111498 criminal procedure/ role of court

በወንጀል ክርክር ሂደት ፍ/ቤት በማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ሂደቶች ውስጥ ሊኖረው(ሊያደርገው) ስለሚችለው ሚና የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 136(4)፣137፣138፣143(1)፣145፣194

 

የሰ/መ/ቁ. 111498

 

የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል

እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አቃቤ ሕግ

 

-   የቀረበ የለም

 

ተጠሪ፡- አቶ ሃብታሙ ካርሎ - የቀረበ የለም

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ክርክር ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በሀድያ ዞን የሆሳእና ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱም ይዘትም፡- ተጠሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 556(2)(ሐ) ስር በመተላለፍ ተጠሪ በሰው አካል ወይም ጤንነት ላይ ጉዳት ለማድረስ አስቦ በቀን 14/05/2006 ዓ/ም ከቀኑ በግምት 6፡00 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በሆሳዕና ከተማ ሜእእል አምባ ቀበሌ ልዩ ስሙ ውሃዋና ፊት ለፊት ባሉ መጋዘኖች አከባቢ ወ/ሮ ነፃነት አለሙ የተባለችውን ሚስቱን አንገቱን አንቆ በመያዝ አንድ ጊዜ በቀኝ እጁ በጥፊ ፊቷን ሲመታት በአፏና በጥርሷ ላይ ደም ከመፍሰሱም በላይ በግንባሯ ላይ በቦክስ አንድ ጊዜ ሲደግማት ወዲያውኑ መሬት ላይ እንደወደቀች ፖሊሶች ደርሰው ያስጣሉት በመሆኑ በሰው አካል ላይ ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል የሚል ነው፡፡ ተጠሪ ክሱ ድርሶት እንዲረዳው ከተደረገ በኋላ ስለእምነት ክህደት ሲጠየቅ ወንጀሉን አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ተከራክሯል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የአመልካችን ሁለት የሰው ምስክሮችን ከሰማና ማስረጃዎቹ የሰጡትን የምስክርነት ቃል ከመረመረ በኃላ በግል ተበዳይ ላይ ተጠሪ በክሱ የተገለፀውን ተግባር ስለመፈፀሙ የተመለከተ ምስክር የሌለ መሆኑ መረጋገጡን ገልጾ   ተጠሪን


ከክሱ ምንም መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ ያሰናበተው ሲሆን አመልካች በዚህ ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን፣ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ የሰበር አቤቱታውን ያቀረበ ቢሆንም ተጠሪ ሳይጠራ ቅሬታው ተሰርዞበታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- በግል ተበዳይ ላይ በተጠሪ የአካል ጉዳት ስለመድረሱ በተረጋገጠበትና ማን እንደአደረሰው ደግሞ ለፍርድ ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃል የሰጡት ፖሊሶች በምርመራ ጊዜ መስክረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ መቀየራቸው እየታወቀ የሥር ፍርድ ቤት የምስክርነት ቃል ሲቀበል ተገቢውን ጥያቄ ሳይጠይቅና የግል ተበዳይ ቀርባ እንድትመሰክር ያለማድረጉና፣ ፖሊሶች በምርመራ ጊዜ የሰጡትን ቃል በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 145(1) አስርቀቦ ሳይመለከት ተጠሪን በነፃ ማሰናበቱ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን  ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል፡፡

 

ከሥር የክርክሩ አምጣጥና ለዚህ ሰበር ችሎት የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ድርጊቱን ስለመፈፀሙ አልተመሰከረበትም በሚል ምክንያት በነፃ እንዲሰናበት ማድረጋቸው ህግን መሰረት ያደረገ ነው? ወይሰ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ የአካል ጉዳት አድርሷል ተብሎ የተከሰሰው በሚስቱ ላይ ሲሆን ይህ አድራጎት ሲፈፀም በጊዜውና በቦታው ደርሰው የግል ተበዳይን ከድብደባው ተግባር ያስቀሯት ሁለት ፖሊሶች መሆናቸው በአመልካች ክስ ተጠቅሶ እነዚህ ፖሊሶች ለምስክርነት ተቆጥረው ፍርድ ቤት ቀርበው የመሰከሩ መሆኑን፣ ፖሊሶቹ ፍርድ ቤት ቀርበው በተመሳሳይ የሰጡት ምስክርነት ቃል ደግሞ በጊዜው በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በጥበቃ ስራ ላይ የነበሩ መሆኑን፣ ተጠሪ ቀደም ሲል ፖሊስ ጣቢያ ገብቶ እንደነበር፣ የግል ተበዳይ ከቀኑ 6፡00 ላይ መጥታ ከተጠሪ ጋር ጭቅጭቅ ስትፈጥር ጊዜ በዚያ ግቢ ውስጥ እንዲህ አይነት ጭቅጭቅ መፍጠር አግባብ ያለመሆኑን አስረድተዋት የግል ተበዳይን ያረጋጉ መሆኑን፣ ሆኖም የግል ተበዳይ በግንባር ላይ እብጠት ይታይባት እንደነበርና አፏ ላይም ደም ይታይባት የነበረ ቢሆንም ማን እንደመታትና እንዳቆሰላት የማያውቁ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፣ ፖሊሶቹ በጥበቃ ስራ ላይ የነበሩና የግል ተበዳይ ጉዳት ደረሰባት የተባለው በሜዕላባ ቀበሌ ልዩ ስሙ ውሃ ዋና ፊት ለፊት ሁኖ በዚህ ቦታ ላይ የነበረውን ክስተት ምስክሮቹ እንደማያውቁና በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ስለነበረው ሂደት የመሰከሩ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት ማስረጃዎቹን መዝኖ በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጣቸው ነጥቦች መሆናቸውንና በዚህ ረገድ ተመሳሳይ ስልጣን ያለው የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ የደረሰ መሆኑን ነው፡፡


