104858 jurisdiction/ land reclamation/ compensation/ Addis Ababa

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በምትክ ቦታ ይሰጠኝ ጥያቄ ላይ የሚሰጠው የመጨረሻ ፍርድ የሠበር አቤቱታ ለከተማው ፍ/ቤት ሳይቀርብ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ የሚቀርብበት የህግ አግባብ የሌለ ስለመሆኑ የከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 43(5)፣ አንቀጽ 42(2) አንቀጽ አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(6)

 

የሰ/መ/ቁ. 104858

 

ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

 

 

አመልካች፡-   አቶ ታደሰ ካሣ - ጠበቃ እንዳልካቸው ይሳቅ - ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1ኛ. ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር

2ኛ. ቦሌ ክ/ከተማ የመሬት አስተዳደር     አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

የሰበር አቤቱታው የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት ከከተማ ቦታ ማስለቀቅ እና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምትክ ቦታን በተመለከተ በተሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ አቤቱታን ተቀብሎ ለመወሰን የዳኝነት ሥልጣን የለኝም በማለት ያሳለፈውን ትዕዛዝ በመቃወም ነው፡፡

 

አመልካች ነሀሴ 27/2006 ዓ.ም ያቀረቡት የሰበር ማመልከቻ ተመርምሮ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ትዕዛዝ ከአዋጅ ቁጥር 721/2003 አንቀጽ 29 እና 30 ድንጋጌዎች አንፃር ተገቢ መሆኑን  ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ተጠሪዎች መጥሪያ ደርሷቸውና መልስ ለመስጠትም ቀጠሮ እንዲለወጥላቸው ጠይቀው ነገር ግን መልስ ስላላቀረቡ በፅሑፍ መልስ የማቅረብ መብታቸው ታልፎ መዝገቡ ለምርምራ ተቀጥሯል፡፡ በበኩላችን የከተማው ሰበር ችሎት ያሳለፈውን ትዕዛዝ አመልካች ካቀረቡት ቅሬታ እና ተገቢነት ካላቸው ህጎች ጋር በማያያዝ መርምረናል፡፡


ከመዝገቡ መረዳት እንደሚቻለው አመልካች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር ውስጥ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በ200 ካ.ሜ ቦታ ላይ ቤት ገንብተው እየኖሩ ከተጠሪዎች ቦታው ለልማት ይፈለጋል በሚል እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ በፅሑፍ ስለተሠጣቸው የቤት ካሣ እና ምትክ ቦታ እንዲሠጣቸው ጠይቀው አስተዳደሩ በህግ ተቀባይነት በሌለው ምክንያት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎብኛል በሚል ይግባኙን ለመስማት ለተቋቋመው ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የተጠሪዎችን መልስ ተቀብሎ ጉዳዩን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ለንብረት ካሣ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሠን ከወጣው አዋጅ ቁጥር 455/1997፤ ስለ ካሣው አወሳሰን ከወጣው የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 135/1999 እንዲሁም አዋጅና ደንቡን ለማስፈፀም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከወጣው መመሪያ ቁጥር 3/2002 አንፃር በመመርመር በህጎቹ እንዲቀርብ የሚጠበቀው የንብረት ካሣ እና ምትክ ቦታ ለማግኘት የሚያበቁ ማስረጃዎ አልቀረቡም ስለሆነም ይግባኙ ተቀባይነት የለውም በማለት ወስኗል፡፡

አመልካች የምትክ ቦታ ጥያቄውን በተመለከተ የጉባኤው ውሳኔ የመጨረሻ ነው በማለት የሰበር አቤቱታ ለከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የሚኖረው የአ/አበባ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ነው፤ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም ሥልጣን ያለው የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ነው በመሆኑም ጉዳዩ በከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀርቦ ሊታይ የማይችል ነው በማለት መዝገቡን ዘግቷል፡፡

 

እንደመረመርነው የከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምትክ ቦታን በሚመለከት በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ በሰበር አይቶ ለመወሰን የዳኝነት ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? የሚለው የህግ ጭብጥ ውሳኔ የሚሻ ነው፡፡

የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(3) መሠረት በካሣ ክርክር ላይ ካልሆነ በቀር ምትክ ቦታን ጨምሮ በሌሎች በህግም ሆነ በፍሬ ነገር ላይ  የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡ በሌላ በኩል በካሳው ላይ የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት  ይግባኝ  ሊቀርብ እንደሚችል በአንቀጽ 29 (4) ሥር ተመልክቷል፡፡ የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ደግሞ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ በከተማው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 43(5) እና አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(6) ድንጋጌዎች መሠረት የመጨረሻ በመሆኑ በዚህ ውሳኔ ላይ አቤቱታ ሊቀርብ የሚችለው በሰበር ስርዓት ለከተማው ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ስለመሆኑ በቻርተሩ አንቀጽ 42(2) ተመልክቷል፡፡


የከተማ ቦታ ማስለቀቅ እና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤም በቻርተሩ አንቀጽ 40 ከተዘረዘሩ በህግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጣቸው አካላት የሚመደብ ነው፡፡

በመሆኑም ጉባኤው ምትክ ቦታን በተመለከተ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑና ጉባኤውም በህግ የመዳኘት ስልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመ የአስተዳደሩ አካል መሆኑ እየታወቀ በዚህ ውሳኔ ላይ የቀረበውን የሰበር አቤቱታ የከተማው ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የመመለስ ሥልጣን የለውም ተብሎ የተሰጠው ትዕዛዝ ህጉን የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ. 104857 ህዳር 24/2008 ዓ.ም በዋለ ችሎት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሣ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በምትክ ቦታ ይሰጠኝ ጥያቄ ላይ የሚሰጠው የመጨረሻ ፍርድ የሠበር አቤቱታ ለከተማው ፍ/ቤት ሳይቀርብ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ የሚቀርብበት የህግ አግባብ እንደሌለም ተወስኗል፡፡ ይኸው ውሳኔም በተያዘው ጉዳይ በተመሳሳይ ተፈፃሚ ነው፡፡

 

በመሆኑም የከተማው ሰበር ችሎት ያሳለፈው ትዕዛዝ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ተከታዩ ተወስኗል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 22374 ነሀሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡

2ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ተቀብሎ ለመወሰን ሥልጣን ያለው በመሆኑ ጉዳዩን ተመልክቶ ተገቢውን እንዲወሰን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 341(1) መሠረት መልሰናል ይፃፍ፡፡

3ኛ. ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ መዝገቡ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

 


 

 

የ/ማ


 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 
 
 

Google Adsense