116002 labor dispute/ backpayment

ውዝፍ ያልተከፈለ ደሞዝ ከስራ ስለተሰናበተ ሠራተኛ የሚከፈል ሳይሆን ወደ ስራ እንዲመለስ ለተወሰነበት ሰራተኛ ስለመሆኑ

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 43(5)

የሰ/መ/ቁ. 116002

ቀን 6/3/2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- አቶ ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ አብርሃ መሰለ ፈይሳ ወርቁ

አመልካች፡- የአንቦ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ዩንየን አልቀረቡም ተጠሪ፡- አቶ ጨመዳ መገርሳ ቀርበዋል

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለውን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ የሰበር አቤቱታ መዝገብ ክርክር የአሁኑን አመልካች የአንቦ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ዩንየን በቀን 13-11-2007 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ የኤሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁጥር 202963 በቀን 29-10-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም የቀረበ ነው፡፡ ቅሬታውም የስር ፍ/ቤት የ12 ወር ውዝፍ ደሞዝ ለከሳሽ /ለአሁን ተጠሪ/ሊከፍለው ይገባል ብሎ ቢወስን ምንም ነገር ማሳመኛ ምክንያት ሳይጠቅስ ነው፡፡ ከሳሽ / የአሁን ተጠሪ/የአሁን አመልካች ንብረት መጥፋቱን ባልካደበትና የአሁን አመልካች ተጠሪ ወደ ስራ እንዳይመለስ ተከራክሮ እያለ አመልካች የተጠሪን ወደ ስራ መመለስ አልቃወምም ብሏል በማለት ወደ ስራ እንዲመለስ የተሰጠው ውሳኔ ስህተት ነው፡፡፡ ውዝፍ የዓመት ዕረፍት ለተቋረጠ የስራ ውል የሚከፈል እንጂ በህጉ አዋጅ 377/96 አንቀጽ 77/5/ መሠረት ወደ ስራ እንድመለስ ለተወሰነ ሠራተኛ አይደለምና በስር ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ይታረምልኝ የሚል ነው፡፡

 

መዝገቡ ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች የወሰደው የስንብት እርምጃ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/3/ መሠረት በይርጋ ይታገዳል በማለት ለተጠሪ የተለያዩ ክፍያ ተከፍሏቸው ወደ ስራ


ይመለሱ የመባሉን አግባብነት ከሰበር ውሳኔ መ.ቁ.106371 አንፃር ለመመርመር ሲባል ቀርቧል፡፡ መልስና የመልስ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡

 

የአሁን ተጠሪ በቀን 14 12 2007 በተፃፈ መልስ አመልካች ያቀረበው አቤቱታ ቅሬታና ሙሉ ሃሳብ እንዲሁም የተያዘው ጭብጥ በዚህ ችሎት የሚታይ ስህተት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 183802 በቀን 22-3-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የተሰጠው ውሳኔ እና ወደ ስር ፍ/ቤት በተመለሰው ላይ የአሁን አመልካች በወቅቱ ይግባኝ ያላለበት በመሆኑ አሁን እንደ ቅሬታ ልያነሳ አይችልም፡፡ አመልካች የአሁን ተጠሪን የዓመት ፋቃድ 76 ቀን መሆኑንን አልካደም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ቅር የሚያሰኝ ባለመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ውድቅ ይሁንልኝ የሚል ነው፡፡  የአሁን አመልካችም በቀን 29/12/2007 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ የቀረበውን አቤቱታ በማጠንከር የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 183802 ወደ ስር ፍ/ቤት በውሳኔ የመለሰው የይርጋን ጉዳይ ጭብጥ ይዞ በመሆኑ ይርጋን በበተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ አይደለምና አሁን ቢነሳ ስህተት አይደለም፡፡ ተጠሪ ጥፋት መፈፀሙ እየታወቀ ወደ ስራ እንዲመለስ መወሰኑ ስህተት በመሆኑ ልታረም ይገባል የሚል ነው፡፡

 

