112168 contract/ force majuer

ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ተከስቷል ሊባል የሚችለው በባለእዳው በምንም መልኩ በቅድሚያ ሊያስበው ወይም ሊገምተው የሚያስችል ክስተት ሲፈጠር ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ. 1792 በየብስ የእቃ ማጓዝ ስራን ለመደንገግ ተሻሽሎ የወጣው አዋጅ ቁ. 547/1999

 

የሰ/መ/ቁ. 112168

 

የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡-     የሺ ትራንስፖርት /የሺ ትራንስፖርት የጭነት ማመላለሺያ ባለንብረቶች  ማህበር/ ደምሴ ገበየሁ

 

ተጠሪ፡-   አቶ እስክንድር ዘርፉ - ዳዊት አባተ

 

መዝገቡ   የተቀጠረው   መርምሮ  ፍርድ   ለመስጠት   ነው፡፡   በመሆኑም   ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ የሰበር አቤቱታ ሊቀርብ የቻለው አመልካች የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 205919 በቀን 13/02/07 ዓ.ም የሰጠውን ፍርድ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 162749 በቀን 09/07/0227 ዓ.ም በማጽናቱ መሠረታዊ ስህተት የተፈፀመበት መሆኑን በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለታቸው ነው፡፡

 

ጉዳዩ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ጉዳት መድረስን የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የጀመረው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጀ ፍ/ቤት ሲሆን ከሳሽ የነበረው የአሁን ተጠሪ ሲሆን አመልካች 2ኛ ተከሳሽ እንዲሁም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ትራንዚት ሎጀስቲክ አገልግሎት 1ኛ ተከሳሽ ሲሆኑ ጣልቃ ገብ የነበሩት ደግሞ ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ እና አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ ነበሩ፡፡ ተጠሪ በተከሳሾች ላይ አቅርቦት የነበረው ክስ ቶዮታ ያሪስ 998 ሲሲ. የሻንሲ ቁጥር VNKKG96320A001372 የ2005 ምርት ዋጋ ብር 3000 ዩሮ የሆነ ከቤልጂየም ኢንትዊፕ ወደብ ኢትዮጵያ ሞጆ ደረቅ ወደብ ለሟጓጓዝ እና ለማስረከብ በሰነድ ቁጥር  LAU538 ከ1ኛ


