98263 Execution of judgment/ agreement between judgment creditor and debtor/ registration of agreement

በፍርድ ውሣኔ በተሰጠበት ጉዳይ አፈፃፀምን ለማስቀረት በፍርድ ባለመብት እና በፍርድ ባለ ዕዳ የሚደረግ የእርቅ ውል በፍርድ ቤት ቀርቦ  ካልፀደቀ በቀር አፈፃፀምን ሊያስቀር የሚችል ስላለመሆኑ፣

የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 276፣277

የሰ/መ/ቁ. 98263 ጥር ዐ6 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- ወ/ሮ እናናይቱ ይሳ - አልቀረቡም

 

ተጠሪ፡- ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ወራሽ መክያ ከንዙ - ቀረቡ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 34482 የካቲት 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 356ዐ8 የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት የደረሰበት መደምደሚያ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በአፈፃፀም ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ አፈፃፀሙ በመጀመሪያ የታየው በፎገራ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪ የአፈፃፀም ከሳሽ አመልካች የአፈፃፀም ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ ተጠሪ አመልካች በመዝገብ ቁጥር 11394 በተሰጠው ፍርድ መሰረት በመሬቱ ላይ የገነባቸውን ንብረት በማንሳት ቦታውን እንድታስረከብ ይወሰንልኝ የሚል የአፈፃፀም ክስ ለወረዳው ፍርድ ቤት በማቅረቧ ነው፡፡ አመልካች በተከሳሽነት ቀርባ፤ የፍርድ ባለመብት ከነበረችው ከሟች ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም የዕርቅ ውል ተዋውለናል፡፡ በዕርቁም የፍርድ ባለዕዳ ለፍርድ ባለ መብት ብር 6ዐዐዐ

/ስድስት ሺ ብር/ ለመከፈልና ቦታውንና ቤቱን ባለበት ሁኔታ ይዥ ለመቆየት ተስማምተናል፡፡ የዕርቅ ውሉን ለማስመዝገብ መጋቢት 27 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ፍርድ ቤት ማመልከቻ ይዘን ቀርበን፣ በቀጠሮው ቀን ቅረቡ ተብሎ የተመለስን ሲሆን ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን የቀጠሮው ቀን ከመድረሱ በፊት በመሞታቸው ምክንያት የዕርቅ ውሉ፣ በፍርድ ቤት ሣይመዘገብ ቀርቷል፡፡ ጉዳዩ በዕርቅ ያለቀ ስለሆነ ቤቱን አፍርሼ ቦታውን እንዳስረክብ አልገደድም በማለት ተከራክራለች፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤት የፍርድ ባለዕዳ መከራከሪያ ያደረገችው የዕርቅ ውል በመዝገቡ ያልተያያዘና ያልተመዘገበ በመሆኑ ፍርድን ባለመፈፀም መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም በማለት አመልካች አዋሳኝ ምልክቱ በተገለፀው    ቦታ


ላይ የሰራችውን ቤት አፍርሳ ለፍርድ ባለመብት ታስረክብ ማለት ጥቅምት 7 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የአፈፃፀም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

2. አመልካች በዚህ የአፈፃፀም ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ለደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርባለች፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የፍርድ ባለመብትና የፍርድ ባለዕዳ የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በፍርድ ቤት የተሰጠዉን ፍርድ ቀሪ በማድረግ የተስማሙ በመሆኑ ተጠሪ እንደ ፍርዱ እንዲፈፀምላት ያቀረበችውን ጥያቄ በመቀበል የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠው የአፈፃፀም ትዕዛዝ ተገቢነት የለውም በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን የአፈፃፀም ትዕዛዝ ሽሮታል፡፡ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ተጠሪ ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርባለች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የዕርቅ ውሉ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277 መሰረት በፍርድ ቤት ተመርምሮ ለሕግና ለሞራል ተቃራኒ አለመሆኑ ያልተመዘገበና በዕርቅ ውሉ ሰበብ፣ የመሬት ሽያጭ የሚመስል ስምምነት የተደረገ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ተፈፃሚነት የሌለው ነው በማለት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን የአፈፃፀም ትዕዛዝ አፅንቷል፡፡ አመልካች የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርባለች፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

