110549 Rural land/ Tigray region

በትግራይ ክልል ገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ መሰረት ባለይዞታ አርሶ አደር ይዞታውን የመሸጥ መብት የሌለውና የኸው ተፈፅሞ ሲገኝ ይህ ውል እንዳይረጋ በማንኛውም ጊዜ ተቃውሞ ሊነሳና ጉዳዩ የቀረበለትም ፍ/ቤትም ውሉ ከጅምሩ ህገወጥ መሆኑን አውቆ ውሉ ህጋዊና ተፈፃሚነት የለውም በማለት ሊወሰን የሚገባ ስለመሆኑ የትግራይ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ቁ. 55/1994፣ አዲሱ አዋጅ ቁ. 236/2006 የፍ/ሕ/ቁ. 1678፣1716፣1718፣1195 እና 1196

 

 

የሰ/መ/ቁ 110549

 

የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ተኸሊት ይመስል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ወ/ሮ ደመቀች ንርአ  ጠበቃ ኪሮስ  አቢዲ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ጋለመ ረብሶ                      ተወካይ አለ ረብሶ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የገጠር እርሻ መሬት የሚመለከት ሆኖ በአሁኑ ተጠሪ ከሳሽነት የተጀመረው በአላማጣ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ደግሞ ተከከሽ ነበሩ፡፡ ተጠሪ ባቀረቡት ክስ፡- አዋሳኙ በክስ ማመልከቻቸው የጠቀሱትና በአላማጣ ወረዳ፣ ኩልግዘ ለምለም ጣብያ፣ በጆሃን ጎጥ ውስጥ የሚገኘውንና ስፋቱ 33ሜትር በ50 ሜትር የሆነውን የእርሻ መሬት በሕግ አግባብ ከአያታቸው ከሟች ወ/ሮ ሙሽራ አራርሶ ወርሰው የይዞታ ማረጋገጫ ያወጡበት መሆኑን፣ ይዞታውን ለአመልካች በኪራይ እያከራዩ የነበሩ መሆኑን፣ ቦታው ወደ አላማጣ ከተማ ሲገባ ግን ተጠሪ የታመሙበትን አጋጣሚ በመጠቀም የጎጆ መውጫ የነበረ ቦታ በማስመሰል አመልካች ይዞታውን በስማቸው እንዲሆን ማድረጋቸውን ዘርዝረው አመልካች ቦታውን እንዲያስረክቡ ወይም የአስር አመት አላባ፤ የመሬቱን ቋሚ ማሻሻያ ብር 126,500.00(አንድ መቶ ሃያ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ብር) እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኗ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም በይዞታቸው ስር ያለው በተጠሪ ክስ ውስጥ አዋሳኙ የተጠቀሰው ይዞታ ያለመሆኑን፣ በይዞታቸው ስር ያለው መሬት የሚታረስ ሳይሆን የጎጆ መውጫ ሁኖ ባለቤታች ሟች አቶ አድሃና አስፋው በቀን 10/10/1994 ዓ/ም ከወ/ሮ ሙሽራ ልጆች ከሆኑት ወ/ሮ ቡልቡላ ብርዋን በሽማግሌ ፊት በብር 1500.00 የገዙት መሆኑን፣ ይህ መሬት ታራሽ መሬት ነው፣ ይገባኛል በማለት ወ/ሮ ቡልቡላ ብርዋን በተወካያቸው አቶ መሃመድ ጎሳ በ2000 ዓ/ም ክስ መስርተውባቸው ቦታው ጎጆ መውጫ ነው በኩሉግዘ ለምለም ቀበሌ የመሬት ዳኝነት በ12/5/2000 ዓ/ም የተወሰነ መሆኑንና በፍርድ ያለቀ ጉዳይ መሆኑን፣ ጎጆ መውጫ  ሁኖ ባለቤታቸው በ1994


