120762 criminal procedure/ prosecution in absentia/ representation by lawyer

በወንጀል ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ጠበቃ ብቻውን ሊቀርብ አይችልም የሚለው ጉዳይ ተፈፃሚ የሚሆነው ለተፈጥሮ ሰዎች እንጂ የህግ ሰውነት ላላቸው ሰዎች ስላለመሆኑ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.127

 

የሰ/መ/ቁ/120762 የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

 

 

አመልካች፡-የፌደራል ዐቃቤ ሕግ - ሮዛ በላቸው      ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- 1. ዱባይ አውቶ ጋለሪ-ኤል.ኤል.ሲ             ጠበቃ አበበ አስማረ 2. ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪዞን ካምፓኒ

መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ነው፡፡ በመሆኑም ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ የሰበር አቤቱታ ሊቀርብ የቻለው አመልካቾች ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 155568 ታህሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው ትእዛዝ ላይ የቀረበውን ይግባኝ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 111863 ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት መዝገቡን በመዝጋቱ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለቱ ነው፡፡

 

ጉዳዩ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት የወንጀል ክስ በቀረበበት ጊዜ በጠበቃ የመወከል ላይ የተሰጠ ትእዛዝ ይግባኝ ሊቀርብበት የሚገባ መሆን አለመሆኑን የሚመለከት ነው፡፡ በስር ፍ/ቤት ከሳሽ አመልካች ሲሆን ተከሳሾች እነአሽረፋ አወል አብዩ /17 ሰዎች/ ሲሆን ተጠሪዎች 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች ነበሩ፡፡ አመልካች በተከሳሾች ላይ 6 የተለያዩ ክሶችን ያቀረበ ሲሆን በተጠሪዎች ላይ ያቀረበው ክስ 3ኛ ክስ የወ/ህ/ቁ 32/1/ /ለ/፣ 34/1/ እና የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 96 የተመለከተውን በመተላለፍ የንግድ ትርፍ ግብር  ባለመክፈል፣ 4ኛ ክስ የወ/ህ/ቁ 32/1/ /ለ/፣ 34/1/ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 በመተላለፍ


ግብይት ባካሄዱባቸው ሥራዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ አሳውቆ ባለመክፈል፣ 5ኛ ክስ የወ/ህ ቁጥር 32/1/ /ለ/34/1/ እና የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 37/1/ /ሀ/፣/ለ/ እና 3/ለ/ በመተላለፍ ለባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት መካተት የሚገባውን ነጥብ በማስቀረትና ሀሰተኛ ወይም አሳሳች ማስረጃ በማቅረብ 6ኛ ክስ የወ/ህ/ቁ 32/1/ /ሀ/ /ለ/፣ 34/1/ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 50/1/1ሀ/ /ለ/ እና /3/ በመተላለፍ ለግብር ሰብሳቢ ባለሥለጣን መሥሪያ ቤት መካተት የሚገባውን ነጥብ በማስቀረት እና ሀሰተኛ ወይም አሳሳች ማስረጃ በማቅረብ የሚሉ ሲሆኑ 12ኛ ተከሳሽ የነበረው 1ኛ ተጠሪ በፍ/ቤቱ ጥሪ መሠረት 13ኛ ተከሳሽ የነበረው 2ኛ ተጠሪ በጋዜጣ ጥሪ መሠረት ጠበቃው ቀርበው የክሱ ማመልከቻ የደረሳቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ በጋዜጣ ተጠርተው ባልቀረቡት ላይ በሌሉበት ክርክሩ እንዲቀጥል አዞ በክሱ ላይ የተጠሪዎች ጠበቃን መቃወሚያ መቀበል ሲጀምር አመልካች የተጠሪዎች  ሥ/አስኪያጅ እና ባለቤት የሆኑት በክሱ በተራ ቁጥር 14፣15 እና 16 የተጠቀሱት ከህግ ተሰውረዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህን የወከሉ ጠበቃ ለድርድቶቹም መከራከር አይችሉም፡፡ ድርጅቶቹ የሚከሰሱት ሥ/አስኪያጅ ወይም ሠራተኞች በፈፀሙት ድርጊት ነው፡፡ ሥ/አስኪያጅ በሌለበት እንዲታይ ከታዘዘ የድርጅቶቹም ጉዳይ በሌሉበት መታየት አለበት በማለት ያቀረበው ከአቤቱታ በመመርመር አመልካች ያቀረበው ክስ የድርጅቶቹ ከሥራ አስኪያጆች የተለያየ ነው፡፡ በጠበቃ የመወከል መብት ደግሞ ለሁሉም እኩል የሚያገለግል መብት ነው፡፡ አንድ ድርጅት በወንጀል ህግ ድንጋጌ ተከሳሽ ለመሆን የሚያበቃ ሁኔታ አለ ተብሎ ክስ ከቀረበ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 20/5/ መሠረት በጠበቃ የመወከል መብት አለው ይህንን የሚጻረር አሠራርም ሆነ ሌላ ህግ ተፈጻሚነትየሌለው መሆኑን ይደነግጋል ስለዚህ የአሁን ተጠሪዎች በጠበቃ መወከል ይችላሉ አለ፡፡