3. አመልካች ለዚህ ሰበር ችሎት የካቲት 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ ያቀረበችው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡትን ውሳኔ ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች ቤት አፍርሽ ቦታ እንዳስረክብ በወረዳው ፍርድ ቤት ተወስኖብኝ ይግባኝ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቤ ጉዳዩ በቀጠሮ ላይ እያለ ከፍርድ ባለመብት ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም የዕርቅ ውል አድርገናል፡፡ ቦታው የከተማ ቦታ በመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዕርቅ ውሉ የመሬት ሽያጭ የሚመስል ነው በማለት የዕርቅ ውሉን ውድቅ ማድረጉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የዕርቅ ውሉ ይፍረስልኝ የሚል ክስ ሣይቀርብ ዕርቅ ውሉን ማፍረስ ተገቢ አይደለም፡፡ አመልካች በርካታ ገንዘብ በማውጣት የገነባሁት 56 ዚንጎ ቆርቆሮ ቤት እንዳፈርስ የተሰጠው ውሳኔ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ተከራክራለች፡፡ ተጠሪ በበኩሏ፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አመልካች ከአውራሽ ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን  ጋር ያደረገችው የዕርቅ ውል የለም፡፡ የቀረበው ሰነድ በሀሰት የተዘጋጀ የዕርቅ ሰነድ ነው፡፡ አውራሽ ወዳና ፈቅዳ የፈረመችው ሰነድ አይደለም፡፡ ዕርቁ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት ያልተደረገና ህጋዊ ውጤት የሌለው ነው በማለት መልስ ሰጥታለች፡፡ አመልካች ግንቦት 4 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርባለች፡፡

4. ከስር የክርክሩ አመጣጥና ለዚህ ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት አመልካች የአፈፃፀም ክስ የቀረበበትን ውሳኔ ገዥነትና አስገዳጅነት ለማስቀረት ከተጠሪ አውራሽ ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ጋር የዕርቅ ስምምነት አድርገናል በማለት ያቀረበችውን ክርክር ውድቅ ያደረጉት በሕግ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5. ጉዳዩን እንደመረመርነው በወረዳው ፍርድ ቤት የተጠሪ አውራሽ ወ/ሮ ሀሲና ሁሴንና አመልካች ተከራክረው፣ አመልካች በአከራካሪው ቦታ ላይ የሰራችውን ቤት በማፍረስ ቦታውን እንድታስረክብ ፍርድ የተሰጠበት መሆኑን ግራ ቀኙ አይካካዱም፡፡ የወረዳው ፍርድ


ቤት በሰጠው ፍርድ የተጠሪ አውራሽ የፍርድ ባለመብት፣ አመልካች የፍርድ ባለዕዳ ሆነዋል፡፡ ተጠሪ ለፎገራ ወረዳ ፍርድ ቤት ለዚህ ክርክር መነሻ የሆነውን የአፈፃፀም ክስ ያቀረበችው አውራl የፍርድ ባለመብት የሆነችበት ፍርድ እንዲፈፀምላት ነው፡፡ አመልካች ተጠሪ ያቀረበችው የአፈፃፀም ክስ የማትፈፅምበት ምክንያት እንዳላት መከራከሪያ አድርጋ ያስቀረበችው፣ የወረዳው ፍርድ ቤት ቤቱን አፍርሽ ቦታውን እንዳስረክብ የሰጠውን ውሳኔ ተፈፃሚነትና አስገዳጅነት ለማስቀረት የፍርድ ባለመብት ከነበረቸው ሟች ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 የዕርቅ ስምምነት አድርገናል በማለት ነው፡፡

6. አመልካች ከተጠሪ አውራሽ ጋር አድርገነዋል በማለት ያቀረበችውን የዕርቅ ስምምነት ሰነድ በተጠሪ በኩል የታመነ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ተጠሪ የዕርቅ ስምምነት የተደረገ መሆኑን ያሳያል በማለት አመልካች ያቀረበችው ሰነድ፣ በሀሰት ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡ በሰነድ ላይ ያለው ፊርማ የአውራሽ የወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ፊርማ አይደለም፡፡ ሰነዱ በፍርድ ቤት ያልተመዘገበና ያልፀደቀ በመሆኑ ህጋዊ ውጤት የለውም በማለት የተከራከረች መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔና ግራ ቀኙ ለዚህ በሰበር ችሎት ካቀረቡት ክርክር ተረድተናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ተጠሪ ሰነዱን ለመቃወም የአውራሽ ፊርማ አይደለም ብላ መከሪከሯ በቂ እንደሚሆን ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2ዐዐ7 ንዑስ አንቀፅ 2 ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ከተጠሪ አውራሽ ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ባደረገችው የዕርቅ ውል የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈፃሚ እንዳይሆን የዕርቅ ስምምነት አድርጋለች የሚል ውሳኔ የሰጠው፣ አመልካች የዕርቅ ውል ነው ካለ ባቀረበችው ሰነድ ላይ ተጠሪ ያቀረበችውን መቃወሚያ በመቀበል፣ ፊርማው ለምርመራ ወይም በሌላ መንገድ እንዲጣራ በማድረግና የሰነዱን ትክክለኛነት በማስረጃ በማረጋገጥ እንዳልሆነና የአመልካችን መከራከሪያ ዕውነት ነው ብሎ በመቀበል እንደሆነ ከውሳኔው ተረድተናል፡፡ ይህም ተጠሪ የዕርቅ ውል ነው ተብሎ የቀረበውን ሰነድና በሰነዱ ላይ ያለውን ፊርማ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2ዐዐ7 ንዑስ አንቀፅ 2 በተደነገገው መሰረት ክዳ ተከራክራ እያለ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰነዱን ትክክለኛነት በፍትሐብሔርሕግ ቁጥር 2ዐዐ8 በተደነገገው መሰረት ተገቢው ማጣራትና ምርመራ ሳያደርግ፣ ሰነዱን ትክክለኛ የዕርቅ ውል ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ የደረሰ መሆኑን ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተረድተናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2ዐዐ7 ንዑስ አንቀፅ 2 እና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2ዐዐ8 ድንጋጌዎች መሰረት የሚጥስና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