ዓ/ም የገዙት ከመሆኑም በላይ በ2001 ዓ/ም ወደ ስማቸው ዙሮ የሚጠቀሙበትና ቦታው ታራሽ ነው በሚል የአላባ ጥያቄ መቅረቡ ያላግባብ ነው የሚሉ ነጥቦችን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ እንዲሁም ከሚመለከተው አካል ተጣርቶ እንዲቀርብለት ያደረገውን ማስረጃ በመመርመር የአሁኑ ተጠሪ በውርስ ያገኙት ታራሽ መሬት መሆኑን፣ክርክሩ በመታየት ላይ ባለበት ጊዜ ግን ይዞታው ወደ አላማጣ ከተማ ስለገባ በስም የተጠሪ ሁኖ እንዲመዘገብ፣ የአንድ አመት አላባ ብር 5238.65 ደግሞ ለተጠሪ እንዲከፈላቸው፣ በአመልካች ባለቤት ስም ያለው ሳይት ፕላንም  እንዲሰረዝ በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለአላማጣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው መሬት እስከ 2005 ዓ/ም ድረስ ከከተማ ውጪ ሁኖ በገጠር መሬት አስተዳደር ቁጥጥር የነበረ ሁኖ አመልካች ከ12 አመታት በላይ ይዘው በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ቤት ስርተውና የተለያዩ ተክሎችን ተክለው የሚኖሩበት የነበረ ጎጆ መውጫ በ2001 ዓ/ም ወራሽነት ማስረጃ አውጥቼአለሁ በሚሉ ተጠሪ በ2006 ዓ/ም ክስ ሊመሰርትባቸው አይገባም እንደማይገባ፣ የሽያጭ ውሉም የይርፍረስልኝ ጥያቄ ሳይቀርብበት ክርክር ሊነሳበት የማይገባ መሆኑን እና በክፍሉ ማዘጋጃ ቤት አመልካች የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር ያገኙ በመሆኑ በፍርድ ቤት ሊመክን የማይችል መሆኑን በምክንያትነት ይዞ የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር አመልካች ለተጠሪ የሚያስረክቡት መሬትና የሚከፍሉት አላባ ግምት የለም ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ይዞታው  ወደ ከተማ ክልል ከመግባቱ በፊት የሚታረስ የነበረ መሆኑ መረጋገጡን፣ አመልካች ይዞታውን አገኘሁ የሚሉት ደግሞ በሽያጭ በመሆኑና የገጠር እርሻ መሬት የሚሸጥበት  ወይም የሚለወጥበት አግባብ በሕግ የተከለከለ ተግባር መሆኑነ፣ ከሕግ ውጪ የተሰጠ የይዞታ ማረጋገጫ ደግሞ በፍርድ ቤት ውሳኔ የማይመክንበት ምክንያት የሌለ መሆኑን በምክንያት ይዞ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር ይዞታው በተጠሪ ስም እንዲመዘገብ፣በአድሃና አስፋው ስም የተመዘገበው ሳይት ፕላን ሕገ ወጥ በመሆኑ እንዲሰረዝ፣ አላባውን ግን ያልተጠየቀ ዳኝነት በመሆኑ ለተጠሪ ሊከፈላቸው የማይገባ መሆኑን ገልጾ ወስኗል፡፡

 

በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አፅንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ይዞታው የጎጆ መውጫ ሁኖ በሽያጭ ለአመልካች ባለቤት በ1994 ዓ/ም ተላልፎ ቆይቶ


ይዞታው ወደ አላማጣ ከተማ ክልል ከገባ በኋላም በ2001 ዓ/ም በአመልካች ስም የይዞታ ማረጋገጫ ከአላማጣ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ተሰጥቶአቸው ይዞታው ላይ ቤት ሰርተውና የተለያዩ ተክሎችን አልምተው የሚገኙ መሆኑን ዘርዝረው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ  ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎና ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠው ውሳኔ ሊታረም ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪዎች ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ አከራካሪው ይዞታ ወደ አመልካች የተላለፈው በሽያጭ ውል ነው ተብሎ ሽያጩ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ አመልካች አከራካሪውን ይዞታ ለተጠሪ እንዲያስረክቡ  የመወሰኑን አግባብነትና ተያያዥ ነጥቦችን በጭብጥነት መያዙ ተገቢ ሁኖ ተገኝቷል፡፡

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአመልካች ባለቤት የነበሩት ሟች አቶ አድሃና አስፋው 10/10/1994 ዓ/ም ከወ/ሮ ሙሽራ ልጆች ከሆኑት ወ/ሮ ቡልቡላ ብርዋን በሽማግሌ ፊት    በብር