 

አመልካች ይህንን ትእዛዝ በመቃወም ያቀረቡትን ይግባኝ የተመለከተው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በሰጠው ውሳኔ ዳኝነተት የሚታየው በህጉ በተመለከተው መሠረት ነው፡፡ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 184 እና 185 በግል ይግባኝ የሚባልባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር የተቀመጠ በመሆኑ አሁን ይግባኝ የተባለበት ጉዳይ ወደፊት በክርክር መጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥ ተጠቃልሎ ይግባኝ ሊባልበት የሚችል እንጂ አሁን በዚህ ደረጃ ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት ዘግቶታል፡፡  የአመልካች 8 ገጽ የሰበር አቤቱታ መሠረት ያደረገውም በዚሁ ውሳኔ ሲሆን ይዘቱም የወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 184 ይግባኝ የማይባልባቸውን ትእዛዞች የሚዘረዝረው ሆኖ በስር ፍ/ቤት ይህንኑ በመጥቀስ ውድቅ ማድረጉ መሠታዊ ስህተት ነው፡፡ የወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 185 የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ላይ የሚቀርብ እንጂ ከዚህ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ይግባኝ ማለት ይቻላል አይልም፡፡ ከቁጥር 184 ጋር ተጣጥሞ ሊተረጐም የሚገባና ከሰበር መ/ቁ 93234 ከተሰጠው ትርጉም ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ የወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 127/1/ በወንጀል ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ጠበቃ ብቻውን ሊቀርብ እንደማይችል የሚያሳይ ነው፡፡ የተከሳሽ በጠበቃ የመወከል መብት የተቀመጠው ተከሳሹ በቀረበ ጊዜ ተፈጻሚነት


ያለው እንጂ ለመቅረብ ፈቃደኛ ባልሆነ ጊዜ አይደለም፡፡ የወ/ህ/ አንቀጽ 34/1/ እንደተመለከተው ድርጅት በወንጀል የሚጠየቀው የድርጅቱ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ በሰራው ወንጀል በመሆኑና ለጠበቃው ውክልና የሰጠው 15ኛ ተከሳሽ የሆነው የ12ኛ እና 13ኛ ተከሳሽ ድርጅቶች ባለቤትና ሥራ መሪ ከቀረበባቸው ክስ ተሰውረው በሌሉበት እየታየ በጠበቃ ተወክለው መከራከር የህግ መሠረት የለውም፣ በወንጀል ጉዳይ ህጋዊ ሠውነት ያላቸው ድርጅቶት ከድርጅቱ ባለቤት ወይም ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች ተነጥለው የሚታይ አይደለም፡፡ ተጠሪዎች በ15ኛ ተከሳሽ በተሰጠ ውክልና እንዲከራከሩ መፍቀድ በሌሉበት እንዲታይ ብይን የተሰጣቸውን ተከሳሾች በጠበቃ እንዲከራከሩ የመፍቀድ ውጤት አለው፡፡ ስለዚህ በወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ  ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ እንዲሻርልኝ የሚል ነው፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የስር የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ከወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 184 እና 185 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ጋር አገናዝቦ ለመመርመር ለሰበር ችሎት ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪዎች በሰጡት መልስ የስር ፍ/ቤት ተጠሪዎች በጠበቃ መወከል  አይችሉም በማለት አመልካች ያቀረበው ተቃውሞ የመሰረታዊ ህግም ሆነ የስነ-ሥርዓት ህግ መሠረት የሌለው በመሆኑ ፍ/ቤቱ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 184 ውጭ በመሆኑ ሊያልፈው ይገባ ነበር፣ በጠበቃ የመወከል መብት ሕገ-መንግስታዊ ሆኖ በአንቀጽ 20/5/ የተደነገገ ሲሆን አመልካችም በውጤት ደረጃ በወንጀል ፍትህ ሥርህቱ የሚያስገኘው አሉታዊ ተጽዕኖ አንጻር አክብሮ ሊቀበለው የሚገባ ነው፣ ሰበር መ/ቁ 93234 የሰጠው ውሳኔ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 185 /2/ የይግባኝ መብቱ የተገደበውን አመልካችን የሚመለከት አይደለም፡፡ ከአመልካችና ከተጠሪ ክርክር ጋር  ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት የለውም፣ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በመልስ ሰጪዎችላይ የወንጀል ዳኝነት ሥልጣን የላቸውም፣ የወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 127/1/ እና 197 ተፈጻሚ የሚሆነው ለተፈጥሮ ሠዎች እንጂ የህግ የሰውነት ባላቸው ሰዎች አይደለም፣ አንድ ሠው በግሉ የተከሰሰበት ጉዳይ በሥ/አስኪያጅነት ከሚመራው የህግ ሠውነት ካለው ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፣ ውክልና ለመስጠት መብት ያለው የተፈጥሮ ሠው ስለድርጅቱ በመሆን ጠበቃ መወከል የተፈቀደ ተግባር ነው፡፡ ተጠሪዎች ከ14፣15 እና 16ኛ ተከሳሾች ጋር ፈፀሙ ያለው ተግባር ምንም ግንኙነት የለውም ተጣምረው ወይም በግብረ አበርነት የቀረበባቸው ክስ የለም፣ የወ/ህ/ቁ 34/1/ ተፈጻሚ የሚሆነው በኢትዮጵያ ለተመዘገቡ ድርጅቶች ሲሆን ተጠሪዎች ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመዘገቡ ዓለምዓቀፋ የንግድ ድርጅቶች ናቸው ስለዚህ በተጠሪዎች ላይ ተፈጻሚነት የለውም፣ የድርጅት የወንጀል ኃላፊነት የሥ/አስኪያጅ የወንጀል ኃላፊነት አያስከትልም 15ኛ ተከሳሽ የተከሰሰው በራሱ በግሉ ሲሆን ከተጠሪዎች ጋር ክስ አልቀረበበትም፣ ሌሎች በአመልካች ተነስተዋል ባሉት ነጥብም በዝርዝር መልስ ሠጥተዋል፡፡ አመልካችም የመልስ  መልስ አቅርበዋል፡፡