7. ከላይ የገለፅነዉ ተጠሪ የሰነዱን ትክክለኛነትና ፊርማውን በመካድ ያቀረበችው ክርክር የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሣያጣራና በማስረጃ ሳያረጋግጥ ማለፋ የመጀመሪያው የሕግ ስህተት ሆኖ፣ አመልካች ከተጠሪ ወራሽ ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም አድርጌዋለሁ በማለት ያቀረበችው የዕርቅ ውል፣ ትክክለኛና ሟች የፈረመችበት ሰነድ ነው ቢባል ተጠሪ ያቀረበችውን የአፈፃፀም ክስ ቀሪ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ወይም አለመሆኑ መመርመር ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ አመልካች ከተጠሪ አውራሽ ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም የዕርቅ ስምምነት ፈፅመናል በማለት ያቀረበችው ሰነድ አመልካች በወረዳው ፍርድ ቤት የተፈረደባት ፍርድ አፈፃፀም ቀሪ ለማድረግና በምትኩ ብር    6ዐዐዐ

/ስድስት ሺህ ብር/ ለተጠሪ አውራሽ  ለመክፈል፣  የተስማሙ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሰነዱ አመልካች የተጠሪ ወራሽ ተከራክረው የተሰጠን ፍርድ ህጋዊ ውጤትና ተፈፃሚነት ለማስቀረት የተደረገ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዕርቅ ስምምነት ሰነድ


የተፈረመው በወቅቱ አመልካች ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርባ በክርክር ላይ በነበረበት ወቅት እንደሆነ አመልካች ለስር ፍርድ ቤትና በዚህ ሰበር ችሎት ካቀረበችው የፅሁፍ ክርክር ተረድተናል፡፡

8. ይህም አመልካች ከተጠሪ አውራሽ ጋር አድርጌዋለሁ የምትለው የዕርቅ  ውል በፍርድ የተሰጠ ውሳኔ ተፈፃሚነት ቀሪ የማድረግ ዓላማና ይዘት ያለው ከሆነ፣ በሕግ ፊት ውጤት እንዲኖረው ምን ምን መስፈርቶችን አሟልቶ መገኘት አለበት የሚለውን ነጥብ እንድንመረምር የሚያስገድድ ነው፡፡ የዕርቅ ውሉ በፍርድ ያለቀ ጉዳይ ተፈፃሚ እንዳይሆን የማድረግ ይዘት እና አላማ ካለው፣ ከሌሎች የዕርቅ ስምምነቶች ለየት ባለ መንገድ የተደረገና ይዘቱ ተመርምሮ የፀደቀ መሆን እንዳለበት ከፍትሐብሔር ስነ ስርዓት  ሕግ ቁጥር 274 እስከ ፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 279 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች መሰረታዊ ዓላማና ይዘት በመመርመር ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተለይም የዕርቅ ውሉ በፍርድ የተወሰነ ውሳኔ አፈፃፀም ቀሪ ለማድረግ የተደረገ በሆነ ጊዜ፣ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 276 እና በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 277 ንዑስ አንቀፅ 1 ድንጋጌ የተቀመጡ መስፈርቶች በጥብቅ የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በፍርድ የተወሰነ ጉዳይ ተፈፃሚነት ለማስቀረት የሚደረግ የዕርቅ ውል፣ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 መሰረት ተደርጐና በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277/1/ መሰረት ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ቀርቦ ካልፀደቀ ህጋዊ ውጤትና ተፈፃሚነት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በፍርድ የተወሰነ ውሳኔ ተፈፃሚነት ለማስቀረት የፍርድ ባለመብትና  የፍርድ ባለዕዳ ያደረጉት ስምምነት በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 በሚደነግገው መሰረት ተዘጋጅቶ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277/1/ መሰረት ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ባልፀደቀበት ሁኔታ ፍርድ ቤቶች እየተቀበሉ የሚያከራክሩና ህጋዊ ውጤት የሚሰጡ ከሆነ፣ በዳኝነት አካሉ ክስ ቀርቦባቸው ተከራክረው በፍርድ ውሳኔ የተሰጠባቸው ሰዎች፣ የፍርዱን ውሳኔ ተፈፃሚነት ለማስቀረት ከፍርድ ቤት ዕውቅና ውጭ የዕርቅ ውል ተዋውለናል የሚል መከራከሪያ እያቀረቡ የፍርድ አፈፃፀም ስርዓቱን እንዲያጓትቱና እንዲያስተጓጉሉ ሰፊ ዕድል፣ የሚፈጥር አጠቃላይ የስነ ስርዓት ሕጉን አላማ የሚፃረርና ጉዳዮች በፍርድ ከተቋጩ በኋላ እንደገና ማቆሚያ የሌለው ክርክር እንዲቀርብላቸው የሚያደርግ ይሆናል፡፡

