103940 criminal law/ telecommunication offense

ህጉ በሚጠይቀው አግባብ ፈቃድ ሳያወጣ ወይም የጸና ፈቃድ ሳይኖረው ከቴሌኮሚኒኬሽን እውቅናና ፈቃድ ወጭ ሶፍትዌሮችን በመገልግል በኢንተርኔት ስልኮች ማስደወል ሊያስከትለው ስለሚችለው ኃላፊነት የቴሌኮሚኒኬሽን አዋጅ ቁጥር 49/1989 ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 281/1994 አንቀጽ 13

 

የሰ/መ/ቁ. 103940

ቀን 24/05/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል

.እንደሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ወ/ሮ አመለወርቅ ጌታነህ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐ/ህግ የቀረበ የለም መዝገቡ መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ክስ የሚመለከት ሲሆን የተጀመረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ የአሁኗ አመልካች ጨምሮ በ17 ተከሳሾች ላይ ክስ ማቅረቡን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በስር ፍ/ቤት 9ኛ ተከሳሽ በነበሩት የአሁኗ አመልካች ያቀረበው ክስ ባጭሩ፡- በንፋስ ስልክ ከተማ ቀበሌ 12/13 የቤት ቁጥር የማይታወቅ ንግድ ቤት ውስጥ ስልክ የማስደወል ፈቃድ ሳይኖራት ከቴሌ ኮሚንኬሽን ሲስተም በመደበቅ ስልክ ማስደወል የሚያስችል  ራስ አዲስ ፒሲቶከር እና ራስ ዳሽን የተባሉ ሶፍትዌሮችና የካርድ ቁጥሮች (Accounts numbers) ከ3ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በመግዛት እንዱሁም ለጊዜው ማን እንዳስመጣው የማይታወቅ ኔት 2ፎን ዲያለር የተባለ ሶፍትዌር በመጠቀም 3ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በስውር በመመሳጠር ባዘጋጁት ህገወጥ ተግባር በመታገዝ ወደ ወጭ አገር ስልክ በማስደወል እ.ኤ.አ ከ01/11/2004 እስከ 06/10/2010 ለ5 አመታት ከ339 ቀናት 779,040 ደቂቃዎች ወደ ተለያየ አገራት ከኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ሲስተም መደበቅ የሚያስችል ቴክኖሎጄ በመጠቀም በህገወጥ መንገድ በማስደወል ብር 7,70,400 (ሰባት ሚሊዮን ሰባት መቶ ዘጠና ሺህ አራት መቶ ብር)


በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲዲረስ በማደርገና በህገወጥ መንገድ ብር 3895200.00 (ሶስት ሚሊዮን ዘጠና አምስት ሺህ ሁለት መቶ ብር) ተጠቃሚ በመሆኗ እንዲሁም በሽያጭ የተዘጋጁ ግምታቸው USD 17500 የሚያወጡ የካርድ ቁጥሮች በህገ ወጥ ሱቋ ውስጥ በመገኘታቸው የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)፤ 33፣ 411(1) ሐ  የተመለከተው በመተላለፍ በህዝብና በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሳለች የሚል ነው፡፡

 

አመልካች በተጠሪ የቀረበባት ክስ ክዳ በመከራከሯ የስር ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግ ማስረጃ ካደመጠ በኃላ እንድትከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡ የአሁኗ አመልካች የበኩሏን የመከላከያ ማስረጃ በማስቀረብ አስምታለች፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ የአሁኗ አመልካች እና ሌሎች ተከሳሾች በክሱ በተገለጸው አግባብ ከቴሌኮሚኒኬሽን እውቅናና ፈቃድ ውጭ ሶፍትዌሮችን በመገልግል በኢንተርኔት ስልኮች በማስደወል ከፍተኛ ገንዘብ መሰብሰባቸውንና መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የቴሌኮሙኒኬሽንን መስርያቤት ማስጣታቸውን ተረጋግጦባቸው አልተከላከሉም፡፡ በክሱ ላይ የተገለጹት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች መከላከላቸው የተረጋገጠ ስለሆነ ጉዳዩ የሙስና ወንጀል መሆኑ ይቀራል ይህ በመሆኑም በ1ኛ ክስ የቀረበባቸው ዘጠኝ ተከሳሾች (3ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ 7ኛ፣ 9ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች) በህገወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል ስልክ ለማስደወል ሶፍትዌሮች ማስደወያ ካርድ ቁጥሮችን በማከፋፈል ለአገኙት ህገወጥ ጥቅምና ለአሳጡት ጥቅም ተጠያቂና ጥፋተኛ የሚሆኑት በሙስና ወንጀል መሆኑ ቀርቶ ተከሳሾች ሊጠየቁ የሚገባቸው በኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን አዋጅ ቁጥር 49/1989 ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 281/1994 አንቀጽ 23 ንኡስ አንቀጽ 11(4)  ድንጋጌ ኢንተርኔት በመጠቀም የድምጽ መልእክትን ማስተላለፍ ወይም የማስተላለፍ አገልግሎት መስጠት ድንጋጌ ተላልፎ መገኘት በመሆኑ የተከሰሱበትን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)፣ 33፣ 411(1) (ሐ) እና (2) ድንጋጌዎች በወ/መ/ስ/ስ/ቁ. 113(2) በመለወጥ ከላይ በተጠቀሰው የአዋጅ ቁጥር 281/1994 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 13 ድንጋጌ ጥፋተኛ ናቸው በማለት በአብላጫ ድምጽ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 

የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ ክርክር የመረመረ ሲሆን ወንጀሉ በከፍተኛ ደረጃ መድቦ ቅጣቱ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሰረት በማስላት ወስኗል፡፡ ድንጋጌው ከ3 እስከ ከ5 አመት የሚያስቀጣ በመሆኑ ለከባድ ወንጀል የቕጣት መነሻና መድረሻ ከ4 ዓመት አስከ 4 ዓመት ከ6 ወር የሚያስቀጣ በመሆኑ በእርከን 18 የሚውድቅ ነው፡፡ በአሁኗ አመልካች የቀረበው አንድ የቅጣት ማቅለያ ተቀብሎ በእርከን 17 ስር በ3 አመት እንዲትቀጣ፤ የገንዘብ መቀጮ በተመለከተ ከኢፌዴሪ የኢንፎርመሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በ11/04/2003 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ መሰረት በአሁኗ አመልካች ተሰበሰበ የተባለው የገንዘብ መጠን 3,895,200 (ሶስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ሺ ሁለት መቶ) ያለፈቃድ በሰሩበት ጊዜ ውስጥ


አግኝተውታል ተብሎ የቀረበባቸውንና በመከላከያቸው ያላስተባበሉት ገንዘብ እጥፍ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ያደረጉ ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 

የአሁኗ አመልካች የስር ፍርድ ቤት የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበገውም የስር ፍ/ቤቶች በሰጡት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል በማለት ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የወንጀል ድርጊቱ እንዳልፈጸሙ፤ በማስደወል አገኙት የተበለው ገንዘብም ሆነ በመንግስት ላይ ደረሰ የተባለው ጉዳት አልተረጋገጠም፤ የተወሰነው የእስራት ቅጣት ይሁን የገንዘብም መቀጮ የግህ መሰረት የለውም በማለት መከራከራቸውን ያሳያል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በበኩሉ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የተፈጸመው የወንጀል ድርጊት ያገናዘበ ስለመሆኑ ሊጸና ይገባል በማለት መልስ አቅርበዋል፡፡ የመልስ መልስም ቀርባዋል፡፡

 

ከስር የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆነ እኛም ግራ ቀኘ በጽሁፍ ያደርጉት ክርክር ፤ ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ውሳኔ አግባብነት ካለው ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ እንዲሁም ጉዳዩን ለሰበር ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር እንዲሚከተለው መርምረናል፡፡ ጉዳዩን ለሰበር ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ በስር ፍ/ቤት የተሰጠው የጥፋተኝነትና የእስራት ቅጣት በአግባቡ ሆኖ በወንጀል ስራ ምክንያት አመልካች አግኝታለች የተባለው የገንዘብ መጠን የተወሰነበት ስርዓት በህጉ አግባብ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ነው፡፡

 