1500.00 የገዙት መሆኑና አከራካሪው መሬት ወደ አላማጣ ከተማ አስተዳደር ከመግባቱ በፊት ታራሽ መሬት እንጂ ጎጆ መውጫ ያልነበረ መሆኑን ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች ያረጋገጧቸው ነጥቦች መሆናቸውን ነው፡፡ ስለሆነም አመልካች ግዥው ሲደረግ ይዞታው ላይ የጎጆ መውጫ ነው፣ ቤት ተሰርቶና ተክሎችን በመትከል ይዞታውን አልምተን ለብዙ አመታት በመጠቀም ላይ ቆይተን ይዞታ ወደ ከተማ ክልል ገብቶ ከሚመለከት አስተዳደር አካል የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ያገኘሁበት ነው በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ሕጋዊነት ከክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ እና ስለጠቅላላ ውል በፍትሓብሔር ሕጋችን የተመለከቱትን የውል አመሰራረት መርሆች ጋር  ተዛምዶ መታየት ያለበት መሆኑን ተረድተናል፡፡

በመሰረቱ አንድ ውል በሕግ ጥበቃ እንዲደረግለት ወይም እንዲጸና በሕጉ ተለይተው የተቀመጡት ሁኔታዎችን አሟልቶ ሊገኝ ይገባል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም ውሉ ውል ለመዋዋል ችሎታ ባላቸው ሰዎች መካከል ጉድለት የሌለው ስምምነት መኖር፣በቂ የሆነ እርግጠኛነት ያለውና ህጋዊ የሆነ ጉዳይ መሆንና የውሉ አጻጻፍ ፎርም በህግ በታዘዘ ጊዜ ይህኑ ልዩ ፎርም አሟልቶ መገኘት የሚሉትን ሶስት መሰረታዊ የሆኑ ሁኔታዎች ስለመሆናቸው የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1678 ድንጋጌው- ከሀ- ሐ ፊደላት ስር በዝርዝር አስቀምጧቸዋል፡፡ የአንቀጹ ፊደል "ለ" ድንጋጌ በተለይ ሲታይም ውሉ በቂ የሆነ እርግጠኛነት ያለውና ሕጋዊ የሆነ ጉዳይ ላይ መደረግ እንደሚገባው የሚያስገነዝበው ሲሆን በህግ እንዲደረግ ያልተፈቀደ፤የህግ ክልከላ ባለበት ጉዳይ ላይ የተደረገ ውል ደግሞ ህገ


ወጥ ውል ( unlawful contract )ይሆናል፡፡ አንድ ውል የተደረገበት መሰረታዊ ጉዳይ  (object of contract) በህግ ክልከላ የተደረገበት በሆነ ጊዜም ውሉ በህግ ፊት ምንም ዓይነት ህጋዊ ውጤት የማያስከትል (void contract) መሆኑ ይታመናል፡፡

ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አከራካሪው ይዞታ ወደ አመልካች እጅ ሊገባ የቻለው ሟች ባለቤታቸው አቶ አድሃና አስፋው በ10/10/1994 ዓ/ም አደረጉ በተባለው የገጠር እርሻ መሬት ይዞታ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በኢ/ፌ/ዲ/ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40(3) የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና ህዝብ እንደሆነና መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ሀብት መሆኑ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የክልሉ ሕገ መንግስትም በዚህ ረገድ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ድንጋጌ አስቀምጦአል፡፡ በሌሎች ዝርዝር ህጎችም ማለትም፡- በአዋጅ ቁጥር 456/97"ም" ቢሆን ባለይዞታ አርሶ አደር የመሬት ይዞታውን ለመሸጥ መብት አልተሰጠውም፡፡ አሁን በስራ ላይ ባለው የክልሉ መንግስት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 239/2006ም ሆነ በ1994 ዓ/ም ስራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 55/1994 የገጠር መሬትን በሽያጭ ማስተላለፍ በሕግ ጥበቃ የሚደረግለት ተግባር አይደለም፡፡ በመሆኑም በአመልካች ባለቤት በ1994 ዓ/ም ተደረገ የተባለው ውል በገጠር መሬት ላይ በግልጽ በሕግ ክልከላ ተደርጎ እያለ የተደረገ በመሆኑ ሕገወጥ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ ህገ ወጥ ውል ደግሞ በፍ/ህ/ቁ/1716 መሰረት በህግ ፊት ውጤት የማይኖረው ፈራሽ ውል ነው፡፡

 