አመልካች በዚህ የክርክር ደረጃ አጥብቆ የሚከራከረው የስር ፍርድ ቤት ምስክሮቹ መጠየቅ ይገባቸው የነበራቸውን ማጣሪያ ጥያቄዎችን አልጠየቀም፣ ፖሊሶቹ በምርመራ ጊዜ የሰጡት የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ ለውጠው በወንጀልም የተቀጡ በመሆኑ በምርመራ ጊዜ የሰጡት የምስክርነት ቃላቸው በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 145(1) ቀርቦ መታየት ነበረበት፣ የግል ተበዳይም ለምስክርነት የተቆጠረች በመሆኑ መሰማት ነበረባት በሚል ነው፡፡

 

በመሰረቱ በወንጀል ክርክር ሂደት ምስክሮች ሲጠየቁ በተከራካሪ ወገኖችም ሆነ በፍርድ ቤት የሚጠየቁ ጥያቄዎች አይነታቸው የትኞቹ እንደሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ በቁጥር ጥር 137፣ 138 እና 140 ስር የተመለከተ ሲሆን የማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ስርዓትም በዚሁ ሕግ ተመልክቶአል፡፡ አቃቤ ሕግ ክሱን ያስረዱልኛል ብሎ የቆጣራቸው ምስክሮችን ሲያሰማ በዋና ጥያቄ ስር ተገቢ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ፍርድ ቤቱ ማጣሪያ ጥያቄ ሊጠየቅ የሚችለውም ያልተብራራለት የምስክርነት ቃል ሲኖር መሆኑን ስለፍርድ ቤቱ ሚና የሚያመላክተው የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 136 (4) እና 143 (1) ድንጋጌዎች ይዘት ያስገነዝባሉ፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መረዳት የሚቻለው በመሰረቱ ማስረጃ ማቅረብና ምስክሮችን መመርመር የዓቃቤ ህግና የተከሳሹ ኃላፊነት ቢሆንም ፍርድ ቤቱም ውስን ሚናዎች የአሉት መሆኑን ነው፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎችና በሌሎች ድንጋጌዎች መሰረት ምስክሮችን መመርመር የባለ ጉዳዮች ሚና ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ትክክኛ ፍርድ ለመስጠት አስፈላጊ መስሎ ከታየው ፍርድ ቤቱ በማንኛውም ጊዜ ምስክሮቹን የማብራሪያ ጥያቄ መጠየቅ እንደሚችል በወ/መ/ህ/ቁ 136/4/ የተመለከተ ሲሆን በወ/መ/ህ/ስ/ስ/ቁ 143/1/ መሰረት ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት ምስክርነቱ አስፈላጊ ከመሰለው ፍርድ ቤቱ ፍርድ ከመስጠቱ በፊት በማንኛውም ጊዜ ማንኛውንም   ምስክር