የክርክሩ አጠቃላይ ሂደት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የተነሱትን ክርክሮች ያስቀርባል ከተባለበት ጭብጥ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

 

አመልካች በእነ አሽረፍ አወል /17 ሰዎች/ ላይ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው የወንጀል ክስ የአሁን ተጠሪዎች 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች በመሆን በጠበቃቸው አማካኝነት በችሎት የተገኙ ቢሆንም አመልካች ተከሳሾች ያልቀረቡና ሥራ አስኪያጆችም በሌሉበት ክርክሩ እንዲሰማ ትእዛዝ ተሰጥቶ ባለበት እነዚህ ተከሳሾች በጠበቃ ተወክለው መከራከር አይችሉም በማለት የቀረበውን ተቃውሞ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ ትእዛዝ የሠጠ ሲሆን በዚሀ ትእዛዝ ላይ የቀረበውን ይግባኝ ሠሚው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደፊት በክርክሩ መጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥበት ይግባኝ ሊባልበት የሚችል እንጂ በዚህ ደረጃ ይግባኝ የሚቀርብበት አይደለም በማለት በወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 184 እና 185 መሠረት መዝገቡን ዘግቷል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሰበር ችሎት በቅድሚያ መታየት ያለበት ተጠሪዎች በጠበቃ ሊወከሉ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ጭብጥ እና አመልካችና ተጠሪ በሰፊው ያደረጋቸውን ክርክሮች ሳይሆን ተጠሪዎች በጠበቃ ሊወከሉ ይገባል በማለት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ትእዛዝ ላይ ይግባኝ ሊቀርብ አይገባም በማለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይ/ሰሚ ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ መሠታዊ ስህተት መኖር አለመኖሩን ነው፡፡

 

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍድ ቤት ለውሳኔው መሠረት ያደረገው የወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 184 የትእዛዝ ይግባኝ ስላለመኖሩ እና የወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 185 የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ይግባኝ ስለማለት የሚደነግገውን ነው፡፡

 

ይግባኝን በተመለከተ መሠረቱ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግስት ሲሆን የተከሰሱ ሰዎችን መብት በሚደነግገው አንቀጽ 20/6/ ላይ ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ፍርድ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት ያላቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ አንድ የበታች ፍርድ ቤት በሰጠው ትእዛዝ ወይም በፍርዱ ቅር የተሰኘና ፍትህ ተዛባብኝ የሚል ተከራካሪ ወገን ቅሬታውን ለበላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍርዱ እንዲመረመር እና ተፈፀመ ያለው ሥህተት እንዲታረምለት ይግባኝ የማለት መብት ተሠጥቶታል፡፡

