99689 higher education/ award of diploma

አንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ላስተማራቸው ተማሪዎች ጊዜያዊ ዲፕሎማ ከሠጠ በኋላ ዋናው ዲፕሎማ ሳይሠጣቸው የማስተማር ፈቃዱ ቢነጠቅ እንኳ ፈቃዱን ተነጥቄያለሁ፣  ዋናውን ዲፕሎማ ልሰጥ አልችልም የማለት መብት የሌለው ስለመሆኑ፣

አዋጅ ቁጥር 650/2001፣ ደንብ ቁጥር 199/2003

 

የሰ/መ/ቁ. 99689

 

ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡-ዶ/ር መኮንን ንዋይ የአዲስ አበባ ዴንታል ሳይንስና ኮሌጅ ባለቤትና   ዲን   - ጠበቃ ግርማ ኃይሌ ቀረቡ

 

 

ተጠሪ፡- 1. መንግስቱ ጋሞ

2. አቶ እንዳለ አለማየሁ

3. አቶ ኢሳያስ አበራ

4. አቶካሊድ አባስ

5.ወ/ሮ መሰረት መላኩ              ሌሎች አልቀረቡም

6. አቶ አዲስአለም አለማየሁ

7. አቶ ታዬ አዱኛ……….ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ ኦርጂናል ዲፕሎማ ይሰጠኝ ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡የተጠሪዎች የክስ ይዘትም፡-አመልካች በ1999 ዓ/ም አዲስ አበባ ዴንታል ሳይንስ ኮሌጅውስጥ ለማስተማር ተቀብሎ ለሶስት አመታት የጥርስ ህክምና ትምህርት አስተምሮ በ2002 ዓ/ም ካስመረቀ በኋላ ትራንስክርቢትና ጊዚያዊ ዲፕሎማ የሰጣቸው ቢሆንም ኦርጂናል ዲፕሎማውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን ገልጸው ይህንኑ  ማስረጃ እንዲሰጧቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም ተጠሪዎች ትምህርቱን ጨርሰው ጊዜያዊ ዲፕሎማ መውሰዳቸውንአምነው ዋናውን ዲፕሎማ ለመስጠት ኮሌጁ ዝግጅት ላይ እንዳለ የመንግስት ክልከላና የፈቃድ ስረዛ በማጋጠሙ የተነሳ ማህተምም ሆነ ፊርማ የሚፈርም ባለስልጣን ባለመኖሩ ለተጠሪዎች ኦርጂናል ዲፕሎማ እንዳልተሰጠና በፍርድ ቤት ቢወሰንም ሊፈጸም የማይችል መሆኑን ገልጸው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማና ተገቢ ነው ባለው መንገድ ሁሉ ከሚመለከተው አካል ስለ ጉዳዩ አጣርቶ የተጠሪዎችን ኦርጂናል ዲፕሎማ አመልካች ሊሰጥ የማይችልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ ማስረጃውን አመልካች  ለተጠሪዎች  ሊሰጥ  ይገባል  ሲል  ወስኗል፡፡በዚህ  ውሳኔ  የአሁኑ  አመልካች ቅር


በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አፅንቶታል፡፡የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካቸ የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም በስር ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን የክርክር ነጥቦችን የሚያሳይ ሁኖ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊሻር ይገባል በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪዎች ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የክርክሩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንጻር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪዎች በአመልካች ባለቤትነትና በሚታወቀውና አመልካቹ በዲንነት ያስተዳድሩት ኮሌጅ ውስጥ ተመዝግበው በተገቢው መንገድ ትምህርታቸውን መከታተላቸውና መጨረሳቸው ተረጋግጦ ትራንስክርቢትና ጊዜያዊ ዲፕሎማ በአመልካቹ የተሰጣቸው መሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከረ ከመሆኑም በላይ ኮሌጁ በመንግስት ክልከላና ፈቃድ ስርዛ ምክንያት ስራውን ያቆመ ቢሆንም ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ላጠናቀቁት ተማሪዎች ዋናውን ዲፕሎማ እንዳይሰጥ የሚከለክል መመሪያ የሌለ መሆኑና ኮሌጁ ዲፕሎማውን የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጂንሲ በቁጥር ኤ./4015/ተስጥመ/12/67 በቀን 17/10/2005 ዓ/ም ለስር ፍርድ ቤት በጻፈው ደብዳቤ መረጋገጡን ነው፡፡በመሆኑም ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካች ኮሌጅ  በመንግስት ስልጠና ለመስጠት መከልከሉና ፈቃድ መሰረዝ ከዚህ የመንግስት እርምጃ በፊት ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው የጨረሱ ተማሪዎች ኦርጂናል ዲፕሎማ እንዳያገኙ የማያደርግ መሆኑን ከሚመለከተው አካል ምላሽ ተሰጥቷቸው በሚገባ አረጋግጠዋል፡፡አመልካች ማህተም የሌለው ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ካለመረጋገጡም በላይ ማህተም ያለመኖሩ ወይም ቀድሞ ለተጠናቀቀ የትምህርት ስልጠና በፊርማ አረጋግጦ ማስረጃ ለመስጠት በወቅቱ የነበረው ኃላፊ ያለመኖሩ ተፈፃሚነትባላቸው ሕጎች መሰረት ኦርጂናል ዲፕሎማውን ለተጠሪዎች  ላለመስጠት የሚያስችለው መሆኑን አላስረዳም፡፡ይልቁንም አግባብነት ያለው አካል ኦርጂናል ዲፕሎማውን ማግኘት መብታቸው መሆኑን፣ማስረጃው መስጠት ደግሞ የአመልካች ግዴታ መሆኑን በሚያስገነዝብ መልኩ አረጋግጧል፡፡በመሆኑም አመልካች  ከአዋጅ  ቁጥር 650/2001፣ደንብ ቁጥር 199/2003 እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጎች የተጣለበትን ኃላፊነት ያልተወጣ መሆኑ በአንጻሩ ተጠሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ለመማር  የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልተውና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ስርዓቱን በተከተለ አግባብ ስልጠናውን ተከታትለው የጨረሱ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ ይህንኑ የሚያረጋግጥላቸውን ማስረጃ ከአመልካች የማግኘት መብት ያላቸው ስለሆነ የበታች ፍርድ ቤቶች ፍሬ ነገሩን በአግባቡ አጣርተውና አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ተጠሪዎች ኦርጂናሉ ዲፕሎማ ሊሰጣቸው ይገባል በማለት መወሰናቸው ሕጋዊ ነው ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡


 

 

 ው ሣኔ

 

1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 81505 ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር143008 መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡

2. አመልካች ለተጠሪዎች ኦርጂናል ዲፕሎማ የመስጠት ግዴታ አለበት ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች አለበት

 

 

የ/ባ