99743 execution of judgment/ counter-claim/ set-off

የፍርድ ባለመብት ፍርዱን እንዲፈፀምለት ሲጠይቅ የፍርድ ባለዕዳው የፍርድ ባለመብቱ ተነፃፃሪ የሆነ ግዴታውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ይሠጥልኝ በማለት ጥያቄ ለማቅረብ የሚችለው በአንድ ፍርድ ቤት ውስጥ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች የፍርድ ባለመብት መሆናቸው ተረጋግጦ ውሳኔ ተሰጥቶበት እንደሆነ ብቻ ስለመሆኑ፡-

 

አንድ የፍርድ ባለእዳ እንደ ፍርዱ እንዲፈጽም ሲጠየቅ ፍርድ ያላረፈበትን ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ በአፈፃፃም ሊከራከር ሥላለመቻሉ፣

 

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 398፣ 378

የ/ሰ/መ/ቁ 99743

 

መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ንብ ኢንሹራንስ (አ.ማ) - ነገረ ፈጅ ተስፋሁን ሽብሩ - ቀረቡ ተጠሪ፡- ራዲካል ኢንጅነሪንግ ኃላ/የተ/የግል ማህበር - አልቀረበም፡፡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 147896 መጋቢት 22 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው የአፈፃፀም ትዕዛዝና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 99409 ሚያዝያ 3 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ ፍርድ አፈፃፀም የሚመለከት ነው፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው የአፈፃፀም ክስ ነው፡፡ ተጠሪ አመልካች ወጪና ኪሣራን ጨምሮ አመልካች በፍርድ የተወሰነበትን ብር 589880/ አምስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሰማኒያ ብር / እንዲከፍል የአፈፃፀም ትዕዛዝ ይሰጥልኝ በማለት ለሥር ፍርድ ቤት የአፈፃፀም ክስ አቅርቧል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት አመልካች በፍርዱ መሠረት የማይፈፀምበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቶ አመልካች የፍርድ   ባለመብት

/ተጠሪ/ የሚከናወን ቅሪት ለመሸጥ የሚያስፈልግ ሊብሬና ውክልና እንዲሰጠን ብንጠይቀው ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፍርድ የተወሰነብኝን ገንዘብ አልከፈልኩም የሚል  መከራከሪያ አቅርቧል፡፡ የስር ፍርድ ቤት አመልካች ያቀረበው መከራከሪያ በፍርድ የተወሰነበትን ገንዘብ ባለመክፈል በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም በማለት አመልካች እንደ ፍርዱ እንዲፈፅም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡

2. አመልካች በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ሚያዝያ 6 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ አቅርቧል፡፡ አመልካች በመኪናው ላይ የደረሰውን ጠቅላላ ጉዳት ብር 450,000 በመክፈል ተሽከርካሪውን የማስቀረት መብት በመድን ውሉ ውስጥ ተሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ተጠሪ በፍርድ የተወሰነበትን   ገንዘብ   እንዲከፈለው   ጉዳት   የደረሰበትን   ተሽከርካሪ    ለአመልካች


እንዲያስረክብ፣ጉዳት የደረሰበትን ተሽከርካሪ አስጠግኖ ለመሸጥ፣ለመለወጥ የሚያስችል ውክልና የመኪና ሊብሬና ተሽከርካሪ ከዕዳና እገዳ እንዲሁም ከግብር ዕዳ ነፃ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃና ክሊራንስ ለአመልካች የመስጠት ግዴታውን መወጣት  ይገባዋል፡፡ ተጠሪ ይህንን ሳይፈፅም ገንዘቡን ክፈል መባሉ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

