97132 evidence law/ expert opinion/ ownership of gun

ለክርክሩ መነሻ የሆነ ሽጉጥ (የጦር መሳሪያ) የንምራ ቁጥር አከራካሪ በሆነበት ወይም የመጀመሪያው ንምራ ቁጥር በሌላ ተተክቷል የሚል ክርክር በተነሳ ጊዜ በመሳሪያው ላይ ያለው ንምራ ቁጥር ኦሪጅናል ነው? ወይስ በሂደት የተተካ ቁጥር ነው? የሚለውን አግባብነት ባለው አካል ሞያዊ አስተያየት/expert opinion/ አጣርቶ መወሰን አስፈላጊ ስለመሆኑ፣

 

የሰ//.97132 መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- አቶ መሀመድ ከማል ሀምዛ ቀረቡ

 

ተጠሪዎች ፡-1ኛ የከሚሴ ከተማ ወረዳ ፖሊስ           ተወካይ አይኔ አዲስ አሰጋኸኝ ቀረቡ 2ኛ የከሚሴ ከተማ ወረዳ ሚሊሻ ጽ/ቤት

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ በኢግዚቢት ተይዞ ነበር በተባለው እስታር ማክሮቭ ሽጉጥ አመላለስ ጋር በተያያዘ የቀረበ ሲሆን በሥር የደ/ሥ/ፈ/ወረዳ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካች በተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ ውድቅ የተደረገባቸው በመሆኑ በሰበር ተጣርቶ እንዲወሰን የቀረበ ነው፡፡ አመልካች በሥር ወረዳ ፍርድ ቤት በአሁኑ ተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ አጭር ይዘት፡- ቁጥሩ 635 የሆነው እስታር ማክሮቭ ሽጉጥ ከ8 መሰል ጥይቶች ጋር ህገ ወጥ መሣሪያ ይዘሃል ተብሎ በፖሊስ ተጠይቀው መሣሪያውም በኢግዚቢት ተይዞ ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ሽጉጡ ፈቃድ ያለው የግላቸው መሆኑ ቢከራከሩም የሥር ፍርድ ቤት ሳይቀበል ጥፋተኛ ያላቸው መሆኑን፤ ለአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ በነፃ እንደተለቀቁ፣ በኢግዚቢት የተያዘው ሽጉጥ በፍትሐብሄር መጠየቅ እንደሚችሉ ሰበር ሰሚ ችሎቱ መብታቸው የጠበቀላቸው በመሆኑ፣ በኢግዚቪት ተያዘ የተባለውን ሽጉጥ ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አለመስጠቱን፤ ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ ኃላፊዎች በመሆናቸው ሽጉጡ ከመሰል ጥይቱ በዓይነት እንዲመልሱ፤ በዓይነት ማስረከብ የማይችሉ ከሆነም በድምር 33‚400 ብር እንዲከፈሉ እንዲወሰንላቸው የሚጠይቅ ነዉ፡፡

 

ተጠሪዎች በሥር ፍርድ ቤት በሰጡት መልስ ከአመልካች የተያዘው ሽጉጥ ቁጥር 635 ሳይሆን ቁጥር 165231 መሆኑን፤ ሽጉጥ የተያዘው መሃመድ ከማል የተባለው ግለሰብ ሲያስፈራሩበት የነበረ ስለመሆኑ በመግለጽ ከክሱ በነፃ እንዲሰናበቱ ማመልከታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም የግራቀኙ የቃል ክርክር እንዲሁም የተጠሪዎች የሰው ምስክሮች ካደመጠና የአመልካች የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ፖሊስ ከአመልካች የያዘው ሽጉጥ ቁጥሩ 635 የሆነ ማክሮቭ ሽጉጥ ሳይሆን ፈቃድ የሌለው ማክሮቭ ሽጉጥ ቁጥር 165231 ከሁለት መሰል ጥይቶች ጋር መሆኑን በወቅቱ ጉዳዩን ያጣራው መርማሪ ፖሊስ እና ሽጉጡን በኤግዚቢት ገቢ  ያደረገው