9. በመሆኑም በፍርድ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ አፈፃፀም ለማስቀረት የፍርድ ባለመብት እና የፍርድ ባለዕዳ የሚያደርጉት የዕርቅ ውል፣ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 እና በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277/1/ የተደነገገውን ጥብቅ መስፈርት የሚያሟላ ባልሆነበት ጊዜ፣ ህጋዊ ውጤትና ተፈፃሚነት እንደማይኖረው የሚያረጋግጥ፣ ጥብቅ የሆነ የሕግ አተረጓጐም መርህ መከተል የፍርድ አፈፃፀም ስርዓቱን ውጤታማና ቀልጣፋ በሆነ ሁኔታ እንዲከናወን ለማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች ከተጠሪ አውራሽ ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም አድርጌዋለሁ በማለት ያቀረበችው የዕርቅ ውል ሰነድ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 እና በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277/1/ መሰረት ፍርድ ቤት ቀርቦ ያልፀደቀ በመሆኑ ከጅምሩ ተጠሪ ያቀረበችውን የአፈፃፀም ክስ ለማቋረጥ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንን ሰነድ በመቀበል አፈፃፀሙ እንዲቋረጥ የሰጠው የሕግ ትርጉምና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዕርቅ ሰነዱን አፈፃፀሙን ለማቋረጥ ሊቀርብ የሚችል ማስረጃ አድርጎ ከወሰደ በኋላ፣ የሰነዱን ይዘት መርምሮ ሰነዱ በይዘቱ የመሬት ሽያጭ የሚመስል በመሆኑ ለህግ ተቃራኒ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ ከላይ በዝርዝር የገለፅነውን የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 እና የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ


ቁጥር 277/1/ በፍርድ የተወሰነ ውሳኔ ተፈፃሚነት ቀሪ በማድረግ በሚደረጉ የእርቅ ስምምነት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ጥብቅ ተፈፃሚነት ያላገናዘበና መሰረታዊ የሕግ አተረጓጎም ስህተት የተፈፀመባቸው ናቸው፡፡

10. ከላይ በዝርዝር በገለፅናቸው ምክንያቶች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ መሻራቸው ተገቢነት ያለው ቢሆንም፣ በፍርድ የተወሰነ ውሳኔ ተፈፃሚነት ለማሰቀረት የፍርድ ባለመብትና የፍርድ ባለዕዳ ከፍተኛ ዕውቅና ማረጋገጫ ሣይሰጠው አድርገነዋል የሚሉት የዕርቅ ውል ህጋዊ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው አድርገው የሰጡት የሕግ ትርጉም፣ ስህተት ያለበት በመሆኑ፣ ምክንያቱን ለውጠንና አሻሽለን፣ በውጤት ደረጃ መሰረታዊ  የህግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

1. የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡት ውሳኔ በውጤት ደረጃ ፀንቷል፡፡

2. አመልካች ከተጠሪ አውራሽ ወ/ሮ ሀሲና ሁሴን ጋር የካቲት 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ተዋውለናል በማለት ያቀረበችው የዕርቅ ስምምነት ሰነድ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 እና የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277/1/ መሰረት በፍርድ ቤት ያልፀደቀ በመሆኑ ተጠሪ ያቀረበችውን የአፈፃፀም ክስ ለማሰቀረት ህጋዊ ተፈፃሚነትና ውጤት የለውም በማለት ወሰነናል፡፡

3. በዚህ ፍርድ ቤት መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡ የዕግድ ትዕዛዝ የተነሳ መሆኑ ለሚመለከተው ክፍል ይፃፍ፡፡

4. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ፡፡

 

 

ብ/ይ