104512 environment law/ dangerous substance/ license

የአካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ፈቃድ ሳይዝ ማንኛውንም አደገኛ ቆሻሻን ማመንጨት፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ ማጓጓዝ፣ ማምከን ወይም ማስወገድ የተከለከለ ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 300/95 አንቀጽ 4/1/

 

የሰ/መ/ቁ/104512 መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ሌሊሴ ደሳለኝ

 

አመልካች፡- አቶ አባስ ኢብራሂም   ቀረቡ ተጠሪዎች፡- የሐረር ቢራ አ/ማህበር                              አልቀረቡም

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የንብረት ጉዳት ካሳ ክፍያ ጥያቄን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የጀመረው ያሁን አመልካች በሀረሪ ክልል ጠ/ፍ/ቤት በሰበር ተጠሪ ላይ በመሰረተው ክስ መነሻነት ነው፡፡ የክሱ ፍሬ ነገርም ባጭሩ፡- ተጠሪ ኮስቲክ ሶዳና ሃይድሮሊክ አሲድ የተባለ መርዛማነት ያለው ተረፈ ምርት በእርሻ ማሳዬ ላይ አፍስሶ የተለያዩ ቋሚ ተክሎችና ሰብሎቹን በማድረቅ ስላወደመብኝ በዚህ ምክንያት ለደረሰብኝ ጉዳት በድምሩ ብር 1,526,700 ካሳ ይከፈለኝ የሚል ነው፡፡ ተጠሪም በበኩሉ ቀርቦ ለክሱ በሰጠው መከላኪያ መልስ፡- በክሱ የተጠቀሰውን መርዛማ ኬሚካል በአመልካች ማሳ ላይ አለማፍሰሱን፣ ያም ሆኖ ግን የድርጅቱን ፍሳሽ ወይም ተረፈ ምርት የክልሉ አርሶ አደሮች ለእርሻ ማሳቸው በማዳባሪያነት ጠቃሚነቱን ተረድተው እንዲደፋላቸው በጠየቁት መሰረት የተደፋላቸው መሆኑን፣ ተረፈ ምርቱም ለእርሻ ማሳ ማዳበሪያነት ጠቃሚ መሆኑን፣ በጉዳዩ ላይ በሐሮሚያ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ያለው ጥናትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑንና የጉዳት ካሳ መጠኑም የተጋነነ ነው የሚልና የመሳሰሉትን በማንሳት ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክርና ምስክሮች ቃል ከሰማ በኃላ በተጨማሪነትም ከክልሉ አካባቢና ጥበቃ ባለስልጣን ጽ/ቤትም ባለሙያ አስቀርቦ በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየቱን ከተቀበለ በኃላ ጉዳዩን መርምሮና ማስረጃውንም ከመዘነ በኃላ የተጠሪ ተረፈ ምርት በአመልካች ማሳ  ላይ  መፍሰሱን፣ይህንን  ተከትሎም  ተክሎችና  ሰብሎቹ  በመድረቅ  ጉዳት የደረሰባቸው


መሆኑን፣ ለዚህም ጉዳት ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 300/95 አንቀጽ 4 /1/ ና ፍ/ብ/ህግ/ቁ/2035 መሰረት ኃላፊነት ያለበት መሆኑንና የደረሰውን ጉዳት መጠንም ብር 145,840 መሆኑን መረጋገጡን ከገለጸ በኃላ በሌላ በኩል ደግሞ ተረፈ ምርቱንም አመልካች እራሱ እንዲደፋለት በጠየቀው ጥያቄ መሰረት በማሳው ላይ እንዲደፋ መደረጉንና እንዲሁም አመልካችም ሌሎች አርሶ አደሮች እንደሚያደርጉት ተረፈ ምርቱ የሚያመጣውን ጉዳት ለማስቀረት ፍሳሹን በየጊዜው በመጥረግ የበኩሉን አስተዋዕፆ ማድረግ ሲገባው ይሄንን አለማድረጉም በምስክሮች ቃል መረጋገጡን ገልፆና ይህም በአንድ ላይ ተገናዝቦ ሲታይ ክፊሉ ጉዳት ራሱ በአመልካች ጥፋት መድረሱን መገንዘቡን በውሳኔው በማስፈርና ይህንኑም በካሳ ክፋያ አሰላሉ ሂደት ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ጭምር ከገለጸ በኋላ ተጠሪ ከብር 145,845 ውስጥ የበኩሉን የኃላፊነት ድርሻ 100,00፣ የጠበቃ አበል10% /10,000/ እና የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ብር 3,350 ጋር ለአመልካች ይክፈል ሲል ወስኗል፡፡ አመልካችም በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ ቅሬታውን ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አሁን ለዚህ ሰበር ችሎት የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይህንኑ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ሲሆን አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ አመልካች የተጠሪ ተረፈ ምርት በእርሻው ማሳው ላይ እንዲደፋ መፍቀዱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ለደረሰው ጉዳት እሱም አስተዋፆ አለበት ተብሎ ሊከፈለው ከሚገባው የጉዳት ካሳ መጠን ውስጥ ብር 45,840 ተቀንሶ እንዲከፈለው የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎና ለተጠሪም በህጉ መሰረት መጥሪያ እንዲደርሰው ቢደረግም ባለማቅረቡ በፅሁፍ መልስ የመስጠት መብቱ እንዲታለፍ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን አቤቱታው ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ሲደረግ ተይዞ ከነበረው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡

