98583 contract/ authentication of date/

የአንድን የውል ሰነድ እርግጠኛ ቀን የሚባለው ሰነዱን የፃፈው ወይም የተቀበለው እንደ ሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ፅ/ቤትን የመሰለ የመንግስት መስሪያ ቤት ሲሆን የፃፈበት ወይም የተቀበለበት ቀን ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.2015(ሀ)

የሰ//.98583

መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

 

ተሻገር ገ/ሥላሴ ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብረሃ መሰለ

አመልካቾች፡- 1ኛ/ ወ/ሮ ኤደን ሲሳይ         ጠበቃ አቶ በላይነህ ማሞ ቀረበ 2ኛ/ ወ/ሮ አስቴር ደምሴ

ተጠሪ፡- አቶ ሰይፈ ዓለሙ - የህፃን ናትናኤል ሰይፋ እና የህፃን ዮናታን ሰይፋ ሞግዚት ጠበቃ አለማየሁ አበበ

 

መዝገቡን መርምረን ተከታዮን ወስነናል ፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ጉዳዩ የውል ይፍረስልኝ የዳኝነት ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ጉዳዩ የጀመረው በፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ነው ፡፡ የአሁን ተጠሪ ከሳሽ ፤የአሁን አመልካቾች ደግሞ ተከሳሽ ነበሩ፡፡

 

ከሥር ፍ/ቤቾች የውሳኔ ግልባጮች መረዳት እንደሚቻለው ከሳሽ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ የሟች ወ/ሮ ፈትለወርቅ ተረፈ በህይወት በነበሩበት ወቅት በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ቀበሌ 09/14 የቤት ቁጥር 750 የሆነ የድርጅት ቤት የነበራቸው ሲሆን ይህን ቤት 1ኛ ተከሳሽ ከሟች ውክልና ተሠጥቶኛል በሚል ሟች በከፍተኛ ህመም በነበሩበት ጥቅምት 25/2002 ዓ.ም ተደረገ በተባለ ውል ለ 2ኛ ተከሳሽ የሸጡ በመሆኑና ውሉንም አደረግን የሚሉት በውል አዋዋይ ፊት ሟች ከሞቱ ከዘጠኝ ቀን በኃላ በመሆኑ ፤ውክልናው በሞት ምክንያት ቀሪ ከተደረገ በኃላ የተደረገ በመሆኑና ፤ቤቱም በሚሊዮን የሚቆጠር ዋጋ የሚያወጣ ሆኖ እያለ ሞግዚት የሆንኩላቸውን ተተኪ ወራሾች ለመጉዳት በብር 250,000.00 ተሸጠ መባሉ ተገቢ ባለመሆኑ ውሉ እንዲፈርስ እንዲወሰን በማለት ጠይቀዋል ፡፡


ተከሳሾችም በየራሳቸው በሠጡት መልስ ሟች ቤቱን ሚያዝያ 1/2001 ዓ.ም በተደረገ የመንደር ውል የሸጡ መሆኑን፤በዚህ ውል ቤቱን ከዕዳ ነፃ ሲያደርጉ በአዋዋይ ፊት ለመፈረም በተስማሙት  መሠረት  ይህን  ለማክበር  ጥቅምት  25/2002 ዓ.ም የሽያጭ  ውል  መደረጉን

፤በዕለቱም በሠነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ለመፈራረም ውሉንና ምስክሮች ይዘው በአካል ቀርበው ወደ እገዳ ማጣሪያ ክፍል ተመርቶ ግብሩ ላይ እንዲታረም የተነገራቸው ታርሞ ከተጠናቀቀ በኃላ ውሉ በ 27/2/2002 ዓ.ም የተፈረመ መሆኑንና፤ ህዳር 7/2002 ዓ.ም የግዥ አገልግሎት ክፍያ የተፈፀመበት እንጂ ውሉ የተፈረመበት አለመሆኑን ፤ውሉ ከተፈፀመ በኃላ ሟች ወ/ሮ ፈትለወርቅ ተረፈ ጥቅምት 28/2002 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዮ መሆኑን ነገር ግን በ1/08/2001 ዓ.ም ከሽያጩ ገንዘብ ብር 200,000.00 መከፈሉን በመጥቀስ ውሉ ሊፈርስ እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡

 

