90722 execution of judgement/ immovable property of judgment debtor/ absence of title deed

በፍርድ ባለዕዳው ሥም የሚታወቅ ቤት ቤቱ በህጋዊ  መንገድ የተገነባና የፍርድ ባለዕዳው እስከሆነ ድረስ ካርታና ፕላን የሌለው መሆኑ እና ለሌላ ሶስተኛ ወገን ተሠጥቷል መባሉ ስጦታው ህጋዊ በሆነ መንገድ እስካልተከናወነ ድረስ ቤቱ ለፍርድ  አፈፃፀም እንዳይውል ሊያደረግው የሚችል ስላለመሆኑ፣

የፍ/ሕ/ቁ 276፣277

የሰ/መ/ቁ. 90722

 

ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

 

አልማው ወሌ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ወ/ሮ መዓዛ  መዝገቡ -  VC ሰላልሰራ መቅረባቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ተጠሪ፡- አቶ መሰለ ገላነው - VC ሰላልሰራ መቅረባቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት በስር የፍርድ ባለመብት (በአሁኑ ተጠሪ) እና በስር የፍርድ ባለዕዳ (የአሁኗ አመልካች የቀድሞ ባለቤት በአቶ ሰመረ ኃይሉ) መካከል በነበረው የአፈጻጸም ክርክር የአማራ /ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በስር ሁለቱ ፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮ በፍርድ ባለዕዳው ስም የሚታወቀው ቤት ካርታ እና ፕላን የሌለው መሆኑ እና የቀድሞ ተጋቢዎች የፍቺ ውሳኔን ተከትሎ ቤቱን ለልጆቻችን ሰጥተናል በማለት በንብረት ክርክሩ መዝገብ ላይ ማስመዝገባቸው ቤቱ ለፍርድ አፈጻጸም እንዳይውል ሊያደርገው የሚችል ባለመሆኑ አፈጻጸሙ በቤቱ ላይ ሊቀጥል ይገባል በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

የጉዳዩን አመጣጥ በተመለከተ በስረ ነገሩ ክርክር ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በስረ ነገሩ 1ኛ ተከሳሽ እና የአሁኗ አመልካች ባለቤት ከነበሩት ከአቶ ሠመረ ኃይሉ ጋር በ22/06/2000 ዓ.ም. ጋር አቋቁመውት በነበረው ውል መሰረት ባለመፈጸማቸው አቶ ሠመረ ኃይሉ ጉዳት አድርሰውብኛል በማለት ብር 270,926.50 እንዲከፍሏቸው በሁለቱ ተጋቢዎች ላይ በባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ መመስረታቸውን፣2ኛ ተከሳሽ የነበሩት የአሁኗ አመልካች በሰጡት መልስ በውሉ ተዋዋይ ወገን ባለመሆናቸው በውሉ አለመፈጸም ሳቢያ በከሳሽ ላይ ደርሷል ለተባለው ጉዳት በኃላፊነት ሊጠየቁ የሚችሉበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን በምክንያትነት በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ ከክሱ እንዲያሰናብታቸው መጠየቃቸውን፣ፍርድ ቤቱም ጥያቄቸውን ተቀብሎ 1ኛ ተከሳሽ ለክሱ ኃላፊ የሚደረጉ ከሆነ 2ኛ ተከሳሽ ተጠያቂ ሊደረጉ የሚችሉበት ሁኔታ መኖር አለመኖሩ በአፈጻጸም ጊዜ ከሚታይ በስተቀር 2ኛ ተከሳሽ በስረ ነገሩ ሊከሰሱ የሚችሉበት አግባብ የለም ሲል 2ኛ ተከሳሽን አሰናብቶ 1ኛ ተከሳሽን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ ብር 198,371.40 ለከሳሽ እንዲከፍሉ በመዝገብ ቁጥር 17174 በ30/04/2002 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱን፣ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የተሰጠላቸውን ፍርድ ለማስፈጸም በዚያው የስረ ነገሩ መዝገብ የአፈጻጸም ማመልከቻ ባቀረቡበት  ጊዜ  ከስረ  ነገሩ  ክስ  የተሰናበቱትን  አመልካች  በ2ኛ  የፍ/ባለዕዳነት   አካተው


