ህግም የወንጀል ክስ ለመቀጠል የሚያስችል ነገር የሌለው በመሆኑ ጉዳይ አያስከስስም በማለት ስለ መዝጋቱ የስር ፍርድ ቤት መዝገብ የውሳኔ ግልባጭ ያሳያል፡፡ ተጠሪ በስር ፍ/ቤት የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው


ጥፋተኛ ተብለው አልታሰሩም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከ30 ቀን በለይ ከስራ መቅረቱን ተረጋግጦ ያልተወሰነበት ሰራተኛ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ማሰናበት የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 /1/በ/ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ነው፡፡ ተጠሪ በአመልካች በተሰጣቸው ኃላፊነት ሙያዊ ግዴታቸው ሲወጡ በተከሰተው የመኪና ግጭት ተጠርጥረው በመታሰራቸው ምክንያት ብቻ ፍ/ቤት ጥፋተኝነታቸው ሳያረጋግጥ አመልካች በራስ አነሳሽነት ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችለው የህግ መሰረት የለውም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ/37256 ህዳር 4 ቀን 2001 ዓ/ም የሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ከተያዘው ጉዳይ ጋር ግንኙነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች አመልካች የተጠሪ የስራ ውል ከህግ ውጭ ማቋረጡን በማረጋገጥ ወደ ስራ እንዲመለሱ መወሰናቸው በአግባቡ መሆኑ ከሚያሳይ በቀር የፈጸሙት መሰረታዊ የህግ ስህተት የለም፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸው  አይደሉም ብለን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  በአብክመ የምስራቅ  ጎጃም   አስተዳደር   ዞን  ከፍተኛ   ፍርድ ቤት  በመዝገብ  ቁጥር

0119921 በ27/04/2007 ዓ/ም የደብረማርቆስ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/10694 በ20/20/2007 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በማሻሻል የሰጠው ፍርድ የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ/44956 በ26/09/2007 ዓ/ም በድምጽ ብላጫ የሰጠው ፍርድ ጸንቷል፡፡

2.  አመልካች ተጠሪን ወደ ስራ እንዲመልሰው መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

3.  የዚህ ችሎት ክርክር ያስከተለው ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ

-   ሰኔ  30/2007   /ም  በዚህ   /ቤት  የተሰጠው   የእግድ  ትእዛዝ   ተነስቷል፡፡ ለሚመለከተው ይፃፍ፡፡

-   መዝገቡ ውሳኔ አግኝቷል፡፡ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

መ/ተ