ጉዳዮን በቅድሚያ የተመለከተዉ የሥር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ተመልክቶ በመጨረሻ በሰጠው ውሳኔ ሟች ለ 1ኛ ተከሳሽ ውክልና የሠጡትና በሠነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በ27/02/2002 ዓ.ም በወኪሉ 1ኛ ተከሳሽ እና በገዥ 2ኛ ተከሳሽ መካከል ውል ሲፈረምና ከሽያጩ የቀረው ገንዘብ ብር 5000.00 ሲከፈል በህይወት የነበሩ በመሆኑ ፤በፍ/ብ/ህ/ቁ.2232/1/ መሠረት ወካዮ ከሞተ የውክልናው ስልጣን ወዲያውኑ ቀሪ የሚሆን ቢሆንም በንዑስ ቁጥር 2 ሥር በእንዲህ አይነት ሁኔታ ተወካይ ሥራውን ቢያቋርጥ በጉዳዩ ላይ አደጋ የሚደርስበት እንደሆነና በዉክልናው ሥልጣን መሠረት ሥራውን ጀምሮ እንደሆነ የዋናው ወካይ ወራሾች ወይም ህጋዊ እንደራሲዎች አስፈላጊውን እስኪያደርጉና ራሳቸውም ሊያስቡበት እስኪችሉ ድረስ ስራውን መቀጠል አለበት በማለት የሚደነግግ በመሆኑ፤በተያዘውም ጉዳዮ 1ኛ ተከሳሽ ተወካዮ መሆናቸው ያልተካደና ውሉም ቀደም ብሎ በመንደር የተደረገውን ውል ለማዋዋል ሥልጣን ባለው አካል ፊት ለማድረግ መሆኑን መገመት የማያዳግት በመሆኑ ፤ይህ ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2232/2/ መሠረት ተወካዮ (1ኛ ተከሳሽ )ሥራውን ጀምሮት ስለ ነበር መቀጠል እንዳለበት የተደነገገውን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ከሳሽ ውክልናው ቀሪ ከሆነ በኃላ የተደረገው የሽያጭ ውል እንዲፈርስ ያቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡

 

ይግባኙ የቀረበለት የፌ/ከ/ፍ/ቤት በበኩሉ ክርክሩን ከሰማ በኃላ ባሳለፈው ውሳኔ ሚያዝያ 1/2001 ዓ.ም ተደረገ ስለተባለው የገንዘብ አከፋፈል በተመለከተ የአሁን 1ኛ አመልካች የሽያጭ ገንዘቡን እኔ እራሴ ቆጥሬ ተቀብያለሁ ሲሉ 2ኛ አመልካች ደግሞ ለሟች ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገንዘቡን ቆጥሬ በእጃቸው ሰጥቻለሁ በማለት የሚቃረን መልስ ማቅረባቸው የሽያጭ ውሉ ሚያዝያ 1/2001 ዓ.ም የተጀመረ ነው በማለት የሚያቀርቡትን ክርክር አሳማኝ የማያደርገዉ በመሆኑ፤ጥቅምት 25/2002 ዓ.ም የተደረገው የሽያጭ ውል ሟች ከመሞታቸው ከ3 ቀናት በፊት መሆኑና በሠነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት የተመዘገበው ደግሞ ህዳር 7/2002 ዓ.ም ሟች ከሞቱ ከዘጠኝ ቀን በኃላ


መሆኑ የታመነ ጉዳይ በመሆኑ፤የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2232(2) አግባብነት የሚኖረዉ በወኪሉ ቀድሞ የተጀመረው ሥራ ወራሾችን በሚጠቅም መልኩ እንዲቀጥል የተደረገ እንደሆነ ብቻ ሲሆን በተያዘው ጉዳዮ ግን ወኪሉ ወካያቸው ከሞቱ በኃላ በሟች ንብረት ላይ የሽያጭ ውል መፈራረማቸው ወራሾችን የሚጠቅም ሳይሆን ንብረቱን ለሌላ አሳልፎ በመስጠት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግና በእጅጉ የሚጐዳቸው በመሆኑ፤ የቤት ሽያጭ ውሉ ስልጣን ባለው አካል ፊት የተደረው ሟች ከሞቱ በኃላ ህዳር 7/2002 ዓ.ም ነው እንጅ እንደ መ/ሰጭዎች /የአሁን አመልካቾች / አባባል ሟች ከመሞታቸው ከ 3 ቀን በፊት ተጀምሮ ነበር ቢባል አንኳን ሟች በጠና ታመው ኮማ ውስጥ ነበሩ በተባለበት ሰዓት ላይ በመሆኑ በጅምር የቤት ሽያጭ ውሉ ላይ የሟች ፈቃድ ነበረበት ለማለት አያስደፍርም በማለት የሥር ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር በአመልካቾች መካከል ጠቅምት 25/2002 ዓ.ም የተጀመረውና ህዳር 7 ቀን 2002 ዓ.ም የተመዘገበው የሽያጭ ውል ሊፈርስ ይገባል በማለት ወስኗል ፡፡

 

የአሁን አመልካቾች ይህን ውሣኔ በመቃወም ይግባኙን ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ያቀረቡ ሲሆን ውሳኔው ጉድለት የለበትም ተብሎ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.337 መሠረት ይግባኙ ተሠርዟል ፡፡ የሰበር አቤቱታው ለዚህ ፍ/ቤት የቀረበው በዚህ ነው አመልካቾች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ተጠሪ መልስ እንዲሠጡበት ጥሪ የተደረገ ሲሆን ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በፅሑፍ አቅርበዋል ፡፡ ይህ ችሎትም የሠበር አቤቱታውን ቅሬታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካለው ህግ ጋር በማገናዘብ መርምሯል፡፡

 

ከላይ እንደተገለፀው አመልካቾች የሽያጭ ውሉ የተደረገው ሟች በህይወት ሳሉ በመሆኑ ወራሾች ሟች በህይወት ሳሉ የፈፀሟቸውን ህጋዊ ተግባራት መቃወም መብት ስለሌላቸው ውሉ እንዲፈርስ ያቀረቡት ክስ ተቀባይነት እንዳይኖረው የተከራከሩ ሲሆን ተጠሪ በበኩላቸው ውክልናው በወካዮ ሞት ምክንያት ቀሪ ከሆነ በኃላ የተደረገ ውል በመሆኑ ውሉ ሊፈርስ እንደሚገባ ተከራክረዋል ፡፡ ስለሆነም የሸያጭ ውሉ ተደረገ የሚባለው መቼ ነው የሚለውን አግባብ ካለው ህግ ጋር በማያያዝ መመርመሩ ተገቢ ይሆናል፡፡

 

የሸያጭ ውሉ የሚመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረትን በመሆኑ ውሉ በጽሑፍ ከመደረጉ በተጨማሪ ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው ሰው ወይም በዳኛ ፊት መደረግ ያለበት ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.1723/1/ ሥር ተደንግጓል ፡፡ የቤት ሽያጭ ውሉ ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው በዚህ የህግ ስርዓት /ፎርም/ መደረግ ይኖርበታል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በአዋዋይ ወይም በዳኛ ፊት እንዲደረግ የሚያስፈልገው የተዋዋዮችን ማንነት፣ያላቸውን ችሎታና መብት እንዲሁም ነፃ ፈቃዳቸውን መስጠታቸውን ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ውሉ የተደረገበትን ቀንም ለማረጋገጥ ነው፡፡


በተያዘው ጉዳይ እንደ አመልካቾች ክርክር ቤቱን የተመለከተ ዕዳና እገዳ ለማጣራትና ክፍያ ለማስፈፀም የውልና ማስረጃ ጽ/ቤት የተወሰኑ ቀናት መውሰዱ የተመለከተ ቢሆንም በውሉ ላይ ማህተሙ የተደረገውና የኘሮቶኮል ቁጥር ተሠጥቶት የተረጋገጠው ህዳር 7/2002 ዓ.ም መሆኑ እና በዚህ ቀን ውክልና ስልጣን ሰጭ በህይወት እንዳልነበሩ አላከራከረም፡፡

 

በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2015/ሀ/ መሠረት ሠነዱ የተፃፈበት እርግጠኛ ቀን ነው የሚባለው ሠነዱን የፃፈው ወይም የተቀበለው እንደ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤትን በመሠለ የመንግስት መ/ቤት ሲሆን የፃፈበት /የተቀበለበት/ ቀን መሆኑም ተደንግጓል፡፡ ፍሬ ነገሩን ለማጣራት በህጉ ሥልጣን የተሰጣቸው ፍ/ቤቶች የአመልካቾችን ክርክር ተቀብለው የሽያጭ ረቂቅ ሰነዱን ጽ/ቤቱ የተቀበለበትን ቀን እስካላረጋገጡ ድረስ በሰነዱ ላይ የተፃፈበት ቀን ተደርጐ የሚወሰደው በባለሥልጣኑ የተጻፈው ቀን ነው፡፡

 

ስለሆነም የቤት ሽያጭ ውሉ ስልጣን ባለው አካል ፊት የተደረገው ህዳር 7/2002 ዓ.ም ሲሆን በዚህ ጊዜ በሿሚው ሞት ምክንያት ለሻጭ /1ኛ አመልካች/ የተሰጠው ውክልና ቀሪ በሆነበትና ንብረቱን በሽያጭ ማስተላለፍ የሚያስችል ሥልጣን በሌለበት የተደረገ በመሆኑ ውሉ እንዲፈርስ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ ይገባል ተብሎ በመወሠኑ የተፈፀመ የህግ ስህተት የለም ብለናል፡፡

 

በሌላ በኩል የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል የተባለበትን ነጥብ በሥር ፍ/ቤቶች ያልተረጋገጠን ፍሬ ነገር የያዘና ለጉዳዮ አወሳሰን ተገቢነት የሌለውን የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2232/2/ መሠረት ያደረገ በመሆኑ መመርመር አላስፈለገንም ፡፡ በመሆኑም ተከታዮ ተወስኗል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ.131733 ታህሳስ 10/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ.96979 የካቲት 12/2006 ዓ.ም ያሳለፈው ተእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348/1/ መሠረት ፀንቷል፡፡

2.  በዚህ ፍ/ቤት ስለተደረገው ክርክር ግራ ቀኙ ወጪያቸውን ይቻሉ፡፡

3. የተሰጠ የዕግድ ትእዛዝ ካለ ተነስቷል ይፃፍ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡


 

መ/ብ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 
 
 

Google Adsense