ማቅረባቸውን፣አመልካቿ በስረ ነገሩ ኃላፊ ተደርጌ የተሰጠብኝ ፍርድ ሳይኖር የፍ/ባለመብቱ በፍ/ባለዕዳነት ሰይሞ ያቀረበኝ አላግባብ በመሆኑ ከአፈጻጸሙ ልሰናበት ይገባል የሚል ክርክር በማቅረባቸው ፍ/ቤቱ ይህንኑ ተቀብሎ አመልካች ከአፈጻጸም ክስ ነፃ ናቸው በማለት በ05/05/2003 ዓ.ም. በተሰጠ ትዕዛዝ ያሰናበታቸው መሆኑን፣ከዚህ በኃላ የፍ/ባለመብቱ ለአፈጻጸሙ ይውል ዘንድ በባህር ዳር ከተማ በቀበሌ 16 የሚገኝ የፍ/ባለዕዳውን ቤት መምራታቸውን፣ቤቱ ተከብሮ እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ለሰጠው ትዕዛዝም የክፍሉ ቀበሌ ቤቱ የሚታወቀው በፍርድ ባለዕዳው በአቶ ሰመረ ኃይሉ ስም ቢሆንም የተገነባው በጊዜያዊ ይዞታ ላይ በመሆኑ እና ካርታ እና ፕላን የሌለው በመሆኑ ምክንያት ለማስከበር  እንደሚቸገር በ20/11/2002 በተጻፈ ደብዳቤ መግለጹን፣የቤቱ ሁኔታ ተጣርቶ እንዲቀርብለት እና ተከብሮ እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ በድጋሚ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረትም የፍርድ ባለዕዳው እና  ባለቤታቸው ፍቺ በፈጸሙበት ጊዜ ቤቱ ለልጆቻቸው እንዲሆን ለፍርድ ቤት አቅርበው ማስወሰናቸውን በመግለጽ የክፍሉ ቀበሌ በ15/06/2003 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ምላሽ መስጠቱን፣ፍርድ ቤቱም ከቀበሌው የተገለጹለትን ሁለት ምክንያቶች መሰረት በማድረግ የፍርድ ባለመብቱ ሌላ ንብረት አፈላልገው ማቅረብ የሚችሉ ከመሆኑ ውጪ አፈጻጸሙ በቤቱ ላይ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ አለመኖሩን ገልጾ በ21/06/2003 ዓ.ም.የአፈጻጸም መዝገቡን በብይን መዝጋቱን  የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

በብይኑ ቅር በመሰኘት የአሁኑ ተጠሪ ባቀረቡት ይግባኝ ሳቢያ የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የወረዳውን ፍርድ ቤት ብይን ያጸናው ሲሆን ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ቤቱ የሚታወቀው በፍርድ ባለዕዳው ስም መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ካርታ እና ፕላን የሌለው መሆኑ ለፍርድ አፈጻጸም እንዳይውል ከማድረግ የማይከለክል መሆኑን እና የቀድሞ ተጋቢዎች ቤቱን ለልጆቻቸው ሰጥተዋል መባሉን በተመለከተም ስጦታው ሕጉ እንደሚያዘው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2443 በተመለከተው ስርዓት መሰረት የተከናወነ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ተጋቢዎቹ በፍቺ ውሳኔ መዝገቡ ላይ ቤቱ ለልጆቻቸው እንዲሆን መስማማታቸው እና ስምምነታቸው የፍቺ እና የንብረት ውሳኔውን ባጸደቀው ፍርድ ቤት ተቀባይነት ማግኘቱ ቤቱ በሕጉ አግባብ በስጦታ ተላልፏል የሚያሰኝ አለመሆኑን እና ከፍቺ ጋር የተያያዘ ክርክር የቀረበለት ፍርድ ቤት ፍቺን እና የፍቺ ውጤቶችን ከመወሰን በቀር ስጦታን የማጽደቅ ስልጣን የሌለው መሆኑን ገልጾ የሁለቱን የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመሻር አፈጻጸሙ በቤቱ ላይ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡትም ይዘቱ ከላይ የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ የተደረገው በግራ ቀኙ መካከል ክርክር ሲካሄድበት ከነበረው ቁጥሩ 90723 ከሆነው መዝገብ ጋር ተጣምሮ እንዲታይ ተብሎ ቢሆንም በሁለቱ መዝገቦች ተከራካሪ ወገኖቹ ተመሳሳይ ቢሆኑም ለክርክር የቀረቡት ጭብጦች ግን የተለያዩ መሆናቸው በመረጋገጡ ቁጥሩ 90723 በሆነው መዝገብ የቀረበው ክርክር ተነጥሎ ውሳኔ የተሰጠበት ሲሆን በዚህ መዝገብ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ግን ለአፈጻጸሙ የተያዘው ቤት የተገነባው በጊዜያዊ ይዞታ ላይ መሆኑ እና በተጨማሪም በአመልካች እና በአቶ ሰመረ ኃይሉ መካከል የነበረው ጋብቻ ፈርሷል መባሉን ተከትሎ ቤቱ ለቀድሞ ተጋቢዎች ልጆች የተሰጠ መሆኑ በተገለጸበት ሁኔታ ቤቱ ለአፈጻጸሙ ሊውል ይገባል ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ የአቤቱታውን ግልባጭ ከመዝገቡ ወስደው መልስ


