95922 contract/ commercial code/ contract of carriage/ period of limitation

የመጓጓዣ ውልን መሰረት ያደረገ የካሳ ጥያቄ ሲቀርብ ጉዳዩ በየትኛው የህግ ማዕቀፍ እንደሚገዛ መለየት የይርጋውንም ሆነ የካሳ ስሌቱን በአግባቡ ለመዳኘት የሚያስችል ስለመሆኑ የን/ሕ/ቁጥር 587፣595 ፣597፣599 እና 603 የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143፣ 2090

 

የሰ/መ/ቁ. 95922

መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ሌሊሴ ደሳለኝ

 

 

አመልካች፡- 1.አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ አ.ማ - ነ/ፈጅ ብሩክ ዘረሁን - ቀረቡ 2. አቶተፈራ ታርቄ - ቀረቡ

ተጠሪ፡-    1.ሃምሳ አለቃ ለገሰ ክፍለይ    ጠበቃ አወግቸው መኮንን ቀረቡ 2. ወ/ሮ አክበረት አማረ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 

 ፍ ር ድ

 

 

ጉዳዩ የአጓዥ ተጓዥ ውልን መሰረት ያደረገን የጉዳት ካሳ ይከፈለን ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች በአሁኑ 2ኛአመልካች ላይ በሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትግንቦት 28 ቀን 2005 ዓ.ም በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- ንብረትነቱ የአሁኑ 2ኛአመልካች የሆነ የሰሌዳ ቁጥር ኢት 3-10457 ፣ የጎን ቁጥሩ 1320 የሆነ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ የተጠሪዎች ልጅ የሆነውን አለም ለገሰ ከአዲስ አበባ ተሳፍሮ ወደ መቐሌ በመጓዝ ላይ እያለ ደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ 09 ተብሎ  ከሚጠራው ስፍራ ሲደርስ መኪናው ተገልብጦ በዚህ ምክንያት የልጃቸው ህይወት ማለፉንና በህይወትእያለም በግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ ይረዳቸው የነበረ መሆኑን ገልጸው በጠቅላላው ብር 484,000.00( አራት መቶ ሰማንያ አራት ሺ ብር) ካሳ እንዲከፈላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኑ 2ኛ አመልካችም ሟች በመኪናቸው ተሳፍረው ሲሄድ መሞቱን ሳይክዱ ግንኙነቱ የመጓጓዣ ውልን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ክሱ ከውል ውጪ ሊቀርብ እንደማይገባ፣ በአጓዥ ግንኙነትም ክሱ መቅረብ የነበረበት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁኖ እያለ ከአራት ዓመታት በላይ ቆይቶ መቅረቡ ያላግባብ መሆኑን፣ በተሳፋሪዎች ለሚደርስ ጉዳትም ከአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የመድን    ውል


የገባ  መሆኑን  ጠቅሶ  ይኼው  አካል  ወደ  ክርክሩ እንዲገባለት    ጠይቆአል፡፡  የአሁኑ 1ኛ አመልካችም ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብቶ የተጠሪዎች ክስ ከውል ውጪ ሕግን መሰረት አድርጎ መቅረቡ ያላግባብ መሆኑን፣ ክሱም በይርጋ የሚታገድ መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያቀረበ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም የተጠሪዎች የካሳ ስሌት ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን ሕግና በእርግጥም ያጡትን ጥቅም ያህል በማስረጃ አስደግፎ ያልቀረበ መሆኑን ጠቅሶ ተከራክሯል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም የይርጋ መቃወሚያውን ያለፈው ሲሆን ፍሬ ነገሩን በተመለከተ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ ግንኙነቱ በንግድ ሕጉ የሚገዛ መሆኑንና አደጋው የደረሰውም በንግድ ሕጉ አንቀፅ 599 አግባብ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ መረጋገጡን ደምድሞ ተጠሪዎች ብር 40,000.00 የጉዳት ካሳ፣ ብር 1000.00 የሕሊና ጉዳት ካሳ፣ ለአስክሬን ማጓጓዣ የአወጡት  ብር

