94511 civil procedure non-appearance of parties Dismissal of case and its effect

civil procedure

non-appearance of parties

Dismissal of case and its effect

 

 

በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 74(2) መሰረት ፍ/ቤቱ የተዘጋን የይግባኝ አቤቱታን እንደገና ስለሚያይበት አግባብ፣

 

የሰ/መ/ቁ. 94511

30/01/2007 ዓ.ም.

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሡልጣን አባተማም መኮንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

አመልካቾች፡-

1.  ወ/ሮ ብዙ ሰንበታ      ቀረቡ

2.  ወ/ሮ ባይሴ ሰንበታ

ተጠሪ፡- አቶ ታደሰ ሰንበታ - መብታቸው ታልፏል

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቱል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካቾች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ይግባኙ ሊሰማ  በተቀጠረበት ዕለት በቀጠሮው ሰዓት ለመድረስ ያልቻሉት ለጠበቃቸው የሰጡት የውክልና ስልጣን ማስረጃ በእጃቸው በመቅረቱ እና የሚመጡትም ከርቀት አካባቢ በመሆኑ ምክንያት መንገድ በመዘጋጋቱ በመሆኑ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 73 መሰረት የተዘጋው የይግባኝ መዝገብ  በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 74(2) መሰረት ተከፍቶ እንዲታይላቸው ያቀረቡት አቤቱታ  በበቂ ምክንያት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተሰጥቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት በውሳኔ የጸናው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካቾቹ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በነበራቸው ክርክር መዝገቡ በ4፡00 ሰዓት ተዘግቶ አመልካቾቹ በዚያኑ ቀን በ4፡30 ሰዓት በፍርድ ቤቱ የደረሱ መሆናቸውን እና በሰዓቱ ለመድረስ ያልቻሉትም በመንገድ ስራ ምክንያት መንገድ በመዘጋጋቱ መሆኑን ገልጸው በሚከራከሩበት ሁኔታ አመልካቾቹ ያቀረቡት  ምክንያት በቂ ምክንያት የሚባል አይደለም በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የአመልካቾቹን አቤቱታ ውድቅ የማድረጋቸውን አግባብነት "በቀዳሚው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረው በቂ ሆኖ በሚገመት እክል ምክንያት መሆኑን ፍርድ ቤቱ የተረዳው እንደሆነ" በሚል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 74(2) ስር ከተመለከተው ሐረግ ይዘት እና ተፈጻሚነት አንጻር ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ መልስ እንዲሰጡ የተላከላቸውን መጥሪያ ፈርመው ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው በስርዓቱ መሰረት በመረጋገጡ የመከራከር መብታቸው እንዲታለፍ ተደርጓል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ


የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት የአሁኖቹ አመልካቾች ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ይግባኝ ሳቢያ የግራ ቀኙን የይግባኝ ክርክር ለመስማት ለ18/03/2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ በ3፡00 ሰዓት ተይዞ በነበረው ቀጠሮ በይግባኝ ባዮቹ በኩል የቀረበ ሰው ባለመኖሩ ተጠሪው ያቀረቡትን ክርክር በመቀበል ፍርድ ቤቱ መዝገቡን በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 73 መሰረት የዘጋው መሆኑ፣አመልካቾቹ በዚሁ ዕለት ከጠዋቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ቀርበው በሰዓቱ በቀጠሮ ሊገኙ ያልቻሉት ለጠበቃቸው የሰጡት የውክልና ስልጣን ማስረጃ በእጃቸው በመቅረቱ፣የሚመጡትም ራቅ ካለ አካባቢ በመሆኑ እና አዲስ አበባ ከተማ ከገቡ በኃላም ፍርድ ቤቱ የሚገኝበትን አካባቢ እና የታክሲ መያዣ ቦታውን በትክክል ባለማወቃቸው መሆኑንበመግለጽ መዝገቡ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 74(2) መሰረት ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው በጽሁፍ የጠየቁ መሆኑ በክርክሩ የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች ሲሆኑ ፍርድ ቤቱ በአቤቱታቸው ላይ የሌላኛውን ተከራካሪ ወገን አስተያየት ከተቀበለ በኃላ መዝገቡ ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል አመልካቾቹ ያቀረቡትን ጥያቄ ሳይቀበል የቀረው ይዘቱ ከላይ የተመለከተው በአመልካቾቹ በኩል የቀረበው ምክንያት በቂ ሊባል የሚችል አይደለም በማለት ነው፡፡

