100474 civil procedure/ amendment of pleading/ new issues

በክስ ማሻሻል ሥርዓትና ዓላማ ቀድሞ ዳኝነት ከተጠየቀበት ጉዳይ ፈጽሞ የተለየ ጥያቄ ለማቅረብ የማይቻል ስለመሆኑ፣

ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 91

ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 342

የሰ/መ/ቁ. 100475

 

ታህሳስ 20 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመስል እንደሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- አቶ ሳምሶን አበራ ጠበቃ ክፍሌ አማረ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ፀሐይ አበራ ጠበቃ አሸናፊ ወጂ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን እንደቅደም ተከተላቸው አመልካች እና ተጠሪ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩም ፍቺን ተከትሎ የተነሳ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ነው፡፡ ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለው መሠረታዊ ጭብጥም የአሁኑ አመልካች የንብረት ክፍፍል በጠየቀበት ጊዜ ለአሁን ክርክር መነሻ የሆነችውን የሰሌዳ ቁጥር 3-15556 መኪና በተመለከተ መኪናው የተፈራችው በጋብቻ ውስጥ ሳይሆን እንደባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ የተፈራች ስለመሆኑ ለማሳየት አመልካች የክስ ማሻሻያ ጥያቄ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ፈቅዶ ክሱ ከተሻሻለ በኃላ ጋብቻ ከመመሰረቱ በፊት ከጥቅምት 1998 እስከ ህዳር 2001 ዓ.ም  አብሮው ይኖሩ እንደነበር ግምት ተወስዶ መኪናው የጋራ ንብረት ነች ተብሎ ተወስኗል፡፡

 

የአሁኑ ተጠሪ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 91 አቤቱታ የሚሻሻልበት ሥርዓትና ዓላማው ዳኝነት ከተጠየቀበት ጉዳይ ፈፅሞ የተለየ ጥያቄ ለማቅረብ እንደማይፈቀድ፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት አብረን ኖረን ነበር በዚህ ጊዜ የተፈሩ  ንብረቶች  እንዲከፈል  በሚል  ማስረጃዎች  ጭምር  በመጥቀስ  የቀረበው     ጥያቄ


የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.256 ድንጋጌን ያላገናዘበ ስለመሆኑ፤ የፍቺ ውጤት በተጠየቀበት መዝገብ እንደባልና ሚስት አብረው ኑረዋል ወይስ አልኖሩም? የሚለው ጥያቄ በክስ ማሻሻል ምክንያት ተቀብሎ መታየቱ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን የተከተለ አይደለም፡፡ እንደባልና ሚስት አብረው ሳያቋርጡ ኖረዋል ወይስ አልነበረም? የሚለው ነጥብም ማየት ባያስፈልገውም እንደተመለከተው ከጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም እስከ ነሃሴ 19 /1998 ዓ.ም ድረስ አብረው ቆይተው ከዛ በኃላ ግንኝነታቸው እንደተቋረጠ እንደገና አብረው መኖር የጀመሩት ጋብቻ ከተመሰረተበት ህዳር 2001 ዓ.ም ጀምሮ ስለመሆኑ የአሁን ተጠሪ ምስክሮች የአመልካች ምስክሮች ከሰጡት ቃለ ሚዛን በሚደፋ አግባብ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የሰሌዳ ቁጥር 3-15556 የሆነውን መኪና  የግለ ንብረት ነው በማለት የሥር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል፡፡ ባንክ ላይ ነበር በተባለው ገንዘብ በተመለከተ ግን የስር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ በማየት እንዲወስን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.343 /1/ መልሶታል፡፡የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቅሬታ ቢያቀርቡም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡ ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን ውሳኔና ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

ጉዳዩ ለሰበር ይቅረብ በመባሉ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ የአመልካች ቅሬታ መሠረታዊ ይዘትም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት አብረው ይኖሩ እንደነበር የፍቺ ጥያቄ የቀረበበት መዝግቦ ለመግለጽ እንደማይገደዱ፤ በአመለካች የቀረቡ ምስክሮችም በተጠሪ ከቀረቡ ምስክሮች በተሻለ አግባብ ያስረዱ በመሆኑ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት  በመሆን አብረው ይኖሩ እንደነበር የሕግ ግምት እንዲወሰድላቸው ጠይቋል፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው ከ1998 እስከ ተጋቡበት 2001 ዓ.ም ያልተቋረጠ ግንኙነት መኖሩን አመልካች አላስረዱም፡፡ በግል የተፈራ ንብረት የግል ነው መባሉ በአግባቡ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ የመልስ መልስም ቀርቧል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም ግራ ቀኙ በጽሑፍ ያደረጉት ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና ጉይዩ ለሰበር ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

 

ከሥር የክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ቤት የሰሌዳ ቁጥሩ 3-15556 የሆነውን መኪና የአመልካች እና ተጠሪ የጋራ ንብረት ነው በማለት የደረሰበት ድምዳሜ በመሻር መኪናው የተጠሪ የግል ሀብት ነው በማለት ወስነዋል፡፡ አመልካች ከሥር ፍ/ቤት አንስቶ አጥብቆ የሚከራከረው የፍቺ ጥያቄ በቀረበበት መዝገብ ላይ እንደባልና ሚስት አብረው ይኖሩ ነበር የሚል ክርክር የማቅረብ ግዴታ እንደሌላቸው ነው፡፡ የሥር  ከፍተኛ