ተከሳሽ ጋር ውል የገባ ቢሆንም 1ኛ ተከሳሽ ከተጠሪ ጋር የማጓጓዣ ውል የሌለው ንብረትነቱ የ2ኛ ተከሳሽ /የአሁን አመልካች/ የሆነ የሠሌዳ ቁጥር 3-51671 ኢት/3-17327 ኢት ተሳቢ በሆነ ተሽከርካሪ ከጅቡቲ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ ሲጓጓዝ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ ወድማል ስለዚህ በመኪናው የጉዞ ሰነድ ላይ የተቀነሰውን ብር 87148.50 /3000ዩሮ/፣ ለጭነት ብር 23546/1272.76 ዩ.ኤስ.ዲ/ እና ብር 3862.08፤ ለኢንሹራንስ ብር 235.60 እንዲሁም የተቀረጠ ጥቅም ብር 50000 በድምሩ ብር 164792.24 እንዲከፍሉኝ የሚል ነው፡፡ 1ኛ ተከሳሽ የነበረው የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት ሎጀስቲክ አገልግሎት በሰጠው መልስ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን መኪና ከቤልጂየም ኢንትዋፕ ጅቡቲ ወደብ ለማድረስ በተሰማማው መሠረት ያደረሰ እና ከተጠሪ ጋር በነበረው ውል አጓጓዡ ሁሉንም ወይም ከፊሉን የሟጓጓዙ ሥራ በውለታ ለሌላ ማስተላለፍ የምንችል መሆኑ ስለተገለፀ ለ2ተኛ ተከሳሽ የአሁን አመልካች ያስተላለፈ መሆኑን አመልካች ተረክቦ በሟጓጓዝ ላይ እያለ በደረሰ ቃጠሎ መኪናዋ ሙሉ ለሙሉ መውደሟን መኪናው የተጓዘው በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ውል በመሆኑ በአዋጅ 348/44 መሠረት ኃላፊነት ያለበት አመልካች ነው ስለዚህ ክስ ሊያቀርብብን የሚያስችል መብት የለውም ኃላፊ ነው ከተባልንም ልንጠየቅ የሚገባው በዕቃው ክብደት ልክ በኤስ.ዲ.አር ወይም በጥቅል ሲሆን ይህም ብር 63900 ነው የሚሆነው እንዲሁም ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ እና አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ የመድን ሽፋን የሰጡ በመሆኑ ወደ ክርክሩ ይግቡልኝ ብሏል፡፡ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ከከሳሽ ጋር ውል የገባው 1ኛ ተከሳሽ በመሆኑ ኃላፊነት የለብንም በከሳሽ መኪና ላይ ጉዳት አልደረሰም፣ መኪናው ጉዳት የደረሰበት በአመልካች መኪና ሳይሆን በደረሰ ቃጠሎ ምክንያት ነው ይህ ደግሞ ከአቅም በላይ የደረሰ ጉዳት ነው፡፡ የመኪናው ዋጋ የመድን ውል ሲገባ የተገለፀው ብር 76868.88 እያለ ተጠሪ ያቀረበው ያለአግባብ ነው፡፡ በማጓጓዝ የከፈለው ምንዛሬ መሠራት ያለበት መኪናውን ለመጫን በተከፈለ ቀን ነው ተጠሪ አጣሁ ያለውን ጥቅም በተመለከተም የቀረበ ማስረጃ የለም አለ ቢባልም መተካት ያለበት መድን ሠጪው ነው ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱም ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ እና አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ ወደ ክርክሩ እንዲገቡ አዞ መልሳቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ጉዳት ደረሰበት ለተባለው መኪናም የመድን ሽፋን ያልሠጡ መሆናቸውን የገለጹ መሆኑን መዝግቧል፡፡ እንዲሁም የአሁን አመልካች በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 256 መረት እንዲቀርብ ጠይቆ መኪናው የተቃጠለበትን ሁኔታ የሚገልይ የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ለቃጠሎው መፈጠር ምክንያት የሆነው የተሽከርካሪው ተሳቢ የፊት የግራ ጐማዎች የውስጥ ጐማ በመፈንዳቱ ምክንያት ቸርኬው  ከመሬት  ጋር በመጋጨቱ የተፈጠረ እሳት ከተቀጣጣይ ነገሮች ጋር መያያዙ መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ቀርቧል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በአዋጅ 547/99 አንቀጽ 36 አጋዥ የማጓጓዝን ሥራ በአንድ ውል የሚገዛ  ሆኖ  በተለያዩ አጓጓዦች በመቀባበል የሚፈጽሙ  ከሆነ    የመጀመሪያው


አጓጓዥ በገባው የመጓጓዣ ውል መሠረት 2ኛ አጓጓዥና ተከታዮች የመጓጓዥያ ሰነዱንና ውሉ የሚያስከትለውን ግዴታ በመቀበላቸው የተነሳ የማጓጓዥያ ውሉ ተዋዋይ ወገን ተደርገው በመቆጠሩ እያንዳንዱ አጓጓዥ በተናጠል ስለአጠቃላዩ የማጓጓዝ ስራ ኃላፊነት የሚኖርበት መሆኑ የተደነገገ በመሆኑ ተጠሪ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር የነበረው የማጓጓዥያ ውል ስምምነት መሠረት ከጅቡቲ ወደብ ሞጆ ደረቅ ወደብ ድረስ የማጓጓዝ ሥራ ለአመልካች መስጠቱን በግራ ቀኙ ወይም ውልም ሆነ በህጉ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ 1ኛ ተከሳሽ መኪናውን ለአመልካች ካስረከበ በኋላ የተፈጠረ አደጋ በመሆኑ የመጨረሻ ኃላፊነት የሚወድቀው በ2ኛ ተከሳሽ ነው፡፡ አመልካች የማጓጓዝ ሥራውን በሚረከብ ጊዚ እንደውሉ አካል የሚቆጠር እና ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ከተረከበ በኋላ ለተፈጠረው አደጋ አመልካች ኃላፊ ነው በማለት  የኋላፊነት መጠን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 547/99 አንቀጽ 27/3/ እና 29 መሠረት መኪናው የተገዛበት ብር 87148.5፣ የመኪናውን ማስጫኛ እና የኢንሹራንስ ክፍያ በውላቸው አንቀጽ 5/2/ መሠረት ለጭነት ብር 23546 ለኢንሹራንስ ብር 235.60 በድምሩ ብር 107930.10 እንዲሁም መኪናው የተገዛበትን ዋጋ ክስ ከቀረበበት 12/04/2005 ዓ.ም ጀምሮ 9% ወለድ ጋር አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል 1ኛ ተከሳሽ እና ጣልቃ ገቦች ከክሱ በነፃ ተሰናብተዋል በማለት ወስኗል፡፡

