አንድ ሰው ከህግ ውጪ የገጠር እርሻ መሬት ለመውረስ የሚያስችል የወራሽነት ማስረጃ ስላወጣ ይሰረዝበት የሚል አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜ ፍ/ቤት ጭብጥ ይዞ ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ እንጂ የመሬት ክርክር ሲነሳ የሚታይ ነው ተብሎ ክሱን ውድቅ ማድረግ አግባብነት የሌለው ሥለመሆኑ፣
የአ/ብ/ክ/መንግስት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 133/98
እና ደንብ ቁጥር 51/99
የሰ/መ/ቁጥር 108539
መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል
አመልካች፡- አቶ አበባው አጥናፉ - ቀረቡ
ተጠሪዎች፡- 1. ወ/ሮ የካባ ግዛው - ወኪል ተሻገር ካሤ - ቀረበ 2. አቶ ጌቴ ግዛው - ቀረቡ
3. ወ/ሮ ምሳዬ ግዛው - የቀረበ የለም፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የገጠር እርሻ መሬት መብት በውርስ የሚተላለፍበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የጀመረው በመቄት ወረዳ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካች የአሁኑ ተጠሪዎች የሟች እማሆይ እቴ አለማየሁ የገጠር መሬት ይዞታ ሕጋዊ ወራሽ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ማስረጃ በወረዳው ፍርድ ቤት ሰኔ 21 ቀን 2004 ዓ/ም መውሰዳቸው ከክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር ህግ ውጪ ነው በማለት ተጠሪዎች የወሰዱት ማስረጃ እንዲሰረዝ መስከረም 20 ቀን 2006 ዓ/ም ባቀረቡት አቤቱታ መነሻ ነው፡፡ አመልካች ለተጠሪዎች የገጠር መሬት ይዞታ ውርስ ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲሰረዝ መሰረት ያደረጉት ምክንያት የሟች እማኋይ እቴ አለማየሁ የቤተሰብ አባልና የራሳቸው መሬት ይዞታ የሌላቸው ሁኖ እያለ ተጠሪዎች የሟቿ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች በመሆናቸው ብቻ መሬቱን ሊወርሱ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም የሚል ሲሆን ተጠሪዎች ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት መልስ የሟች ልጆች ሁነው በሕጉ አግባብ የወራሽነት ማስረጃውን መውሰዳቸውን ፣ የአሁኑ አመልካች ደግሞ የሟቿ የቤተሰብ አባል ቢሆኑም እማሆይ እቴ አለማየሁ ከነበራቸው ሁለት ቃዳ መሬት ከመሞታቸው በፊት እኩሌታውን ከፍለው ለአሁኑ አመልካች የሰጧቸውና አመልካቹ የራሳቸው የሆነ ይዞታ እያላቸው የሟቿን ድርሻ ለመውሰድ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገቢነት የለውም የሚል ነው፡፡ በዚህ መልክ ክርክር የቀረበለት የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳዳር አዋጅና ደንብ መሰረት ሳይናዘዝ የሞተ አርሶ አደር ይዞታ መብት የሚተላለፍበትን የሕግ አግባብ ዘርዝሮ ከአስቀመጠ በኋላ አመልካች መሬት ያላቸው የሟች የቤተሰብ አባል ሲሆኑ ተጠሪዎች ደግሞ መሬት ላቸው የሟች ልጆች ናቸው የሚል ምክንያት ይዞ ተጠሪዎች ይዞታውን ለመውረስ ማስረጃ መውሰዳቸው በአግባቡ ነው በማለት የአመልካችን ተቃውም ውድቅ አድርጎ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለሰሜን ወሎ
አስተዳዳር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው በፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮይዞታውን የመውረስ መብት ያላቸው የአሁኑ አመልካች እንጂ የአሁኑ ተጠሪዎች አይደሉም በማለት የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪዎች ቅር በመሰኘት ይግባኝቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪዎች ያወጡት የወራሽነት ማስረጃ በደንብ ቁጥር 51/99 አንቀጽ 11/7/ሐ// መሰረት መሬት ያላቸው የሟች ልጆች መሆናቸውን የሚገልጽ ነዉ ፣ የአሁኑ አመልካች ያወጣው የወራሽነት ማስረጃ በደንቡ አንቀጽ 11/7/ለ// መሰረት የሟች የቤተሰብ አባል መሆኑን የሚገልጽ ነው የሚል ምክንያት ጠቅሶና ማስረጃው የሟችን መሬት ለመውረስ ያላቸውን ደረጃ የሚገልጽ ገላጭ የሆነ ማስረጃ ነው ፣ በመሬቱ ላይ ያላቸውን የመውረስ ቅደም ተከተል ደግሞ በመሬቱ ላይ ክርክር በተደረገ ጊዜ የሚታይ እንጂ የማስረጃ ይሰረዝልኝ ጊዜ የሚታይ አይደለም ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ውጤቱን አጽንቶታል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት የሠበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪዎች የሟች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ በመሆናቸው ብቻ በመሬቱ ላይ ያገኙት የወራሽነት ማስረጃ ሊሰረዝ አይገባም ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እነዲታይ በመደረጉ 1ኛ እና 3ኛተጠሪዎች መጥሪያ ደርሷቸው ሊቀርቡ ባለመቻላቸው በጹሑፍ መልስ የመሰጠት መብታቸው የታለፈ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ ግን ቀርበው ከአመልካች ጋር በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን በሥር በሚገኙት በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ያደረጉትን ክርክር እና በእነዚህ ፍርድ ቤቶች የተሰጡትን ዳኝነት አግባብነት ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ካላቸው ህጎች ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡
እንደተመለከትነው ክርክር ያስነሳው የእርሻ መሬት ይዞታ ሟች እማሆይ እቴ አለማየሁ ኑዛዜ ሳይተው ከዚህ አለም በመለየታቸው ምክንያት አመልካችና ተጠሪዎች የክልሉን የገጠር መሬት አስተዳደር ሕግ መሰረት አድርገው የውርስ ይገባናል ጥያቄ አቅርበው የወረዳው ፍርድ ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕጉ ያለውን የገጠር መሬት የውርስ ቅደም ተከተል መሰረት አድርገው ተገቢ ነው ያሉትን ዳኝነት የሰጡ ቢሆንም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን የቅደም ተከተሉን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው በመሬት ላይ ክርክር በተደረገ ጊዜ የሚታይ ነው በሚል ያለፈው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ይሄው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ተገቢነት ነው፡፡
በአንድ ክርክር ዳኝነት ሊሰጥ የሚገባው የክርክሩን አርእስት በማየት ሳይሆን ዝርዝር ይዘቱን በአግባቡ በመለየትና ተገቢነት ያለውን ህግ መሰረት በማድረግ መሆኑን የክርክር አመራርና የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓት የሚያስገነዝበን ጉዳይ ነው፡፡ ክርክር የሚመራው ደግሞ በሕጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ነው፡፡ የፍትሐብሔር ክርክር የሚመራው በ1958 ዓ/ም በወጣው የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግና ተፈጻሚነት ባላቸው ሌሎች የክልል ሕግጋት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ መሰረታዊ ዓላማም ክርክሮች በአነስተኛ ወጪ፣ ጉልበት እና በአጭር ጊዜ ታይተው ፍትሓዊና ትክክለኛ ዳኝነት ለመስጠት ማስቻል መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ክርክር ይህንኑ የክርክር አመራር መሰረታዊ አላማ በሚያሳካ መልኩ ሊመራ ይገባዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የተያዘውን ጉዳይ ስንመለከተውም አመልካች በወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳዳር ሕግ ከተዘረጋው ስርዓት ውጪ ተጠሪዎች
የሟቿን ይዞታ ለመውረስ የሚያስችላቸው ማስረጃ መሰጠቱን ገልጸውና ይዞታውን በህጉ አግባብ መውረስ የሚችሉት አመልካች መሆኑን ጠቅሰው ለተጠሪዎች የተሰጣቸው ማስረጃ እንዲሰረዝላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪዎች ደግሞ የአከራካሪው ይዞታ ህጋዊ ወራሾች መሆን የሚገባቸው ተጠሪዎች እንጂ አመልካች አለመሆናቸውን ገልጸው ማስረጃው ሊሰረዝ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በጭብጥነት ይዞ እልባት የሚሰጥበት ጉዳይ ይዞታውን መውረስ የሚችለው ወገን የትኛው ነው የሚለው ነው፡፡ የዚህ ጭብጥ እልባት ማግኘት ደግሞ ይዞታው ላይ መብት ያለውን ሰው የሚለይ በመሆኑ መብቱ የተረጋገጠለት ሰው አዲስ የመሬትይዞታ ይገባኛል ክርክር የሚያቀርብበት አግባብ ሳይኖር ውሳኔውን መሰረት አድርጎ አፈጻጸሙን የሚቀጥልበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም አላስፈላጊ ወጪና የጊዜ ብክነት በማስቀረት ለክርክር እልባት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ተጠሪዎች ከገጠር መሬት ይዞታ ውጪ በሌሎች የሟች ንብረቶች ማስረጃውን የወሰዱ መሆኑን አመልካች ገልጸው የወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝልኝ ጥያቄ ያለማቅረባቸውን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ በመሆኑም የወራሽነት ማስረጃውን መሰረት አድርጎ የሚቀርብ የክፍፍል ጥያቄ በሌለበት ሁኔታ ወይም የገጠር መሬት ይዞታ ላይ የተሰጠውን የወራሽነት ማስረጃ መሰረት አድርገው ግራቀኙ የድርሻ ወይም የክፍፍል ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉበት አግባብ ሳይኖር ከክርክሩ ባህርይና ከፍትሃብሄር ስነ ስርዓት ውጪ የማስረጃ ይሰረዝልኝ ጥያቄ ላይ የመሬት ይዞታ ወራሸነት ቅደም ተከተል የመሬት ክርክር ሲነሳ የሚታይ ነው ተብሎ መወሰኑ የሕግ መሰረት የሌለውና መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. የአማራ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 03-07895 ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ በመ/ቁ 03-09360 ህዳር 03 ቀን 2007 ዓ/ም በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር
348/1/ መሰረት ተሽሯል፡፡
2. የሟች እሟኃይ እቴ አለማየሁ የገጠር እርሻ መሬት ሊወርስ የሚገባው ማን ነው? የሚለው ጥያቄ እልባት ማግኘት ያለበት በሌላ መዝገብ በሚከፈተው የመሬት ክርክር ሳይሆን አመልካች ባቀረቡት የክርክር አግባብ በመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ክርክሩን በመ/ቁጥር 03-07895 ቀጥሎ የወረዳው ፍርድ ቤት እና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጡት ውሳኔ በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሕግ አዋጅ ቁጥር 133/98 እና በደንብ ቁጥር 51/99 የተደነገገውን አግባብ መሰረት ያደረገ መሆን ያለመሆኑን መርምሮ ተገቢውን ዳኝነት ሊሰጥበት ይገባል በማለት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343/1/ መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ ይጻፍ፡፡
3. በዚህ ሰበር ደረጃ ግራ ቀኙ ባደረጉት ክርክር ምክንያት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ይቻቻሉ ብለናል፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ፣ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::