95537 civil procedure/ execution of judgment

የአፈጻጸም ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት ለአፈጻጸሙ ተስማሚ በሆነ መንገድ ፍርድ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሚሰጠው የፍርድ ባለዕዳውን ጠርቶ ከመረመረው በኃላ እንደፍርዱ የማይፈጸምበት ምክንያት አለመኖሩን ካረጋገጠ በኃላ ስለመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 207 እና 320(2) መሰረት በተሰጠው ትእዛዝ ላይ ቅሬታ አቅርቦ ነገር ግን ቅሬታው ተቀባይነት ቢያጣ የይግባኝ መብቱን (የይግባኝ ጊዜ ሊሰላበት) ስለሚችልበት አግባብ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 392 (1)

 

የሰ/መ/ቁ. 95941

 

ታህሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ

 

 

አመልካች፡-   ሔስ ትራቭል ኃ/የተ/የግ/ማህበር - ጠበቃ ረታ አለማየሁ - ቀርበዋል

 

ተጠሪዎች፡- 1. የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓ/ህግ ኃይለመለኮት አበበ - ቀርበዋል 2. የኢትዮጵያ ግዮን ሆቴሎች ድርጅት - ነ/ፈ ሙላት ማሞ - ቀርበዋል፡፡

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ ተከታዩን

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ የሰበር አቤቱታ መዝገብ ክርክር አመልካች ሔስ ትራቭል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ታህሣስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 92474፣ ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም የቀረበ ነው፡፡ ቅሬታውም የአሁን 1ኛ ተጠሪ ሲከራከር የነበረው ለአመልካች የገበሩት ታክስ ቅናሽ እንዲደረግለት ግብሩን ሲያሳውቅ አብሮ ሕጋዊ ደረሰኝ (የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ) ማቅረብ አለበት፡፡ አመልካች ግን ደረሰኝ ብያቀርብም ህጋዊ አይደለም የሚል ሲሆን፤ ከአሁን በፊት የፌ/ከ/ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በጣልቃ ገቢነት የኢትዮጲያ ግዮን ሆቴሎች ድርጅት ገብቶ እንዲከራከር ወስኖ ወደ ፌ/ከ/ፍ/ቤት በመለሰው መሠረት የኢት.ግዮን ሆቴሎች ድርጅት በጣልቃ ገቢነት የሰጠው መልስ በግብር ዘመኑ ገቢ ያደረገ መሆኑን ከአሁን አመልካች ብር 533,951.97 የሰበሰበና የተ.ኦ.ታ. ብር 80,089.97 ብቻ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ይህ የጣልቃ ገቢ (የኢትዮ.ግዮን ሆቴሎች ድርጅት) የሰበሰው የተ.እ.ታ. ብር 80,089.97 ብቻ ያለው ስህተት መሆኑና  ብር  408,619.47  እንደሆነ  ይጣራልኝ  ብዬ  ፍ/ቤቱን  ብጠይቅም አልተቀበለኝም፡፡


በመሆኑም የኢት.ግዮን ሆቴሎች ድርጅት የተ.እ.ታ ሲሰበሰብ የነበረው በአንደኛ ተጠሪ የታወቁ ደረሰኞች እንደሆኑና 2ኛ ተጠሪ (የኢት.ግዮን ሆቴሎች ድርጅት) ታክሱን አልከፈሉም ሳይባል የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሰጠውን ውሰኔ የሥር ፍ/ቤት መሻሩ ስህተት በመሆኑ ይታረምልኝ ይላል፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ ክርክር የተነሳበት የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ በሥር ጣልቃ ገብ የሆነው የአሁን 2ኛ ተጠሪ መክፈሉ ተረጋግጦ እያለና የሂሳብ ስሌት ስህተት ካለም በሂሳብ አጣሪ እንዲታይ ተጠይቆ የሥር ፍ/ቤት ይህን ባለማገናዘብ የሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት ነው የሚለውን የአመልካች ቅሬታ ለመመርመር ሲባል ቀርቧል፡፡ መልስና የመልስ መልስም ተሰጥቶበታል፡፡