 

አመልካች በዚህ ፍርድ ቅር በመሰኘት ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለመቀበል በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡

 

የአመልካች የሰበር አቤቱታም የቀረበው ይህንኑ በመቃወም መሠረታዊ ስህተት ተፈጽሟል በማለት ሲሆን ይዘቱም በክሱ ላይ የተገለፀሙ መኪና ጉዳት የደረሰው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 547/1999 አንቀጽ 10 እና 22 መሠረት ኃላፊነት የለብንም ጉዳት የደረሰበት መኪና  ሙሉ በሙሉ ከነወለዱ የምንከፍል ከሆነ ጉዳት  የደረሰበትን   መኪና

/ሰልባጁን/ እንዲመለስልን ሊወሰን ይገባ ነበር የሚል ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም የአመልካችን አቤቱታ መርምሮ እሳቱ የተፈጠረው የመኪናው የውስጥ ጐማ /ከመነዳሪ/ ፈንድቶ ቸርኬው ከመሬቱ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት መሆኑ በባለሙያ ከመረጋገጡ አንጻር ክስተቱ ከአቅም  በላይ በሆነ ምክንያት ሥር የሚሸፈን መሆን አለመሆን እና ጉዳት የደረሰበትን መኪና ሙሉ ዋጋ አከፋፈል የመኪናውን ቅሪት አካል /ሰልባጅ/ ተመላሽ እንዲሆን በቃል ክርክር ወቅት ጠይቀው መታለፋን ለመመርመር ያስቀርባል በማለቱ ተጠሪ ለሰጠው መልስ አደጋው የደረሰው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤት ያቀረበው ማስረጃ የለም ከፍ/ህ/ቁ 1793 ከተዘረዘረው ምክንያት ውስጥም የሚካተት አይደለም፡፡ የደረሰው ጉዳት ለጉዞ ከመሠማራት በፊትም ሆነ በጉዞ ላይ እያለ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ የደረሰ ጉዳት ነው፡፡ በተለይም የእሳት መከላከያና ማጥፊያ ቁሳቁስ በአጓዥ ተሽከርካሪ ውስጥ አለመኖር ወዲያውኑ እንዲጠፋ አላደረገም፡፡ ጐማው ሲፈነዳም በጥንቃቄ አቁሞ መቀየር ሲገባው መሄዱ ቸልተኝነቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ    በኩል


የተሽከርካሪ አካልን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት አልተነሳም ዳኝነትም አልተከፈለበት፣ አመልካች ይህንን ቅሪትም አላስረከበኝም ስለዚህ የስር ፍ/ቤት ይጽናልኝ ብሏል፡፡ አመልካችም  የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

 

የክርክሩ አጠቃላይ ሂደት ከለይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ፍርድ እና ያስቀርባል ከተባለው ነጥብ አንፃር አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረነዋል፡፡

 

