117390 jurisdiction/ international organizations

በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ስራቸውን የሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር የሚመሰረቱት የሥራ ግንኙነት ስምምነት ያለ እንደሆነ ጉዳዩ የሚዳኘው በዓለም አቀፍ ስምምነቱ መሠረት ስለመሆኑ፡-

 

የሰ/መ/ቁ.117390

ታህሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- አቶ አለማየሁ መኮነን ጠበቃ ሞላ ዘገየ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት ጠበቃ አድምጠው በለጠ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

1. ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ፍርድ  ቤቶች በተጠሪ ላይ ያቀረብኩትን ክስ የማየትና አጣርተው የመወሰን ስልጣን የሌላቸው መሆኑን ገልፆ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሰለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ አመልካች የተጠሪ ሰራተኛ የነበሩ መሆናቸውን ገልፀው ተከሳሽ ሊከፍለኝ ይገባል የሚሏቸውን ክፍያዎች ዘርዝረው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪ አለም አቀፍ ድርጅት መሆኑን ገልፆ፣ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በኢትዮጵያ አቆጣጠር ግንቦት 30 ቀን 1969 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሰኔ 7 ቀን 1977 ዓ.ም በተዋዋለው ውል መሰረት በፍትሐብሔር ጉዳይ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ያለመክሰስ መብት ያለኝ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም የሚል መቃወሚያ አቅርቧል፡፡

2. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተጠሪ ዋና  መስሪያ  ቤት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያደረገው ስምምነት ያለመሆኑንና ስምምነቱም እስካሁን ድረስ የፀናና ያልተሻረ መሆኑን ከኢ.ፊ.ዲ.ሪ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በፅሁፍ ያረጋገጠለት መሆኑን ገልፆ፣ ስምምነቱ በይዘቱ የኢትዮጵያ መንግስት በድርጅቱ ላይ ክስ እንዳያቀርብ የሚገደብ


እንጅ ዜጎች በድርጅቱ ላይ ክስ እንዳያቀርቡ የሚከለክል አይደለም በማለት አመልካች በክሱ የጠቀሰውን ገንዘብ ተጠሪ ክዶ የቀረበው ክርክር ስለሌለ እንዳመነ ይቆጠራል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ስምምነቱ በተጠሪ /ይግባኝ ባይ/ ላይ የማቀረብ የፍትሐብሔር ክስ የኢትዮጵያ መንግስት የመዳኝት ስልጣን የሌለው መሆኑን የሚገልፁ ስለሆነ ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል የዳኝነት ስልጣን የለም በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

3. አመልካች ስምምነቱ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ፍትህ  የማግኘት  መብት በማያጣብብ ሁኔታ መተርጎም ይገባዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የሕገ መንግስቱን ድንጋጌዎች የሚጥስና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ ተጠሪ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አገሪቱ የገባችውን አለም አቀፍ ግዴታና ስምምነት መሰረት በማድረግ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4. እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች በተጠሪ ላይ ክስ ያቀረቡት ከተጠሪ ጋር የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን ውል አለን፡፡ አሰሪው በስር ውሉ መሰረት ለመወጣት የሚገባውን ግዴታ ያልተወጣና መክፈል የሚገባውን  ክፍያ ያልከፈለኝ ስለሆነ እንዲከፍል ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ አለም አቀፍ ድርጅት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 በኢትዮጽያ ግዛት ክልል ባሉ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ለማስተዳደር የወጣ ልዩ የሕግ ክፍል ቢሆንም ይኽ አዋጅ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ልዩ ሁኔታዎች  በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ አዋጅ ተፈፃሚ የማይሆንበት ልዩ ሁኔታ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ስራቸውን የሚያከናውኑ አለማቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያዊን ጋር በሚመሰርቱት የስራ ግንኘነት ላየ ተፈፃሚ እንዳይሆን በአለም አቀፍ ስምምነት የተወሰነ ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ በአዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3/ሀ/ ተደንግጓል፡፡ ይኽ ድንጋጌ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የተደረገና ፀንተው የቆዩ አለም አቀፍ ስምምነቶችንም የሚያካትት ድንጋጌ ነው፡፡

5. የኢትዮጵያ መንግስትና የተጠሪ ዋና መሰሪያ ቤት ያደረጉት ስምምነት አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ 1 በተፃፈበት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ቃል በቃል ሲነበብ “The organization shall, enjoy immunity from the criminal junsdiction of the government. If shall also enjoy immunity from its civil and administrative Jurisdiction except in so far as the counsel of the organization has unvalued the immunity”


የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ይኽ ስምምነት እስካሁን ድረስ የፀናና ሕጋዊ ውጤት ያለው ስምምነት መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚሂስቴር ለስር ፍ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ አረጋግጧል፡፡

6.  ይኽ የስምምነቱ ሃይለ ቃል፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠሪ ከሚቀጥራቸው  ሰራተኞች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚወስን ሕግ የማውጣት፣ በዳኝነት አይቶ የመወሰንና ውሳኔውን በፍርድ ቤትም ሆነ በአስተዳደራዊ መንገድ የማሰፈፀም ስልጣን የሌለው መሆኑን፣ ከተጠሪ ጋር የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ሆነ የሌሎች አገሮች ዜጎች መብታቸውንና ጥቅማቸውን በተጠሪ መተዳደሪያ ደንብና አግባብነት ባላቸው አለማቀፍ ስምምነቶች አለም አቀፍ ልምዶችና ሕግጋት መሰረት ጉዳዩን አይተው ውሳኔ ለሚሰጡ አካላት በማቅረብ እንዲወሰንላቸው ከሚጠይቁ ውጭ በኢትዮጵያ  ሕግና መሰረት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ለማቅረብ የማይችሉና የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችም የዚህ አይነት ጉዳይ በዳኝነት አይተው የመወሰን ስልጣን የሌላቸው መሆኑን ግልፅ የሚያደርግ ነው፡፡ የስምምነቱ አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ 2 ይዘትም ከላይ የተጠቀሰውን ድንጋጌ መልዕክት የሚያጠናክር ይዘት ያለው ነው፡፡

7. የአንድ አለም አቀፍ ድርጅት በግዛት ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ወይም ዋና ፅ/ቤት እንዲከፍት የፈቀደች ወይም አለም አቀፍ ድርጅቱ በግዛት ክልል እያንቀሳቀሰ የተቋቋመበትን መሰረታዊ ዓላማና ተግባር እንዲፈፅም የፈቀደች አገር፣ ከአለም አቀፍ ድርጅቱ ጋር ያደረገችውን ስምምነት የማክበር ግዴታ ያለበት መሆኑን ኮቬና የአለም አቀፍ ስምምነቶች ሕግ እና በልምድ ከዳበረው የግል ማዕቀፍ ሕግ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህም መሆኑ አገሪቱ ለተጠሪ ድርጅት የሰጠችው በፍትሐብሔር ያለመከሰስ ጥበቃ እስካሁን ድረስ የፀናና አገሪቱ ልታከብረው የሚገባው ቃል ኪዳን በመሆኑ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በዳኝነት አይቶ ለመወሰን የሚያስችል ብሔራዊ የዳኝነት ስልጣን የሌለ መሆኑን ገልፆ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ መሻሩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1.  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ፀንቷል፡፡

2. አመልካች ያቀረበውን ክስ አይቶ የመወሰን ስልጣን የኢትዮጵያ  ፍርድ ቤቶች የላቸውም በማለት ወስነናል፡፡

 

3. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