99082 intellectual property/ moral damage

በቅጂና ተዛማጅ መብቶች መጣስ /ለሚደርስ ለጉዳት ካሳ/ ወይም የሞራል ካሳ ዋጋው በተዋዋዮች ወገን ካልተቆረጠ የወቅቱን ዋጋ አጣርቶ መወሰን የሚገባ ስለመሆኑ፣ የሞራል ካሳ አከፋፈል ከፍ/ብ/ሕ/ቁ ውጪ መወሰን የሌለበት ስለመሆኑ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቁ 410/96 አንቀጽ 7፣8፣37 የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2102

 

የሰ/መ/ቁ. 99082

 

ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ

ቀነዓ ቂጣታ

 

አመልካች፡- ወ/ሮ ፍሬ ህይወት ደመቀ (የመካኒኩ ፊልም ኘሬዲውሰር)- ጠበቃ ሙሉጌታ ዘመነ ቀረቡ፡፡

 

ተጠሪ፡- ወ/ት ቤሩት ዳዊት - ጠበቃ መንግስቴ ቀረቡ፡፡

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

                  

 

ጉዳዩ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኗ አመልካች ላይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡

 

የተጠሪ የክስ ይዘትም፡- ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን በመሰዋት በነጠላ ዜማ የለቀቁትን “በትዝታ አቅርቤ” የተሰኘውን የዘፈን ሥራቸውን ያለፈቃዳቸውና ያለ ስምምነታቸው የአሁኗ አመልካች ኘሮዲውስ ላደረጉት "መካኒኩ" ለተባለው ፊልም በማጀቢያነት (ሳውንድትራክ) በመጠቀም ያለአግባብ ቁሳዊ ጥቅም ያገኙበት መሆኑን፣በአመልካች አድራጎትም 164,000.00 የሚገመት የኢኮኖሚ ጥቅም ማጣታቸውንና የብር 100,000.00 የሞራል ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰው በድምሩ ብር 264,000.00 (ሁለት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ብር) ከነወለድ ወጪና ኪሣራ ጨምረው እንዲከፍሏቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

 

የአሁኗ አመልካች ለተጠሪ ክስ በሰጡት መልስም፡- የተጠሪ የሙዚቃ ሥራ ለመካኒኩ ፊልም ማጀቢያነት የተጠቀሙት መሆኑን ሳይክዱ የሙዚቃው ሥራ ለፊልሙ መጠቀም ይችሉ እንደሆነ በአቶ  ዮናስ  ብርሃነ  መዋ  በኩል  ተጠሪን  ጠይቀውና  ተገናኝተንው  የተጠሪን        ስራ