11,000.00 በድምሩ ብር 52,000.00 (ሃምሳ ሁለት ሺህ ብር) እንዲከፈላቸው፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ  የአሁኑ  1ኛ  አመልካች በሰጠው       የመድን  ሽፋን  መጠን  ብር  10,000.00 (አስር ሺህ)፣የአሁኑ 2ኛ አመልካች ደግሞ ቀሪውን ብር 42,000.00 (አርባ ሁለት ሺህ) ለተጠሪዎች እንዲተኩ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካቾች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ይግባኛቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞባቸዋል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የተጠሪዎች   ልጅ     በ2ኛ አመልካች ንብረት በሆነው የሕዝብ ተሸከርካሪ ተሳፍረው በመሄድ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ ሕይወቱ ያለፈ ሁኖ እያለ ክሱ ከሁለት አመት በላይ ቆይቶ ቀርቦ የይርጋው መቃወሚያ ታልፎ ለተጠሪዎች ከብር 40,000.00 (አርባ ሺህ) በላይ የጉዳት ካሳ እንዲከፈል መወሰኑ በን/ሕ/ቁጥር 587 እና ተከታይ ድንጋጌዎች በተለይም የን/ሕ/ቁ/ጥር 603 እና 597 ድንጋጌዎችን ያላገናዘበ ነው የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገው    አመልካቾች ያቀረቡት የይርጋ ተቃውሞ ታልፎ አመልካቾች ለክሱ ኃላፊ የመባላቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ግራ ቀኙ በጹሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራቀኙን ክርክርለሰበር አቤቱታ      መነሻ        ከሆነው ውሳኔ   እና    አግባብነት  ካላቸው ድንጋጌዎችጋርበማገናዘብ            ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው አበይት ጭብጦች፡-

1. ጉዳዩ መዳኘት ያለበት ከውል ውጪ ኃላፊነትን በሚገዙት ድንጋጌዎች ነው? ወይስ በንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች ነው? እና

2.  ክሱ በይርጋ ሊታገድ ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚሉትን ሁኖ አግኝቷል፡፡

 የ መጀ መሪያ ውን ጭብጥ በተመ ለከተ፡ - ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው በግብርና እርሻ ስራ ተሰማርቶ ይኖር የነበረው የተጠሪዎች ልጅ የህዝብ ማመላለሻ ሁኖ ለንግድ በሚሰራው ንብረትነቱ