እንዲሰጡበት በቪዲዮ ኮንፈረንስ በችሎት ተነግሯቸው መልስ ሳይሰጡ በመቅረታቸው የመከራከር መብታቸው እንዲታለፍ ተደርጓል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት ለአፈጻጸሙ የተያዘው ቤት በጊዜያዊ ይዞታ ላይ የተገነባ እና ካርታ እና ፕላን የሌለው ቢሆንም በሌላ በኩል ግን ተመዝግቦ የሚታወቀው በአቶ ሰመረ ኃይሉ ስም መሆኑን ጉዳዩ የሚመለከተው የአስተዳደር አካል ለወረዳው ፍርድ ቤት በጽሁፍ አረጋግጧል፡፡ በሌላ አነጋገር ቤቱ ከሚመለከተው የአስተዳደር አካል ዕውቅና ውጪ በሕገወጥ መንገድ የተገነባ ስለመሆኑ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ይልቁንም አመልካች እና በፍቺ ተለያይተዋል የተባሉት የቀድሞ ባለቤታቸው አደረጉት በተባለው እና በፍርድ ቤት በተመዘገበው የፍቺ ስምምነት  ቤቱ ለልጆቻቸው እንዲተላለፍ መስማማታቸው እና ጉዳዩ የሚመለከተው የአስተዳደር አካልም ቤቱ በቀድሞ ተጋቢዎች ስምምነት ለልጆቻቸው የተሰጠ በመሆኑ የፍርድ ቤቱን የማስከበሪያ ትዕዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገር ገልጾ አፈጻጸሙን ለያዘው ፍርድ ቤት ምላሽ መስጠቱ ካርታ እና ፕላን የሌለው ከመሆኑ ውጪ የቤቱ ሕጋዊነት ጉዳይ በአስተዳደር አካሉ ዘንድ ጥያቄ ያላስነሳ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡

ቤቱ ለቀድሞ ተጋቢዎች ልጆች ተሰጥቷል በማለት የቀረበውን ክርክር በተመለከተም አመልካች እና ፍቺ ፈጽመዋል የተባሉት የቀድሞ ባለቤታቸው የፍቺ ክርክሩን በተመለከተው ፍርድ ቤት ቤቱን ለሕጻናት ልጆቻቸው መስጠታቸውን ገልጸው የፍቺ ስምምነት ከማስመዝገባቸው ውጪ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በውሳኔው ላይ እንደገለጸው ስጦታውበሕጉ በተደነገገው ስርዓት መሰረት የተደረገ ነው የሚባል ካለመሆኑም በላይ የፍቺ ስምምነቱ በፍርድ ቤት ተመዝግቧል የተባለውም ተጠሪው ክስ ከመመስረታቸው ከአምስት ቀናት በፊት መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ የሚያመለክት በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው ክርክርም ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ አልተገኘም፡፡

ሲጠቃለል የሁለቱን የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመሻር በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. በባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 17174 በ21/06/2003 ዓ.ም. ተሰጥቶ በምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 45472 በ29/05/2004 ዓ.ም. የጸናውን ብይን በመሻር የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 20652 በ07/09/2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ፀን~ል፡፡

2. እንዲያውቁት የዚህ ውሳኔ ግልባጭለባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት፣ለምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ  ፍርድ ቤት እና  ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ይላክ፡፡

3.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

 

4. ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