ጉዳዩ እንደመረመረነውም አመልካች ፈቃድ ሳያወጡ ወይም የፀና ፈቃድ ሳይኖራቸው ስልክ በማስደወላቸው ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ባደረገው ማጣራት የአሁኗ አመልካች ምንም ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ስልክ በማስደወል ብር 3895200.00  እንደሰበሰቡ ቴሌኮሚንኬሽን ደግሞ ብር 7790400.00 ማጣቱን ከኢፌዴሪ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ማስረጃ መቅረቡን በውሳኔው አስፍሯል፡፡ አመልካች የወንጀል ድርጉቱን አልፈጸምኩም፣ ስልክ በማስደወል ገንዘብ አላገኘሁም በማለት የተከራከሩ ቢሆንም የስር ፍ/ቤት በውሳኔው እንደገለጸው የቀረበው ማስረጃ የሚያስተባብል ነገር አለማቅረባቸውን ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤት ፍሬ ነገር በማጣራት እና ማስረጃ በመመዘን ረገድ የሚደርስበት ድምዳሜ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዳለ የሚቀበለው እንጂ በድጋሚ የሚያጣራበት ስርዓት የሌለ ስለመሆኑ  ከኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 80(3) (ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/88  አንቀጽ  10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው የአሁኗ አመልካች (የስር 9ኛ ተከሳሽ የነበሩ) ያለ ፈቃድ ስልክ በማስደወል ሶስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ሺ ሁለት መቶ ብር ጥቅም እንዳገኙ ነው፡፡ ይህ የፍሬ ነገር ድምዳሜ ይዘን


የአዋጅ   ቁጥር   49/1989  ለማሻሻል   የወጣው   አዋጅ   ቁጥር   281/1994   አንቀጽ   13  ስር የተመለከተው መቀጮ ዓይነትና ባህሪ መርምረናል፡፡

 

በዚህ አዋጅ ክልከላ የተደረገባቸው ድርጊቶች ፈጸሞ ጥፋተኛ የተበለው  ግለሰብ በእስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ተመልክቷል፡፡ የድንጋጌው የአማራኛ እንግልዝኛ ይዘት፡- “በዚህ አዋጅ ወይም በሌሎች አግባብ ባለቸው ህጎች መሰረት ፈቃድ ሳያወጣ ወይም የጸና ፈቃድ ሳይኖረው አገልግሎት የሰጠ ማንኛውም ሰው ያለፈቃድ በሰራበት ጊዜ ውስጥ ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚወሰነውን ገቢ እጥፍ የገንዘብ መቀጮና ከ3 አመት እስከ አምስት አመት በሚደረስ እስራት ይቀጣል በማለት የተደነገገ ሲሆን የእንግልዝኛው ትርጉም “any person who engages in tele communication service without having license or a valid license as per this proclamation or any other relevant laws shall be punished with fine equal  to double the revenue estimated to have been earned by the person during the period of time he operated the service and with imprison mint from 3 up to 5 years” በማለት ተደንግጓአል፡፡ በዚህ ድንጋገ የመቀጮው መሰረት ወንጀል ፈጻሚው ካገኘው ጥቅም ወይም ሊያገኘው ይችላል ተብሎ የሚገመት የገንዘብ መጠን  መሰረት የሚያደረግ ስለመሆኑ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች በህገ ወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል ያገኙት የገንዘብ መጠንና መንግስት ያጣው ገቢ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ እና ተረጋግጦ መቅረቡን የስር ፍ/ቤት መዝገብ ያሳያል፡፡ የአዋጅ ቁጥር 281/1994 አንቀጽ 13 ላይ እንደተገለጸው የመቀጮው መጠን እጥፍ እንደሚሆን ነው፡፡ ድንጋጌው ተቀጪው እጥፍ እንደሚከፈል በግልጽ ካስቀመጠ የስር ፍርድ ቤቶች አመልካች በህገ ወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል ያገኙው ጥቅም እጥፍ እንዲከፍሉ መወሰናቸው ሲታይ በህጉ አተረጓጉም ረገድ የፈጸሙት ስህተት መኖሩን አያሳይም፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው በአዋጅ ቁጥር 281/94 አንቀጽ 13 ድንጋጌዎች መሰረታዊ የመቀጮ አወሳሰን ስርዓት ተቀጪው ወንጀል በመስራቱ ያገኘው ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ በመሆኑ ወንጀል በመስራቱ ብቻ ጥቅም ሲያገኝ የሚወሰንበት ስርዓት መሆኑን ተረደተናል፡፡ ከዚህ አንጻር በአመልካች ላይ የተወሰነው መቀጮ ተገኘ የተባለው ጥቅም በማስረጃ መረጋገጡን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 281/94 አንቀጽ 13 ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘትና መንፈሰ ያገናዘበ ነው ብለናል፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ በዚህም ተከታዩን ወስነናል፡፡


 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት ፍርድና ትዕዛዝ ጸንቷል፡፡ ይጻፍ፡፡

2. አመልካች በህገወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል አገኙት የተባለው የገንዘብ መጠን እጥፍ እንዲከፍሉ መወሰኑ በህጉ አግባብ ነው ብለናል፡፡

 

መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ተመለሰ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ሃ/ወ