ፍርድ ቤት የክስ ማሻሻል ጥያቄው የተለየ ውጤት የሚያመጣ መሆን የለበትም እንዲሁም አመልካችና እና ተጠሪ እንደባልና ሚስት አብረው ስለመኖራቸው አላስረዱም በማለት ውሳኔ መስጠቱ መዝገቡ ያሳያል፡፡

 

በመሰረቱ አቤቱታ የሚሻሻልበት ዓላማና ማሻሻያው የሚቀርብበት ስርዓት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 91 ሥራ ተመልክቷል፡፡ የክስ ማሻሻያ ጥያቄ መሠረታዊ ዓላማም ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ የሚረዳ መሆኑ በፍርድ ቤቱ የታመነ ከሆነ ነው፡፡ አመልካች የፍቺ ጥያቄ በቀረበበት መዝገብ ላየ እንደባልና ሚስት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ሲኖሩ ቆይተው በ2001 ዓ.ም ስለመጋባታቸው ያቀረቡት ክርክር የነበረ ስለመሆኑ መዝገቡ አያሳይም፡፡ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደባልና ሚስት እንኖር ነበር የሚለው አከራካሪ ጥያቄ የተነሳው የጋራና የግል ንብረት ለመለየት የተደረገው ክርክር ስለመሆኑ የሥር ፍ/ቤት መዝገብ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

 

በሥር የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፍቺን ተከትሎ የቀረበው የንብረት ክፍፍል ጥያቄ የቀረበው በአመልካች ነው፡፡ አመልካች የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ሲያነሱ ለክርክሩ መሠረት የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች በዝርዝር መገለጽ ያለባቸው ስለመሆኑ ከፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 222/1/ ድንጋጌ መሠረታዊ ይዘት የምንረዳው የጋራ ንብረት የተፈጠረበት /የተገኘበት/ አግባብ እና  ሁኔታ በቀረበው ክስ በግልጽ ማመላከት ይጠበቅ ነበር፡፡ አመልካች ለክርክሩ መነሻ የሆነው የሰሌዳ ቁጥሩ 3-15556 በክስ ማሻሻያ እንደገለጹት እንደባልና ሚስት ሲኖሩ በነበሩበት ጊዜ ከሆነ መጀመሪያ ክስ ሲያቀርቡ ዳኝነት ያልጠየቁበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ አንድ የመብት ጥያቄ የሚያቀርብ ተከራካሪ ወገን ለክርክሩ መነሻ የሆነ መሠረታዊ ፍሬ ነገሮች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 222(1)(2) በሚያዘው አግባብ "ምክንያት የሆኑ ነገሮች እና የተፈጠሩበት ሁኔታ" በግልጽ ዳኝነተ መጠየቅ እየተገባው የፍቺ ውጤት ክርክር ሲደረግ ከጋብቻ ውጭ እንደባልና ሚስት አብረን ኖረናል የሚለው አዲስ የተለየ ክርክር ማቅረብ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 91 ያላገናዘበ ነው የሚለው የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድምዳሜ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

የሥር ፍርድ ቤት የአቤቱታ ማሻሻያ ጥያቄ የቀረበበት አግባብ ብቻ ሲሆን በእርግጥም በአመልካች እና ተጠሪ መካከል ከ1998 ዓ.ም እስከ 2001 ዓ.ም ያልተቋረጠ ግንኙነት ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ጭብጥ መርምሮ በፍሬ ነገር ደረጃ ግንኙነት አልነበረም ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዎል፡፡ አንድ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በመዝገቡ ላይ በሰፈረው ማስረጃ መሠረት ተገቢ ሁኖ ሲያገኘው ጭብጥን በማሻሻል ወይም በመለወጥ ተገቢ የመሰለውን የመጨረሻ ፍርድ መስጠት የሚችል ስለመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 342 ሥር ተደንግጓል፡፡ የተያዘው ጉዳይ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመረመረው አቤቱታው የተሻሻለበት አግባብ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም አመልካች እና ተጠሪ እንደባልና ሚስት አብረው ኖረዋል ወይስ አልኖሩም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ    የግራ


ቀኙ ማስረጃ መርምሮ ግንኙነት አልነበረም፡፡ መኪናው የግል ሀብት ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የፍሬ ነገር እና የማስረጃ ምዘናና ድምዳሜ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የሚለወጥበት አግባብ የለም፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሕግ ተለይቶ የተሰጠው ሥልጣን በማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት መፈጸም ያለመፈፀሙን በማረጋገጥ ፍርድ መሰጡት ስለመሆኑ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ /ሀ/ እና አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች መሠረታዊ ይዘት የምንገነዘበው ነው፡፡ በነዚህ ሁሉ ምክንያት የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰሌዳ ቁጥሩ 3-15556 በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ በመሻር መኪናው የተጠሪ የግል ንብረት ነው ማለቱና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መጽናቱ በጉዳዩ መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈፀሙን ስለማያሳይ ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 135453 በ21/04/2006 ዓ.ም የሰጠው፣ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 89470 በ15/08/2005 ዓ.ም የሰሌዳ ቁጥር 3-15556 በተመለከተ የሰጠው ፍርድ መሻሩ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ. 97972 በ30/07/2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል፡፡

2.  የሰሌዳ ቁጥር 3-15556 የተጠሪ የግል ሀብት ነው መባሉ በአግባቡ ነው በማለት ወስነናል፡፡

3.  የዚህ ችሎት ክርክር ያስከተለው ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ

የተሰጠ የዕግድ ትዕዛዝ ካለ ተነስቷል፡፡ መዝገብ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡


 

ወ/ከ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