የከሚሴ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት የግምጃ ቤት ሠራተኛ አስረድቷል በማለት የአመልካች ክስ ውድቅ አድርጐታል፡፡ አመልካች ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እና ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይህ የሰበር ቅሬታ የቀረበውም የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት  ቀርቦ እንዲመረመር በመደረጉ ግራቀኙ የጽሑፍ ክርክር አድርጓል፡፡

አመልካች በሰበር አቤቱታቸው በመሰረታዊነት ያነሳቸው ዋና ዋና ነጥቦች፡- ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ቀን ይዘውት የነበረው ሽጉጥ ፈቃድ ያለው ነው፡፡ የንምራ ቁጥር 635 የነበረው በመፋቅ ሌላ ተለጣፊ ቁጥር ተደርጎበት በፎርጅድ ቁጥር ሌላ ባለሥልጣን የታጠቀው ስለመሆኑ፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ሽጉጥ ንምራ ቁጥሩ 635 ነው ወይስ 165231 የሚለው በፎረንሲክ የባለሙያ/expert/ ምርመራ ያልተደረገበት ስለመሆኑ፤ የሰበር ሰሚ ችሎት ንብረት የመጠየቅ መብታቸው መጠበቁ በመሆኑም በባለሙያ ምርመራ ተደርጎ ቁጥሩ መረጋገጥ እንደሚገባ ማመልከታቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ተጠሪ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረበ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ደግሞ የተያዘው ሽጉጥ 635 ሳይሆን 165231 መሆኑን የሰው ምስክር በቂ እንደሆነ የፎረሲንክ ምርመራ አግባብነት እንደሌለው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲጸና መጠየቁን የሚያመለክት ነው፡፡ የአመልካች የመልስ መልስም የሰበር አቤቱታቸው የሚያጠናክር ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት በአመልካች የቀረበው የጦር መሣሪያ ፈቃድ የመሣሪያው ዓይነት ስታር ሽጉጥ የወግ ቁጥር 635 መሆኑን የሚያመለክት፤ እንዲሁም የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 24840 ህዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ከአመልካች ተያዘ የተባለው ሽጉጥ የንምራ ቁጥር 165231 ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለመቅረቡን፤ አመልካች የንምራ ቁጥር 635 የሆነ ማክሮቭ ሽጉጥ ፈቃድ እንዳለው ማስረጃ በማቅረባቸው ምክንያት ከወንጀል ድርጊቱ በነፃ እንዲሰናበቱ በኤግዝቢትነት የተወሰደባቸው ሽጉጥ በፍትሐብሔር ክስ አቅርበው የመጠየቅ መብታቸው መጠበቁን የሚያሳይ ነው፡፡

ከሥር የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም ግራቀኙ በጽሑፍ ያደረጉት ክርክር ፤ ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

አመልካች ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ አጥብቀው የሚከራከሩት  በኢግዚቢት ተያዘ የተባለው ሽጉጥ ንምራ ቁጥር 635 እንጂ 165231 አይደለም፡፡ የንምራ ቁጥር 165231 የተባለው ፎርጅድ ቁጥር ነው፡፡ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሽጉጥ የንምራ ቁጥር 635 ይሁን 165231 በባለሙያ /expert/ ምርመራ ተደርጎበት ውጤቱ አልቀረበም የሚል ነው፡፡ ተጠሪ በአንፃሩ ከአመልካች የተያዘው ሽጉጥ ንምራ ቁጥር 165231 ስለመሆኑ በሰው ምስክሮች ተረጋግጧል የፎረንሲክ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም በማለት ተከራክሯል፡፡ የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለክርክሩ መነሻ የሆነው ንምራ ቁጥር 165231 አመልካች ይዘው ስለመገኘታቸው አልተረጋገጠም በማለት የሥር ፍርድ ቤቶች የጥፋተኝነት ውሳኔ ሽሯል፡፡ በአንፃሩ አመልካች ፈቃድ ያለው ንምራ ቁጥር 635 የሆነ ማክሮቭ ሽጉጥ እንደነበራቸው በውሳኔው አስፍሯል፡፡