በመሰረቱ በአንድ ነገር ክስ ያቀረበ ሰው ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ እና ተከሳሹ ቀርቦ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉም ሆነ በከፊል ያመነ እንደሆነ ከሳሹ በሌለበትም ቢሆን ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በሙሉ ወይም በከፊል ላመነው ጉዳይ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚችል እና ከሳሹ የካደ እንደሆነ ግን መዝገቡን በመዝጋት እንደሚያሰናብተው በፍትሐብሄር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 73 ላይ የተመለከተ ሲሆን ይህ ድንጋጌ በይግባኝ ክርክር ጉዳዮች ላይ ጭምር ተፈፃሚነት ያለው መሆኑም በቁጥር 32(2) ድንጋጌ ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል በቀነ ቀጠሮው ሳይቀርብ የቀረበትን ምክንያት በመግለጽ ይግባኝ ባዩ መዝገቡ በተዘጋ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መዝገቡ ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል ጥያቄውን ለፍርድ ቤቱ ሊያቀርብ የሚችል ስለመሆኑ እና ይግባኝ ባዩ በቀዳሚው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረው በቂ ሆኖ በሚገመት እክል ምክንያት መሆኑን ፍርድ ቤቱ የተረዳው እንደሆነ ስለኪሳራው እና ስለ ማናቸውም ወጪ አከፋፈል ተስማሚ መስሎ የታየውን ውሳኔ ከሰጠ በኃላ የተዘጋው መዝገብ እንደገና ተከፍቶ ነገሩ እንዲቀጥል ትዕዛዝ መስጠት የሚችል ስለመሆኑ በቁጥር 74(2) ተደንግጓል፡፡እንደሚታየው ይህ ድንጋጌ ይግባኝ ባዩ በቀነ ቀጠሮው ሳይቀርብ የቀረበት ምክንያት በቂ ሆኖ የሚገመት እክል መሆን እንደሚገባው ከመግለጽ ውጪ በቂ ሆኖ በሚገመት እክል ውስጥ የሚካተቱት ሁኔታዎች ምን ምን እንደሆኑ የሚጠቁመው ነገር የለም፡፡ይህም በዚህ ረገድ የሚቀርብላቸውን አቤቱታ ከድንጋጌው ይዘት እና ዓላማ አንጻር መርምሮ ተገቢውን ዳኝነት የመስጠት ኃላፊነት የፍርድ ቤቶች መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

በተያዘው ጉዳይ አመልካቾቹ ጉዳዩ እንዲንቀሳቀስላቸው አቤቱታ ያቀረቡት መዝገቡ በተዘጋ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ እና ለጠበቃቸው የውክልና ስልጣን የሰጡትም ቀጠሮው ከመድረሱ ከስምንት ቀናት በፊት በ10/03/2005 ዓ.ም. በወልመራ ወረዳ ፍትሕ ጽ/ቤት በኩል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡አመልካቾቹ ለጠበቃቸው የሰጡት የውክልና ስልጣን ማስረጃም በእጃቸው የቀረ መሆኑን በመግለጽ የተከራከሩ ሲሆን በአንጻሩ የውክልና ስልጣን ማስረጃው አስቀድሞ ለጠበቃቸው ተሰጥቶ የነበረ ስለመሆኑ በተጠሪው በኩል የቀረበ ክርክር እና ማስረጃ የለም፡፡የስር ፍርድ ቤቶች አመልካቾቹ ያቀረቡት ምክንያት በቂ ሊባል የሚችል አይደለም ከማለት ውጪ በቂ ተደርጎ ሊወሰድ ያልቻለው በምን ምክንያት እንደሆነ በውሳኔአቸው ላይ በግልጽ አላሰፈሩም፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚሰጥ ውሳኔ ደግሞ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 182(1) ስር


በአስገዳጅነት የተቀመጠውን የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት የተከተለ ባለመሆኑ ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡ ይልቁንም አመልካቾቹ ጉዳዩ እንዲንቀሳቀስላቸው አቤቱታ ያቀረቡት መዝገቡ በተዘጋ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ ሲታይ ጉዳያቸውን በአግባቡ በመከታተል ላይ የነበሩ መሆኑን እና በሰዓቱ በቀጠሮው ሳይገኙ የቀሩትም በቂ ሆኖ በሚገመት እክል ምክንያት መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል በመሆኑ አመልካቾቹ መዝገቡ ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል ያቀረቡት አቤቱታ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 74(2) መሰረት ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው ይገባ እንደነበረ ከክርክሩ አጠቃላይ ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡ሲጠቃለል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 73 መሰረት የተዘጋው የይግባኝ መዝገብ  በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 74(2) መሰረት ተከፍቶ እንዲታይላቸው አመልካቾቹ ያቀረቡት አቤቱታ በበቂ ምክንያት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተሰጥቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ቸሎት በውሳኔ የጸናው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

1. የተዘጋው የይግባኝ መዝገብ ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል አመልካቾቹ ያቀረቡት አቤቱታ በበቂ ምክንያት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 141122 በ09/04/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 158692 በ13/01/2006 ዓ.ም. በውሳኔ የጸናው ትዕዛዝ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. አመልካቾቹ በሰዓቱ በቀጠሮው ሳይገኙ የቀሩት በቂ ሆኖ በሚገመት እክል ምክንያት መሆኑን መገንዘብ የተቻለ በመሆኑ መዝገቡ ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል ያቀረቡት አቤቱታ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 74(2) መሰረት ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባው ነው በማለት ወስነናል፡፡

3. መዝገቡን አንቀሳቅሶ ክርክሩን ቀጥሎ በመስማት ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዲመለስ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 341(1) መሰረት ወስነናል፡፡

4. በዚሁ መሰረት መፈጸም ያስችለው ዘንድ የውሳኔው ግልባጭ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይላክ፡፡

5.  ቁጥሩ 141122 የሆነው መዝገብ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይመለስ፡፡

6.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ አመልካቾች የራሳቸውን ይቻሉ፡፡

7.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት:: ሃ/ወ