102061 Bankruptcy law/ Priority of creditors/ employees

አንድ የንግድ ድርጅት ሲከስር የዕዳ ክፍያን በተመለከተ የድርጅቱን ንብረቶች በመያዣነት ከያዛቸው ባንክ ይልቅ የከሰረው ድርጅት ሰራተኞች የቀዳሚነት መብት ያላቸው ስለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 167 አዋጅ ቁጥር 97/1990 እንደተሻሻለ

የሰ/መ/ቁ. 102061

የካቲት 06 ቀን 2007 ዓ/ም


አመልካች፡- የከሰረው ሆላንድ ካር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠበቃ ግርማ አለሙ ቀረቡ ተጠሪ፡- ዘመን ባንክ /አ.ማ/ ነገረ ፈጅ አቶ አዳም ሰገድ በላይ - ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የመዝገብ ቁጥር 140316 ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ   ቁጥር

101131 ግንቦት 28 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የእግድ ትእዛዝ መነሳትን የሚመለከት ነው፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 200820 ተጠሪ የከሰረው የሆላንድ ካር ኃ/የተ/የግል ማህበር ንብረት ታግዶ እንዲቆይ የሰጠውን ትእዛዝ እንዲያነሳለት ጥያቄ አቅርቦ የስር ፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ የሚነሳበት ህጋዊ ምክንያት የለም በማለት ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ ነው፡፡ አመልካች የስር ፍ/ቤት የሰጠው የእግድ ትእዛዝ ሲነሳና በመያዣነት የያዝኳቸውን ንብረቶች በአዋጅ ቁጥር 97/1990 እንደተሻሻለው በተሰጠኝ ስልጣን መሠረት ንብረቶቹን በሀራጅ ለመሸጥ ለብድሩ መክፈያነት ላውል ይገባል በማለት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የስር ፍ/ቤት የዕግድ ትእዛዝ ተነስቶ ተጠሪ በመያዣነት የያዘውን ንብረት በአዋጅ ቁጥር 97/1990 በአዋጅ ቁጥር 216/1992 እንደተሻሻለው በተደነገገው መሰረት ንብረቶቹን በሀራጅ ሽጦ ለዕዳው መክፈያ ሊያደርግ ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ስ/ስ/ህግ ቁ. 337 መሰረት ሰርዞታል፡፡

2. አመልካች ሰኔ 9 ቀን 2006 ዓ/ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ አዋጅ ቁጥር 97/1990 እና አዋጅ ቁጥር 216/1992 ስለመክሰር የሚደነግግ ድንጋጌዎች የሉትም፡፡ በመክሰር ጉዳይ ተፈጻሚነት ሊኖረው የሚገባው የንግድ ህጉ ነው፡፡ የከሰረው ድርጅት ንብረት በንግድ ህጉ መሰረት እንዲጣራና እንዲሸጥ መደረጉ፣ የሁሉንም ገንዘብ ጠያቂዎች መብትና ጥቅም የሚያስከብርና ተጠሪም በመያዣው ላይ አለኝ የሚለውን መብት የማያሳጣው በመሆኑ በተናጠል ንብረት ለመሸጥ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ባለዕዳው  የተጠሪ


እዳ ከመክፈሉ በፊት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊከፈሉ የሚገባ የሰራተኞች ደመወዝ ሌሎች ክፍያዎችና የመንግስት ግብር በአግባቡ ተጣርቶ ባልተለየበት ሁኔታ፣ ተጠሪ መያዥያ በተናጠል እንዲሸጥ ያቀረበውን ጥያቄ መፍቀድ የህጉን ዓላማ የማያሳካ በመያዥያ ያልተያዙ የባለ እዳውን ንብረቶች ለብክነት የሚዳርግና ጥበቃው ከፍተኛ ወጪ እንዲያስወጣ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ እግዱ እንዲነሳ የተሰጠው ውሳኔ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት አመልክቷል፡፡