ይህ ብቻም ሳይሆን ሕገ ወጥ ውል በማናቸውም ጊዜ ሊፈርስ የሚችል እንጂ የይርጋ ገደብ የሌለው መሆኑን ይህ ችሎት የፍ/ህ/ቁ/1678፣1716 እና 1718 ድንጋጌዎችን በጣምራ በመመርመር በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም በሰ/መ/ቁጥር 43226፣79394 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት ወስኗል፡፡ በዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት የውሉ መሰረታዊ ዓላማ በህግ ያልተፈቀደና የተከለከለ ሆኖ ሲገኝ ዳኞች ህገ ወጥ የሆነውን ውል (unlawful contract) በቀረበላቸው ማንኛውም ጊዜ ህጋዊ ውጤትና ተፈጻሚነት የለውም በማለት ለመወሰን እንደሚችሉና ህገ ወጥ የሆነውን ውል ውድቅ ለማድረግ በህጉ የተደነገው የይርጋ ጊዜ ገደብም መቃወሚያ ሊሆን እንደማይችል ችሎቱ በግልጽ አስፍሯል፡፡

 

ስለሆነም አመልካች ለብዙ አመታት ይዞታውን ይዘው መጠቀማቸውን ጠቅሰውና እና ተክል አልምተው ይዞታው ወደ ከተማ ሲከለል ከማዘጋጃ ቤት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አግኝቼአለሁ የሚለውን ምክንያት መሰረት አድርገው የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ የተጠሪን አውራሽ ልጆች የሆኑት ከአመልካች ባለቤት ጋር የገጠር እርሻ መሬት ሲሸጡ ሙሉ ፍላጎትና እውቅና የነበራቸው መሆኑም በሕግ በግልጽ የተደረገውን የገጠር እርሻ መሬት  ሽያጭ


ሕጋዊ ውጤት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል ካለመሆኑም በላይ የሕገ መንግስቱንና ይህንኑ ተከትሎ የወጡትን የክልሉን የገጠር እርሻ መሬት አስተዳደር ሕግጋትን መሰረት ያላደረገ ነው፡፡

 

አመልካች ይዞታው ወደ ከተማ ክልል ከገባ በኋላ ከሚመለከተው የመንግስት አካል የይዞታ ማረጋጋጫ ደብተር መውሰዳቸው በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ቢሆንም ይዞታው ወደ አመልካች የገባበት መንገድ ከመነሻው ሕጋዊ ባለመሆኑና በሕግ አግባብ ባልተገኘ የይዞታ መብት ላይ የሚሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ስልጣን ባለው አካል በመሰጠቱ ብቻ ሕጋዊ ሊሆን የሚችልበት አግባብ የሌለ መሆኑን ከፍ//ብ/ሕ/ቁጥር 1195 እና 1196 ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ እንዲሁም ሕገ መንግስቱ ስለንብረት መብት ከሚሠጠው ጥበቃና የመሬት ሽያጭ ውል ሕገ ወጥ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚችል ሁኖ አልተገኘም፡፡ ሲጠቃለልም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ሰበር ሰሚ ችሎት የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ በግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃዎች በተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች መሰረት የሽያጭ ውሉ ህገ ወጥ ነው በሚል ይዞታውን አመልካች ለተጠሪ እንዲለቁ፣ በአመልካች ባለቤት ስም የተሰራው ሳይት ፕላን እንዲሰረዝ በማለት መወሰናቸው ስለገጠር መሬት ይዞታ በፌዴደራሉም ሆነ በክልሉ ሕግጋተ-መንግስታት፣ሽያጩ ተደረገ በተባለው ጊዜ ስራ ላይ በነበረው የክልሉ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 55/94፣ እንዲሁም ክርክሩ በተነሳበት ጊዜ ተፈጻሚነት ባለው አዋጅ ቁጥር 236/2006 ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ባገናዘበ መልኩ የሰጡት ውሳኔ ሁኖ ስለአገኘን በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. በትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 682220 በ11/02/2007 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 70901 በ18/05/2007 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡

2. አከራካሪው ይዞታ የሚታረስ መሬት ነው ሁኖ በሽያጭ ወደ አመልካች በሕገ ወጥ መንገድ ዙሮአል ተብሎ በመወሰኑ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል፡፡ ሆኖም በይዞታው ላይ በአመልካች የተፈሩትን ንብረቶችን አመልካች በሕግ አግባብ ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና  ኪሳራ  የየራሳቸውን ይቻቻሉ ብለናል፡፡

 ት እ ዛ ዝ

በ25/06/2007 ዓ/ም የተሰጠው እግድ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ይጻፍ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት