በአንድ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ ለሚሰራ ሠራተኛ አሰሪው ተቋም ለሰራተኛው ለመኖሪያ የሚሆን ክፍል ከሰጠው እና ሰራተኛው በአሰሪው ተቋም ፍቃድ ተጨማሪ ግንባታ በራሱ ወጪ ከገነባ እና አሰሪው ሰራተኛው እንዲወጣ ካስገደደው አሰሪው ተቋም ሰራተኛው ለተጨማሪ ግንባታ ያወጣውን ወጪ መክፈል ያለበት ወይም ሰራተኛው ተጨማሪውን ግንባታ አፍርሶ የመውሰድ መብት ያለው ስለመሆኑ፡-
የፍ/ሕ/ቁ. 1446፣1454፣1455
የሰ/መ/ቁ. 96495 ቀን 05/06/2007 ዓ/ም
ዳኞች፡-አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል
አመልካች፡- ኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት - ነገረ ፈጅ ወይንሽት እንድሪስ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ኃይሌ ብሩ - ተወካይ ዓመተ ኃይሌ ቀረቡ
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 46873 በ30/08/2005 ዓ/ም የተሰጠው ፍርድ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት የቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በአመልካች ፈቃድ ተመስረተው ተጠሪ የገነቡት ቤት የሚኖረው ህጋዊ ውጤት የተመለከተ ነው፡፡ በስር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ ሲሆኑ የአሁኑ ተጠሪ ያቀረቡት ክስ ባጭሩ፡- በአመልካች ተቀጥረው ሲሰሩ በ1967 ዓ/ም አንድ ክፍል መኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸው በሒደት የቤተሰባቸው አባላት ቁጥር በመጨመሩ በራሳቸው ወጪ ተጨማሪ ክፍል 2 መኝታ ፤ ሳሎን ፤ 2 ክፍል ኩሽና መስራታቸው በሰሩት ቤትም ከ1975 ዓ/ም ጀምሮ ለ 30 ዓመታት ሲጠቀሙ እንደነበር አሁን ግን አመልካች ቤቱን እንዲለቁ እያስገዳዳቸው በመሆኑ ድርጊቱ እንዲቆም ወይም ቤቱን የተሰራበት አርባ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍላቸው ጠይቋል፡
የአሁኑ አመልካች በሰጠው መልስ ተጠሪ ቤቱን ያገኙት በስራ ምክንያት ነው ፤ ቤቱ የተገነባው ለህዝብ ጥቅም ሲባል የተቋቋመ በመሆኑ ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተቋቋመ ንብረት ላይ የይዞታ መብት ማቋቋም ስለማይቻል ክስ ማቅረብ አይችሉም፡፡ ቤቱም የገነቡት አመልካች እየተቃወመ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
የስር የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ማስረጃ እና ክርክር ከመረመረ በኃላ በአሰሪና ሰራተኞች ማህበር በተፈረመው የህብረት ስምምት መሰረት የተቋሙ ሰራተኛ በጡረታ ወይም በሌላ ምክንያት ከስራ ገበታው ሲገለል የተረከበው ቤት በነበረበት ሁኔታ ሊያስረክብ እንደሚያስገደድ በመጥቀስ ተጠሪ ቤቱን ለቀው ያስረክቡ፡፡ ቤቱን ለመስራት ያወጡት ወጪም አመልካች የመክፈል ግዴታ የለበትም በማለት ወስኗል፡፡
የአሁኑ ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ አቤቱታቸው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ ተጠሪ ቤቱን
የሰሩት በ1975 ዓ/ም ሲሆን የህብረት ስምምነቱ የተቋቋመው በ1989 ዓ/ም ነው፡፡ አመልካች ተጠሪ ቤቱን ሲሰሩ ምንም ተቃውሞ አላቀረቡም፡፡ ተጠሪ በተጨማሪነት ሁለት ክፍል ቤቶች መኝታ ቤት ሳሎን ኩሽና በቤት ቁጥር 420 ላይ ሲገነቡ አመልካች ምንም ያቀረበው መቃወሚያ የሌለ መሆኑን ፍርድ ቤቱ መገንዘቡን ፤ በዚሁም የተነሳ ተጠሪ ለእነዚህ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች ባለሁበት ሆነዋል፡፡ አመልካች ለተጠሪ ግምቱን ሰጥቶ ማሰናበት አሊያም ደግሞ ተጠሪ ቤቱን አፍርሰው እንዲሄዱ መብት አላቸው በማለት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔውን ሽረዋል፡፡ የአሁኑ አመልካች ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው ይግባኝ ቅሬታ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 337 ተሰርዟል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ለማስለወጥ ነው፡፡ግራ ቀኙ ከዚህ ችሎት የጽሁፍ ክርክር አድርገዋል፡፡ አመልካች በዋናነት የሚከራከረው አመልካች ድርጅት ለህዝብ ጥቅም የተቋቋመ በመሆኑ በነዚህ ይዞታዎች ላይ ግዙፍ መብት በማቋቋም ባለመብት ለመሆን እንደማይቻል በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1446፣1454 እና 1455 በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ የስር ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች እንዲሻሩ የሚያመለክት ሲሆን ተጠሪ በበኩላቸው የሰጡት መልስ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት በአመልካች ፈቃድ የገነቡት መሆኑን በድርጅቱ ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው በጡረታ ተገለው እየኖርበት እንደነበር የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚነቀፍ አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካች የሰበር አቤቱታው የሚያጠናክር የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡
ከስር የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማዛመድ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረነውም አመልካች እና ተጠሪ እያከራከረ ያለው ለመኖሪያነት ተፈቅዶ በነበረው ይዞታ ላይ ተጨማሪ ቤቶች በመሰራታቸው ተጠሪ በቤቱ ላይ ያለቸው ህጋዊ መብትና ጥቅም በአመልካች ክርክር እንደተነሳው ለህዝብ ጥቅም በተቋቋመ ድርጅት መብት ማቋቋም አይችልም የሚለው የፍ/ህ/ቁ. 1454 እና 1455 መሰረታዊ ይዘትና መንፈስ ያገናዘበ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ከአጠቃላይ የህጉ ዓላማና መንፈስ ተገናዝቦ መታየት አለበት፡፡ በስር ፍርድ ቤት የክርክር ሂደት በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠው ነገር ቢኖር ተጠሪ የአመልካች ሠራተኛ በነበሩበት ጊዜ ለመኖሪያነት በተሰጣቸው ይዞታ ላይ ተጨማሪ ክፍሎች ሲገነቡ በአመልካች በኩል የቀረበ ተቃውሞ ስለመኖሩ አልተረጋገጠም፡፡ ተጠሪ ቤቱን ሰሩት የተባለው እና በአመልካች ድርጅት እና ሠራተኞች የተፈረመው የህብረት ስምምነት ቤቱ ከተገነባ በኃላ ስለመሆኑ በአመልካች የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ ተጠሪ በሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረቡት መልስ ቤቱን በአመልካች የጽሁፍ ፈቃድ የተገነባ ስለመሆኑ የገለጹ ሲሆን አመልካች ለተጠሪ ፈቃድ እንዳልተሰጠ የመልስ መልሱ ላይ አላሰተባበለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ ለክርክሩ መነሻ በሆነው ቤት ላይ ጡረታ ከወጡ በኃላም እየኖሩበት እንደሆነ አልተካደም፡፡
አመልካች ከስር ፍርድ ቤት አንስቶ አጽንኦት በመስጠት የሚከራከረው ለህዝብ ጥቅም በተቋቋመ የመንግስት ይዞታ ላይ መብት ማቋቋም አይቻልም በሚል ነው፡፡ በእርግጥ ለህዝብ በተቋቋም መንግስት ይዞታ ላይ መብት ማቋቋም እንደማይቻል በፍ/ህ/ቁ. 1454 እና 1455 በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይሁንና የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት ፣ ዓላማና ግብ መታየት ያለበት መብቱን ባቋቋመ ግለሰብ እና መንግስት የነበረው ህጋዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ ነው፡፡ አመልካች እና ተጠሪ የስራ ውል ግንኙነት የነበራቸው ስለመሆኑ የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፤ አመልካች ለተጠሪ መኖሪያ ቤት የሰጣቸው መሆኑን ፤ በሂደት ቤተሰብ መስርተው የቤተሰብ አባላት ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ተጨማሪ ቤት እንዲገነቡ በአመልካች በጽሁፍ ፈቃድ መሰጠቱ በአመልካች አልተካደም፡፡ አመልካች እና ተጠሪ ህጋዊ ግንኙነት የነበራቸው በመሆኑ ተጠሪ
ቤቱን የገነቡት ከአመልካች ፈቃድና እውቅና ውጭ ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ህጋዊ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች የተቋቋመው መብትና ግዴታ ምንም ህጋዊ ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች እንደተገነባ ጥቅም መታየት የለበትም፡፡ ከላይ የተመለከትነው የህግ ድንጋጌም ህጋዊ ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች የተገነባ ጥቅም /መብት/ ካለ የህግ ጥበቃ የሚሰጠው መብት ማቋቋም እንደማይችሉ የሚያስገነዝበን ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ በአመልካች እና ተጠሪ መካከል የነበረው የስራ ውል ግንኙነት መሰረት በማድረግ በአመልካች ፈቃድ ተጠሪ የግል ሀብታቸው በማውጣት የገነቡትን ቤት አፍርሰው ለመውሰድ አልያም የቤቱን ግምት የመጠየቅ መብት ሊነፈጉ አይገባም፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ተጠሪ አመልካች ሳይቃወም ለገነቧቸው ተጨማሪ ቤቶች ያወጡት ወጪ ብር 45,000 (አርባ አምስት ሺህ) ይክፈሉ ወይም ደግሞ ቤቱን አፍርሰው ይውሰዱ በማለት መወሰኑ እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐብሄር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔውን ማጽናቱ ህጉን በአግባቡ ተግባራዊ አድርገዋል ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ው ሳ ኔ
1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 127167 በ12/11/2005 ዓ/ም የፌዴራል የመጀመሪ ደረጃ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 46873 በ30/08/2005 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ በመሻር የሰጠው ፍርድ ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/መ/ቁ. 93048 በ22/02/2006 ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ ፀንቷል፡፡
2. ተጠሪ አመልከች ሳይቃወም ለገነቧቸው ተጨማሪ ቤቶች ያወጡትን ወጪ ብር አርባ አምስት ሺህ /45,000.00/ ይከፈላቸው ወይም ቤቱን አፍርሰው እንዲሄዱ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡
3. የዚህ ፍ/ቤት ወጪና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ይመልስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::
ሃ/ወ