3.  ተጠሪ ነሀሴ 27 ቀን 2006 ዓ/ም በተፃፈ መልስ አዋጅ ቁጥር 97/1990 እና አዋጅ ቁጥር

216/1990 አንድ የንግድ ድርጅት ሳይከስርም ሆነ መክሰሩ በፍርድ ከተረጋገጠ በኃላ ባንኮች ብድር ሲያበድሩ በመያዣነት የያዙትን ንብረት በሀራጅ ሽጠው የዕዳው መክፈያ እንዲያደርጉ ታስበው የታወጁ ህጎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ተጠሪ ለከሰረው ሆላንድ ካር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ገንዘብ ሲያበድር በመያዣነት የያዘውን የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት በሀራጅ ለመሸጥ ያቀረበውን ጥያቄ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት ትእዛዝ ስህተት የለበትም የሰራተኞች ደመወዝና የመንግስት ግብርን በተመለከተ ተጠሪ በሀራጅ ንብረቱን ሲሸጥ በራሱ የሚከፍላቸውና የሚፈጽማቸው ግዴታዎች በመሆናቸው አመልካች መከራከሪያ አድርጎ ማቅረቡ የህግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች ተጠሪ በመያዥያነት ይዥዋለሁ የሚለውን ፋብሪካ ህንጻና ማሽነሪዎች በተናጥል ከሸጠ፣ ያልተገጣጠሙ መኪናዎችን ገጣጥሞ ለመሸጥና ለእዳው መክፈያ ለማድረግ የማያስችል ነው፡፡  የሰራተኞቹን የቀዳሚነት መብትና የመንግስትን ግብር በቀዳሚነት የመክፈል ግዴታ ለመወጣት የማያስችል በመሆኑ የዕግድ ትእዛዝ ጸንቶ ሊቆይ ይገባል በማለት መስከረም 30 ቀን 2007 ዓ/ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4. ከስር የክርክር አመጣጥና በዚህ ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ያቀረቡት የጹሁፍ ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የከሰረው ሆላንድ ካር መኪና መገጣጠሚያ ድርጅት የሚንቀሳቀስ ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዳይሸጥ እንዳይለወጥና ለሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ የስር ፍ/ቤት የሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቶ ተጠሪ በተናጥል በመያዥያ የያዘውን የፋብሪካ ህንፃና ማሽነሪ በሀራጅ እንዲሽጥ የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5. ጉዳዩን እንደመረመርነው ባንኮች ያበደሩት የብድር ገንዘብ በወቅቱ  ሳይከፈላቸው በሚቀርበት ጊዜ በመያዥነት የያዙትን ንብረት በሀራጅ በመሸጥ ብድራቸውን እንዲከፈል ለማድረግ የሚያስችላቸው ስልጣንና ስርዓት በአዋጅ ቁጥር 90/1997 በአዋጅ ቁጥር 216/1998 እንደተሻሻለ በአዋጅ ህግ አውጭው ደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል አንድ የንግድ ድርጅት መክሰሩ በፍርድ ተረጋግጦ ከተወሰነ በኃላ ከከሰረው የንግድ ድርጅት ገንዘብ የመጠየቅየቀዳሚነት መብት ያላቸው አበዳሪዎች እና ሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች ጥያቄ ሊስተናገድ የሚችልበት ዝርዝር አሰራር በንግድ ህጉ በአምስተኛው መፅሐፍ በዝርዝር ተደንግጓል፡፡

6. በያዝነው ጉዳይ አመልካችንና ተጠሪ የሚከራከሩበት በጉዳዩ ተፈፃሚነት  ሊሰጠው የሚገባው አዋጅ ቁ.97/1990 እንደተሻሻለ መሆን ይገባል? ወይስ በንግድ ህጉ አምስተኛው መጽሐፍ የተደነገጉ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ሊሆን ይገባዋል የሚለውን  መከራከሪያ በማንሳት ነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ፍ/ቤት የሰጠው የእግድ ትእዛዝ እንዲነሳ ውሳኔ የሰጠው አዋጅ ቁጥር 97/1990 እና አዋጅ ቁጥር 216/1992 ከንግድ ህጉ