እንዲያስተዋውቁላቸው ተነጋግረው ሰኔ 8 ቀን 2003 ዓ.ም በአቀነባባሪያቸው የእጅ ጽሑፍ የተፃፈ ሲዲ ተጠሪ አምጥተው የሠጧቸው መሆኑን፣ በዚህም ተጠሪ ወደውና ፈቅደው በማጀብያነት አመልካች እንዲጠቀሙበት ሰጥተዋቸው እያለ ያለፍቃዴ ነው ማለታቸው ሐሰት መሆኑን ጠቅሰው ተጠሪ ክስ ለመመስረት የሚያስችላቸው ምክንያት የለም በማለት ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያቀረቡ ሲሆን በአማራጭም እንደተጠሪ ያለ ጀማሪ ዘፋኝ የዘፈነው ዘፈን ከብር 3000.00(ሶስት ሺህ) ባለይ እንደማይሸጥ እየታወቀ ተጠሪ ብር 164,000.00 የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሶብኛል በማለት ዳኝነት መጠየቃቸው ያላግባብ መሆኑንና በዚህ ረገድ የቀረበውን የተጠሪን ግምት እንደሚቃወሙ፣አዲስ ዘፈን እንደመሆኑ መጠን ለዘፈኑ ገንዘብ ከሚከፈላቸው ክሊፕ እንዲሰራላትና ዘፈኑ የፊልም ማጀቢያ እንዲሆን የምረቃ ቀን ቀርበው ምስጋናና ሰርቲፊኬት እንዲሰጣት፣ዘፈኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ተሰራጭቶ እንዲተዋወቅላት በዝርዝር ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሰኔ 08 ቀን 2003 ዓ/ም ተፈራርመው ከስምምነቱ በኋላ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ/ም በአቀናባሪያቸው የእጅ ፅሑፍ የተፃፈ ሲዲ እራሷ አምጥታ የሰጠቻቸው መሆኑን፣በዚህም መሰረት የሙዚቃ ሲዲዋን በላይ ላይ ድምፃዊት እራሷ መሆኗን አቀናባሪያቸው ሮቤል ዳኜ መሆኑን፣ ስራቸው በቅርብ ቀን በአልበም እንደሚወጣ፣ሲዲውም ላይ በመግለፅ የተለያዩ ሚዲያዎች በፕሮግራማቸው በማስተላለፍ እንዲያስተዋወቁላቸው ያደረጉ መሆኑን፣ፊልሙ በሚመረቅበት ጊዜም ለፊልሙ ማጀቢያነት የተጠቀሙት ሙዚቃ የተጠሪ መሆኑን በማስተዋወቅ በመድረክ ላይ ተጠርተው ሰርቲፊኬት እንዲሰጣቸው ማድረጋቸውንና በስምምነቱ መሰረት በአመልካች በኩል ሳይፈፀም የቀረው የዘፈኑን ክሊፕ ማዘጋጀት ብቻ ሲሆን ይህን በተመለከተም ስራው ያልተሰራው ተጠሪ የዘፈኑን ታሪክ አዘጋጅተው ባለማቅረብና ለክሊፑ የሚሆነውን አልባሳትና ቦታ አዘጋጅተው ባለመቅረባቸው ጥፋት መሆኑን፣ ክሊፑ  የሚሰራበት ዋጋ ከብር 4000.00 እንደማይበልጥና ተጠሪ ዜማቸውን በመሸጥ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አመልካች ያለማስቀረታቸውንና በፈቃዳቸው መሰረት ለተከናወነ ተግባርም የሞራል ካሳ የሚከፈልበት አግባብ የሌለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክር እና የአመልካችን የሰው ምስክሮችን ከሰማ በኋዋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ከተጠሪ ዕውቅና ውጭ ማጀቢያ ዘፈኑን ለፊልሙ ያለመጠቀማቸውን ያስረዱ ስለሆነ ከሳሽ የደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊም ሆነ የሞራል ጉዳት የለም በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያነት የተጠቀሙት በተጠሪ ሙሉ ፍቃድ ስለመሆኑ ተረጋግጦአል ተብሎ በስር ፍርድ ቤት መወሰኑ ባግባቡ ነው በማለት


የተቀበለው ሲሆን ተጠሪ ዘፈናቸውን ለአመልካች ፊልም ማጀቢያ በፍቃዳቸው ሲሰጡ ተጠሪ በአመልካች በኩል የማስተዋወቅ ስራ እንዲሰራላቸው፣በገንዘብ መልክ ከሚሰጣቸው ይልቅ የዘፈኑ ክሊፕ እንዲሰራላቸው አመልካች መዋዋላቸውን አልካዱም፣አመልካች እንደውሉ ያልፈጸምኩት ተጠሪ የዘፈኑ ታሪክ፣ አልባሳት እና ክሊፑ የሚሰራበት ቦታ ባለመምረጣቸው ነው ቢሉም አመልካች ክሊፑን ለመስራት የጠቀሷቸው ነገሮች ተጠሪ ሟሟላት እንደሚገባቸው የሚያመላክት ስምምነት ስለመኖሩ አላስረዱም በሚል ድምዳሜ ተጠሪ እነዚህ ነገሮች ባይሟሉኳ በክሊፑ ፈንታ ገንዘብ ሊከፈላቸው ይችል እንደነበረ፣ አመልካች በክሊፑ ፋንታ ለተጠሪ  ክፍያ ሊፈጽሙ እንደሚገባ ፍርድ ቤቱ አምኖበታል በማለት የካሳውን መጠንም በርትዕ ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ) አድርጎ ይህንኑ ገንዘብ አመልካች ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘትም፡- ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያነት የተጠቀሙት በተጠሪ እውቅና እና ፈቃድ ስለመሆኑ ከአረጋገጠ በኋላ በክሊፑ ፋንታ ተጠሪ ገንዘብ ሊከፈላቸው ይገባል በማለት የሰጠው ውሳኔ ተጠሪ በውሉ መሰረት ግዴታቸውን ባልተወጡበት አግባብ ከመሆኑም በላይ የካሳው መጠንም ማስረጃ ቀርቦ እያለ በርትዕ መወሰኑ ከሕጉ ይዘትና መንፈስ ውጪ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነውም

 

1. አመልካች ለተጠሪ በክሊፑ ፈንታ ገንዘብ እንዲከፍሉ መወሰኑ የግራ ቀኙን ተነፃፃሪ ግዴታ ያገናዘበ ነው? ወይስ አይደለም?

2. የካሳው መጠን በርትዕ መወሰኑን ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም? የሚሉት ነጥቦች በጭብጥነት ሊታይ የሚገባ ሁነው አግኝተናል፡፡

 

 

 የ መጀ መሪያ ውን ጭብጥ በ ተመ ለከተ፡ - የበታች ፍርድ ቤቶች በአመልካችና በተጠሪ ውል መኖሩን በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጡት ጉዳይ ሲሆን ተጠሪ አመልካች በጽሑፍ የተደረገው ውል ጠፍቶአል በማለት በሰው ምስክሮች ማረጋገጥ እንደሚችሉ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መወሰኑ ተገቢነት የሌለውና የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2003 ድንጋጌን የሚቃረን ነው በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ለዚህ ችሎት በጽሑፍ ከአቀረቡት መልሳቸው የተገነዘብን ቢሆንም ይህ የተጠሪ ክርክር በዚህ አመልካች


ባስከፈቱት የሰበር መዝገብ ሊስተናገድ የሚችልበት አግባብ የሌለ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ተጠሪ በዚህ ረገድ ራሱን  የቻለ                      የሠበር አቤቱታ ያቀረቡ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን  በዚህ ረገድ አለ የተባለውን የሰ/መ/ቁጥር 100338 አስቀርበውን ስንመለከተውም መዝገቡ በሰበር አጣሪ ችሎት በ03/10/2006 ዓ/ም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አልተፈፀመበትም ተብሎ መዘጋቱን መረዳትን ችለናል፡፡ በመሆኑም ተጠሪ በግራ ቀኙ መካከል በፅሑፍ የተደረገ ውል የለም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሁኖ አልተኘም፡፡ በግራ ቀኙ መካከል ሕጋዊ ውል መኖሩ ከተረጋገጠ ደግሞ የግራ ቀኙ ተነፃፃሪ ግዴታ የሚለየው በዚሁ ውል በመሆኑ እያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን የሚቀርበው   ክርክር

በዚሁ የውል ሰነድ ይዘት መደገፍ ያለበት መሆኑን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2001 እና 2005 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡

 