የሥር ወረዳ እና ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች አመልካች ይዘውት ተገኙ የተባለው ሽጉጥ ንምራ ቁጥር 165231 ስለመሆኑ በሰው ምስክር ተረጋግጧል የሚል ነው፡፡ ይሁንና ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ይዘት መገንዘብ እንደተቻለው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ሽጉጥ ከተያዘ በኋላ በወ.መ.ሥ.ሕ.ቁ 33/4/ እና 97 መሰረት የተመዘገበ እና ከአመልካች የተያዘ ስለመሆኑም በሰነድ የተደገፈ ክርክር አልቀረበም፡፡ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቁጥር 635 እና 165231 በተለምዷዊ የዓይን ምልከታ መለየት የሚቻል ስለመሆኑ በሕጉ አግባብ የተረጋገጠ


ጉዳይ አይደለም፡፡ አመልካች ንምራ ቁጥሩ ተፍቆ ፎርጅድ ቁጥር ተለጥፎበታል በማለት ይከራከራሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በተጠሪዎች የተካደ ቢሆንም በኤግዝቪት ተያዘ በተባለው ሽጉጥ ንምራ ቁጥር 165231 ተብሎ የተመዘገበው ቁጥር በእርግጥ ኦርጅናል /ዋና/ ቁጥር ስለመሆኑ በልዩ ባለሙያ የተረጋገጠ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለክርክሩ መነሻ በሆነው ሽጉጥ ላይ የተፃፈው ቁጥር ኦርጂናል /ዋና/ መሆን ያለመሆን ደግሞ በቀላል የዓይን እይታ/ምልከታ/ የሚረጋገጥ ሳይሆን በመሣሪያ እውቀት ባላቸው የፎርንሲክ ምርመራ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሥር ፍርድ ቤቶች ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሽጉጥ ላይ የተፃፈው ቁጥር ሽጉጡ በሰራው ኩባንያ /ተቋም/ የተሰጠው ንምራ ቁጥር መሆን ያለመሆኑን በባለሙያ /expert/ ሳይረጋገጥ የአመልካች ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ግራቀኙ እያከራከረ ያለው ሽጉጥ ላይ የተፃፈው ንምራ ቁጥር 165231 በእርግጥ በእናት ኩባንያው የተሰጠው ቁጥር ነው ወይስ በጊዜ ሂደት የተተካ ቁጥር ነው? በአከራካሪው ሽጉጥ የተፃፈው ንምራ ቁጥር 635 ነው ወይስ 165231 ነው? የሚሉ መሰረታዊ ነጥቦች አግባብነት ካለው አካል በሚቀርበው ሙያዊ አስተያየት /expert opinion/ መሰረት ተደርጎ ሊወሰን የሚገባው በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ተሽሮ ጉዳዩ ደግሞ ተጣርቶ እንዲወሰን ወደ ሥር ፍ/ቤት ሊመለስ የሚገባው ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳኔ

1. በአብከመ የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር የደዋ ጤፋ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 02932/05 በ04/10/2005 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ፤ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 0101458 በ26/11/2005 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ፤ የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በጠ/ፍ/የሰ/ይ/መ/ቁ 03-06689 በ 27/03/2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል፡፡

2. የደዋ ጤፋ ወረዳ ፍርድ ቤት በፍርድ ይዘቱ እንደተገለጸው ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሽጉጥ ንምራ ቁጥር 635 ነው ወይስ 165231? ንምራ ቁጥሩ 165231 የተባለው ሽጉጥ ኦርጂናል ቁጥር ነው ወይስ በሂደት የተተካ ቁጥር ነው? የሚሉና ተዛማጅ ነጥቦች በፎረንሲክ ባለሙያዎች ተመርምሮ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ሕጋዊ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 343/1/ መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይፃፍ፡፡

3. የዚህ ፍ/ቤት ወጪና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘጋ፡፡ ወደ መ/ቤት ተመለሰ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::

 

 

ት/ጌ