 

በመሰረቱ ጉዳዩ ከሚመለከተው የአካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ፈቃድ ሳይዝ ማንኛውንም አደገኛ ቆሻሻን ማመንጨት፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ ማጓጓዝ፣ ማምከን ወይም ማስወገድ የተከለከለ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 300/95 አንቀጽ 4/1/ ስር በግልጽ ተደንግጎ እናገኛለን ፡፡ ከዚህም መገንዘብ እንደሚቻለው አስቀድሞ የአካባቢው ጥበቃ መስሪያ ቤት ሳያስፈቅዱ የፋብሪካ ውጤት የሆነውን መርዛማነት ያለው ተረፈ ምርት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ማጓጓዝ ወይም ማስወገድ በህጉ የተከለከለ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ ቆሻሻ ውሃ የተቀላቀለበትና መርዛማነት ያለው ተረፈ ምርት በአመልካች ማሳ ላይ ማፍሰሱና ይህንንም ያደረገው ያለ አካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ፍቃድ ስለመሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ፍሳሹም በአመልካች ሰብሎችና አትክልቶች ላይ ጉዳት በማድረሱ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር   300/95


አንቀጽ 4/1/ እና ፍ/ብ/ህ/ቁ/ 2035 መሰረት ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት እንዳለበት በስር ፍ/ቤት ተወስኗል፡፡ በሌላ በኩል ግን የስር ፍ/ቤት ተረፈ ምርቱ እንዲደፋ አመልካችም በመፈቀዱና እንዲሁም ተረፈ ምርቱ በእርሻ ውጤቶች ምርት ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ለማስቀረት አመልካችም ያደረገው ጥረት ባለመኖሩ እሱም ከዚህ አንፃር ላደረሰው ጉዳት አስተዋዕፆ አድርጓል በሚል ምክንያት ሊከፈለው የሚገባውን የካሳ መጠን በፍ/ብ/ህ/ቁ/2098 መሰረት ቀንሶበታል፡፡ ይሁንና ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው የፋብሪካ ተረፈ ምርት የሚደፋበትን ቦታ ለመፍቀድ በህግ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው ለአካባው ጥበቃ መስሪያ ቤት እንጂ ለግለሰቦች አይደለም፡፡ ስለሆነም ተጠሪ ተረፈ ምርቱን በማሳ ላይ የደፋሁት አመልካችን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አርሶ አደሮች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነው በማለት ያቀረበው ክርክር ከዚህ አንፃር ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፋብሪካው ተረፈ ምርት በሰብል ምርቱ ላይም ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ጉዳትም አመልካች እንደ አርሶ አደርነቱ ያውቃል ወይም ሊያውቅ ይገባ ነበር በሚል ደምዳሚ ግምት መውሰድም የሚችል አይሆንም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች የጉዳቱን ውጤት እንዴት እንዲቀንስ ማድረግ ይችል እንደነበርም በዚህ ረገድ ክርክሩ በግልጽ በተጠሪ ቀርቦና በማስረጃም ባልተረጋገጠበትና እንዲሁም አመልካችም በዚህ ረገድ ከቅን ልቦና ውጪ እንቅስቃሴ ማድረጉም ተጠሪ ባላስረዳበት ሁኔታ በፍ/ብ/ህ/ቁ/2098/1/ ድንጋጌ መሰረት እሱም ለጉዳቱ አስተዋዕፆ አድረርጓል ተብሎ በዚህ ምክንያት ሊከፈለው ከሚገባው የካሳ ክፍያ መቀነሱ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ስለሆነም የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ከዚህ አንፃር የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ሊታረም የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የሐ/ሕ/ክ/መንግስት ጠ/ፍ/ቤት በመ/ቁ/ 02554 በ 6-8-2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔና ይህንን ውሳኔ በማጽናት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በኮ/መ/ቁ/101454 በ17/10/2006 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ/348/1/ መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. በአመልካች ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠሪ ሙሉ ሐላፊነት አለበት  ብለናል፡፡ ስለሆነም በስር ፍ/ቤቶች ከተወሰነው በተጨማሪ ብር 45,840 ተጠሪ ለአመልካች እንዲከፍል ተብሏል፡፡

3. የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፣ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡


 

መ/ተ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 
 
 

Google Adsense