117517 labor dispute/ unlawful labor practice

አሰሪው በሰራተኛው ህይወት ላይ አደጋ ሊያደርስ በሚችል አኳኋን እንዲሰራ ማድረግ ህገ ወጥ ተግባር ሲሆን ይህም ሰራተኛው የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለመቋረጥ በቂ ምክንያት ነው ይህ ከተረጋገጠ ደግሞ ሠራተኛው በአዋጅ መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን የማግኘት መብት  ያለው ስለመሆኑ

አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀፅ 14 (1) (ሠ)፣32(1)(ለ)

የሰ/መ/ቁ. 117517

ቀን ጥር 30/2008ዓ/ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ማህበር - አልቀረበም

 

ተጠሪ፡- ወ/ት ጀላኔ ጌታቸው - ከጠበቃ መስታውት አሸናፊ ጋር - ቀርበዋል መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሰሪና ሰራተኛ የተነሳውን የስራ ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ በፌ/መ/ደረጃ ፍርድ ቤት ሲጀመር ከሳሽ የነበረችው ተጠሪ ናት፡፡ በአመልካች ላይ ክስ የመሰረተው የስራ ውል ከሕግ ውጪ አቋርጠዋል በማለትነው፡፡ በዚህ መሰረትም ልዩ ልዩ ክፍያዎችን እንዲከፈላት ጠይቃለች፡፡

 

በአመልካች ድርጅት ተመድቤ የምሰራበት ሥራ ከኬሚካል ንኪኪ ያለው በመሆኑ ለሰራተኛው በየጊዜው ምርመራ ይደረጋል፡፡ በመጀመሪያ የተወሰደው የደም ናሙና ውጤቱ የደም ጥራት መጠን በታች በመሆኑ ለሶስት ወር ከኬሚካል ጋር ግንኙነት በሌለበት ሥራ እንዲያዛውር በባለሙያ የተሰጠው አሰተያየት ከአንድ ወር በላይ በመደበቅ ውጤቱ አውቄ ራሴን እንዲጠናቀቅ አልቻልኩም፡፡ ወደ ሌላ ስራ አላዘወረኝም፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የደም ናሙና ተወስዶ ውጤቱ እንዲያሰውቀኝ ብጠይቅም ምላሽ አልሰጠኝም፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 32/1/ለ/ መሰረት ከመስከረም 5 ቀን 2007 ዓ/ም ጀምሮ ስራዬን ለማቋረጥ ተገድጃሎህ፡፡ ስለዚህ ስንብቱ ሕገ ወጥ ተብሎ የተለያዩ ክፍያዎች እና ማስረጃዎች እንዲሰጣት እንዲወሰንላት ዳኝነት ጠይቃለች፡፡

 

የአሁኑ አመልካች መከላከያ መልሱን እንዲያቀርብ ተደርጓል፡፡ ተጠሪ በገዛ ፍቃድዋ ሥራውን ያቋረጠች እንጂ በአመልካች ምክንያት ወይም በህገ ወጥ መንገድ አይደለም፡፡ የመጀመሪያ


ምርመራ ውጤት መሰረት ወደ ሌላ ስራ ተዛውራ እንድትሰራ ተደርገዋል፡፡ በሁለተኛ የደም ናሙና ውጤቱ ወደ ኖርማል የተመለሰ በመሆኑ ወደ ቀድምዋ ስራ ተመልሳለች፡፡ ከተሰናበተች በኋላ የ3ኛው የደም ናሙና ምርመራ ውጤት ከጤነኛ ደም ሬንጅ ውስጥ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ የ30 ቀን ማስጠንቀቅያ ሳትሰጥ የለቀቀች ስለሆነ የ30 ቀን ደመወዝ  በመቀነስ እንድትሰናበት የተደረገው፡፡ ሰለሆነም የቀረበው ክስ የህግ መሰረት የለውም ተብሎ ውድቅ እንዲደረግ በማለት መልሳቸውን አቅረበዋል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማና ከመረመረ በኋላ የስራ ወሉ የተቋረጠው ከሕጉ ውጭ ነው በማለት የተለያዩ ክፍያዎችን በድምሩ ብር 59,103 አመልካች ለተጠሪ  እንዲከፍል ሲል ወስኗል፡፡ የአሁኑ አመልካች በዚሁ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት ስላላገኘ ይግባኙን ሰርዞበታል፡፡ የአሁኑ ሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚሁ ላይ ነው፡፡ አመልካች ነሀሴ 21 ቀን 2007 ዓ/ም በፃፈው ማመልከቻ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟአል የሚልበትን ምክንያት በመግለፅ አቤቱታውን አቅርበዋል፡፡ አቤቱታውን መሰረት በማድረግ ተጠሪ እንዲቀርብ በማድረግ ክርክራቸውን በፅሁፍ አቅርቧል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ እንደተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

 

አመልካች የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ስሕተት ነው የሚልበት የስራ ውሉ የተቋረጠው በተጠሪ እንጂ በአመልካች አይደለም፡፡ በመጀመሪያው በተደረገው ምርመራ ውጤት  ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ የተደረጉት ምርመራ ውጤት ጤነኛ መሆኑን በመረጋገጡ አመልካች ለተጠሪ አደጋ የሚጥል ሁኔታ እንዲትሰራ አላደረገም፡፡ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 12 ግዴታው አልተወጣም የሚያሰኝ ሁኔታ ሳይኖር ሕገ ወጥ መባሉ አግባብነት የለውም የሚል ነው፡፡ በተጠሪ በኩል ደግሞ ስራውን ለመቋረጥ የተገደድኩት ለጤነንቴ ስል ነው፡፡ የምርመራ ውጤት ከአንድ ወር በላይ በመደበቅ፤ ከኬሚካል ነፃ የሆነ ሰራ ለሶስት ወር እንድሰራ በባለሙያ የተገለፀው ባለመፈፀሙ፤ ሁለተኛው ምርመራ ውጤት በፅሑፍ ብጠይቅም ምላሽ አልሰጠኝም፡፡ ይህ ደግሞ አመልካች ግዴታውን አልተወጣም በማለት የተሰጠ ውሳኔ በአግባቡ ስለሆነ ሊፀና ይገባል የሚል ነው፡፡