አምስተኛ መጽሀፍ ከተደነገጉት ድንጋጌዎች በኃላ የወጡ ስለሆነ ተፈፃሚነትና ገዥነት አላቸው በማለት ነው፡፡ አመልካች የሚከራከረው ከአዋጅ ቁጥር 97/1990 እና አዋጅ ቁጥር 216/1992 ስለመክሰር የሚመለከት ድንጋጌ የላቸውም የከሰረ የንግድ ድርጅት ንብረት ስለሚሸጥበትና የቀዳሚነት መብት ላላቸው ለሌሎች የገንዘብ ጠያቄዎች የሚከፍልበትን ስርዓት የሚደነግጉ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘው የንግድህጉ አምስተኛው መጽሀፍ በመሆኑ፣ በዚህ ጉዳይ ተፈፃሚነት ሊኖራቸው የሚገባው የንግድ ህጉ ልዩ ድንጋጌዎች ናቸው በማለት ነው፡፡ ይህም ተጠሪ በኃላ የወጣው ህግ በፊት ከወጣው ህግ ላይ የበላይነትና ተፈፃሚነት አለው የሚለውን የህግ አተረጓጎም መርህ መሰረት በማድረግ የሚከራከር መሆኑን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል አመልካች ልዩ የህግ ድንጋጌዎች በጠቅላላ የህግ ድንጋጌዎች ላይ የበላይነትና ተፈጻሚነት አላቸው የሚለውን የህግ አተረጓጎም መሰረት በማድረግ የሚከራከር መሆኑን ተረድተናል፡፡

7. በእኛ በኩል በዚህ መዝገብ አመልካችና ተጠሪ ለሚከራከሩበት ጉዳይ ተፈጻሚነት ያለው አዋጅ ቁጥር 97/1990 እንደተሻሻለ መሆን ይገባዋል ወይስ የንግድ ህጉ አምስተኛው መጽሀፍ የሚለው ምርጫ ከመምረጥና አመልካችና ተጠሪ ከጠቀሳቸው የአተረጓጎም መርሆች በላይ የሆኑ በርካታ ሁኔታዎቹን በመመርመር እና መመዘን የሚጠየቅ ሆኖ አግኝተነዋል ይኸውም ተጠሪ በተናጥል የከሰረውን የሆላንድ ካር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ህንጻና ማሽነሪዎች በሀራጅ እንድሸጥ ቢደረግ የከሰረው የሆላንድ ካር ንብረት ተሸጦ በሚገኘው ገንዘብ ላይ ከተጠሪ በፊት የቀዳሚነት መብት ያላቸውን የሰራተኞችና የመንግስት የግብር ዕዳ ለማጣራትና ለመክፈል የማያስችል መሆኑን አለመሆናቸውን የከሰረው ድርጅት ንብረት ጠባቂና መርማሪ ዳኛ ተጣርቶ እንዲሸጥ መደረጉ ተጠሪ በመያዣነት በያዘው ንብረት ላይ ያለውን ልዩና የቀዳሚነት መብት የሚያሳጣ መሆኑን ወይስ አለመሆኑን እንደዚሁም የከሰረው ድርጅት ንብረት በንብረት ጠባቂና መርማሪ ዳኛ በኩል ተጣርቶ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በፍርድ ቤት ፈቃድና ትዕዛዝ መሰረት እንዲሸጥ መደረጉ የቀዳሚነት መብት የሌላቸውን ገንዘብ ጠያቂዎች መብትና ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማስከበርና ዕዳቸው እንዲከፈላቸው ለማድረግ የሚያስችል ነው ወይስ አይደለም? የሚሉትን ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መንገድ ሊታይ የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

8. ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ተጠሪ በመያዣነት የያዘውን የፋብሪካ ህንጻና የመኪና መገጣጠሚያ ማሽነሪ በተናጥል የሀራጅ ማስታወቂያ አውጥቶ እንዲሸጥ ቢደርግ የከሰረው ድርጅት ሰራተኞች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 167 የተሰጣቸውን የቀዳሚነት መብት በተሟላ ሁኔታ ለማጣራትና የሰራተኞች ጥያቄ ከተጠሪ በፊት ተከፋይ እንዲሆን በማድረግ የሚያስችል አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 97/1990 በተናጠል የሚያከናውነው የሀራጅ ሽያጭ፣ መንግስት ከከሰረው ሆላንድ ካር መኪና መገጣጠሚያ ድርጅት የሚጠይቀውን ትክክለኛ የግብር ዕዳ በተሟላ ሁኔታ ለማጣራትና ለመወሰን እንደዚሁም ከድርጅቱ ሰራተኞች ቀጥሎ ከተጠሪ በፊት መንግስት ያለውን የቀዳሚነት የግብር እዳ           የመጠየቅ   መብት   የሚያረጋግጥ   አይደለም፡፡   ከዚህ  በተጨማሪ  ተጠሪ በተናጥል የሚያከናውነው የሀራጅ ሽያጭ ለሌሎች ገንዘብ ጠያቄዎች እዳ መክፈያ ሊሆኑ የሚችሉ ያልተገጣጠሙ መኪናዎች እና ሌሎች ንብረቶች ባለበት ሁኔታ በመጠበቅ ሽጦ የሌሎች ገንዘብ ጠያቄዎቹን ዕዳ ለመክፈል የማያስችል መሆኑን ተጠሪ በመያዣነት ያልያዛቸውን የከሰረው ሆላንድ ካር ንብረቶች ለማጓጓዝና ለማስቀመጥ ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅና የሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች መብትና ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ግራ ቀኙ ካቀረቡት ክርክር ተረድተናል፡፡