በዚሁ መሠረት መዝገቡን እንደመረመርነው ክርክሩ የጀመረው ከኦሮሚያ ክ/መ/የአምቦ ወረዳ ፍ/ቤት ሲሆን ከሳሽ የአሁን ተጠሪ አቶ ጨመዳ መገርሳ ያቀረበው ክስ በተከሳሽ የአምቦ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ተቀጥሬ እየሰራሁ ሳለ ያለምንም ጥፋት በሕግ ወጥ መንገድ ከሥራ ስላሰናበተኝ ወደ ኪራዩ እንዲመልሰኝ ካልሆነ ከሕግ ውጭ ከስራዬ ያሰናበተኝ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ሊከፈለኝ የሚገባ ክፍያዎች እንዲከፍለን በማለት አቅርቧል፡፡ ተከሳሽም/ የአሁን አመልካች/ በሰጠው መልስ ከሳሽ የሥራ ድርሻውን የጥበቃ ስራ ባግባቡ ባለመወጣቱ በ29-11-2005 ዓ.ም የተሽከርካሪ ሞተርም ስለተወሰደና በተከሳሽ መ/ቤት ላይ ጉዳቱ ስላደረሰ ከስራ ተሰናብቶአልና የስራ ውሉ የተቋረጠው ህጋዊ ነውና ክሱ ውድቅ ይሁንልኝ በማለት ተከራክሏል፡፡

 

የአምቦ ወረዳ ፍ/ቤትም በመ.ቁ. 35655 አከራክሮ በቀን 7-5-2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ ይርጋን በተመለከተ ጥፋት መፈፀሙ ከታወቀበት ከቀን 29-11-2005 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ውሉ መቋረጡን ደብዳቤ እስከተፃፈበት ቀን 8-1-2006 ዓ.ም ድረስ ሲቆጠር 31 የስራ ቀናት

/ሆኗል፡፡ በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/3/ መሠረት በይርጋ የታገደ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመሆኑም ጥፋት ተፈፅሞ ከሥራ ማሰናበት ከሚገባበት ጊዜ ካለፈ በኃላ ተከሳሽ ከሳሽን ከሥራ ያለማስጠንቀቂያ ያሰናበተው በመሆኑ ህገ ወጥ ነው ብሎ ከሳሽ ወደ ስራ እንዲመለስና የደሞዝ መክፈያ ከተቋረጠበት ጊዜ ደምሮ ውዝፍ እንዲከፈለው በማለት ወስኗል፡፡


የምዕ/ሸዋ ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁጥር 02963 በቀን 4-6 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁጥር 183802 በቀን 22-8-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት አጣርቶ እንዲወሰን በውሳኔ የመለሰለት መሆኑን ገልፃ የሰጠው ፍርድ ግራና ቀኝ ተከራካሪዎች ይግባኝ ባይ /ከሳሽ/ ወደ ስራ ይመለስ በሚለው ውሳኔ ላይ ክርክር ወይም ተቋውሞ የላቸውም ሊከፍለው የሚገባ ውዝፍ ደሞዝና የአመት እረፍት ክፍያን በተመለከተ ውዝፍ ደሞዝ በማስላት የ12 ወራት ብር 22,080 የ76 ቀን የዓመት ዕረፍት ብር 4657.50 በአጠቃላይ ብር 26737.50 ለከሳሽ ይከፈለው ከሳሽ ወደ ሥራ ይመለስ ብሎ ወስኗል፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁን አመልካች አቤቱታ አቅርቦ በመ.ቁጥር 202963 አከራክሮ በቀን 29-10-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ አመልካች ለክርክሩ ተጠሪ የዓመት ዕረፍት እንደሌለው አልተከራከረም፡፡ በመሆኑም የዓመት ዕረፍትን በተመለከተ ሕጉ አዋጅ 377/96 የዓመት ዕረፍት ከሁለት ቀጣይ ዓመታት በላይ ማስተላለፍ አይችልም ይላል ይህ ማለት ተጠሪ ከ2006 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም የዓመት ዕረፍት ተደምሮ ሊከፈለው ይገባል በመሆኑም የተጠሪ 76 የዓመት እረፍት ቀናት ከህጉ ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ ውዝፍ ደሞዝ በተመለከተ ወደ ስራ ይመለስ የተባለ ሠራተኛ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ተከራክሮ ከተወሰነ የ12 ወር ውዝፍ ደሞዝ ስለሚከፈለው የስር የምዕ/ሸዋ/ከፍ/ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ባለመሆኑ ፀንቷል፡፡ በማለት ወስኗል፡፡