በመሠረቱ ውል ሕጋዊ ውጤት ያለው ተግባር እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን በውሉ የተጣለበትን ግዴታ መፈጸም ይኖርበታል፡፡ ተዋዋዮች በውሉ በተገለጸው ስምምነት መሰረት ግዴታቸውን ከተወጡ ውለታው በታሰበው ዓላማ መሰረት ተፈፅሟል ለማለት የሚቻል ሲሆን ይህም ማለት የውሉ ግዴታ ያለበት ሰው በውሉ ላይ የተገለጸውን የመስጠት፣ የማድረግ ወይም ያለማድረግ ተግባር በተገቢው መንገድና በብቃት ማከናወኑን ማረጋገጥ መሆኑ ይታመናል፡፡ ተዋዋይ  ወገኖች በምን አይነት አኳኋን፣ ጊዜና ቦታ የውል ግዴታቸውን መፈጸም እንዳለባቸው በፍትሓ ብሔር ሕጉ ከቁጥር 1740 እስከ 1762 ድረስ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡ አንድ ተዋዋይ ወገን በውሉ የገባውን ግዴታ በውላቸውና በሕጉ ውስጥ በተደነገገው አኳኋን ያልፈፀመ እንደሆነ የውል ግዴታውን እንደጣሰ የሚቆጥር ሲሆን የውሉ ተጠቃሚ የሆነ ተዋዋይ ወገን ደግሞ እንደውሉ እንዲፈጸምለት ወይም ውሉ እንዲፈርስለት የመጠየቅ መብት ያለው ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1771(1) ስር ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1757 ድንጋጌ እንደሚየሳየው ውሉ እንዲፈፀምለት የሚጠይቀው ወገን ጥያቄውን ማቅረብ ያለበትና ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው በውሉ መሠረት አስቀድሞ ሊወጣው የሚገባ ግዴታ የተወጣ ስለመሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ክሊፕ ለማሰራት ግዴታ መግባቸውን ሳይክዱ የክሊፑ ስራ እንደውሉ ያልተፈፀመው በተጠሪ ጥፋት ነው፣ተጠሪ የዘፈኑን ታሪክ፣አልባሳት ባላማቅረባቸውና ክሊፑ የሚሰራበትን ቦታ ባለመምረጣቸው ነው በማለት የሚያቀርቡት ክርክር በማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በዚህ ረገድ ስልጣን ያለው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም አመልካች ውሉ መኖሩን አምነው የተጠሪ ግዴታ ነው እስካአሉ ድረስ ይህንኑ የማስረዳት ግዴታ መወጣት የነበረባቸው መሆኑን ከክርክራቸው አቀራረብ መረዳት ችለናል፡፡ ስለሆነም ተጠሪ በውሉ የገቡትን ግዴታ ያልተወጡበት መንገድ ስለመኖሩ ያልተረጋገጠ በመሆኑ አመልካች በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት  ክርክር


ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 258 እና 259፣ እንዲሁም ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1757፣ 2001 እና 2005 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባው ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

 

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተ መ ለከተ፡ - ከክርከሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ዘፈኑ ለፊልም ማጀብያ እንዲውል ፈቅደው ከሰጡ የሞራል ጉዳት ደርሶብኛል፣ የሞራል ጉዳት ካሣ ይከፈል ሊሉ አይችሉም በማለት መወሰናቸውን፣ግራ ቀኙን እስከዚህ ችሎት የሚያከራክራቸው ነጥብ ግን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በክሊፑ ፈንታ አመልካች ለተጠሪ ገንዘብ ሊከፍሉ የሚገባ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አምኖአል በማለት አመልካችን ኃላፊ አድርጎ የኃላፊነቱን መጠንም በርትዕ ብር 100,000.00 ነው በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል መሆኑን ነው፡፡

 

የተጠሪ ስራ በአዋጅ ቁጥር 410/96 አግባብ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑና አመልካች ለፊልማቸው ማጀቢያነት የተጠቀሙበት መሆኑ ግራ ቀኙን ያከራከረ ጉዳይ አይደለም፡፡ አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊማቸው ማጀቢያነት ሲጠቀሙ ግን ለተጠሪ የከፈሉት ገንዘብ ስለመኖሩ በፍሬ ነገር ደረጃ አልተረጋገጠም፡፡ ይልቁንም ለተጠሪ ገንዘብ ከሚከፈላቸው የክሊፑን ወጪ አመልካች ሸፍነው ክሊፑን ሊሰሩላቸው መስማማቸውን፣ ሆኖም ይህ ስምምነት ተፈፃሚነት ሳያገኝ የቀረው ተጠሪ በራሳቸው በኩል የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ባለመወጣታቸው ነው በማለት አመልካች ተከራክረው ይህ የአመልካች ክርክር በማስረጃ ያለመደገፉን ይግባኝ ሰሚው ችሎት ማረጋገጡን ይህ ችሎት ተገንዘቦአል፡፡ በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 410/96 ጥበቃ ያገኘውን የተጠሪን ዘፈን አመልካች መጠቀማቸው እስከተረጋገጠ ድረስ አንድ ዘፈን ለፊልም ማጀቢያነት ሲውል ለዘፈኑ ባለቤት ሊከፈል የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያህል ተጠሪ የማያገኙበት አግባብ የለም፡፡ ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ አመልካችን ኃላፊ ማድረጉ ከአዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 7፣ 8 እና 34 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንጻር የሚነቀፍ ሁኖ ስላልተገኘ በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ክርክር የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

በዚህ ረገድ የዚህን ችሎት ምላሽ የሚሻው አቢይ ነጥብ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ካሳውን የወሰነበት አግባብ ሕጋዊ መሆን ያለመሆኑ ነው፡፡ በቅጅ ወይም በተዛማጅ መብቶች መጣስ ምክንያት ለፍ/ቤት የቀረቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮች የካሣ አከፋፈል ባለመብቱ የደረሠበት የገንዘብ ጉዳት እና በመብቱ መጣስ ምክንያት የተገኘ ትርፍን መሰረት ያደረገ መሆን እንደአለበት የሕጉ ይዘትና መንፈስ ያስገነዝባል፡፡ የካሳ አከፋፈሉ ባለመብቱ መብቱ ለተጣሰበት ሥራ ያወጣውን ወጪና ተከሣሹ ያገኘው ትርፍን ኢኮኖሚያዊ መብቱን ለማስከበርና የሞራል ካሣ የመክፈል ኃላፊነትን የሚያጠቃልል መሆኑ ይታወቃል፡፡ አዋጁ ለሞራል ጉዳት የሚከፈል ካሣ በጣም አነሰ ቢባል ከ100,000 /አንድ መቶ ሺህ ብር/ የማያንስ ሆኖ እንደ ጉዳቱ መጠን ከ100 ሺህ ብር በላይ


ሊወሠን እንደሚችል የአንቀፅ 34(4) ድንጋጌ በግልፅ ያስቀመጠ ሲሆን የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን በመጣስ የሚኖር የፍትሐብሔር ኃላፊነት የጉዳት ካሣና የሞራል ካሣ ከመክፈል በተጨማሪ ለካሣ አከፋፈሉ ምክንያት የሆነው ሥራ በባለመብቱ ላይ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ ከንግዱ እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ ወይም እንዲወገዱ ወይም በሌላ ተገቢ አኳኋን እንዲጣሉ ለማዘዝ እንደሚቻልም ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ፍርድ ቤት በዚህ አግባብ ውሳኔ ሲሰጥ የተከራካሪ ወገኖችን የማስረዳት ግዴታ ግንዛቤ ባስገባ መልኩ ማስረጃን መሰረት ማድረግ እንዳለበት የሚታወቅ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ማስረጃ ቀርቦ በማስረጃው መወሰን አስቸጋሪ ሁኔታ ካለም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 በተመለከተው አግባብ ካሳውን መወሰን እንደሚቻል የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1790(2) ድንጋጌን በምንመለከትበት ጊዜ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ካሳ በርትዕ ከሚወሰንባቸው ምክንያቶች ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ስር የተመለከቱት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የነገሮች ተራ ሁኔታዎች የሚለው  ሐረግ ይገኝበታል፡፡ ይህ የድንጋጌው ይዘት ነባራዊ አለምን መሰረት በማድረግ የነገሮች ተራ ሁኔታዎች ተመዛዝነው የካሳ መጠኑ ሊወሰን እንደሚችል የሚያስገነዝብ ነው፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያ በመጠቀማቸው ምክንያት በተጠሪ የደረሰ የኢኮኖሚ ጉዳት አልያም አመልች የተጠሪን ዘፈን በፊልም ማጅብያ ሲጠቀሙበት በገንዘብ ምን ያህል ይከፈላቸዋል ለሚለው ጥያቄ ተጠሪ 164,000.00 (አንድ መቶ ስድሳ አራት ሺህ ብር) የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሶብኛል ከማለታቸው በቀር ይህንኑ የኢኮኖሚ ጉዳት የደረሰባቸው ለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ እንዳላቀረቡ፣ አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልም ማጀብያ ሲያውሉ ሊከፍላቸው ያሰቡት አልያም ለዘፈኑ ክሊኘ ምን ያህል እንደሚያወጡ ተዋውለናል ከማለታቸው ውጪ በጽሑፍ ውስጥ አስፍረው የነበረ ስለመሆኑ ያስረዱት ነገር የለም የሚሉትን ምክንያቶችን ጠቅሶ በተጠሪ ላይ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ወይም የቀረ ጥቅም ለመገመት አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን መደምደሙን በዚህም ምክንያት አመልካች በርትዕ ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል በማለት መወሰኑን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ አመልካች በውል ሰነዱ ላይ የሰፈረውን ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ባያስረዱም ለአንድ ፊልም ማጀቢያነት የሚውል ዘፈን ሊከፈልበት የሚገባው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ገበያውን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ዘፋኞች ለተያዩ ፊልሞች የተከፈላቸውን ዋጋ ለይተው በመግለፅ፣ በዚህ ረገድም የሰነድ ማስረጃ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የተከራከሩ መሆኑን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ተጠሪም አመልካች የጠቀሷቸው ዘፈኖችና ዋጋቸው በስር ፍርድ ቤት በክርክር ደረጃ አልተነሱም ሳይሉ አመልካች ሊከፈል ይገባል የሚሉት ዋጋ የወቅቱን የፊልም ማጀቢያ ዘፈን ዋጋ ያላገናዘበ ነው በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ለዚህ ችሎት ከሰጡት የፅሑፍ መልስ ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች በዚህ ረገድ ማስረጃ ቆጥረው እያሉና ማስረጃዎቹ ለጉዳዩ ያላቸውን አግባብነት ሳይመረምር በውል


