112906 rural land

አንድ አርሶ አደር የሚጠቀምበት ይዞታ (መሬት) በህግ ስልጣን በተሰጠው አካል የተሰጠው መሆኑን እስካላረጋገጠ ድረስ የመንግስትና የህዝብ መሬትን ለረዥም ዓመት ይዤዋለሁኝ ስለዚህ ይርጋ አይመለከተኝም ብሎ የሚያነሳው ክርክር ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ

 

 

የሰ/መ/ቁ. 112906

ቀን የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ/ም


ተጠሪ፡- የማቻካል ወረዳ አካባቢ ጥበቃ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽ/ቤት ተወካይ የክልሉ ዓ/ሕግ ቀረቡ

መዝገቡ መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል ፡፡

 ፍ ር ድ

ጉዳዩ የመሬት ይዞታ እና የሰብል ግምት ክርክር የሚመለከት ሲሆን ጉዳዩ የተጀመረው በአብኪመ የማቻኮል ወረዳ ፍ/ቤት የአሁኑ ተጠሪ በዓቃቤ ህግ በኩል በአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረበው ክስ መነሻነት ነው፡፡

 

የአሁኑ ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ባጭሩ ፡- አመልካች ከማንም ሕጋዊ መብት ካለው አካል ሳይሰጠው በመቻከል ወረዳ በሸይ ቀበሌ ልዩ ስሙ ገለቦ በተባለው ቦታ በምስራቅ መንገድ በምዕራብ ተምጫ ወንዝ፣ በሰሜን የኔወርቅ ለቀው በደቡብ አሚጋ የሚያዋስነው የህዝብ ግጦሽ መሬት በወርድ 50 ሜትር በቁመት 80 ሜትር የሆነውን የመስኖ መሬት በመያዝ በ2004፣2005 እና 2006 እህል በመዝራት፤ አትክልት በማፍራት ገቢ በማግኘቱ የሰብል ግምት በመክፈል የህዝብና የመንግስት ይዘት ለቆ እንዲያሰረክብ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሰይ ነው፡፤

 

የአሁኑ አመልካች የመከለከያ መልስ ያቀረበ ሲሆን ዋና ፍሬ ነገሩ የሰብል ግምት መቅረብ ያለበት በመሬት ይዞታው ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ መሆን እንዳለበት፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን መሬት በ1994 ኣ/ም የቀበሌ አመራር ኮሚቴዎች ለወፍጮ መትክያ የተሰጠው ስለመሆኑ በመግለጽ መልስ አቅርበዋል፡፤

 

የስር ወረዳ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ የአሁን አመልካች መሬቱ ከ1994 ዓ/ም የያዝኩት ስለሆነ ጉዳዩ በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት ያቀረበው ክርክር በተመለከተ በዚህ ጉዳይ በ1999 ዓ/ም በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተበለ በመሆኑ በይርጋ የሚቋረጥ አይደለም ፡፡ አመልካች መሬቱን በቀበሌ የአመራር አካላት የተሰጠኝ ነው በማለት የተከራከረ ቢሆንም መሬት የማስተዳደር ስልጣን የወረዳው መሬት አስተዳደር አጠቃቀም  ጽ/ቤት


እንጅ የቀበሌ አመራር አይደለም፡፡ አመልካች በመሬቱ ላይ የዘራው ሰብል ግምት በድምሩ 11,474/ አስራ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰባ አራት ብር ይክፈል ይዞታውም ይልቀቅ በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች የስር ወረዳ ፍ/ቤት ውሳኔ በመቃወም ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙ ከከራከረ በኃላ አመልከች ለክርክሩ መነሻ የሆነውን መሬት ለወፍጮ ተጠቃሚ ህብረተሰብ አህያ እንዲያስርበት በቀበሌ አስተዳደር የተሰጠው መሆኑ በወቅቱ የቀበሌ አስተዳደር ኃላፍዎች የነበሩ ቀርበው የመስከሩ ቢሆንም መሬት የመስጠት ስልጣን የወረዳ አስተዳደር መሆኑ በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 133/98 ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም አመልካች መሬቱን ያገኘው ህጋዊ ሥልጣን ከሌለው የቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤት በመሆኑ ይልቀቅ መባሉ በአግባብ ነው። የሰብል ግምት በተመለከተ አመልካች መሬቱን ያረሰው መብት ያለው መስሎት በመሆኑ በፍ/ህ/ቁ/1173 (2) መስራት ሊሻሸል እንደሚገባው የጤፍ ሰብል ግምት ዳኝነት ያልተጠየቀበት በመሆኑ የዚህን ግምት መጠን ተቀንሶ ብር 7,726.5 ይክፈል ሲል ወስኗል፡፡ አመልካች ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደርጓል የአሁን ሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ይቅረብ በመባሉ ተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር አደርጓል፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘት መሬቱ በ1994 ዓ/ም የተሰጠው በመሆኑ በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ እንንደሚሆን ለክርክሩ መነሻ የሆነውን መሬት የሰጡት የቀበሌ አስተዳደር በመሆኑ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ እንዲሻር መጠየቁን የሚያሰይ ነው፡፡ ተጠሪ በበኩሉ አመልካች የህዝብና የመንግስት ንብረት በህገወጥ የያዘ በመሆኑ ጉዳዩ በይርጋ ህግ ቀሪ የሚሆን አይደለም መሬቱም ሥልጣን በሌለው የቀበሌ አስተዳደር የተሰጠው በመሆኑ ይልቀቅ መባሉ በህጉ አግባብ ነው የሚል መልስ አቅርበዋል፡፤ አመልካች የሰበር አቤቱታው የሚያጠናክር የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡ የጉዳዩ አመጠጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎት የስር ፍርድ ቤቶች በሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸም ያለመፈፀሙን መርምረዋል፡፡ እንደመረመርናውም የአሁኑ አመልካች አጥብቆ የሚከራከራው የመሬት ይዞታው በቀበሌ አስተዳደር እንደተሰጠው እና ለረጅም  ዓመት ሲጠቀምበት እንደነበር ነው፡፡ ተጠሪ በበኩሉ የቀበሌ አስተዳደር መሬት የመስጠት ስልጣን እንደሌለው እና ሰብል በማምረት ያገኘው ህገወጥ ጥቅም ገቢ እንዲያደርግ መወሰኑ በአግባቡ ነው የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡


በስር ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠው አመልካች ከዚህ መሬት ጋር በተያየዘ በ1999 ዓ/ም በወንጀል ተከሶ እንደተቀጣ መሬት የመስጠት ስልጣን በሌለው የቀበሌ  አስተዳደር የተመራው ስለመሆኑ ነው፡፡ አመልካች የመሬት ይዞታው በቀበሌ አስተዳደር ተሰጠኝ ይበል እንጂ የቀበሌ አስተዳደር መሬት የመስጠት ኃላፊነት እንደነበራቸው በህግ የተደገፈ ክርክር አላቀረበም፡፤ በህጉ አግባብ ሥልጣን ባለው አካል የመሬት ይዞታው ማግኘቱ ካልተረጋገጠ ደግሞ የህዝብና የመንግስት ይዞታ ሊለቅ ይገባል መባሉ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ጉዳይ አይደለም፡፡ አመልካች ያቀረበው የይርጋ ክርክር የህግ ድጋፍ የለውም ብለናል፡፡

 

አመልካች በህገ ወጥ መንገድ በያዘው መሬት ላይ ሰብል ዘርቶ ገዚ በማግኘቱ ምክንያት ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ወረዳ ፍ/ቤት ውሳኔ በማሻሸል 7,726 ብር የሰብል ግምት እንዲከፍል ወስኗል፡፡ አመልካች ሰብሉን የዘራበት አግባብ ሲታይ የመሬት ይዞታው በቀበሌ አስተዳደር የተሰጠው ስለመሆኑ እምነት በመያዝ ነው፡፡ በስር ፍርድ ቤት ቀርበው የተሰሙ የቀበሌ የስራ ኃላፊዎች የነበሩ ግለሰቦች መሬት ሰጥተው እንደነበረ አስረድቷል፡፡ ይህ ሲታይ አመልካች መሬቱ ስልጣን ባለው አካል ተሰጥቶኛል ከሚል እምነት በመነጨ በቅን ልቦና ሰብል ያመረተ መሆኑን መረዳት ይቻላል ተጠሪም መሬቱ ሥልጣን ባለው አካል አልተሰጠውም በማለት ተከራከረ እንጅ የቀበሌ አስተዳደር ያልሰጠው ስለመሆኑ ክዶ አልተከራከረም፡፡ ይህ ከሆነ አመልካች ሰብል በመዝራት አገኘው የተበለው ግምት 7,726 ብር ይክፈል መባሉ በህጉ አግባብ ሆኖ አላገኘነውም፡፡

 

በመሆኑም አመልካች መሬቱ እንዲለቅ የተሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ሆኖ የሰብል ግምት ይክፈል ተብሎ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ግን ሊሻሻል የሚገባው ነው፡፤ በዚህም ተከታዩን ወስነናል፡፤

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የምስራቅ ስደሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 011806 በ 24/06/2007 ዓ/ም የመቻከል ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 11475 በ2/08/2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ በማሻሸል የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሏል፡፤

2. አመልካች ለክርክሩ ምክንያት የሆኑትን መሬቶች እንዲያሰረክብ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል።

3. አመልካች የሰብል ግምት 7726 /ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ሃያ ሰድስት ብር 50/100 የሆነውን ለመልስ ሰጭው ሊከፍል ይገባል ተብሎ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሸሯል

4.  የወጪና ኪሰራ ይቻቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ተመለሰ

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