የክርክሩ አጠቃላይ ሂደትም የሚያስገነዝበው ተጠሪ አንድ ቶዮታ ያሪስ 998 ሲሲ የሻንሲ ቁጥር VNKKG96320a001372 የ2005 ምርት የሆነች መኪና ከቤልጅየም ኢንትዊፕ ወደብ እስከ ኢትዮጵያ ሞጆ ደረቅ ወደብ ድረስ ለማጓጓዝና ለመረከብ በስር ፍ/ቤት 1ኛ ተከሳሽ ከነበረው ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ትራንዚት ሎጅስቲክ አገልግሎት ጋር ውል ገብተዋል፡፡ ይህ 1ኛ ተከሳሽ በውላቸው ላይ ሁሉንም ወይም ከፊሉን የማጓጓዝ ሥራ በውል ለሌላ ማስተላለፍ የሚችል መሆኑን በተስማሙት መሠረት ከጅቡቲ ወደብ እስከ ኢትዮጵያ ሞጆ ደረቅ ወደብ እንዲያጓጉዝ ለአሁን አመልካች ጅቡቲ ወደብ አስረክቧል፡፡ አመልካች በዚሁ መሠረት ሲያጓጉዝ የአጓዥ ተሽከርካሪ ተሳቢ የፊት የግራ ጐማዎች የውስጥ ጐማ በመፈንዳቱ ምክንያት ቸርኬው ከመሬት ጋር በመጋጨቱ በተፈጠረ እሳት መኪናው መቃጠሉ ሲሆን ይህም በስር ፍርድ ቤት የተረጋገጡ ናቸው፡፡ አመልካች አጥብቀው እየተከራከሩ ያሉት በመኪናው ላይ የደረሰው ጉዳት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 547/1999 አንቀጽ 10 እና 22 ኃላፊነት የለብኝም የሚል ነው፡፡ በየብስ የዕቃ ማጋዝ ስራን ለመደንገግ ተሻሽሎ በወጣው በአዋጅ ቁጥር 547/1999 ዓ.ም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ “በማለት ምን ማለት እንደሆነ የተመለከተ ነገር ስለሌለ ትርጉሙን ለማወቅ ወደ ጠቅላላ ህጉ በተለይም ደግሞ ስለውሎች በጠቅላላ ስለሚመለከቱ ድንጋጌዎች መምራት የግድ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት በፍ/ህ/ቁ 1792 ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ አለ ለማለት የሚቻለው መቼ እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን ይህም ከአቅም በላይ የሆነ ሊመልሱት የማይቻል ኃይል ደርሷል የሚባለው ባለዕዳው ባላሰበው ነገር ድንገት ደራሽ ሆኖበት ግዴታውን እንዳይፈጽም ፍፁም መሰናክል በሆነበት አይነት የሚያግደው ነገር ባጋጠመው ጊዜ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ በአእምሮ ግምት ባለዕዳው ቀደም ብሎ ሊያስብበት የሚችል መሆኑ የታወቀ አንድ ድንገተኛ ደራሽ ነገር ወይም ለውሉ አፈጻጸም ከባድ የሆነ ወጪ በባለዕዳው የሚደርስ ቢሆን ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ነው ተብሎ እንደማይገመት ተልክቷል፡፡

 

ስለሆነም በእነዚህ የህጉ ድንጋጌዎች መሠረት ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ተከስቷል ሊባል የሚችለው በባለዕዳው በምንም መልኩ በቅድሚያ ሊያስበው ወይም ሊገምተው የሚያስችል


ክስተት ሲፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ባለዕዳው ሁኔታው ሊፈጠር ወይም ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ ሊገምት ወይም ሊያስብና ጥንቃቄ ሊያደርግበት የሚችል ከሆነ ሁኔታው ድንገት ደራሽ ቢሆንም እንኳን ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ተብሎ እንደማይገመት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተያዘው ጉዳይም የሥር ፍርድ ቤቱ አመልካችን ኃላፊ ያደረገው የክሱ ምክንያት የሆነው መኪና በእሳት ቃጠሎ ምክንያት ሊወድም የቻለው የመኪናው የውስጥ ጐማ /ከመነዳሪ/ በመፈንዳቱ እና ቸርኬው ከመሬቱ ጋር ሲጋጭ ለተፈጠረ እሳት ምክንያት መሆኑን ነው፡፡ አመልካች ይህ አጓዡ ሊገምተውና ሊያስቀረው የማይችል በመሆኑ ሁኔታው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠረ ነው የሚል ነው፡፡ ይሁንና የተሽከርካሪው አጓዥ የሆነው አመልካች ተሽከርካሪውን በዚህ አይነት ሥራ በሚያሠማራበት ወቅት ምንም አይነት ቴክኒካዊ ችግሮች እንዳያጋጥሙ ተሽከርካሪው የሚጓዘውን ርቀት የአየር ሁኔታ ሌሎች በሚያረጋግጥበት ጊዜ ጐማውን ማየት እና ደረጃውን መገመት የሚቻለው ሲሆን በጉዞ ላይም ችግሩ በድንገት ደርሷል ቢባል እንኳን ሊቆጣጠረው የሚችል እና ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ነው ተብሎ ሊገመት የሚችል መሆኑ የፖሊስ ቴክኒካል ማስረጃን የስር ፍርድ ቤት የመዘነበት አግባብ ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም የስር ፍርድ ቤት አደጋው የደረሰው የአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አይደለም የማለት የደረሰበት ድምዳሜ መሠረታዊ ስህተት ያለበት አይደለም፡፡

 

በሌላ በኩል አመልካች ጉዳት የደረሰበትን መኪና ሙሉ ለሙሉ ከነወለዱ የምከፍል ከሆነ ጉዳት የደረሰበትን መኪና /ሰልባጁን/ እንዲመልስልኝ ሊወሰን ይገባ ነበር በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ አመልካች ይህንን አስመልክቶ በስር ፍርድ ቤት አንስተው የተከራከሩበት ሁኔታ እንደሌለ ተጠሪ የገለፀ ሲሆን የስር ፍርድ ቤት መዝገብም እንደሚያስገነዝበው አመልካች በስር ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ ከነበረው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ትራንዚት ሎጀስቲከ የተጠሪ ንብረት የሆነውንና ለዚህ ክርክር ምክንያት የሆነውን ቶዮታ ያሪስ መኪና ጅቡቲ ወደብ መረከባቸውንና ወደ ኢትዮጵያ ሞጆ ደረቅ ወደብ ሲያጓጉዙ በእሳት ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጉዳት ደረሰበት የተባለው መኪና በእሳት መውደሙን አሊያም በአመልካች እጅ መሆኑን የሚያመለክት ከመሆኑም ባሻገር በስር ፍ/ቤትም አልተነሳም፡፡ አመልካች በስር ፍርድ ቤት በህጉ በተቀመጡት ሁኔታዎች መሠረት ሊያነሳቸው የሚገቡ እና ያላነሳቸውን መከራከሪያዎች በራሱ ምክንያት ሳያቀርብ እና ተጠሪም ባልተከሪከረበትና ባልተነሳ ሁኔታ በይግባኝ ወይም በዚህ ሰበር ችሎት የቀረበው ከፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 329/1/ እና 182/2 ድንጋጌዎች ዓላማ ጋር የማይጣጣም ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ ያቀረቡት አቤቱታ ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች ተቀባይነት ያላቸው አይደሉም፡፡

 

በአጠቃላይ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ፍርድ እና ትእዛዝ መሠረታዊ ሥህተት  የተፈፀመበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስለሆነም የሚከተለው ተወስኗል፡፡


 ው ሳ ኔ

 

1. የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 205919 በቀን 13/02/07 የሰጠው ፍርድ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 162749 በቀን 04/07/2007 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348/1 መሠረት ፀንቷል፡፡

2.  አመልካች ጉዳት የደረሰበትን መኪና ለተጠሪ ስለማስረከባቸው እና የመኪናውን    ቅሪት

/ሰልባጅ/ አስመልክቶ ክስ ለማቅረብ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም፡፡ 3.  ግራ ቀኙ በዚህ ችሎት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ፡፡

 

 ት እ ዛ ዝ

 

ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተሰጠ ትእዛዝ የስር ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 225335 የተጀመረው አፈጻጸም እንዲታገድ የተሠጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡ ይጻፍ፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ብ/ይ