ሰነዱ ላይ ሰፍሮ የተገኘ ዋጋ አልተገኘም በሚል ምክንያት ብቻ ወደ ርትዕ  መሄዱ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ድንጋጌን ይዘትና መንፈስ እንዲሁም የተከራካሪ ወገኖችን ማስረጃ የመስማት መብት እና ፍርድ ቤቱ እውነትን መሰረት ያደረገ ዳኝነት ለመስጠት ይቻለው ዘንድ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 ድንጋጌን ተግባራዊ ሊያደርግ የሚገባበትን አግባብ ያላገናዘበ ሁኖ ተገኝቷል፡፡

 

አንድ ዘፈን ለአንድ ፊልም ማጀቢያ ሲውል ዋጋው በተዋዋይ ወገኖች ሊቆረጥለት የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም ዋጋው በውሉ መታወቅ ካልተቻለ ግን ተከራካሪ ወገኞች በሚያቀርቧቸው አግባብነት ባላቸው ሌሎች ማስረጃዎች ወይም ፍርድ ቤቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 መሰረት መድቦ በሚያጣራው ባለሙያ ሊታወቅ የሚችል መሆኑን የነገሮች ተራ ሁኔታዎች የሚያስረዱ መሆኑን ነባራዊው አለም ያስገነዝባል፡፡ ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተጠሪ ዘፈን ለፊልም ማጀቢያነት ሲውል ሊከፈል ይችል የነበረውን ዋጋ አመልካች በዚህ ረገድ ማስረጃዎቼ ናቸው በማለት ከአቀረቧቸው የሠነድ ማስረጃዎች ወይም ከሚመለከተው የሙያ ማህበር አግባብነት ያለውን ባለሙያ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 መሰረት እንዲመደብ  አድርጎ ትክክለኛውን የወቅቱን ዋጋ አጣርቶ መወሰን ሲገባ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ውጪ በርትዕ መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

              

 

1. በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 117093 ሐምሌ 16 ቀን 2005 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 93456 ጥር 30 ቀን 2006 ዓ/ም በከፊል የተሻረው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1 መሠረት ተሻሽሏል፡፡

2. አመልካች የተጠሪን ዘፈን ለፊልሙ ማጀቢያ በመጠቀማቸው ዋጋውን ሊከፍሉ ይገባል ተብሎ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል፡፡

3. ሆኖም አመልካች ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) ክሱ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ ህጋዊ ወለድ 9% (ዘጠኝ በመቶ) ጋር ለተጠሪ እንዲከፍሉ በርትዕ መወሰኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102 ትክክለኛ አፈፃጸም ያላገናዘበ በመሆኑ ተሸሯል፡፡በመሆኑም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ኃላፊ የተባሉ መሆኑን በመገንዘብ የኃላፊነት መጠኑን ግን በፍርድ ሀተታው ላይ በተገለጸው አግባብ አግባብነት ባላቸው የአመልካች ማስረጃዎች እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 መሰረት ከሚመለከተው የሙያ ማህበር ተጣርቶ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት በመመርመር ሊወሰን ይገባል በማለት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ ይጻፍ፡፡


4. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራቸውን ይቻቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡ የማይነበብ የአምሰት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