3. ተጠሪ ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ መልስ፣ፍርድ የሚፈፀመው የተሰጠው ፍርድ ይዘት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አመልካች በአፈፃፀም ወቅት ካነሳቸው መከራከሪያዎች በዋናው ጉዳይ ስንከራከር አንስቶ ፍርድ አላረፈበትም ይህ ከሆነ አመልካች በፍርድ የተወሰነበትን እንድፈጽም ስጠይቅ በፍርድ ተረጋግጦ ውሣኔ ያላረፈበትን ቅድመ ሁኔታ በመደርደር ፍርዱን ለመፈፀም እንቢተኛ መሆኑ የሕግ መሠረት ያለው አይደለም፡፡ ስለዚህ የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ችሎት የሰጡት ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች ግንቦት 27 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት የአፈፃፀም ትዕዛዝ ተገቢ  ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5.  ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች በተጠሪ ብር 589,850 / አምስት መቶ ሰማኒያ  ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሃምሳ ብር/ ለተጠሪ እንድከፍል በፍርድ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑንና የፍርድ ባለመብቱ ተጠሪ በፍርድ የተወሰነለትን ገንዘብ አመልካች እንዲከፍለውና ፍርዱ እንዲፈጽምለት ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን ግራቀኙ በሥርና በሰበር ደረጃ ካቀረቡት ክርክር ተረድተናል፡፡ አመልካች በፍርዱ መሠረት ፍርድ የማይፈፀምበትን ቀርቦ እንዲያስረዳ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 383 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት እንዲያቀርብ የተጠሪው አመልካች ከተጠሪ ጋር ባለው የመድን ውል መሠረት በመኪናው ላይ የደረሰው ጉዳት ሰባ አምስት ፐርሰንት ከሆነ የመኪናውን በመድን ውሉ የተመለከተውን ሙሉ ዋጋ ከፍሎ የመረከብ መብት እንዳለው ገልፆ፣ገንዘቡን ለመክፈል በመጀመሪያ የመኪናውን  ቅሪት፣ተጠሪ ሊያስረክበኝ ይገባል፡፡ የመኪናውን ሊብሬና ውክልና ሊሰጠኝ ይገባል የሚል መቃወሚያ አቅርቧል፡፡ አመልካች በመድን ውሉና አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት አለኝ የሚለው የመኪናውን ቅሪትና ሌሎች መኪናውን ለማስጠገንና ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች የመረከብ መብት፣የፍታብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 30 እና የፍታብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215(2) መሠረት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ በማቅረብ በፍርድ ያስወሰነ ስለመሆኑ ያቀረበው የፍርድ ቤት ውሣኔ የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አመልካች በአፈፃፀም ወቅት መከራከሪያ አድርጎ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የክስ መከላከያ አድርጎ አቅርቦ፣ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት በጭብጥነት ይዞ፣ውሣኔ የሰጠባቸውና ፍርድ ያረፈባቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ የፍርድ ቤት ውሣኔ አላቀረበም፡፡

6. ፍርድ የሚፈፀመው በፍርድ ውስጥ በተገለፀው ውሳኔ መሰረት መሆኑን የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 378 ንዑስ አንቀጽ 1 ደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፍርድ ባለመብት ፍርዱን እንዲፈፀምለት ሲጠይቅ፣የፍርድ ባለዕዳው፣የፍርድ ባለመብቱ ተነጻጻሪ የሆነ ግዴታውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ይስጥልኝ በማለት ጥያቄ ለማቅረብ የሚችለው በአንድ ፍርድ ውስጥ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች የፍርድ ባለመብት መሆናቸው ተረጋግጦ ውሳኔ ተሰጥቶበት እንደሆነ መሆኑን ከፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር  398  ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በያዝነው ጉዳይ አመልካች ከመድን ውሉና አግባብነት ካላቸው የሕግ  ድንጋጌዎች


ተጠሪ ሊፈፅምልኝ የሚገባው ግዴታ አለ በማለት በአፈፃፀም መከራከሪያ አድርጎ ያቀረባቸው ነጥቦች በዋናው ጉዳይ መከራከሪያ ሆነው ቀርበው ፍርድ የተሰጠባቸው አይደሉም ይህ ከሆነ አመልካች ከተጠሪ የሚጠይቀው መብት ካለ፣በሕግ አግባብ ክስ አቅርቦ በፍርድ ተረጋግጦ እንድንወስንለት ከሚጠይቅ በስተቀር፣ፍርድ ያላረፈበትን ቅድመ ሁኔታ በአፈፃፀም ክርክር በመደርደር ፍርዱን የመፈፀም ግዴታ የለብኝም በማለት ያቀረበው  መቃወሚያ የሕግ መሠረት ያለው አይደለም፡፡ በመሆኑም አመልካች ፍርዱን የማይፈፅምበት በቂ አሳማኝና ህጋዊ ምክንያት አላቀረበም በማለት የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት የአፈፃፀም ትዕዛዝ ከላይ የጠቀስናቸውን የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ያደረገና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

 ው ሳኔ

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ትዕዛዝ ፀንቷል፡፡

2. በዚህ ፍርድ ቤት ሚያዚያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከተው ይፃፍ፡፡

3.  በዚህ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙ ያወጡትን ወጭ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

 


መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡


 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