9. በአንጻሩ ተጠሪ በመያዣነት የያዘው የፋብሪካ  ህንጻና  ማሽነሪዎች  ከሌሎች የከሰረው ሆላንድ ካር ንብረት ጋር ተጣርተው እንዲሸጡ ቢደረግ አመልካች በመያዣነት ይዟቸው የነበሩት ንብረቶች ተሸጠው በሚገኘው ገንዘብ ላይ ያለውን የቀዳሚነት መብት የማያሳጣው መሆኑን ከንግድ ህጉ አንቀጽ 104 እና ሌሎች ተከታይ ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሂደቱ ከንብረት ጠባቂና መርማሪ ዳኛ በላይ የሆኑ ጉዳዮች ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት እየታዩ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ እንደሆነ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 989 እና አንቀጽ 990 ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከላይ በዝርዝር በገለጽናቸው ምክንያቶች የማጣራትና የሽያጭ ሂደቱ፣ ተጠሪ በመያዣነት የያዘው የፋብሪካ ህንጻና የመኪና መገጣጠሚያ ማሽነሪ በተናጠል ይሆን ከሌሎች የከሰረው የሆላንድ ካር ንብረቶች ጋር በአንድ ላይ የሚጣራበት የሚከናወነበትንና በመጀመሪያ ከተጠሪ በፊት የቀዳሚነት መብት ያላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ጥያቄና የመንግስት የግብር ዕዳ ተከፍለው የተጠሪ ቀዳሚነት መብት ተጠብቆ መያዣው ተሽጦ የተገኘው ገንዘብ እንዲከፈለው መደረጉ ከተጠሪ በፊት የቀዳሚነት መብት ያላቸውን ገንዘብ ጠያቂዎች የተጠሪንና የሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች መብትና ጥቅም የሚያስከብርበመሆኑ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚ ችሎት አዋጅ ቁጥር 97/1990 በንግድ ህጉ አምስተኛ መጽሀፍ በኃላ የታወጀ ነው በሚል ምክንያት የዕግድ ትእዛዝ እንዲነሳ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ትእዛዝ ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪ በመያዣነት በያዛቸው የፋብሪካ ህንፃና የመኪና መገጣጠሚያ ማሽነሪዎች በአዋጅ ቁጥር 97/1990 ለመሸጥና ለሌላ ሰው ለማስተላለፍ የስር ፍ/ቤት የሰጠው የእግድ ትእዛዝ እንዲነሳለትያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ወስነናል፡፡ ንብረቶቹ እንዲከበሩየስር ፍ/ቤት የሰጠው ትእዛዝ ጸንቷል፡፡

3. ተጠሪ በመያዣው ላይ ያለው መብት እንዲከበር የከሰረው ሆላንድ ካር ሂሳብ ተጣርቶ ንብረቶቹ ተሽጠው በመያዣው ላይ ያለው የቀዳሚነት መብት እንዲከበርለንብረት ጠባቂ ለመርማሪ ዳኛና ስልጣን ላለው ፍ/ቤት በህግ አግባብ የማቅረብ መብቱን ይህ ውሳኔ የሚገድበው አይደለም ብለናል፡፡

4. ጉዳዩ የተጠሪ የመያዣያ መብት ያለበት በመሆኑ በተቀላጠፈ መንገድና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈጸም ይገባል ብለናል ፡፡

5. በዚህ ፍርድ ቤት የወጡትን ውጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::