 

የአሁን አመልካች ይህን ውሳኔ በመቃወም የቀረበ ነው፡፡ ለዚህ ሰበር አቤቱታ መዝገብ ክርክር ምክንያት የሆነው የክርክር ጭብጥ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 183802 በቀን 22-3-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የመከራከሪያ ጭብጥ በመያዝ ለምዕራብ  ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341/1/ የመለሰውና እንዲጣራ ጭብጥ  ተይዞ የተመለሰውም የአሁን ተጠሪ ወደ ሥራ ይመለስ ወይስ አይመለስ በሚለውና አይመለስ ከተባለ ስለሚከፈለው ክፍያ በተመለከተ ነው፡፡ በመሆኑም ስለ ከሥራ ማሰናበት ሕጋዊነት ወይም ሕገወጥነት እና የይርጋ ጉዳይ የጭብጡ አካል አይደሉም፡፡ ስለዚህ የአሁን አመልካች በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፍርድ የታለፈን ጉዳይና ለከፍተኛው ፍ/ቤት ጭብጥ ያልሆነውን የይርጋ ጉዳይ አሁን በአቤቱታ ሊያንሱ የሚችሉበት የህግ መሠረት የለም፡፡ የአሁን ተጠሪ ወደ ስራ ይመለስ ወይስ አይመለስ የሚለውን ጭብጥ በተመለከተ የስር ፍ/ቤት የአሁን አመልካች የተጠሪን ወደ ሥራ መመለስ የተስማማ መሆኑን አረጋግጦ  የወሰነ መሆኑን ከተሰጠው ፍርድ ላየ መገንዘብ የሚቻል ነው የስር ፍ/ቤት ውሳኔዎችን ከህግ ወጪ ከስራ የተሰናበተ ሠራተኛ ወደ ስራ ሲመለስ ሊከፍሉት የሚገቡ ክፍያዎች የዓመት እረፍትና ያልተከፈለ ውዝፍ ደሞዝን በተመለከተ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43/5/ እና አንቀጽ 79/5/ መሠረት ተሰልቶ የተወሰነው ክፍያ ስህተት ያለበት አይደለም፡፡


በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43/5/ የሚደነግገው የአሁን አመልካች እንደሚከራከረው ውዝፍ ያልተከፈለ ደሞዝ ከሥራ ስለተሰናበተ ሰራተኛ የሚከፈል ሳይሆን ወደ ሥራ እንዲመለስ ለተወሰነበት ሰራተኛ ነው፡፡ ውሳኔውም ጉዳዩ በይግባኝ ታይቶ ወደ ስራው ይመለስ ውሳኔ ከፀና እስከ አንድ አመት ውዝፍ ደሞዝ እንደሚከፈል ይገልፃል፡፡ የአመት ፍቃድ ክፍያንም በተመለከተ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንድ 79/5/ የዓመት እረፍት ከሁለት ቀጣይ ዓመት በላይ እንጅ እስከ ቀጣይ ሁለት ዓመት ማስተላፍን የሚከለከል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የስር ፍ/ቤት የአሁን ተጠሪ ከህግ ወጪ ከስራ የተሰናበተ መሆኑን አረጋግጦና የተጠሪ”ን ወደ ሥራ መመለስ የአሁን አመልካች የተስማማበት መሆኑን በማየት መወሰኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43/5/ እና 79/5/ መሠረት ወደ ሥራ ለሚመለስ ሠራተኛ የሚከፈለውን ያልተከፈለ ውዝፍ ደሞዝና የዓመት ዕረፍት መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የአምቦ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 35655 በቀን 7-5 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 02963 በቀን  4-6-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 202963 በቀን 29-10-2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሠረት ፀንቷል፡፡

2.  በዚህ መዝገብ ውጪና ኪሳራ ተቻቻሉ ብለናል፡፡

3.  መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ወ/ከ