 

በአመልካችና ተጠሪ የተደረገው የስራ ውል በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት መብትና ግዴታ ያቋቁማል፡፡ በሕጉ አንቀጽ 12 የአሰሪው ግዴታ በአንቀጽ 13 ደግሞ የሰራተኛው በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ሕገ ወጥ ድርጊት የተባሉት የአሰሪና ሰራተኛ በቅደም ተከተል በአንቀጽ 14 /1/ እና 14/2/ በዝርዘር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የአሰሪው ግዴታ ከተገለፁት 12/4/ ከስራው ጋር


በተያያዘ ሰራተኛውን ደኀንነትና ጤንነት ለመጠበቅና ከአደጋ ለመከላከል የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች ሁሉ የመውሰድና እነዚሁንም እርምጃዎችን በሚመለከት ረገድ አግባብ ባላቸው ባለስልጣኖች የሚሰጡትን ደረጃዎችን መመሪያዎች የመከተል በአሰሪው ግዴታ ላይ የጣለ ነው፡፡ በሌላ በኩል አሰሪውና ሰራተኛው ሕገ ወጥ ድርጊት ተብለው ከተገለፁት ውስጥ በሕጉ አንቀጽ 14/1/ሠ/ በአሰሪው ሰራተኛውን በሕይወቱ ላይ አደጋ ሊያደርስበት በሚችል አኳኋን እንዲሰራ ማድረግ ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን የተመለከተ ነው፡፡አሰሪው ግዴታውን ካልፈፀመና ሕገ ወጥ ድርጊት መፈፀሙ ከተረጋገጠ ሰራተኛው ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውሉ ማቋረጥ በቂ ምክንያት ይሆናል በማለት በአንቀጽ 32/1/ለ ይደንግጋል፡፡ ይህን ከተረጋገጠ ደግሞ ሰራተኛው በአዋጁ መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን ከአሰሪው የማግኘት መብት አለው፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ የአመልካች ክርክር በአንቀጽ 32/1/ለ የተመለከቱትን ሳይሟላ የተሰጠ ውሳኔ ስለሆነ ሊሻር ይገባል ሲል፤ በተጠሪ ደግሞ በማስረጃ የተረጋገጠና በአግባቡ የተወሰነ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ የስር ፍርድ ቤት መዝገብ እንደሚያመለክተው አመልካች ለሰራተኞቹ በየሶስት ወር ምርመራ እንደሚያደርግ ግልፅ ነው፡፡ እዚህ ላይ አከራካሪ የሆነው ውጤቱ ከሚመለከተው አካል በወቅቱ ማምጣት፤ እንደመጣም በጊዜ መግለፅ  እና በውጤቱ መሰረት ተገቢውን እርምጃ መውስድ የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በፍሬ ጉዳይ የማጣራትና የየመመዘን ስልጣን በተሰጣቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት የተጠሪ የምርመራ ውጤት እንድታውቅ የተደረገው ዘግይቶ መሆኑ፤ ከኬሚካል ንኪኪ ነፃ በሆነ ስራ ለሶስት ወር እንዲሰሩ አለማድረጉ እና ውጤት በወቅቱ ሂዶ አለማምጣት የተደጋገመ ድርጊት መሆኑን የአመልካች ክሊኒክ ሓላፊ የሰጡት የምስክርነት ቃል ውጤት ሂዶ በወቅቱ የማይመጣው ትራንስፖርት የለም እየተባሉ እንደሆነ፤ የተጠሪ የምርመራ ውጤት መሰረት በሌላ ስራ እንዲመደቡ የሰጡት ምክር ተቀባይነት እንደለገኘ፤ የነርቭ ችግር እንደሚያስከትል፡፡ የተጠሪ የደም ናሙና ሶስት ተወስዶ ዝቅተኛ ስለሆነ ወደ ጤነኛ ተመልሰዋል ለማለት የሚቻለው ሶስት ጊዜ ምርመራ ከተደረገ በኋላ የሚረጋገጥ እንጂ በአንድ በሁለት የተደረገ ምርመራ ውጤት ጤነኛ ነው ለማለት እንደማይቻል ሙያዊ ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡

 

አመልካች ምርመራ እንዲደረግ ማድረጉ ብቻ በቂ ነው ግዴታውን ወጥቷል የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ከምርመራ በኋላ በተገኘው ውጤት መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ላይ ነው፡፡ በትራንሰፖርት ምክንያት በወቅቱ አለማምጣት፤ ከመጣም በኋላ በባለሙያ የተሰጠ ምክር ተግባራዊ አለማድረጉ ግዴታው አለመወጣቱና ለጉዳዩ ትኩረት ያለሰጠው መሆኑን በማረጋገጥ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስሕተት ያለበት ሆኖ ተገኝተዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡


 

 

 

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌ/መ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 15958 በቀን 11/09/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የተሰጠ ውሳኔ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 168399 በቀን 29/11/2007 ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ፀንተዋል፡፡

2.  ከዚህ በፊት የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስተዋል፡፡ ይፃፍ፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ወገኖች ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግተዋል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

የ/ማ