/አስቀድሞ ቃሉን የሰጠም ሆነ ያልሰጠ/ መጥራት የሚችል ሲሆን እንዲሁም አቃቤ ህጉ ወይም ተከሳሹ በምስክር ዝርዝር ላይ ያልተጠቀሱ ምስክሮች እንዲቀርቡላቸው በጠየቁ ጊዜም ምስክሮቹ ነገሩን ለማዘግየት ሳይሆን ለትክክለኛ ፍትህ አስፈላጊ መስሎ ከታየው ምስክሮቹ እንዲጠሩ ፍርድ ቤቱ ለማዘዝ ይችላል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ተጨማሪ ማስረጃ ሊሰማ የሚችለው ተጨማሪ መስማት የሚያስፈልግ መስሎ ሲታየው ስለመሆኑ በወ/መ/ህ/ቁጥር 194/1/ ስር ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህ በማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ሂደቶች ፍርድ ቤቱ ስለሚኖረው ሚና ከሚደነግጉት ሕጋዊ ስርዓቶች መረዳት የሚቻለው በሕጉ ተለይቶ የተሰጠውን ሚና ፍርድ ቤቱ ሊያከናውን የሚችለው የፍርድ ቤቱን ገለልተኛነነቱን በማይነካ መልኩ በጥንቃቄ መሆን የአለበት መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 136/4/ እና 143 እንዲሁም 194/1/ ድንጋዎች ይዘትና መንፈስ ውጪ ፍርድ ቤት ወይም ዳኛው የቀረበለትን ጉዳይ በተመለከተ ማስረጃ ለመፈለግ የግሉን ምርመራና የምርመራ ስራ ለማድረግ የሚችልበት የዳኝነት አሰጣጥ ስርአት የለም፡፡ እንዲሁም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ላይ አንድ ምስክር በፖሊስ


ምርመራ ወቅት የሰጠው ቃል ዓቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሹ ባመለከተ ጊዜ የተሰጠውን ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው እንደሚችል የተደነገገ ቢሆንም የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ አላማም በምርምራ ጊዜ ተሰጠ የተባለውን የምስክርነት ቃል በፍርድ ቤት ምስክሩ ቀርቦ ቢለውጠው ይኼው ምስክርነት እንዲቃናና ፍርድ ቤት ለያዘው ክስ ሁልጊዜ ከብደት እንዲሰጠው ለማድረግ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡

ከላይ ከተመለከቱት በወንጀል ጉዳይ የማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ስርዓቶች አንጻር የተያዘውን ጉዳይን ስንመለከትም አመልካች ድርጊቱ ሲፈጸም በቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል የተባሉት ፖሊሶች ቃላቸውን ስለቀየሩና በወንጀል ስለተቀጡ በምርመራ ጊዜ የሰጡት የምስክርነት ቃል ለማስረጃነት መቅረብ ነበረበት፣ ፍርድ ቤቱም ማጣሪያ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነበረበት በማለት የሚያቀርበው የሰበር ክርክር የሕግ መሰረት የሌለው ሁኖ አግኝተናል፡፡ እንዲሁም የግል ተበዳይ የሆኑት ወ/ሮ ነጻነት አለሙ በስር ፍርድ ቤት መሰማት ነበረባቸው የሚለው ቅሬታውም ምስክሯ በጉዳዩ ምስክር ሁነው እስከተቆጠሩ ድረስ በስር ፍርድ ቤት እንዲሰሙ ማድረግ የአቃቤ ሕግ ግዴታ ሁኖ እያለና ምስክሯ ሳይሰሙ የታለፈበት ሂደት በፍርድ ቤቱ ግድፈት ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበት አግባብ በሰበር ቅሬታነት ሊነሳ የሚችልና ተቀባይነት የሚያገኝ ሁኖ አልተገኘም፡፡ በአጠቃላይ አቃቤ በሕጉ የተጣለበትን የማስረጃ ማቅረብና ጉዳዩን በበቂና በአሳማኝ የማስረዳት ግዴታውን ባልተወጣበት ሁኔታ በማስረጃ አቀራረብናና አቀባበል ረገድ ለፍርድ ቤቱ  በሕጉ በግልጽ ተለይተው የተሰጡት ሚናዎችን ባላገናዘበ መልኩ ፍርድ ቤቱ የምርመራና የምርመር ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል በሚል ይዘትና መንፈስ የቀረበው የአቃቤ ሕግ  የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ደግሞ ፍሬ ነገሩን በማጣራትና ማስረጃን በመመዘን ተጠሪ በግል ተበዳይ ላይ በክሱ ላይ የተገለፀውን አድራጎት ስለመፈጸሙ እንደክሱ አልተነገረበትም በማለት በነፃ እንዲሰናበት የሰጡት ብይን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሣ ኔ

 

1. በሆሳእና ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 15/99 በ06/06/2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር  13598 ታህሳስ 09 ቀን 2007 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ  ችሎት በመ/ቁጥር 63871 በ29/05/2007 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2(ሀ) መሰረት ፀንቷል፡፡ ፡፡

2. ተጠሪ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸሙ አልተረጋገጠም ተብሎ በነፃ እንዲሰናበት በተሠጠው ብይን የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል፡፡

 

 

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