 

1ኛ ተጠሪ መጋቢት 25 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካች በትክክል የዚህን ዘመን የተ.እ.ታ በስሙ የከፈለ ለመሆኑ የሚያስረዳ ተጨባጭ ደረሰኝ ማቅረብ  ሲገባው ያላቀረበ በመሆኑና 2ኛ ተጠሪ በስሙ ለተጠሪ ገቢ ያደረገው ታክስ በስሜ እንደተከፈለ ተቆጥሮ ይቀነስልኝ በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ ድጋፍ የሌለው በመሆኑና የሥር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ስህተት ያለበት በመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ውድቅ ይሁንልኝ በማለት ተከላክሏል 2ኛ ተጠሪም የስር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ በተ.እ.ታ. አዋጅና በደንቡ ላይ ተመስርቶ ህጉን ተከትሎ በመሆኑ ስህተት የተፈፀመበት ባለመሆኑ ያፅናልኝ ሲል ተከራክሯል፡፡ አመልካችም ሚያዚያ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

 

በዚሁ መሠረት መዝገቡን እንደመረመርነው ከፌ/ከ/ፍ/ቤት ሲሆን የፌ/ከ/ፍ/ቤት ጉዳዩን በይግባኝ አይቶ ውሳኔ የሰጠበት በመጀመሪያ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 115 መሠረት የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የካቲት 3 ቀን 2002 ዓ.ም በሰጠው መሠረት በቀረበው ላይ ነው፡፡ የአሁን አመልካች (ይግባኝ ባይ) ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ያቀረበው ይግባኝ የግብር ዓላማ በሕጎቹና በደንቦቹ ላይ እንደተጠቀሰው ከሚሰጡ አገልግሎች ላይ ግብሩ ተሰብስቦ በጊዜው ለግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ገቢ መደረጉ ሲሆን፤ ይሄውም ገቢ መደረጉ ግብሩን የሰበሰበው በጊዜው የተጨማሪ እሴት ታክስ ከከፈሉት ድርጅቶች ማረጋገጫ ለተገኘበት ሂሳብ በእኛ በኩል እንዳልተከፈለ ተደርጎ ተቀባይነት ማጣቱ ተገቢ ባለመሆኑ የቀረቡትን ማስረጃ በተገቢው ሁኔታ ዝርዝሩ ታይቶ ይስተካከልልኝ የሚል ሲሆን መልስ ሰጪ የኢት/ገ/ጉ/ባለሥልጣንም የሰጠው መልስ በተጨማሪ እሴት ታክስ አ.ቁ 285/94 አንቀጽ 21 የተ.እ.ታ ከፋይነት ታክስ ተመዝጋቢ ሰው ከቫት በተቀበለው የተ.እ.ታ ደረሰኝ መሆን አለበት፡፡ ይግባኝ ባይ ታክስ የከፈለበትን የተ.እ.ታ ደረሰኝ ሳያቀርብ ታክሱ እንዲቀነስለት መጠየቁ ተቀባይነት የለውም ይግባኝ ባይ ከ1995 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም የግብአት ታክስ ከፍያለሁ ቢልም የተ.እ.ታ የከፈለበትን ማስረጃ ያላቀረቡ በመሆኑ ይግባኛቸው ውድቅ ይሁንልኝ በማለት ተከላክሏል፡፡


የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤውም የካቲት 3 ቀን 2002 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ይግባኝ ባይ ለተጠየቁት ግብር ከ1995 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም የግብር ዘመን የተ.እ.ታ የግዮን ሆቴሎች ድርጅት በጊዜው በትክክለኛ ፎርማት መሠረት ደረሰኞቹን እንዳላሳተመና በኢንቮይስ እንዲጠቀም የፈቀደለት መሆኑን ገልŠ የግዮን ሆቴሎች ድርጅት በይግባኝ ባይ ስም የተሰበሰበ የተጨማሪ እሴት ታክስ በትክክል ለመልስ ሰጪ ገቢ ያደረገበት ማስረጃ እና ይህንኑ የሚያስረዳ ባለሙያ ቀርበው ገቢ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ይግባኝ ባይ በመልስ ሰጪ መሥሪያ ቤት የተጠየቀውን የተ.እ.ታ.መክፈሉን የጊዮን ሆቴሎች ያረጋገጠ ሲሆን መልስ ሰጪ ገቢው በትክክል አልደረሰም የሚል ከሆነ የጊዮን ሆቴሎች ድርጅት መጠየቅ እንጂ በይግባኝ ባይ ላይ የወሰነው ግብር አለአግባብ ነው በማለት ወስኗል፡፡ ይህን ውሳኔ መልስ ሰጪ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ ብሎ የፌ/ከፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ የአሁን አመልካች ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ብሎ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በጣልቃ ገቢነት የኢትዮ. ግዮን ሆቴሎች ድርጅት አከራክሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ወደ የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት በመመለሱ የፌ/ከፍ/ፍ/ቤ በመ.ቁጥር 94730 ይግባኝ ባይ የኢት.ገ/ጉ ባለሥልጣን መልስ ሰጪ ሔስ ትራቭል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጣልቃ ገቢ የኢት.ግዮን ሆቴሎች ድርጅትን አከራክሮ ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ ይግባኝ ባይ አጥብቆ የሚከራከረው መልስ ሰጭ (ሔስ ትራቭል ኃ/ተ/የግ/ማ) የግብአት ታክስ እንዲቀነስለት ግብር ሲያስታውቅ አብሮ የተጨማሪ እሴት ደረሰኞችን ማቅረብ አለበት፡፡ መልስ ሰጪ ደግሞ ግብሩን የከፈለው መሆኑን ህጋዊ ደረሰኝ ያልቀረበና በጣልቃ ገቢ በኩል ያልተከፈለ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ መልስ ሰጭ ግብሩን በጣልቃ ገቢ በኩል ከፍያለው ቢልም በስሙ የተከፈለ መሆኑን ማስረጃ አላቀረበም፡፡ በመሆኑም ይግባኝ ባይ መልስ ሰጪን የግብር ክፍያ የጠየቀው ጣልቃ ገቢ በግብር ዘመኑም የሰበሰበው ታክስ እንደከፈለ ግን በመልስ ሰጪ ስም ለይቶ ያልከፈለ መሆኑን የገለፀ ስለሆነ በመልስ ሰጪ ላይ የሚፈለገው ታክስ በራሱ ስም ገቢ ሆኗል ለማለት አይቻልም በማለት የፌድራል ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በመ.ቁ. 625/1/02 የሰጠውን ውሳኔ ሽሯል፡፡

 

የአሁን አመልካች ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢልም የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 92474 ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ..337 መሠረት የስር ፍ/ቤት ፍርድ ጉድለት የሌለበት ሆኖ አግኝተናል ሲል መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ የአሁን አመልካች ይህን ትዕዛዝ በመቃወም የቀረበ ነው፡፡ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁን አመልካች አቤቱታ 1ኛ ተጠሪ (የኢት/ገ/ጉ/ባለሥልጣን) በሥር ፍ/ቤት ሲከራከር የነበረው ለአመልካች የግብአት ታክስ ቅናሽ እንዲደረግለት ግብሩን ሲያሣውቅ አብሮ ሕጋዊ ደረሰኝ አያይዞ ማቅረብ አለበት፤ አመልካች ግን ደረሰኝ ቢያቀርቡም ህጋዊ አይደለም በሚል ሲሆን 2ኛ ተጠሪ የኢት.ግዮን ሆቴሎች ድርጅት የወቅቱን የግብር ታክስ አልከፈለም ሣይባል በግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የተሰጠው ውሳኔ መሻሩ ተገቢ አይደለም የሚል ነው፡፡ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲጣራ የተያዘው ጭብጥ ክርክር


የተነሣበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ በሥር ጣልቃ ገቢ የሆነው 2ኛ ተጠሪ የወቅቱ ግብር መከፈሉ ተረጋግጦ እያለና የሂሣብ ስሌት ስህተት ካለም በሂሣብ አጣሪ እንዲታይ ተጠይቆ የሥር ፍ/ቤት በማለፍ የሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት ነው የሚለውን የአመልካች  ቅሬታ ለማጣራት ነው፡፡ በዚሁ በተያዘው ጭብጥ መሠረት እንደመረመርነው የአሁን አመልካች የተጨማሪ እሴት ታክስ ለ2ኛ ተጠሪ የከፈልኩት ተቀናሽ ያደረግልኝ ሲል ለ1ኛ ተጠሪ ያቀረባቸው ደረሰኞች አሉ፡፡ 1ኛ ተጠሪ እነዚህን ደረሰኞች ህጋዊ ደረሰኞች ባለመሆናቸው ተቀናሽ ማድረግ አልችልም በማለት ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ በሥር ፍ/ቤት በተደረገው ክርክር የአሁን አመልካች ያቀረባቸው ደረሰኞች ህጋዊነትን ለመለየት 2ኛ ተጠሪ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር ተወስኖ 2ኛ ተጠሪም ጣልቃ ገብቶ ሲከራከር በወቅቱ የሰበሰባቸውን ግብር ለ1ኛ ተጠሪ ገቢ ያደረጋቸው መሆኑን፣ ከአሁን አመልካች የሰበሰበውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ብር 80,089.97 በስሙ ገቢ ያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ 2ኛ ተጠሪ በዘመኑ ግብር ሲሰበስብ የነበረው በተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሣይሆን 1ኛ ተጠሪ በፈቀደለት ደረሰኝ በመሆኑ የአሁን አመልካች ተቀናሽ እንዲደረግለት ለ1ኛ ተጠሪ ያቀረባቸው ደረሰኞች ሁሉም ከ2ኛ ተጠሪ የተሰጡ ለመሆኑ ሊረጋገጥ የሚችለው በ2ኛ ተጠሪ (ደረሰኙን በሰጠውና) በ1ኛ ተጠሪ የደረሰኙን በፈቀደው ስለሆነ ከ2ኛ ተጠሪ የተሰጡ ደረሰኞች ስለመኖራቸው 2ኛ ተጠሪ ከአመልካች የሰበሰበውን ግብር ከራሱ ሰነዶች እና ደረሰኞች ላይ በማመሣከር የተገኘውን የግብር መጠን አሳውቋል፡፡ የ2ኛ ተጠሪ የተጨማሪ እሴት ታክስ መክፈል አለመክፈል ለመመርመር ሥልጣኑ የተሰጠው ለ1ኛ ተጠሪ ነው፡፡ የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት 2ኛ ተጠሪን ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር ካደረገ በኃላ የአሁን አመልካች ተቀናሽ እንዲደረግለት 1ኛ ተጠሪ ያቀረባቸው ደረሰኞች ህጋዊ ደረሰኝ ያለመሆናቸውን፣ 2ኛ ተጠሪም በጣልቃ ገብ የሰጠው መልስ ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን በማረጋገጥ የግብር ይግባኝ ጉባኤን ውሳኔ  የሻረውና፣ የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤትም የከፍ/ፍ/ቤትን ውሳኔ ያፀናው መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አልተገኘም፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 94730 ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ፣ የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁጥር 92474 ጥቅምት 2 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1/ ፀንቷል፡፡

2.  በዚህ መዝገብ ወጪና ኪሣራ ተቻቻሉ ብለናል፡፡

3.  መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡

 

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