የ2ኛ አመልካች ተሽከርካሪ ላይ ተሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ መቐሌ  ሲሄድ ተሸከርካሪው በመገልበጡ ምክንያት ለሕልፈተ ህይወት የተዳረገ መሆኑን ነው፡፡ የበታች ፍርድ ቤቶች የተጠሪዎችን የካሳ ጥያቄ በመመልከት ተገቢ ነው ያሉትን ዳኝነት ሲሰጡ የአመልካቾችን ኃላፊነት የወሰኑት የንግድ ሕጉን መሰረት በማድረግ ስለመሆኑም ከውሳኔው ግልባጭ ተመልክተናል፡፡ በ2ኛ አመልካችና በሟች መካከል የንግድ ህግ ቁጥር አንቀጽ 587 በሚደነግገው መሠረት የአጓዥና የመንገደኛ ግንኙነት መኖሩን አመልካቾችና ተጠሪዎች በስር ፍርድ ቤትና በዚህ ሰበር ባቀረቡት ክርክር የሚተማመኑበት ጉዳይ ስለመሆኑ ተገንዝበናል፡፡ በአመልካቾችና በሟች መካከል ሰው ለማጓጓዝ የተደረገ ውል መኖሩን አመልካቾችና ተጠሪዎች የሚስማሙበት ከሆነ 2ኛ አመልካች ሟች ዋጋ ከፍለው ሲጓጓዙበት የነበረው የትራንስፖርት ተሽከርካሪ ባለሀብት  ሲሆኑ 1ኛ አመልካች ደግሞ በመኪናው ተሳፋሪ ለሚደርሰው ጉዳት የመድን ሽፋን የሰጠ ነው፡፡ በን/ሕ/ቁጥር 588 ድንጋጌ ይዘት ሲታይ አጓዡ መንገደኛውን በመልካም ይዞታና ጥበቃ እንደዚሁም ስለ ምቾቱና ስለ ጉዞው በውሉ የተወሰነውን ጊዜ አክብሮ እንደተወሰነው እመድረሻ ስፍራ የማድረስ ግዴታ እንዳለበት በሐይለ ቃል አስቀምጦ እናገኛለን፡፡ የዚህ ድንጋጌ መሠረታዊ ይዘት የአጓዡን የትራንስፖርት መኪና በኃላፊነት ተረክቦ የመኪናውን ደህንነትና ብቃት አረጋግጦ የትራፊክን ደንብና ሥርዓትን አክብሮ የማሽከርከር ኃላፊነት ያለበት አሽከርካሪ /ሹፌር/ ረዳቱና ሌሎች ሰራተኞች መንገደኛውን መልካም ይዞታና ጥበቃ እንደዚሁም ምቾት በመጠበቅ በሰላም ወደሚፈለግበት ቦታ የማድረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስቻል ሲሆን ይህንኑ በሕግ የተጣላባቸውን ግዴታ ካልተወጡ ደግሞ መንገደኛው በጉዞው ላይ ስለሚደርስበት መዘግየትና በጉዞው ጊዜ ወይም በሚሣፈርበት ወይም በሚወርድበት ጊዜ በአደጋ ምክንያት ለሚደርስበት መቁሰል ወይም የአካል ማጉደል ወይም የህይወት ማለፍ አጓዡ ኃላፊ እንደሚሆን በንግድ ህግ አንቀጽ 595 ስር በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ አጓዡ መንገደኛው በጉዞ ጊዜ በሚሣፈርበትና በሚወርድበት ጊዜ በአደጋ ምክንያት ለሚደርስበት መቁሰል ወይም የአካል መጉደል ወይም ህይወት ማለፍ አጓዡ በኃላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን በመሠረታዊ መርህነት የሚያስቀምጥ ሲሆን

፣ አጓዡ ከኃላፊነት ነጻ የሚሆንባቸዉን ልዩ ሁኔታዎች የሀላፊነቱን መጠንና አጓዡ በህግ ከተደነገገው መጠን በላይ በሀላፊነት ሊጠየቅ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች የሚደነግጉ ልዩ ድንጋጌዎች አካቶ ይዟል፡፡ በንግድ ህግ አንቀጽ 595 ከተደነገገው ኃላፊነት አጓዡ ነጻ የሚሆንበትን ሁኔታ የሚደነግገው የንግድ ህጉ አንቀጽ 596 ሲሆን በንግድ ህግ አንቀጽ 596 አጓዡ በመንገደኛው ላይ የአካል መጐዳት ወይም የሞት አደጋ የደረሰው ከአቅም በላይ በሆነ ከፍተኛ ሀይል መሆኑን ፣ ወይም ጉዳቱ የደረሰው በሶስተኛ ሰው ጥፋት መሆኑን ወይም በመንገደኛው ጥፋት መሆኑን ያስረዳ እንደሆነ አጓዡ ከኃላፊነት ነጻ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የካሳ መጠኑን በተመለከተ የቀረበውን ቅሬታ ስንመለከተውም አጉዡ በንግድ ህግ ቁጥር 596 መሠረት አደጋው የደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ካልቻለ በመንገደኛው ላይ ለደረሰው ጉዳት


በኃላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን የንግድ ሕግ ቁጥር 597 ድንጋጌ ያሳያል፡፡ የኃላፊነት መጠን በተመለከተ ደግሞ ለአንድ መንገደኛ ከብር 40,000 /አርባ ሺ ብር/ እንደማይበልጥ የንግድ ህግ አንቀጽ 597 በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ በንግድ ህግ አንቀጽ 597 የተደነገገው የኃላፊነት መጠን አጓዡ በንግድ ህግ አንቀጽ 596 የተደነገጉትና ከኃላፊነት ነጻ የሚያደርጉት ሁኔታዎች መኖራቸውን ለማስረዳት ባልቻለበት ሁኔታና መንገደኛው በንግድ ህግ አንቀጽ 599 በሚደነገገው መሠረት አጓዡ አደጋ ሊያደርስ የሚችል መሆኑን እያወቀ በፈጸመው ተግባር ወይም ጉድለት ምክንያት አደጋው የደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ባልቻለበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆን ድንጋጌ ነው፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ግን የ2ኛ አመልካች ንብረት የሆነውን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ያሽከረክር የነበረው የ2ኛ አመልካች ሰራተኛና የመኪናው ሹፌር የሆነው ለአደጋው ምክንያት ስለመሆኑ ያለመረጋገጡንና በወንጀልም ክስ ተመስርቶበት በሂደት ላይ ያለ ወይም በሕጉ አግባብ የተቋረጠ ወይም የተቀጣ ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤት አልተረጋገጠም፡፡ በንግድ ህግ ቁጥር 588 በሚደነግገው መሠረት የመንገደኛውን መልካም ይዞታ ደህንነትና ምቾት በመጠበቅ መንገደኛውን የማጓጓዝ ኃላፊነቱን ሊወጡ የሚገባቸውን ወገኖች የመኪና ባለቤት፣ ሹፌር፣ ረዳቱና ሌሎች ሰራተኞች ሊሆኑ የሚችሉበት አግባብ መኖሩን፣ በንግድ ህግ አንቀጽ 599 “አጓዡ የተፈፀመው ተግባር ወይም ጉድለት” የሚለው ሀረግ አጓዡ በግሉ የፈጸመውን ተግባር ወይም ጉድለት የሚመለከት ሣይሆን የአጓዡ ሰራተኞች አደጋ ሊያደርስ ወይም ሊፈጠር እንደሚችል እያወቁ የፈጸሙትን ተግባር ወይም ጉድለት የሚያካትት ስለመሆኑ  በሰ/መ/ቁጥር  67973 በሆነው መዝገብ ላይ በቀረበው ጉዳይ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በማናቸውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያሰገድድ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት የተያዘው ጉዳዩ ሲታይም አደጋው የደረሰው የ2ኛ  አመልካች  መኪና ሲያሸከረክር የነበረው ሹፌር ባጠፋው ጥፋት ስለመሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች የክርክር ሂደት ያልተረጋገጠ በመሆኑ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ያለው የን/ሕ/ቁጥር 599 የሚሆንበት አግባብ የሌለ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እንዲህ ከሆነ 2ኛ አመልካች በተጠሪዎች ልጅ ላይ ለደረሰው  የሞት ጉዳት በንግድ ህግ አንቀጽ 597 ከተደነገገው በላይ ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አይኖርባቸውም፡፡ በመሆኑም አመልካች በንግድ ህግ አንቀጽ 597 ከተደነገገው የኃላፊነት መጠን በላይ ለተጠሪ ካሣ የመክፈል ሀላፊነት እንደሌለባቸው የንግድ ህግ አንቀጽ 599 ድንጋጌ የሚያስገነዝበን ነው፡፡ በን/ሕ/ቁ ህግ ቁጥር 599 ድንጋጌ መሠረት ለመንገደኛው ካሣ የመክፈለ ኃላፊነት ያለበት አጓዥ ለመንገደኛው የሚከፍለው የካሣ መጠን ለመወሰን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2091 እና 2092 የተደነገጉት የካሳ አከፋፈል መርሆች አግባብነት ያላቸው ስለመሆናቸውም ይህ ችሎት ከላይ በተጠቀሰው የሰበር መዝገብ አሰገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ጉዳዩ ሲታይም ካሳ የሚከፈለው ጉዳት መኖሩ ሲረጋገጥ ሲሆን የካሳ አተማመን፣ መጠንና አከፋፈልን    በተመለከተ


በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090፣ 2091፣ 2092፣ 2095 እና በሌሎች ድንጋጌዎች የተቀመጠ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ለሚጠየቅ የአጓዥ ተጓዥ ግንኙነት ተፈፃሚነት የሚኖረው የይርጋ ጊዜ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143 ድንጋጌ ስር ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ተጠሪዎች ክሱ ከውል ውጪ ኃላፊነትን የሚገዙትን ድንጋጌዎችን መሰረት አድርገው ማቅረባቸውም ሆነ የስር ፍርድ ቤት ይርጋውን በተመለከተ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143 ድንጋጌን መሰረት አድርጎ መመልከቱ በ2ኛ አመልካችና በሟቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ያላገናዘበ ሁኖ አግኝተናል፡፡ የካሳውን መጠን በን/ሕ/ቁጥር 597 ድንጋጌ ማስላቱ ተገቢነት የነበረው ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተመለ ከተ፡ -አጓዡ በንግድ ህግ ቁጥር 596 መሠረት አደጋው የደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ካልቻለ በመንገደኛው ላይ ለደረሰው ጉዳት በኃላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን የንግድ ሕግ ቁጥር 597 ድንጋጌ ያሳያል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ሟች የሞቱት ንብረትነቱ በ2ኛ አመልካች በሆነ የሰው መጓጓዣ አገልግሎት ይሰጥ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ሲሆን በመካካላቸው ካለው የትራንስፖርት ውል ግንኙነት አኳያ ሲታይ አመልካቾች ለጉዳቱ ኃላፊ የሚሆኑበት ሁኔታ በንግድ ህጉ ወይም በዚሁ ሕጉ በልዩ ሁኔታ በአንቀፅ 599 በተመለከተው አግባብ ነው፡፡ ስለሆነም በንግድ ሕጉ ስለ ይርጋም ሆነ ለካሳ የተደገጉትን ድንጋጌዎች ወይም በንግድ ህጉ አንቀፅ 599 በተመለተከው ሁኔታ ጉዳዩን ለመዳኘት ይቻል ዘንድ አስቀድሞ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎችን መለየት የግድ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የመጓጓዣ ውልን መሰረት አድርጎ የሚቀርበው ክስ የሚታገድበት የይርጋ ጊዜና የካሳ መጠኑ የሚሰላበት አግባብ በንግድ ሕጉ አንቀፅ 599 አግባብ በልዩ ሁኔታ ጉዳዩ ሲታይ ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ሊኖረው ከሚገባው የይርጋ ድንጋጌ እና የካሳ አሰላል የተለየ መሆኑን በንግድ ሕጉ አንቀፅ 587፣ 603 እና 597 ድንጋጌዎችን በአንድ በኩል፣ የንግድ ሕጉ አንቀፅ 599 እና ከውል ውጪ ኃላፊነትነት በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143፣ 2090 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች የተቀመጡትን ሁኔታዎች በሌላ በኩል በመመርመር የምንረዳው ጉዳይ ነውና ስለሆነም የመጓጓዣ ውልን መሰረት ያደረገ የካሳ ጥያቄ ሲቀርብ ጉዳዩ በየትኛው የህግ ማዕቀፍ እንደሚገዛ መለየት የይርጋውንም ሆነ የካሳ ስሌቱን በአግባቡ ለመዳኘት የሚያስችል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪዎች ክስ የመሰረቱት ከውል ውጪ ኃላፊነትን የሚገዙ ድንጋጌዎችን ጠቅሰው ሲሆን የአሁኑ አመልካቾች የክሱ አመሰራረት ከውል ውጪ ኃላፊነትን መሰረት ማድረጉ ያላግባብ መሆኑን በመጥቀስ ግንኙነቱ የመጓጓዣ ውል መሆኑንና በንግድ ሕጉ ሲታይም ክሱ በይርጋ የሚታገድ መሆኑን ገልፀው ተከራክረው የስር ፍርድ ቤት የይርጋውን መቃወሚያ በሟች ላይ የደረሰው የሞት አደጋ በወንጀል ተጠቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ጠቅሶና የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(2) ድንጋጌን ዋቢ በማድረግ ከአለፈው በኃላ የካሳውን መጠን


ሲወስን ግን አደጋው የደረሰው በጥፋት ስለመሆኑ ያለመረጋገጡንና የን/ሕ/ቁጥር 599 አግባብ ካሳው ሊሰላ የሚችልበት ምክንያት ያለመኖሩን ገልጾ ካሳውን በን/ሕ/ቁጥር  597 አግባብ መወሰኑን የውሳኔው ግልባጭ በግልጽ ያሳያል፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት ለይርጋ ጉዳይ ከውል ውጪ ኃላፊነትን በተመለከተ መሰረት ማድረጉ በካሳው ስሌት ጊዜ ከደረሰበት ምክንያት ጋር የሚጋጭ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ጉዳዩ በን/ህ/ቁጥር 599 አግባብ በተቀመጠው ልዩ ሁኔታ አግባብ ወደ ውል ውጪ ድንጋጌዎች የሚያስኬድ ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ ለይርጋ አፈጻጸም ወደ ፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143 ድንጋጌ ለመሄድ የሚቻልበት አግባብ የለም፡፡ ተጠሪዎች ጉዳቱ በን/ሕ/ቁጥር 599 አግባብ በተቀመጠው ጥፋት የደረሰ ስለመሆኑ ያላስረዱ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያሳይ ሲሆን የስር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የደረሰበት ድምዳሜ ከሕግ እና ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጪ ነው የሚሉ ከሆነም በስርዓቱ መሰረት ያቀረቡት ይግባኝ ወይም የሰበር ክርክር ስለመኖሩ ተጠሪዎች ገልጸው ያለመከራከራቸውን ተገዝበናል፡፡ እንዲሁም የ2ኛ ተጠሪን ተሽከርካሪ ያሽከረክር የነበረው አሽከርካሪ በወንጀል ተከሶ ነበር የሚል ክርክር ተጠሪዎች ከማቅረባቸው ውጪ ይህንኑ የሚያሳይ ማስረጃ ያለማቅረባቸውንና የወንጀል ክርክሩ ተጀምሮ ከነበረም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሰነድ እንዲያቀርቡ በቂ ጊዜ ተሰጥቶአቸው ማስረጃው ያለመቅረቡ የይርጋው ጉዳይ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(2) ድንጋጌ አግባብ የሚታይ ነው ለማለት የሚያስችል አግባብ ያለመኖሩን የሚያስገነዝብ ሁኖ አግኝተናል፡፡

እንግዲህ በ2ኛ አመልካች በተጠሪዎች ልጅ መካከል የተመሰረተው የመጓጓዣ ውል ነው ከተባለና ግንኙነቱ በንግድ ሕጉ የሚገዛ ነው ከተባለ ይርጋውን አስመልክቶም ይኼው ልዩ ሕግ በአንቀፅ 603 ስር በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት አጓዥ ተጓዥ መሰረት ተደርገው የሚቀርቡት ክሶች በንግድ ሕጉ 603 በተደነገገው አግባብ መሰረት በሁለት ዓመት ጊዜ መቅረብ እንደአለባቸውና በዚህ አግባብ ካልቀረቡ ግን የአጓዥ ተጓዥ ግንኙነትን መሰረት በማድረግ ማቅረብ እንደማይቻል የድንጋጌው ይዘት ያሳያል፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪዎች ክስ የመሰረቱት ልጃቸው ሰኔ 07 ቀን 2001 ዓ/ም በመኪና መገልበጥ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ ግንቦት 28 ቀን 2005 ዓ/ም መሆኑን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ይህ ጊዜ የን/ሕ/ቁጥር 603 መሰረት ተደርጎ ሲታይ ሶስት አመት ከ11 ወራት ከ21 ቀናት በኋላ ክስ መቅረቡን የሚያስገነዝብ በመሆኑና ይርጋውን ሊያቋርጥ የሚያስችል የሕግ ምክንያትም የሌለ ሁኖ ስለአገኘነው የበታች ፍርደ ቤቶች ለጉዳዩ አግባብነት የሌለውን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143 ድንጋጌን መሰረት አድርገው የይርጋ ክርክሩን ማለፋቸው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል፡፡ በዚህም ተከታዩን ወስነናል፡፡


 ው ሣ ኔ

1. በሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 0111646 ህዳር 13 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 01- 14794 ታህሳስ 01 ቀን 2006 ዓ/ም በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሸሯል፡፡

2.  ተጠሪዎች ካሳ እንዲከፈላቸው የመሰረቱት ክስ የሚገዛው በን/ሕ/ቁጥር 587፣   በን/ሕ/ቁጥር

595 597 እና 603 ድንጋጌዎች አንፃር በመሆኑ ክሱ በሁለት ዓመት ይርጋ የታገደ ነው ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ሃ/ወ