 

የሥነ-ሥርዓት ህጐች ዋናው ዓላማ ፍትሐዊ ኢኰኖሚያዊና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ክርክሮች እንዲያልቁ ማስቻል በመሆኑ ፍርድ ቤቶች የሥነ-ሥርዓት ህጉን አስመልክቶ ክርክሮች ሲቀርቡ ከተከራካሪ ወገኖች መብት አልፎም የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መተርጐም ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህም አንጻር በወንጀል ክስ ጉ ዳይ ይግባኝ የሚባልባቸውን የፍርድ ቤት ውሳኔዎች የወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 181 ስለ ይግባኝ መሠረቱ


ሊዘረዘር የሥረ-ነገር ክርክሩን የሚያቋርጡ መሆናቸውን የሚያመለክት ሲሆን ይኸውም የጥፋተኝነት ውሳኔ፣ የቅጣት ውሳኔ፣ ለጊዜው የመለቀቅ /Discharge/ እና በነፃ የመለቀቅ  ውሳኔ

/aquittal/ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የሥረ-ነገር ክርክር የሚያቋርጡ እንደቀጠሮ መስጠት አለመስጠት እንደማስረጃ መቀበል አለመቀበል የመሳሰሉት የብይን /ትእዛዝ/ ሁኔታዎች ወዲያውኑ ይግባኝ የማይባልባቸው ናቸው ሆኖም ግን በእነዚህ ብይን/ትእዛዞች ላይ ወዲያውኑ ይግባኝ ለማለት ባይቻልም ፍርድ ቤቱ ነገሩን ሠምቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ፍርዱን በመቃወም ይግባኝ ሲቀርብ እነዚህን በክርክሩ ሂደት የተሰጡ እትዛዞች የቅሬታው ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ የወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 184 መደንገጉ የተፋጠነ ፍትህ የማይግኝት ህገ-መንግስትዊ መብት ያለውን ተከራካሪ ተጠቃለው መታየት በሚችሉ ሁኔታዎች ምክንያት ክርክሩ እንዳይዘገይ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን የማያስገነዝብ ነው፡፡

 

በዚህ በያዝነው ጉዳይም የስር ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊባልበት የሚገባ አይደለም ያለው በወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 181 እንደተመለከተው የሥረ-ነገር ክርክሩን የማያቋርጥ እና ፍርድ ቤቱ ነገሩን ሠምቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሚሰጥበት ወቅት የቅሬታ ምክንያት ሆነ ተጠቃሎ ይግባኝ ሊባልበት የሚችል መሆኑን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አመልካች የሰበር መ/ቁ 93234 የተሰጠን አስገዳጅ የህግ ትርጉም መሠረት በማድረግ ያቀረቡት መከራከሪያም ቢሆን ጉዳዩ የክስ ማሻሻልን የሚመለከት ሆኖ የተሰጠው ትእዛዝ በቀጣይ የወንጀል ክርክር ሂደት ጋር የሚያስተሳስረው ነገር ባለመኖሩ ድጋሚ ክርክር የሚቀርብበት ዕድል የሌለ በመሆኑ ትእዛዙ የመጨረሻ በመሆኑ ከዋናው ክርክር ጋር ተጠቃልሉ ይግባኝ ሊባልበት የማይችል መሆኑን መሠረት በማድረግ የተሰጠ በመሆኑ ጠበቃ በመወከል ላይ በተሰጠው ትእዛዝ ጋር ተመሳሳይነት የላቸውም፡፡

 

በአጠቃላይ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ በጠበቃ መወከልን አስመልክቶ በተሰጠው ትእዛዝ ላይ ይግባኝ ሊቀርብበት የሚገባ አይደለም በማለት የሰጠው ውሳኔ ከወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 181, 184 እና 185 አንጻር መሠረታዊ ሥህተት የተፈፀመበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስለሆነም ተከታዩ ተወስኗል፡፡


 

 

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 155568 በቀን ታህሳስ 28/2004 በሰጠው  ትእዛዝ ላይ የቀረበው ይግባኝ ላይ የፌ/ጠ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ 111863 በቀን ጥቅምት 1/2008 የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል፡፡

 

 ት እ ዛ ዝ

 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 155568 የቀጠለው ክርክር ለጊዜው እንዲታገድ በ 12/05/08 የሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡

 

 

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡      የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